Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Home Forums Search Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Viewing 15 results - 661 through 675 (of 730 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    (የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ጋዜጣዊ መግለጫ) – የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሰኞ ኅዳር 03 ቀን 2011 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በአዲስ አበባ ውስጥ ብቻ አሰቃቂ ድርጊት የሚፈጸምባቸው 7 ድብቅ እስር ቤቶች መገኘታቸውን፤ ከእነዚህም በተጨማሪ በማረሚያ ቤቶችና በፖሊስ ጣቢያዎችም ጭምር በተጠረጣሪዎች ላይ ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ እጅግ አሰቃቂ ድርጊቶች ሲፈፀሙ መቆየታቸውን ገልፀዋል። ከእነዚህ በሕግ ጥላ ስር በሚገኙ ዜጐች ላይ ከሚፈፀሙት የማሰቃየት ድርጊቶች መካከልም የታሳሪዎችን ሰውነት በኤሌክትሪክ ሾክ ከማድረግ ጀምሮ ብልት ላይ ውሃ የያዘ የፕላስቲክ ኮዳ ማንጠልጠል፣ብልትን በፒንሳ መሳብ፣ ጥፍር መንቀል፣ ከአውሬ ጋር ማሳደር፣ ሴቶች ታሳሪዎችን መድፈር፣ በወንዶች ላይ ግብረሰዶም መፈፀም፣ እንዲሁም ደብዛን ማጥፋት በጉልህ የሚጠቀሱ በሕግ ጥላ ስር በተገኙ ዜጐች ላይ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መሆናቸውን ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ አረጋግጠዋል።

    የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ/ ሰመጉ) ባለፉት 27 ዓመታት ይህ ድርጊት በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፤ ሃሳብን የመግለፅ ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ሃሳባቸውን በነፃነት ሲያንሸራሽሩ በነበሩ ጋዜጠኞች እና አክቲቪስቶች፣ እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰቡ አባላት ላይ እየተፈፀመ መሆኑን በማጋለጥ መንግስት የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ሲወተውት መቆየቱ ይታወሳል። መንግስት ለአመታት ለችግሩ ምላሽ መንፈግ ብቻ ሳይሆን የማሰቃየት ድርጊቶቹን ውጤት በመጠቀም የዜጐችን ሕገ-መንግስታዊ እና ሰላማዊ ጥያቄዎች በኃይል ሲያዳፍን ብሎም ንጹሃንን ሲያሸብር ቆይቷል። ይህንንም የማሸበር ድርጊት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ፊት በመቅረብ በግልፅ መናገራቸው እና ይቅርታ መጠየቃቸው የሚታወስ ነው። እነዚህ የማሰቃየት ድርጊቶች ለዜጐች ከለላ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቅ ከነበረው ፍርድ ቤት የተደበቀ እንዳልሆነ በፍርድ ቤቶች ውስጥ የማሰቃየት ድርጊት ሰለባዎች ለችሎት ከሚያቀርቡት የቃል እና የፅሁፍ አቤቱታዎች በተጨማሪ፤ ልብሶቻቸውን በድፍረት በማውለቅ አካላዊ ጉዳታቸውን ቢያሳዩም በፍርድ ቤቶች በኩል የተወሰዱ እርምጃዎች አለመኖራቸው ታይቷል። በዚህም ፍርድ ቤቶች የዜጐችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የማስከበር ግዴታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ዜጐች እምነት አጥተውበት ቆይተዋል።

    ባለፉት 7 ወራት የመጣውን የመንግስት አስተዳደር ለውጥ ተከትሎ በመንግስት በኩል ሲወሰዱ የነበሩት እርምጃዎች በመልካምነታቸው የሚጠቀሱ ናቸው። በተለይም ላለፉት 27 ዓመታት መንግስታዊ ኃላፊነትን ተገን በማድርግ በንፁሃን ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን ሲፈፅሙ በቆዩ የብሔራዊ ደኅንነት የሥራ ኃላፊዎች እና ድርጊቱን በቀጥታ ሲፈፅሙ በነበሩ ግለሰቦች ላይ እየተወሰደ ያለው ሕጋዊ እርምጃ የሚደገፍ ነው። እስካሁን ከተወሰደው የማጣራት ሥራ በተጨማሪም ተመሳሳይ ድርጊቶችን ሲፈፅሙ እና ሲያስፈፅሙ የነበሩ ሌሎች የመንግስት ኃላፊዎችም ላይ እርምጃው እንዲቀጥል ሰመጉ ይጠይቃል።

    የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፃሚዎች ላይ መውሰድ የጀመረውን ሕጋዊ እርምጃ በመደገፍ ረገድ፤ ከሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ሰለባዎች ያሰባሰባቸውን መረጃዎች ለሚመለከተው የሕግ አስከባሪ አካል መስጠትን ጨምሮ በማናቸውም መንገድ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል። በተጨማሪም የማሰቃየት ድርጊቶቹ ሰለባ የሆኑ ዜጐች የደረሰባቸው አካላዊ ብቻ ሳይሆን ስነ-ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ጉዳት በቀላሉ የሚሽር እንዳልሆነ እሙን ነው። በመሆኑም ለተጐጂዎችና ለቤተሰቦቻቸው ነፃ የህክምና፣ የስነ-ልቦና ምክር አግልግሎት እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ሰመጉ ይጠይቃል።

    በአጠቃላይ መንግስት በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በፍጥነት ለፍትህ ማቅረቡ ሊመሰገን የሚገባው ተግባር ነው። ይህ የፍርድ ሒደት መንግስት ከበቀል በፀዳ መልኩ ሕግን ብቻ መሠረት ያደረገ እንቅስቃሴ በማድርግ ላይ መሆኑን የሚያሳይበት፣ ዜጐች በፍርድ ቤቶች ላይ የተሸረሸረ እምነታቸውን የሚያድሱበት እና የሕግ ልዕልና የሚከበርበት የፍርድ ሒደት እንዲሆን ሰመጉ ይጠይቃል።

    ምንጭ፦ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የሰብዓዊ መብቶች

    Semonegna
    Keymaster

    የዘንድሮው የዓለም የስኳር ህመም ቀን  ቤተሰብ የስኳር ህመምን ለመከላከል ባለው ሚና ላይ ተመሥርቶና “የስኳር ህመም ይመለከተኛል” በሚል መሪ ሀሳብ ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በብሔራዊ ትያትር ይከበራል።

    አዲስ አበባ (ኢ.ዜ.አ) – የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በዓለም አቀፍና በኢትዮጵያ ለ28ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የስኳር ህመም ቀን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

    የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከዓለም አቀፉ ስኳር ህመም ፋውንዴሽን እና “Doctors with Africa CUAMM” ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር ቀኑ ቤተሰብ የስኳር ህመምን ለመከላከል ባለው ሚና ላይ ተመሥርቶና “የስኳር ህመም ይመለከተኛል” በሚል መሪ ሀሳብ በብሔራዊ ትያትር ይከበራል።

    የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር (EDA) ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብዱራዛቅ አህመድ በኢትዮጵያ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ከስኳር ህመም ጋር እንደሚኖሩ ገልጸዋል።

    በኢትዮጵያ የስኳር ህመም ስሜትና ምልክት ሳይታይ የጤና ምርመራ የማድረግ ባህል አነስተኛ በመሆኑ ከስኳር ህመም ጋር እየተኖረ እንኳን ማወቅ ባለመቻሉ የችግሩን አሳሳቢነት እንደሚያጎላው ዶ/ር አብዱራዛቅ ተናግረዋል።

    በህመሙ ከተያዙት 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች በተጨማሪ ሌሎች 9 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች በተለያየ አጋጣሚ የስኳር መጠን መዛባት እየጋጠማቸው መሆኑንና ይህም ችግር ካልተፈታ የታማሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ሊጨምር እንደሚችል አመልክተዋል። በአብዛኛው በኢትዮጵያ በስኳር ህመም የሚኖሩ ሰዎች በምርመራ የጤና ሁኔታቸውን ያላወቁ መሆናቸውን ነው ዶ/ር አብዱራዛቅ ያስረዱት።

    አሁን ባለው ሁኔታ የስኳር ህመም ስርጭት በቁጥጥር ስር ካልዋለ ህመሙ ልብን፣ ዓይንን፣ ኩላሊቶችን፣ ነርቮችንና የደም ቱቦዎችን ተግባር በመጉዳትና ተግባራቸውን በማስተጓጎል ከባድ የጤና ቀውስ እንደሚያስከትልም ጠቅሰዋል።

    የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማኅበር የህመም ስርጭቱን አሳሳቢነት በመገንዘብ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ፣ የመድኃኒት አቅርቦትና የህክምና ተደራሽነቱን ለማስፋትና ለጤና ባለሙያዎች ሙያዊ ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

    ጤናማ ያልሆነ የአኗኗርና የአመጋገብ ዘይቤ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መቀነስ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረትና የደም ግፊት ለስኳር ህመም አጋላጭ ሁኔታዎች እንደሆኑም ነው ዶ/ር አብዱራዛቅ ያስረዱት። በአጠቃላይ የስኳር ህመምን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ መከተል በተለይ ሁለተኛውን የስኳር ዓይነት (Type 2 Diabetes) በ80 በመቶ ለመከላከል እንደሚያስችል ጠቅሰዋል።

    ህብረተሰቡ በተቻለው አቅም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተር እንደሚገባውና አትክልትና ፍራፍሬዎችን መመገብ እንዲሁም ህመም ቢሰማም ባይሰማም በዓመት አንድ ጊዜ የስኳር ህመም ምርመራ ማድረግ እንደሚገባውም ምክራቸውን አቅርበዋል።

    የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ባለሙያ አቶ አፈንዲ ኡስማን በበኩላቸው ሚኒስቴሩ አሁን ያለውን የስኳር ህመም ችግር አሳሳቢነት ለመከላከል የሚያስችሉ ጅምር ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።

    የስኳር ህመም መርሃ ግብር ከፌደራል እስከ ክልል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች (non-communicable diseases) ላይ ከሚሰሩ ሥራዎች መካከል እንደ ዋና መርሃ ግብር በማካተት በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

    ሚኒስቴሩ የአምስት ዓመት አገር አቀፍ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ አቅድ የስኳር ህመምን በዋናነት ባከተተ መልኩ አዘጋጅቶ የመተግበር ሥራንም እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

    የጤና ባለሙያዎችን፣ የጤና ማኅበራትንና የባለድርሻ አካላትን ያካተተ ብሔራዊ የስኳር ህመምን መከላከልና መቆጣጠር አማካሪ ግብረ ኃይልም ተቋቁሞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ነው አቶ አፈንዲ ያስረዱት።

    በተጨማሪም የስኳር ህመምና ተጓዳኝ የጤና ችግሮች መድኃኒቶችን ተመጣጣኝ በሆነ ክፍያ እንዲገኝ ለማድረግም ሁኔታዎችን የማመቻቸት፣ በተቀናጀ መልኩ የስኳር ህመምን ለመከላከል በጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች የበሽታውን የመቆጣጠር መርሃ ግብር ሥራዎችና ሌሎችም ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል። የስኳር ህመምን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካል አስፈላጊውን ጥረት እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

    ዓለም አቀፉ የስኳር ህሙማን ቀን ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በብሔራዊ ትያትር ሲከበር የፓናል ውይይት እንደሚካሄድና የህክምና ባለሙያዎችም ስለ በሽታው ገለጻ እንደሚያደርጉ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተጠቅሷል።

    የስኳር ህመም የሚከሰተው ሰውነታችን ለኑሮም ሆነ ለእድገት የሚያስፈልገውን ስኳር በትክክል ለመጠቀም ሳይችል ሲቀር ሲሆን አንድ ሰው የስኳር ህመም አለው የምንለው በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከሚገባው በላይ ከፍ ብሎ ሲገኝ እንደሆነም የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

    እንደ ዓለም አቀፉ ስኳር ህመም ፌዴሬሽን እ.ኤ.አ በ2017 ባወጣው መረጃ መሠረት በዓለም ደረጃ ከ425 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከህመሙ ጋር የሚኖሩ ሲሆን አስፈላጊው የበሽታው መከላከልና መቆጣጠር ካልተሰራ እ.አ.አ በ2045 የህሙማኑ ቁጥር 629 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ቅድመ ትንበያውን አስቀምጧል።

    ዓለም አቀፉ የስኳር ህመም ፌዴሬሽን (IDF) እ.ኤ.አ ከ1991 ጀምሮ የያዝነው ኅዳር ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ የስኳር ህመምና ተጓዳኝ ችግሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ወር በሚል ተሰይሟል።

    በኢትዮጵያ በበሽታው ከተያዙ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ 90 በመቶው በሁለተኛው የስኳር ዓይነት (Type 2 Diabetes) የተያዙ ሲሆን የተቀሩት በአንደኛው የስኳር ዓይነት (Type 2 Diabetes) የተያዙ ናቸው።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) | Semonegna Health

    የስኳር ህመም

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በሙስና ወንጀል እና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል።

    በዚህም መሠረት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት፦

    1. ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁርንዴ ኢጄታ – በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የማርኬቲንግ ኃላፊ
    2. ብርጋዴር ጄኔራል ብርሃ በየነ – የሜቴክ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ኃላፊ
    3. ብርጋዴር ጄኔራል ጥጋቡ ፈትላ መረሳ – የሜቴክ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኮርፖሬት ሎጂስቲክስና ሰፕላይ ኃላፊ
    4. ብርጋዴር ጀኔራል ሃድጉ ገብረጊወርጊስ ገብረስላሴ – የሜቴክ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኮርፖሬት ኒው ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኃላፊ
    5. ኮሎኔል ሸጋው ሙሉጌታ ተስፋሁን – የሜቴክ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የወታደራዊ ምርቶች ኦፕሬሽን ኃላፊ
    6. ኮሎኔል ሙሉ ወልደገብርዔል ገብረእግዛብሄር – የሜቴክ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኒው ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኃላፊ የነበሩ
    7. ኮሎኔል ዙፋን በርሄ ይህደግላ – የመከላከያ ጤና ኮሌጅ ሠራተኛ
    8. ሌተናል ኮሎኔል አስምረት ኪዳኔ አብርሃ – የጋፋት አርማመንት ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ተወካይ ኃላፊ የነበሩ
    9. ኮሎኔል አለሙ ሽመልስ ብርሃን – የሜቴክ ሎጂስቲክስና ሰፕላይ የትራንስፖርት ኃላፊ
    10. ኮሎኔል ያሬድ ሃይሉ – የሜቴክ በኮርፖሬት ኒው ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት የፕሮጀክት ኃላፊ
    11. ኮሎኔል ተከስተ ሀይለማሪያም አድሃኑ – የሜቴክ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኒው ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኃላፊ የነበሩ
    12. ኮሎኔል አዜብ ታደሰ – የሜቴክ በኮርፖሬት ማርኬቲንግ የሽያጭ ኃላፊ
    13. ሻለቃ ሰመረ ሀይሌ ሀጎስ – የሜቴክ በደጀን አቪዬሽን የኢንዱስትሪ ኦፕሬሽን ኃላፊ
    14. ሻምበል ይኩኖአምላክ ተስፋዬ – የሜቴክ በኮርፖሬት ማርኬቲንግና ሽያጭ የፕሮሞሽን ኃላፊ
    15. ኮሎኔል ደሴ ዘለቀ ብርሃን – የሜቴክ የአዳማ እርሻ ስራዎች ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ
    16. ሌተናል ኮሎኔል ሰለሞን በርሄ – የሜቴክ በብረታ ብረት ፋብሪኬሽን ኢንዱስትሪ የፋይናንስ ኃላፊ
    17. ሻለቃ ይርጋ አብርሃ – የሜቴክ በህብረት ማሽን ቢዩልዲንግ ኢንዱስትሪ የፋይናንስ ኃላፊ
    18. ኮሎኔል ግርማይ ታረቀኝ – የሜቴክ በኮርፖሬት ሎጂስቲክስና ሰፕላይ የንብረት አስተዳደር ኃላፊ
    19. ሻምበል ገብረስላሴ ገብረጊዮርጊስ – የሜቴክ የኮርፖሬት ትራንስፎርሜሽን የአቅም ግንባታ ማዕከል ኃላፊ
    20. ሻምበል ሰለሞን አብርሃ – የሜቴክ በኮርፖሬት ትራንስፎርሜሽን የስልጠና ኃላፊ
    21. ሻለቃ ጌታቸው ገብረ ስላሴ – የሜቴክ የደን ምንጣሮ ክትትል ኃላፊ
    22. ሌተናል ኮሎኔል ይሰሃቅ ሀይለማሪያም አድሃኖም – የሜቴክ በኮርፖሬት ኮሜርሻልና ሲቪል ምርቶች ኦፕሬሽን የፕላኒንግና ኮንትሮል ኃላፊ
    23. ሻለቃ ክንደያ ግርማይ – የሜቴክ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የፋይናንስ ኃላፊ
    24. ሌተናል ኮሎኔል አዳነ አገርነው – የሜቴክ በኮርፖሬት ሎጂስቲክስና ሰፕላይ የንብረት ክፍል ኃላፊ
    25. ሻለቃ ጌታቸው አጽብሃ – የሜቴክ ኢንፍራስትራክችርና ኮርፖሬሽን ማሽነሪ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኦፕሬሽን ኃላፊ
    26. ቸርነት ዳና – የዋይ ቲ ኦ ኩባንያ ባለቤትና ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አመራሮች ጋር የጥቅም ትስስር የነበራቸው ደላላ
    27. አያልነሽ መኮንን አራጌ – ማስረጃ ልታጠፋ ስትል በቁጥጥር ስር የዋለች

    በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት፦

    1. አቶ ጉሃ አጽበሃ ግደይ – የአዲስ አበባ የደህንነት ኃላፊ
    2. አቶ አማኑኤል ኪሮስ መድህን – የሃገር ውስጥ ደህንነት ጥበቃ ዋና መምሪያ ዳይሬክተር
    3. አቶ ደርበው ደመላሽ – የውስጥ ደህንነት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩና የኢኮኖሚ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ
    4. አቶ ተስፋዬ ገብረጻዲቅ – የውስጥ ደህንነት ጥናትና የወንጀል ምርመራ መምሪያ ኃላፊ
    5. አቶ ቢኒያም ማሙሸት – በውስጥ ደህንነት ጥበቃ ዋና መምሪያ የኦፕሬሽን ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ (በዋናነት የግንቦት 7 ጉዳይ ክትትል)
    6. አቶ ተሾመ ሀይሌ – የአማራ ክልል የደህንነት ኃላፊ የነበሩና የጥበቃ ዋና መምሪያ ዳይሬክተር
    7. አቶ አዲሱ በዳሳ – በሃገር ውስጥ ደህንነት የኦሮሚያ ክልል ደህንነት ኃላፊ 
    8. አቶ ዮሃንስ ወይም ገብረእግዚአብሄር ውበት – የውጭ መረጃ
    9. አቶ ነጋ ካሴ – በጸረ ሽብር መምሪያ የኦነግ ክትትል ኃላፊ
    10. አቶ ተመስገን በርሄ – በጸረ ሽብር መምሪያ የኦነግና ኦብነግ ክፍል ዋና ኃላፊ
    11. አቶ ሸዊት በላይ – በሃገር ውስጥ ደህንነት ኦፕሬሽን መምሪያ የግንቦት 7 ክትትል ምክትል መምሪያ ኃላፊ
    12. አቶ አሸናፊ ተስፋሁን – በሃገር ውስጥ ደህንነት የአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደህንነት አስተባባሪ
    13. አቶ ደርሶ አያና – በውጭ መረጃ የአማራ ክልል ክትትል
    14. አቶ ሰይፉ በላይ – በውስጥ ደህንነት የደቡብ ክልል ክትትል ኦፊሰር
    15. አቶ ኢዮብ ተወልደ – በውስጥ ደህንነት የደቡብ ክልል ደህንነት ኃላፊ
    16. አቶ አህመድ ገዳ – በውስጥ ደህንነት የኦሮሚያ ክልል ክትትል ምክትል ኃላፊ
    17. ምክትል ኮማንደር አለማየሁ ሀይሉ ባባታ – ቀድሞ የፌደራል ፖሊስ የሽብር ወንጀል ምርመራ ምክትል ዳይሬክተር የነበረና ዋና ዳይሬክተር ሆኖ ያገለገለ
    18. ምክትል ኢንስፔክተር የሱፍ ሀሰን – የሽብር ወንጀል መርማሪ
    19. ዋና ሳጅን እቴነሽ አራፋይኔ – የሽብር ወንጀል መርማሪ
    20. ኢንስፔክተር ፈይሳ ደሜ – የሽብር ወንጀል መርማሪ
    21. ምክትል ኢንስፔክተር ምንላርግልህ ጥላሁን – የሽብር ወንጀል መርማሪ
    22. ዋና ሳጅን ርዕሶም ክህሽን – የሽብር ወንጀል መርማሪ
    23. ኦፊሰር ገብረማሪያም ወልዳይ
    24. ኦፊሰር አስገለ ወልደጊዮርጊስ
    25. ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አሰፋ ኪዳኔ
    26. ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ገብረ እግዚአብሔር ገብረሐዋርያት – የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የጥበቃና ደህንነት ኃላፊ
    27. ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ተክላይ ኃይሉ – የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሠራተኛ
    28. ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አቡ ግርማ – የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ኃላፊ የነበረና በዝዋይ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ሆኖ ሲያገለግል የነበረ
    29. ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አዳነ ሐጎስ – የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሠራተኛ
    30. ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ተስፋሚካኤል አስጋለ – በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከፍተኛ የደህንነት ባለሙያ
    31. ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ገብራት መኮንን – የዝዋይ ማረሚያ ቤት የጥበቃና ደህንነት ኃላፊ የነበረና የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ጥበቃና ደህንነት ኃላፊ ሆኖ ሲያገለግል የነበረ
    32. ረዳት ኢንስፔክተር አለማየሁ ኃይሉ ወልዴ – በአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል መርማሪ
    33. ረዳት ኢንስፔክተር መንግስቱ ታደሰ አየለ – በአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል መርማሪ
    34. አዳነች ወይም ሃዊ ተሰማ ቶላ
    35. ጌታሁን አሰፋ ቶላ
    36. ሙሉ ፍሰሃ

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ዝርዝር

    Semonegna
    Keymaster

    ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ብርሀኑ ጸጋዬ በሰጡት መግለጫ፥ እስካሁን ድረስ በጥቅሉ 63 የሚደርሱ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፥ ከእነዚህም 27 ግለሰቦች በሙስና፣ 36 ደግሞ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት በቁጥጥር ስር የዋሉ ናቸው።

    አዲስ አበባ – ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ህዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በተለያዩ ቦታዎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በተከሰተው የቦምብ ጥቃት እንዲሁም በሜቴክ አመራሮች በተፈፀመው የሙስና ወንጀል በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ።

    ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ በሰጡት መግለጫ መሰረት እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉት በጥቅሉ 63 የሚደርሱ ናቸው። ከእነዚህም 27 በሙስና፣ 36 ደግሞ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ናቸው። በሙስና ወንጀል የተጠረተሩትን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ከማዋላችን በፊት ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ሂደት ላይ እያለን እንዚህን ማስርጃዎች ማለትም ሊብሬ፣ የአክስዮን ደብተር፣ የቤት ካርታዎች ፣ የባንክ ደብተር የቤት ሽያጭ ውሎች፣ ጦር መሣሪያዎች ማግኘትት ተችሏ በኤግዚብትነትም ተይዘዋል ብለዋል።

    ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ አሁንም የምንጠረጥራቸው ነገር ግን በአገር ውስጥና በውጪ ተሸሽገው ያሉ አሉ። በውጪ ያሉትን መንግስታቶቹ አሳልፈው እንዲሰጡን ተንጋግረር አገራቱ አሳልፈው እንደሚሰጡን ቃል ገብተውልናል ሲሉ ሀገር ውስጥ ያሉት ደግሞ ራሳቸውን ወደ ሕግ እንዲያቀርቡ እንዲሁም ህብረተሰቡ በመተባበር ጥቆማ እንዲሰጥ እና ሰላማዊ በሆነ መልኩ የፍትህ ሂደታቸውን እንዲከታተሉ ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል።

    በቁጥጥር ስር ስለ ዋሉ ግለሰቦች አቃቤ ሕጉ በመግለጫው ካነሷቸው አንኳር ነጥቦች መካከል ምርመራው ከ5 ወር በላይ የፈጀ ሲሆን የዚህ ምክንያቱም በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችን አስረን ከማጣራት አጣርተን ለማሰር ስለሞከርን ነው። ማንንም ተጠርጣሪ ሳንይዝ ነው ያጣራንው። በቁጥጥር ስር ከዋሉ ግለሰቦች መሀል የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ያለአግባብ ሀብት ያከማቹ፣ ሀብት ያሸሹ፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ የተሳተፉ፣ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የተከሰቱ ብጥብጦች ያስተባበሩ ይገኙበታል ተብሏል።

    በሌላ በኩል ደግሞ በብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አባላት መካከል በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በስውር እስር ቤት ግለሰቦችን በማሰር እና በማሰቃየት ተጠርጥረው የተያዙ አሉ። በአዲስ አበባ ብቻ ከሰባት በላይ እስር ቤቶች ተገኝተዋል። እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው ከተያዙ ግለሰቦች መሀል ግለሰቦችን ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት እራሳቸውን እንዲያገሉ ማድረግ እና ማሰቃየት፣ በአንቡላንስ እያፈኑ ሰዎችን መሰወር፣ ሕገ-ወጥ መሣሪያዎችን የራሴ ነው ብሎ እንዲፈርሙ ማድረግ፣ የብልት ቆዳዎችን በፒንሳ መሳብ፣ ጫካ ማሳደር፣ ከአውሬ ጋር ማሰር፣ አፍንጫ ውስጥ እስክርቢቶ መክተት፣ ግብረሰዶማዊ ጥቃት መፈፀም፣ ሴቶችን መድፈር የመሳሰሉ አረመኔያዊ ድርጊቶችን ፈፅመዋል።

    የሰኔ 16ቱ የቦንብ ጥቃት በተመለከተ በዋናነት የተቀነባበረው የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አባል በሆኑ ግለሰብ ነው። ኬንያ ከምትገኝ ገነት ቶሎሺ ከተባለች ግለሰብ ጋር በመሆን ነበር።

    የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ድርጅትን በተመለከተ የውጪ ሀገር ግዥዎችን ያለጨረታ መስጠት፣ ግዥ አፈፃፀሙ ከኮርፖሬሽኑ የበላይ አመራሮች ጋር የጥቅም ትስስር እና ዝምድና ያላቸው ሰዎች የድለላ ሥራ ሠርተው የሚከፈላቸውና እነዚህ የውጪ ኩባንያዎችን የሚያመጡት ደላሎች ለአመራሩ ቅርብ የሆኑ ናቸው። እነዚህ በድለላ ያሉ ሰዎች በሀገር ውስጥ ካካበቱት ሃብት በላይ ወደ ዉጪ ሃብት አሽሸዋል። ከመደበኛው ዋጋ እስከ 400% ተጨማሪ ዋጋ እየተጨመሪ ግዢ ይፈፀም ነበር ተብሏል። ከዚህም ጉዳይ የሀገር ውስጥ ግዢም በግልፅ ጨረታ መፈፀም ሲገባው እስካሁን በዚህ መልኩ የተፈፀመ የለም። ከኮርፓሬሽኑ አመራሮች ጋር የዝምድናና የጥቅም ትስስር ካላቸው ሰዎች በብዙ እጥፍ በተጋነነ ዋጋ ይገዛ ነበር። ከአንድ ድርጅት 21 ጊዜ፣ ከሌላው ደግሞ 15 ጊዜ ግዥ ተፈፅሟል። ለአብነት ያህል ከአንድ ድርጅት በአንድ ጊዜ ብቻ የ205 ሚሊዮን ብር ግዢ ያለጨረታ ተፈፅሟል በማለት አቶ ብርሀኑ ጸጋዬ ጠቅሰዋል። ከተቋሙ ተልዕኮ ውጪ የተፈፀሙ ግዥዎችም አሉ። ከዚህም ውስጥ የመርከብ ግዢ ይገኝበታል። በማይመለከተውም ሥራ ገብቶ ወደ ንግድ ሥራ አስገብቷቸዋል ሲሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ አቶ ብርሀኑ ጸጋዬ ገልጸዋል።

    ምንጭ፦ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አቶ ብርሀኑ ጸጋዬ

    Semonegna
    Keymaster

    ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሜቴክ ከተቋቋመበት ተልዕኮ ውጭ አገልገሎት መስጠት የማይቸሉ ሁለት መርከቦችና አምስት አውሮፕላኖችን ገዝቶ በመንግስት ላይ ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ደርሷል።

    አዲስ አበባ (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)– የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ከተቋቋመበት ተልዕኮ ውጭ አሮጌ ሁለት መርከቦችና አምስት አውሮፕላኖችን ያለአዋጭነት ጥናት ገዝቶ በመንግስት ላይ ጉዳት ማድረሱን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውቀ።

    ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ብርሀኑ ጸጋዬ ህዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፥ ሜቴክ ከተቋቋመበት ተልዕኮ ውጭ አገልገሎት መስጠት የማይቸሉ ሁለት መርከቦችና አምስት አውሮፕላኖችን ገዝቶ በመንግስት ላይ ጉዳት አድርሷል።

    ተቋሙ የተቋቋመበት የራሱ ደንብና መመሪያ ያለው ነው፤ ነገር ግን ከተልዕኮው ውጭ የሆኑ ያለምንም አዋጭነት ጥናት ትልልቅ ግዥዎችን ፈጽሟል ያሉት ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ፥ የግዥዎችን አይነትና የነበረውን ሂደት ዘርዝረው አስረድተዋል።

    ሜቴክ እና የመርከቦች ግዥ

    ቀድሞ የመርከብ ድርጅት ይባል የነበረው የአሁኑ የየባህር ትራንዚትና ሎጅስቲክ ድርጅት አባይ እና አንድነት የሚባሉ ከ28 ዓመት ባለይ ያገለገሉ መርከቦች ነበሩት። እነዚህ መርከቦች በባለሙያ በማስጠናት ከዚህ በላይ መርከቦቹ አገልገሎት ላይ መቆየት የለባቸውም፤ ከቆዩ ከገቢያቸው ወጪያቸው ይበልጣል ስለተባለ እንዲሸጡ የሥራ አመራር ቦርዱ ይወስናል። በዚህ መነሻነት ገዥ ተፈልጎ አንድ የውጭ ድርጅት በሶስት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ዶላር አንዷን መርከብ ለመግዛት ቀረበ።

    ነገር ግን ለውጭ ድርጅት ከሚሸጥ ሜቴክ ቆራርጦ ብረቱን ይጠቀምበት በሚል ድርጅቱ ባቀረበው ዋጋ መሰረት በሶስት ነጥብ 276 ቢሊዮን ብር ሜቴክ እንዲገዛው ይደረጋል። ይሁን እንጂ ሜቴክ መርከቦቹን ቆራርጦ ብረቱን መጠቀም ትቶ መርከቦቹ አዋጭ አይደሉም የሚል ጥናት እያለ ወደ ንግድ ሥራ አስገብቷቸዋል።

    ወደ ንግድ ሥራ ከማስገባቱም በፊት መስከረም 15 ቀን 2005 ዓ.ም. የሜቴክ ሥራ አመራር ቦርድ ተሰብስቦ መርከቦቹ ጅቡቲ ወደብ ላይ ለረጅም ጊዜ ከቆዩና ተጨማሪ ወጭ ካስወጡ በኋላ ለጥገና ወደ ዱባይ ተልከዋል። ለጥገናውክ ከኮርፖሬሽኑ 513 ሚሊዮን 837 ሺህ ብር ወጪ ተደርጎ መርከቦቹ እንዲጠገኑ ተደርጓል። ጥገናውን የሚያከናውኑ ሰዎችን የሚያፈላልጉ ተብለው የተመረጡትም ሜቴክ ውስጥ ያሉ የድልለላ ሥራ የሚሠሩ ከተቋሙ ኃላፊዎች ጋር የስጋ ዝምድና ያላቸው ግለሰቦች ናቸው።

    በመጨረሻም መርከቦቹ ተጠግነው ወጥተዋል ተብለው ወደ ንግድ ገብተዋል። ነገር ግን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ አድረገው መንቀሳቀስ ስለማይችሉ ለጥገና ብለው የተንቀሳቀሱበትን ፈቃድ የዘው ከኢራን ወደ ሞቃዲሾ በማድረግ እሰከ 500 ሺህ ዶላር አካባቢ ይሠራሉ። ይህ ገንዘብ ግን ወደሜቴክ ያልገባበት ሁኔታ አለ። ሥራውም ቢሆን ሕገ-ወጥ ነው። በመጨረሻ መርከቧ ሥራ መሥራት እንደማትችልና ፈቃድ እንደማታገኝ ሲታወቅና ተቃውሞ ሲያጋጥማቸው መርከቧ በሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብረ ተሽጣለች።

    ሜቴክ እና የአውሮፕላን ግዥ

    ይሄ ግዥ የተፈጸመበት ዓላማ በራሱ ችግር የለበትም። “አገራዊ ፐሮጀክቶችን በአውሮፕላን ታግዞ ለመከታተል” በሚል ያለምንም ጨረታ ከአንድ የእሥራኤል ኩባንያ በ11 ሚሊዮን 732 ሺህ 520 ብር ነው ግዥው የተፈጸመው። ነገር ግን ወደ ንግድ መግባት አለብን ተብሎ ፈቃድ በማውጣት ለመሥራት ተሞክሮ አልተሳካም።

    አውሮፕላኖቹ ከ50 ዓመት በላይ ያገለገሉ፣ የሚጠቀሙት ነዳጅ እጅግ ውድ፣ የቴክኒክ ችግርም ያለባቸውና ጥቅም ላይ ሊውሉ የማይቸሉ ናቸው ተብለው አራቱ ተቀምጠዋል። አንደኛው ግን እስካሁን የት እንዳለ አልታወቀም።

    በአጠቃላይም በሁለቱ ግዝዎች በመንግስት ላይ ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ደርሷል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    ሜቴክ

    Semonegna
    Keymaster

    ግንባታው ስድስት ዓመታትን የፈጀው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በቀን 2000 የሚሆኑ ታካሚዎችን ሊያስተናግድ የሚችል፣ 11 የቀዶ ሕክምና ክፍሎች እና 500 አልጋዎች አንዳሉት ተገልጿል።

    ባሕር ዳር (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ207 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነገ በሦስት አገሮች መሪዎች ይመረቃል።

    የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ እና የሕክምና ኮሌጅ የሥራ አፈጻጸም ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር የሺጌታ ገላው በጋራ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ዩኒቨርሲቲው የግንባታ ወጪው 207 ሚሊዮን ብር የፈጀውና ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ የሆነውን ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት በተገኙበት ህዳር 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በድምቀት እንደሚያስመርቅ ገልጸዋል።

    በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ ከሦስቱ መሪዎች በተጨማሪ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ባለስልጣናትና ጥር የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ፕሮፌሰር የሺጌታ ተናግረዋል።

    ከዚሁ መግለጫ ጋር አብሮ እንደተጠቀሰው በዩኒቨርሲቲው የሕክምና ኮሌጅ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ 148 የህክምና ተማሪዎችም ከኮሌጁ ለስድስተኛ ጊዜ ይመረቃሉ።

    በእነዚህ የሆስፒታሉ እና የተማሪዎቹ ምረቃ መርሀ ግብር ላይ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የኤርትራ ሀገረ ግዛት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና የሱማልያ ፌደራላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ በተገኙበት ይከናወናሉ።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንቱ ዶክተር ፍሬው ተገኘ እንደገለጹት በመሪዎቹ የሚመረቀው ሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና የሚጠይቁና ወደ ክፍተኛ ሕክምና መስጫ ቦታ የተላኩ (referral) በሽታዎችን የሚያክምና በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች (ዲፓርትመንቶች) ውስጥ በሕክምና እና በጤና ባለሙያነት ተማሪዎችን የሚያሰለጥን ነው።

    Ethiopia: Are Ethiopian hospitals constructed in environment-suitable and climate-friendly way?

    ግንባታው ስድስት ዓመታትን የፈጀው ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በቀን 2000 የሚሆኑ ታካሚዎችን ሊያስተናግድ የሚችል፣ 11 የቀዶ ሕክምና ክፍሎች ያሉት፣ 500 አልጋዎችን መያዝ የሚችል መሆኑን ፕሮፌሰር የሺጌታ አብራርተዋል። በክልሉ ካሉት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች በጥራትም ሆነ በአገልግሎት የተሻለ ሆኖ ለመገኘት መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

    ሀምሌ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. ከተመረቀው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል በመቀጠል በክልሉ ስድስተኛ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እንደሚሆን አስታውቀዋል። አያይዘውም ሆስፒታሉ ለምርቃቱ ቀን ይብቃ እንጅ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የህክምና ቁሳቁሶችና ሌሎች መሟላት ያለባቸው ነገሮች ስላሉ ከመንግስት በተጨማሪ ለጋሽ አካላትና በዚህ ዙሪያ የሚሠሩ ወገኖችን ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።

    ሚያዝያ 28 ቀን 1992 ዓ.ም በኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር ስር በሙሉ ዩኒቨርሲቲነት የተመረቀው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሀገሪቱ ውስጥ ካሉት ግዙፍ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሲሆን፥ በ2010 ዓ.ም  52,830 ተማሪችዎችን፣  219 የትምህርት  ዘርፎች (69 በመጀመሪያ/ባችለር ዲግሪ፣ 118  በሁለተኛ/ማስተር  እና 32 በሶስተኛ/ዶክትሬት ዲግሪዎች) ተቀብሎ ያስተምራል። ዩኒቨርሲቲው ስምንት ካምፓሶች ሲኖሩት፥ በውስጣቸውም አምስት ኮሌጆች፣ አራት ተቋማት (institutes)፣  ሁለት ፋኩልቲዎችና አንድ የሕግ ትምህርት ቤት (School of Law)  አሉት።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል

    Semonegna
    Keymaster

    ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ድረስ የካንሰር ህክምና አገልግሎት በብቸኝነት ሲሰጥ የነበረው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንደነበረና የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ይህን አገልግሎት መጀመሩ ለታካሚዎች ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል።

    አዲስ አባባ (ዋልታ/ ሰሞነኛ) – የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ከመስከረም 2 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የካንሰር ህክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቋል። ሆስፒታሉ ህክምናውን ከጀመረበት ቀን አንስቶ እስካሁን ድረስ ከ300 በላይ የካንሰር ታማሚዎችን በተመላላሽ ማከሙንም ገልጿል።

    በሆስፒታሉ የካንሰር ህክምና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አብዲ አደም የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ይህንን ህክምና መጀመሩ ከዚህ በፊት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በቦታ ጥበት ምክንያት በወረፋ ለሚንገላቱ ታካሚዎች መፍትሔ ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል።

    እስካሁን በተመላላሽ ህክምና ለታካሚዎች አገልግሎት ሲሠጥ መቆየቱን የገለጹት ዶ/ር አብዲ በቅርቡ አስተኝቶ ማከም የሚያስችል ወደ 350 የሚጠጋ አልጋ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል።

    ዋልታ ያነጋገራቸው በሆስፒታሉ የካንሰር ታካሚዎች እንደገለጹት ከዚህ በፊት ህክምናውን ለማግኘት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እስከ ስድስት ወር እንደሚወስድ ገልጸው አሁን ግን በቅዱስ ጳውሎስ አገልግሎት መጀመሩ ያለምንም ወረፋ ህክምናን ለማግኘት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

    Ethiopia: Are Ethiopian hospitals constructed in environment-suitable and climate-friendly way?

    በኢትዮጵያ የተደራጀ የጥናት ውጤት ባይኖርም በግምት በዓመት ከ160 ሺህ በላይ የካንሰር ተጠቂዎች እንደሚኖሩ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። እ.ኤ.አ በ2012 በተደረገ ጥናት ኢትዮጵያ ውስጥ በዓመት ውስጥ ከሚሞቱ ሰዎች ውስጥ 5.8 በመቶ የሚሆኑት በካንሰር ምክንያት እንደሚሞቱ ይጠቁማል። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስር የብሔራዊ የካንሰር ቁጥጥር ፕላን ባወጣው በዚህ ጥናት ምንም እንኳን ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ አጠቃላይ የሕዝብ ቆጠራን ተገን ያደረገ አሀዝ (population-based data) ባይኖርም ኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ 60,960 ሰዎች በተለያዩ ዓይነት የካንሰር በሽታዎች እንደሚጠቁና 44,000 ሰዎች ደግሞ በካንሰር ምክንያት እንደሚሞቱ ያትታል። በዚህም የካንሰር በሽታ በከፍተኛ ቁጥር ሰዎችን ከሚያጠቁ አራት ተለላፊ ካልሆኑ በሽታዎች [non-communicable diseases] ውስጥ ከልብ በሽታ ቀጥሎ ሁለተኛው ነው። (እነዚህ አራቱ ተለላፊ ከሆኑ በሽታዎች የልብ በሽታ፣ ካንሰር፣ የስኳር በሽታ እና የሳንባ በሽታ ሲሆኑ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎ ከሚሞቱት ሰዎች ቁጥር 80 በመቶ የሚሆነው ከእነዚህ በሽታዎች በአንዱ ምክንያት የሚሞት ነው።) ኢትዮጵያ ውስጥ ወንዶች ላይ የደምየ አንጀት ካንሰሮች፣ ሴቶች ላይ ደግሞ የጡት ካንሰር በከፍተኛ መጠን እንደሚታይ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ሪፖርት ያሳያል።

    የዓለም ጤና ድርጅት ለአንድ ሚሊዮን ሰዎች አንድ የካንሰር ህክምና ተቋም ሊኖር እንደሚገባ ቢመክርም በኢትዮጵያ ግን ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በብቸኝነት የህክምናውን አገልግሎት ይሰጥ እንደነበርና እ. ኤ.አ በ2017 በወጣ አሃዝ ከ6,000 በላይ የካንሰር ታካሚዎችን እያከመ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የስዊዘርላንዱ መድኃኒት አምራች ግዙፍ ኩባንያ ኖቫትሪስ (Novartis) እ.ኤ.አ በ2017 ባወጣው ዘገባ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በቁጥር ስምንት ኦንኮሎጂስቶች (የካንሰር ሀኪሞች) ብቻ እንዳላት አስታውቋል። ሌላ ተመሳስይ ጥናት ደግሞ ብቸኛው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ካሉት 627 ነርሶች ውስጥ 26ቱ ብቻ የካንሰር ህክምና ነርሶች እንደሆነ ይጠቁማል።

    ዋልታ | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል

    Semonegna
    Keymaster

    አቶ ሽመልስ አብዲሳ ኡፍታላ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሲሾሙ፥ ወይዘሮ ቢልለኔ ስዩም ወልደየስ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ሆነው ተሹመዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – አቶ ሽመልስ አብዲሳ ኡፍታላ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው በዛሬው ዕለት (ጥቅምት 26 ቀን 2011 ዓ.ም) ተሾሙ።

    አቶ ሽመልስ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩትን አቶ ፍጹም አረጋ ተክተው ነው የተሾሙት። በዚህም አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሠረት የፕሬስ ሴክቴሪያት ጽህፈት ቤት፣ የብቃትና ፖሊሲ ምዘና ጽህፈት ቤት፣ የአገር ደህንነት ጉዳይ አማካሪ ጽህፈት ቤትና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትን ይመራሉ ተብሏል።

    ከዚህ በፊት የነበሩት አቶ ፍጹም አረጋ ወደ ቀድሞ ቦታቸው፥ ማለትም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ተመልሰዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚነት የነበሩት በላቸው መኩሪያ (ዶ/ር) በመስከረም ወር መጀመሪያ ሳምንት “የግል/ የቤተሰብ ጉዳይ” በሚል ምክንያት ኃላፊነታቸውን (ብሎም ከኮሚሽኑ በአጠቃላይ) መልቀቃቸው ይታወሳል።

    አቶ ሽመልስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰብአዊ መብት የማስትሬት ዲግሪ፣ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ (UNISA) ደግሞ በፖለቲካል ፍልስፍና ሁለተኛ የማስተሬት ድግሪ አግኝተዋል።

    በተያያዘ ዜና፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ስር የፕሬስ ሴክሬታሪ ጽህፈት ቤት የተቋቋመ ሲሆን ወይዘሮ ቢልለኔ ስዩም ኃላፊ ተደርገው ተሹመዋል። ወይዘሮ እና ቢልለኔ ስዩም ስነ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጸሐፊ/ደራሲ ሲሆኑ፣ የሴቶች መብት ላይ እና በጾታ እኩልነት ላይ የሚሠራ ዕሩያን ሶሉሽንስ (Earuyan Solutions) የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራችና ኃላፊ ነበሩ። በትምህርታቸውም የማስተርስ ዲግሪ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፒስ-ኮስታሪካ፣ ሌላ የማስተርስ ዲግሪ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኢንስብሩክ (ኦስትርያ) እና የባችለርስ ዲግሪ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ብሪቲሽ ኮለምብያ (ካናዳ) አላቸው።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሽመልስ አብዲሳ

    Semonegna
    Keymaster

    ከህመሜ እስከ ስደቴ አብሮኝ ለታመመውና በመንፈስ አብሮኝ ለተሰደደው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለመገናኘት አበቃን –  የባህል ሙዚቃ አቀንቃኙ አርቲስት ፋሲል ደመወዝ በባሕር ዳር ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ላደረጉለት ወዳጆቹ እና አድናቂዎቹ

    ባሕር ዳር (አብመድ)– ላለፉት ስድስት ዓመታት ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገውና የባህል ሙዚቃ አቀንቃኙ አርቲስት ፋሲል ደመወዝ ባሕር ዳር ገብቷል። በባሕር ዳር ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስም አድናቂዎቹ አቀባበል አድርገውለታል።

    የሀገር ፍቅር ስሜቱ ከፍተኛ እና ያመነበትን የሚያቀነቅን እንደሆነ የሚነገርለት አርቲስት ፋሲል ደመወዝ በህዝቡ ዘንድ ተወዳጅ ነው። “ነፃነት በተነፈገው ህዝብ መካከል በኖርኩባቸው ዓመታት ከህመሜ እስከ ስደቴ አብሮኝ ለታመመውና በመንፈስ አብሮኝ ለተሰደደው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለመገናኘት አበቃን” ያለው አርቲስት ፋሲል ከዚህ ጋር አያይዞም “መድረክ ላይ እንዳልዘፍን የተከለከልኳቸውን የሙዚቃ ስራዎቸን በዚህ ህዝብ ፊት ለማቅረብ በመታደሌ ደስተኛ ነኝ” ብሏል።

    በቀጣይ በተለያዩ ቦታዎች ተንቀሳቅሰህ ህዝብን የማግኘት ዕድል እንደሚኖረው በአቀባበሉ ላይ የተገኙ ጋዜጠኞች ላቀረቡለት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ አርቲስቱ ከአሜሪካን ሀገር ወደ አገር ቤት ያመጡኝ አስተዋዋቂዎች (ፕሮሞተሮች) የሚያውቁት ሆኖ እስካሁን ባለኝ መረጃ በባሕር ዳር ከተማ አንድ የሙዚቃ ድግስ መኖሩን ነው በማለት ምላሽ ሰጥቷል።

    “ድግስ ጠርቻችኋለሁ” ያለው አርቲስት ፋሲል ደመወዝ ስለታገላችሁለት ነፃነት በነፃነት እንጫዎታለን ነው ያለው። በአርቲስቱ የአቀባበል ሥነ ስርዓት ላያ የተገኙት እማሆይ ፀሃይ ዓለሙ “ፋሲልን በስራዎቹ እና በሀገር ፍቅሩ እወደዋለሁ” መጣ ሲባል ስለሰማሁ እንኳን ለሀገርህ አበቃህ ለማለት ነው የመጣሁት በማለት ለየአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ጋዜጠኞች መልስ ሰጥቷዋል።

    በተመሳሳይ የቀድሞ ጓደኛው እና የሥራ ባልደረባው አርቲስት ቹቹ ምስጋናው ለፋሲል ያለው ፍቅር እና አክብሮት የተለየ መሆኑን ገልፆ “ለኢትዮጵያ ገና በርካታ ሥራዎችን የሚሠራ እና አሉ ከሚባሉ የባህል ሙዚቀኞች አንዱ በመሆኑ እንኳን ወደ ሀገሩ በሰላም ገባ” ሲል በአርቲስቱ መምጣት የተሰማውን ደስታ ገልጻል።

    የአርቲስት ፋሲል ደመወዝ እህት እስከዳር ደመወዝ በወንድሟ ወደ ሀገር መመለስ የተሰማት ደስታ ከፍተኛ መሆኑን ገልጻ በህመሙ እና በስደቱ ወቅት ከጎኑ ለነበረው ህዝብ ምስጋናዋን አቅርባለች።

    አርቲስት ፋሲል ደመወዝ በባሕር ዳር ስታዲየም ህዳር 1 ቀን 2011 ዓ.ም “ሀገሬ ኮንሰርት” በሚል መሪ ሃሳብ የሙዚቃ ሥራዎቹን ለህዝብ ያቀርባል ተብሎም ይጠበቃል ሲል የዘገበው አብመድ ነው።

    አርቲስት ፋሲል ደመወዝ ወደ አሜሪኣ ከተሰደደ በኋላም የሙዚቃ ሥራውን አድናቂዎቹ ያቀርብ የነበረ ሲሆን የተለያዩ ነጠላ ሙዚቃዎችን፣ እንዲሁም አማርኛ ሙዚቃ አድማጭ ዘንድ እጅግ ተቀባይነት ያገኘለትን “እንቆቅልሽ” የተሰኘ አልበም ሠርቷል። በአሜሪካ እና በካናዳ የተለያዩ ግዛቶችም እየተዘዋወረ የሙዚቃ ዝግጅቶች (ኮንሰርቶች) ላይ ከአድናቂዎቹ ጋር ተገናኝቷል። አሜሪካ ውስጥ ፍሎሪዳ ግዛት ካቀረበው ኮንሰርት ላይ የተቀነጨበውን እዚህ ጋር ይመልከቱ

    ምንጭ፦ የአማራ መገናኛ ብዙሀን ድርጅት (አብመድ)

    አርቲስት ፋሲል ደመወዝ

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ) – የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ 34ኛውን እና የዓመቱ የመጀመሪያውን ሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት ምግብ ዋስትና በኢትዮጵያ በተሰኘ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ መስከረም 24 ቀን 2011 ዓ.ም ውይይት አካሄደ።

    ገለፃውን ያቀረቡት ዶ/ር ዓለማየሁ ሥዩም (በዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ተቋም (IFPRI) ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪ) ሲሆኑ፣ አቅራቢው በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና እና በምግብ እራስን መቻል መካከል ያለው ብያኔ የተዛነፈ በመሆኑ በምሁራን እና በፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ወጥ የሆነ አረዳድ እንዳይኖር አድርጓል ብለዋል። ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ማለት በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በአገር፣ በክፍለ-ዓለምና በዓለም ደረጃ፤ ሁሉም ሰዎች፣ ዘወትር፣ በመጠኑ በቂ የሆነ፣ በጤና ላይ አደጋን የማያስከትል እና የተመጣጠነ የአመጋገብ ፍላጎትም ሆነ የአይነት ምርጫ ቁሳዊናኢኮኖሚያዊ ተደራሽነት ሲኖራቸው እንደሆነና ምንም ዓይነት ወቅታዊ መዋዠቅን፣ ያልተጠበቁ ሰው ሠራሽም ሆነ የተፈጥሮ ክስተቶችን (አደጋዎችን) መቋቋም የሚችል ማህበረሰብ ሲፈጠር እንደሆነ አቅራቢው ይገልፃሉ።

    ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ መካከለኛ መጠን ያላቸው ከተሞች በዓመት በአማካይ ከ5-6 በመቶ ዕድገት እያሳዩ መሆኑ እና መንግስት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማዘመን እና ምርታማነትን በመጨመር ገበያ-ተኮር ኢኮኖሚ ለመዘርጋት ጥረት እያደረገ እንደሆነ አብራርተዋል። ነገር ግን ዛሬም የግብርና ምርታማነት በጣም ዝቅተኛ መሆኑ፣ የህፃናት መቀንጨር በአማካይ 38 በመቶ መድረሱ፣ የምግብ እህል እጥረት የሚያጋጥማቸው ዜጎች ቁጥር እጅግ መጨመሩ እና ከፍተኛ የምግብ እህል/ሸቀጥ ከውጪ እንዲገባ መደረጉ “የምግብ ዋስትና ጉዳይ አሁንም እልባት ያላገኘ አገራዊ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል” ብለዋል ዶ/ር ዓለማየሁ።

    ለእንደዚህ ዓይነት የምግብ ዋስትና ስጋት ያጋልጣሉ ያሏቸውንም ምክንያቶች ዶ/ር ዓለማየሁ ዘርዝረዋል። “በገጠር የተወሳሰበ የመሬት ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ሁኔታ (የይዞታ ባለቤትነትና አጠቃቀም ሥርዓት)፣ የእርሻ መሬት ይዞታ ማነስና መበጣጠስ፣ የመሬት ምርታማነት መቀነስ/የአፈር ለምነት መቀነስ፣ የሥራ ዕድል መጥበብ እና ወጥነት የጎደለው የፖሊሲ አፈፃፀም” ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል ዶ/ር ዓለማየሁ። ችግሩም ህፃናትን ለበሽታና ለሞት እንዲሁም ለአካልና አእምሮ ህመም ከመዳረጉ እና የመማርና የማምረት አቅምን ከማኮሰስ አልፎ ድህነት እንዲቀጥል ያደርጋል ተብሏል።

    በሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መድረኩ ከችግሩም ለመላቀቅና የተሟላ ማህበራዊ ዋስትና ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየቶች ተነስተዋል። በውይይቱም ከፍተኛ የግብርና ማስፋፊያ ተግባራት በማከናወን አርሶ አደሮች የተሻለ መረጃ እንዲያገኙና የተሻሻሉ የግብርና ዘዴዎችን እንዲያላምዱ ማትጋት፤ ዘመናዊ የመሠረተ-ልማት ዝርጋታ ማድረግ፤ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማካሄድ አማካይ በህይወት የመኖሪያ እድሜን ማሳደግ እና የምግብ ዋስትና ተጋላጭነትን እያጠኑ ስልት የሚቀይሱ ጠቃሚ ተቋማትን መፍጠር (የፖሊሲ ተቋማት፣ የንብረት ባለቤትነት መብቶች፣ የገበያ፣ የአምራቾች ማህበራት፣ የማህበራዊ ዋስትና ስልት፣ የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ዘዴዎች) ቅድሚያ የሚፈልጉ አገራዊ ተግባራት መሆናቸው ተነስቷል።

    ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪም ከ20-25 ዓመት የሚደርስ የግብርናው ዘርፍን ሊያዘምን የሚችል አሠራር በተለይ ደረቅ-አብቃይ አካባቢዎችን፣ ለድርቅ-ተጋላጭቦታዎችን እና የተጎዱ አካባቢዎችን የሚያሻሽል የተቀናጀ መርሐ-ግብር መንደፍ አስፈላጊ እንደሆነ ተሳታፊዎች አንስተዋል። እንደ ህዝብ ቁጥር መጨመርና የአየር ንብረት መለዋወጥ ያሉ አባባሽ ሁኔታዎችንም መቋቋም የሚያስችል የኢኮኖሚ ዝግጁነት መገንባት የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማስጠበቅ ይረዳልም ብለዋል።

    በጥቅሉ የገለፃው አቅራቢና ተሳታፊዎች፣ ተቋማት መገንባትና በስፋትና በተፈለገው የህብረተሰብ ፍላጎት ልክ የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር መፈጠር አለበት በማለት የዕለቱን ውይይት አጠናቀዋል።

    ውይይቱን ፕሮፌሰር በላይ ካሳ (የፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲ ጊዜያዊ ከፍተኛ አመራር) የመሩት ሲሆን፣ ከ110 በላይ የሚሆኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ባለሙያዎች፣ የአካዳሚው አባላትና የሚዲያ አካላት ተሳትፈውበታል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ

    የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ

    Semonegna
    Keymaster

    ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ከሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የመቄዶንያ የአረጋውያንና አእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከልን ከጎበኙ በኋላ የ15 ዘመናዊ ባለሞተር ዊልቸሮችን ድጋፍ አድርገዋል።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታየቸው ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የአካል ጉዳተኞች መንቀሳቀሻ ወንበር (ዊልቸር/wheelchair) ድጋፍ አደረጉ።

    ቀዳማዊ እመቤቷ የ2011 ዓ.ም አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በማዕከሉ ለሚገኙ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን የምሳ ግብዣ ባደረጉበት ወቅት ባለቤታቸው ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ማዕከሉን እንደሚጎበኙ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።

    በመሆኑም ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ከሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ማዕከሉን ከጎበኙ በኋላ የ15 ዘመናዊ ባለሞተር ዊልቸሮችን ድጋፍ አድርገዋል። ድጋፉ የሚውለውም በማዕከሉ በከፋ የእንቅስቃሴ እክል ውስጥ ለሚገኙ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መሆኑ ተገልጿል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በችግር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ወገን ሲደገፉ ማየት ጥልቅ ሞራልና ተስፋ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። እውነተኛው አክሊል የሚገኘውም እንደዚህ ዓይነቱን ተግባር በመፈጸም ነው ሲሉም አሳስበዋል።

    “መናገር የማይችሉ እራሳቸውን መቆጣጠር የማይችሉ ሰዎችን የሚያየን ያየናል ብለው በንጹህ ልቦና ማገልገል መታደል ነው። እውነተኛው አክሊል የሚገኘው ከእንደዚህ አይነት ስፍራ ነው።እውነተኛውን የሚሹ ሰዎች ዝቅ ብለው መደገፍ የሚገባቸውን ሲደግፉ ሲያግዙ ማየት በኢትዮጵያ እንደዚህም አይነት ስራ የሚሰሩ ግለሰቦችን ማየት ጥልቅ ሞራል ተስፋ የሚሰጥ ነው።” በማለት ተናግረዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

    የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግና ሩህሩህ በመሆኑ ማዕከሉን በቀጣይነት እንደሚደግፍ እምነት እንዳላቸው የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ እርሳቸውም በተቻላቸው አቅም በማዕከሉ ያሉ አረጋውያንንና የአእምሮ ህሙማንን ለመጎብኘት ቃል ገብተዋል።

    “እኔ ልነግራችሁ የምፈልገው ነገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግ ህዝብ ነው። የማየት እድል ካገኘ ይህን የተቀደሰ ዓላማና ተግባር በመደገፍ ከጎናችሁ ሆኖ አልባሌ ቦታ የሚባክን ጉልበትና ሃብት ሰብስቦ እናንተን በማገዝ ከጎናችሁ በመሆን ቤተሰብ መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ሙሉ እምነት አለኝ ፤እኔም አቅሜ በፈቀደ መጠን እናንተን በመጎብኘት ከጎናችሁ እንደምሆን ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ።” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

    የማዕከሉ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ብንያም በለጠ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን በተለይም ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች የጠቅላይ ሚንስትሩን አርአያ በመከተል በማዕከሉ የሚገኙ ወገኖቻቸውን እንድጎበኙ ጥሪ አቅርቧል።

    ለመልካም ሥራ ጊዜ መስጠት እንደሚያስፈልግ በመጠቆም አቶ ብንያም፥ “የዶክተር አብይን አርአያ ተከትለን ዛሬ መጥተው በመጎብኘታቸው ማንም ሰው ከፈለገ ጊዜ እንዳለውና ለእግዚአብሔር ሥራ ጊዜ ሊያንሰው እንደማይገባ ስለአስተማሩን፤ ከእርሳቸው የበለጠ ጊዜ የሌለው ሰው የለም፤ ኢትዮጵያን የሚያህል አገር እየመሩ ጊዜ የለኝም ቢሉ ተቀባይነት አለው። እና ሁላችሁም የመንግስት ሠራተኞችም ብትሆኑ፣ ሚንስትሮችም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችም የእርሳቸውን አርአያ በመከተል ሰዎችን በመርዳት ከእግዚአብሔር ዋጋ እንድናገኝና በዚህ ውሸት በሞላበት ዓለም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለመግለጽ እወዳለሁ።” ብሏል።

    ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታየቸው ያደረጉት ድጋፍም ለማዕከሉ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አቶ ብንያም አክሎ ተናግሯል።

    የመቄዶንያ የአረጋውያንና አእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል አርባ አረጋውያንና አእምሮ ህሙማን በመያዝ የተቋቋመ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን፤ ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ወደ ሁለት ሺህ ለሚጠጉ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታየቸው

    Semonegna
    Keymaster

    ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው የተጣራ ትርፍ 728 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ይፋ ባደረገው ሪፖርት የተመለከተ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ145 በመቶ ብልጫ አለው።

    አዲስ አበባ (ኦኢባ) – ከተመሠረተ አሥረኛ ዓመቱን የያዘው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በታሪኩ ከፍተኛ የትርፍ ዕድገት በማስመዝገብ በ2010 ዓ.ም የሒሳብ ዓመት (fiscal year) ከታክስ በፊት 938 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።

    ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ቅዳሜ ጥቅምት 24 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ይፋ እንዳደረገው፣ የባንኩ የ2010 ዓ.ም የሒሳብ ዓመት የትርፍ መጠን ከቀድሞው የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከ140 በመቶ በላይ ዕድገት አሳይቷል።

    በቀደመው ዓመት ባንኩ ከታክስ በፊት 391 ሚሊዮን ብር ያስመዘገበ ሲሆን፣ የባንኩ ትርፍ በአንድ ዓመት ልዩነት የ547 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለውን ትርፍ ማስመዝገቡ የባንኩን የ2010 የሒሳብ ዓመት የትርፍ መጠን የተለየ አድርጎታል።

    ባንኩ በሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው የተጣራ ትርፍ 728 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ይፋ ባደረገው ሪፖርት የተመለከተ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ145 በመቶ ብልጫ አለው።

    ኢትዮጵያ ውስጥ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ገንዘብን በሞባይል ስልክ ለማንቀስቀስ የሚያስችሉት ሲቢኢ ብር እና አሞሌ

    ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ያስመዘገበው የትርፍ ዕድገት ምጣኔ በባንክ ኢንዱስትሪው ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በዚህም ምክንያት የባንኩ የትርፍ ክፍፍል ወደ 54 በመቶ ከፍ ብሏል፡።

    የ2010 ዓ.ም በሒሳብ ዓመት በአብዛኛው ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ሲሆን፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 19.9 ቢሊዮን ብር እንደደረሰና ጠቅላላ ሀብቱም 23.8 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተመልክቷል።

    መስከረም 11 ቀን 2001 ዓ.ም ተመሥርቶ ጥቅምት 15 ቀን 2001 ዓ.ም የመጀመሪያ ቅርንጫፉን አዲስ አበባ ውስጥ ደንበል ሲቲ ሴንተር ላይ ከፍቶ ሥራ የጀመረው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በአሁኑ ወቅት በመላው ሀገሪቱ ከ200 በላይ ቅርንጫፎች አሉት።

    ምንጭ፦ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል (ኦኢባ)

    ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ

    Semonegna
    Keymaster

    የማህፀን በር ካንሰር ክትባት መሰጠት ያለበት ከ9 ዓመት ጀምሮ ላሉ ልጃገረዶች ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ባጋጠመው ክትባት እጥረት ምክንያት ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሆኑ ብቻ እንደሚሰጥ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

    አዲስ አበባ (የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር) – ከመጪው ህዳር ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ የማህፀን በር ካንሰር ቅድመ መከላከያ ክትባት በአገር አቀፍ ደረጃ መሰጠት ሊጀመር መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ክትባቱ ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃገረዶች በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶችና በጊዜያዊ የክትባት ማዕከሎች ይሰጣል። የማህፀን በር ካንሰር ክትባት በሙከራ ደረጃ በትግራይና ኦሮሚያ በተመረጡ ወረዳዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰጥ ቆይቷል።

    በሚኒስቴሩ የክትባት ባለሙያ አቶ ጌትነት ባየ እንዳሉት፥ ክትባቱን ለማስጀመር በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ለሚገኙ ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ይሰጣል።

    “ከመጪው ህዳር ወር ጀምሮም በአገር አቀፍ ደረጃ ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃገረዶች ክትባቱ መሰጠት ይጀምራል” ብለዋል አቶ ጌትነት ።

    የማህፀን በር ካንሰር ክትባት መሰጠት ያለበት ከ9 ዓመት ጀምሮ ላሉ ልጃገረዶች ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ባጋጠመው ክትባት እጥረት ምክንያት ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሆኑ ብቻ ነው የሚሰጠው።

    የማህፀን በር ካንሰር መንስኤው “ሂውማን ፓፒሎማቫይረስ” (Human papillomavirus) በሚባል ኢንፌክሽን የሚመጣ ሲሆን፥ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) እንደሚያስታውቀው አግባብ የሆነ በሽታን የመከላከል አቅም ያላቸው ሴቶች (women with normal immune systems) በቫይረሱ ከተጠቁ በኋላ የማህፀን በር ካንሰር ምልክት ሳይታይባቸው ከ15 እስከ 20 ዓመታት ሊቆዩ እንደሚችሉ፣ ደካማ የሆነ በሽታን የመከላከል አቅም ያላቸው ሴቶች (women with weak immune systems) ደግሞ ምልክቱ ሳይታይባቸው ከ5 እስከ 10 ዓመታት ሊቆዩ እንደሚችሉ ያትታል።

    ለበሽታው ከሚያጋልጡት ምክንያቶች ውስጥ ዋነኞቹ ልጃገረዶች በለጋነት እድሜያቸው የግብረ ስጋ ግንኙነት መጀመርና ከተለያዩ ሰዎች ጋር ፆታዊ ግንኙነት ማድረግ ሲሆኑ፥ ሲጋራ ማጨስም ሌላው ምክንያት ነው።

    ከ30 እስከ 45 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ እና ወደ ህክምና ተቋማት መጥተው ምርመራ በማድረግ ራሳቸውን ከበሽታው መጠበቅ እንደሚኖርባቸው ይመከራል።

    በታዳጊ ሀገራት የማህፀን በር ካንሰር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል። ከዚህ በተጨማሪ በዓለም ላይ እጅግ በብዛት ከሚታይባቸው ሀያ አገራት ውስጥ አስራ ዘጠኙ የአፍሪካ አገራት እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

    HPV Information Centre የሚባለው ድርጅት እ.ኤ.አ በሀምሌ ወር በ2017 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ በየ ዓመቱ 7,095 ሴቶች ማህፀን በር ካንሰር የሚጠቁ ሲሆን፣ በየዓመቱም 4,732 ሴቶች በዚሁ ካንሰር ምክንያት ለሞት እንደሚዳረጉ ዘግቧል።

    ምንጭ፦ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) እና የዓለም የካንሰር ምርምር ፈንድ (WCRF)

    የማህፀን በር ካንሰር

    Semonegna
    Keymaster

    አገር አቀፍ የተማሪ ወላጆች ህብረት ምሥረታ ላይ ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ግለሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተሳተፉበት ሲሆን ህብረቱን በሊቀመንበርነት፣ በምክትል ሊቀመንበርነት በጸሀፊነት የሚያገለግሎ ወላጆችን ምርጫ ተካሂዷል።

    አዳማ (የትምህርት ሚኒስቴር) – በአገሪቱ እስከ ታኛናው መዋቅር ያሉ የትምህርትና ስልጠና ተቋማትና የተማሪ ወላጆችን ትስስር በማጠናከር በዘርፉ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ የሚያስችል አገር አቀፍ የተማሪ ወላጆች ህብረት ተመሠረተ።

    ክቡር የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አቶ መሀመድ አህመዲን በአገር አቀፍ የተማሪ ወላጆች ህብረት ምሥረታ ወቅት እንደገለጹት የህብረቱን ዓላማ በየደረጃው ባለው መዋቅር የትምህርት ተቋማትና የተማሪ ወላጆችን በማስተሳሰር በሁለንተናዊ ብቃት፣ ዕውቀት፣ ክህሎትና በስነ ምግባር የታነጸ ዜጋ ለማፍራት ረገድ የወላጆችን ሚና ለማሳደግ ነው።

    በትምህርት ጥራት የማረጋገጥ ተግባር የወላጆች ሚና ማሳደግ፣ በወላጆች፣ በመምህራንና በተማሪዎች መካከል ያለውን ግንኙት ውጤታማ ማድረግ፣ ጤናማ የመማር-ማስተማር ሂደት በላቀ ደረጃ እንዲረጋገጥ የወላጆችን ተሳትፎ ማሳደግና ለትምህርት ሥራ ማጎልበት የሚያስችል አደረጃጀትና ትስስር መፍጠር የህብረቱ ቀሪ ዓላማዎች መሆናቸውን ክቡር ሚኒስትር ደኤታው አስታውቀዋል።

    በህብረቱ ምሥረታ ላይ ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ547 የሚበልጡ የሀይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የተማሪ ወላጆች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተሳተፉበት ሲሆን ህብረቱን በሊቀመንበርነት፣ በምክትል ሊቀመንበርነት በጸሀፊነት የሚያገለግሎ ወላጆችን ምርጫ ተካሂዷል።

    በዚህም መሠረት ኢንጅነር ጌታቸው ሠጠኝ ከአዲስ አበባ የህብረቱ ሊቀመንበር ፣ወይዘሮ መሠረት ተክሌ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ የህብረቱ ምክትል ሊቀመንበር ፣ አቶ ሀሰን በዳሶ ከኦሮሚያ የህብረቱ ጸሀፊ ሆነው ተመርጠዋል።

    ህብረቱ በተጨማሪ 11 አባላት ያሉበትን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያዋቀረ ሲሆን በዚህም መሠረት ከትግራይ አቶ ጸጋዬ አለማየሁ፣ ከአፋር አቶ አሊ የጦ፣ ከአማራ አቶ አዱኛ እሸቴ፣ ከሱማሌ አቶ ኻሊድ አብዱልቃድር፣ ከደቡብ አቶ ተሻለ አየለ፣ ከጋምቤላ አቶ አእምሮ ደርበው፣ ከሐረሪ ወ/ሮ ፋጡማ አብዱ በህብረቱ ሥራ አስፈጻሚ አባልነት ተመርጠዋል።

    የኢትዮጵያ የተማሪ ወላጆች ህብረት ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ኢንጂነር ጌታቸው ሰጠኝ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ህብረቱ ለትምህርቱ ሥራ ውጤታማነት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

    ክቡር የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ በበኩላቸው ህብረቱ ለፍኖተ-ካርታው መተግበር ጠቃሚ መሳሪያ መሆኑን ጠቁመው ህብረቱ ለሚያከናውነው ተግባር ውጤታማነት የትምህርት ሚኒስቴር እገዛ እንደማይለየው አስታውቀዋል።

    ህብረቱ በቀጣይ በሰላምና ደህንነት፣ በመማር ማስተማር፣ በትምህርት ተቋማት ፋይናንስ አስተዳደር ጉዳዮች የሚያተኩሩ ንዑሳን ኮሚቴዎች በቀጣይ ተቋቁመው ወደሥራ እንደሚያስገባም በዚሁ ጊዜ መገለጹን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘግቧል።

    ምንጭ፦ የትምህርት ሚኒስቴር

    አገር አቀፍ የተማሪ ወላጆች ህብረት

    Semonegna
    Keymaster

    አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አሠራሩን በማሻሻል ቀልጣፋና ዘመናዊ አሠራርን መሰረት ያደረገ አገልግሎት በመስጠት ፋንታ አንዳንድ የአገልግሎት መስመሮቹን መዝጋቱ ተገቢ አለመሆኑን ተገልጋዮች ጠቁመዋል።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – በአዲስ አበባ ከተማና በዙሪያዋ በረጅም ዘመን አገልግሎቱ የሚታወቀው አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በተወሰኑ አካባቢዎች አገልግሎቱን በማቋረጡ ለትራንስፖርት እጥረት መጋለጣቸውን ተገልጋዮች ተናገሩ።

    የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ሪፖርተር በኮልፌ ቀራንዮ፣ ቀጨኔ፣ ሚኪሊላንድና መሰል አካባቢዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ተገልጋዮች እንዳሉት አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በእነዚህ አካባቢዎች ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎት በማቋረጡ ለችግር ተዳርገዋል።

    የቀጨኔ አካባቢ ነዋሪዋ ወ/ሮ ባዩሽ ለማ ከሰፈራቸው እስከ መርካቶ በሁለት ብር የምታደርሳቸው ስምንት ቁጥር አውቶቡስ አገልግሎት በማቋረጧ ለተጨማሪ ወጪና እንግልት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

    በሚኪሊላንድ የጋራ መኖሪያ ቤት የሚኖሩት መምህር በላቸው አንዳርጌም ከሚኖሩበት አካባቢ ተነስተው ወደ መርካቶ እና ፒያሳ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ አውቶቡሶች አገልግሎት በማቋረጣቸው ህብረተሰቡ ለችግር መዳረጉን ገልጸዋል።

    መምህር በላቸው እንዳሉት አገልግሎቱ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከሚሰጠው የተመጣጠነ አገልግሎት በተጨማሪ ለተማሪዎችና መንግስት ሠራተኞችም የጎላ አስተዋጽዖ አለው።

    አንበሳ የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አሠራሩን በማሻሻል ቀልጣፋና ዘመናዊ አሠራርን መሰረት ያደረገ አገልግሎት በመስጠት ፋንታ የአገልግሎት መስመሮቹን መዝጋቱ ተገቢ አለመሆኑንም ጠቁመዋል።

    በአስኮ የአዲስ ሰፈር ነዋሪው ወጣት ሳሙኤል መንገሻ በአካባቢው በተለይ ጠዋትና ማታ ህብረተሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት እየተቸገረ መሆኑን ገልጾ ከአስኮ አዲስ ሰፈር አገልግሎት ለመስጠት የተመደበችው አውቶቡስ ስራ ማቆሟ ችግሩን እንደሚያባብሰው ተናግሯል።

    ከስድስት ኪሎ በሩፋዔል አስኮ እንዲሁም ከስድስት ኪሎ በሜክሲኮ ቄራ ይመላለሱ የነበሩትን አውቶብሶች ለማግኘት መቸገሩን የተናገረው ደግሞ ተማሪ ያለው ደምሴ ነው። ይህም በተለይ የማታ ትምህርት ለመከታተተል የትራንስፖርት እጥረቱን እንዳባባሰው ነው የተናገረው።

    በአንበሳ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የብዙሃን ትራንስፖርት ዋና ሥራ ሂደት ተጠባባቂ ሃላፊ አቶ መላኩ ካሳዬ የነዋሪዎቹ ጥያቄ ትክክለኛ መሆኑን አምነዋል።

    ይሁን እንጂ ችግሩ የተፈጠረው የአገልግሎት መስመሮች በመታጠፋቸው ሳይሆን በርካታ አውቶብሶች በእርጅና ምክንያት ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው መሆኑን አብራርተዋል።

    ችግሩን ለመፍታ ድርጅቱ ሰባት መቶ አውቶብሶችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው ከመጪው ሰኞ ጀምሮ አዳዲስ አውቶብሶችን እንደሚረከብም ገልጸዋል። አሁን ያሉትን አውቶብሶች በአግባቡ በመጠቀም ችግሩን ለማቃለል ጥረት እደሚደረግም ነው ኃላፊው የተናሩት።

    አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በአሁኑ ወቅት 444 አውቶብሶችን በየቀኑ እያሰማራ ቢሆንም ከ20 በላይ የሚሆኑት አውቶቢሶች በብልሽትና በቴክኒክ ጉድለት ሳቢያ በየቀኑ በአግባቡ አገልግሎት እንደማይሰጡ አስታውቀዋል።

    በ1935 ዓ.ም በአራት ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት የጀመረው አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ድርጅት በ1967 ዓ.ም ወደ መንግስት ይዞታነት ተሸጋግሮ እስካሁን ድረስ ቆይቷል። በተለያዩ የሥራ መስኮችም ከሰባት ሺህ አምስት መቶ በላይ ሠራተኞች አሉት።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

    አንበሳ የከተማ አውቶቡስ

Viewing 15 results - 661 through 675 (of 730 total)