Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Home Forums Search Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Viewing 15 results - 691 through 705 (of 730 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    “ለኢንቨስትመንት በሚል ሰበብ አርሶ አደሩን በማደህየት ኢንቨስትመንቱን ማሳደግ አይቻልም፤ መሬታቸው የሚወሰድባቸው አርሶ አደሮች ተመጣጣኝ ካሳ ማግኘት አለባቸው።” ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

    ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ (አብመድ)

    ባሕር ዳር – የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ በ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ፣ በሕግ ማዕቀፎች እና አሠራሮች ላይ ሲሰጥ የነበረውን ክልላዊ የምክክር መድረክ ዛሬ አጠናቅቋል።

    የአማራ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለኢንቨስትመንት በሚል ሰበብ ብዙ አርሶ አደሮች መብታቸው ተጥሶ እንደነበር በመጥቀስ አርሶ አደሩን በማደህየት ኢንቨስትመንቱን ማሳደግ አይቻልም፤ መሬት የሚወሰድባቸው አርሶ አደሮች ተመጣጣኝ ካሳ ማግኘት አለባቸው ሲሉ አስገንዝበዋል። ቀደም ሲል ካሳ የማያገኙበት ሕግ የነበረ ቢሆንም ሕጉን የማስተካከል እርምጃ መወሰዱንም አስታውቀዋል።

    አርሶ አደሮች እና የነባር ይዞታ ባለቤቶች መሬታቸውን ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲጠቀሙ መደረጉ ጥያቄ በሚያነሱበት ጊዜ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ምላሽ ለመስጠት ከማገዙም በላይ ህብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዲሠራ ያደርገዋል። በመሆኑም አርሶ አደሩን ከአላስፈላጊ እንግልት የምናድንበት በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

    አርሶ አደሮች በጉልበተኛ ጥቅማቸውን የሚያጡበት ፍትሃዊ ያልሆነ አሠራር ካለ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ቢሮ ህዝባዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ጠንክሮ መሥራት እና የፍትህ ስርዓቱን ማስከበር ይጠበቅበታልም ነው ያሉት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው።

    ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራን በተመለከተ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራ ርዕሰ መስተዳድሩ በጥብቅ አሳስበዋል። በተለይ የወል መሬቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ግለሰቦች ይዞታ ስር እየገቡ በመሆኑ በፍጥነት መግታት ካልተቻለ ስር እየሰደደ ሄዶ ግለሰቦች ላይ ጫና ማሳደሩ እንደማይቀር አስገንዝበዋል።

    በመድረኩ የተሳተፉ አካላት በባለቤትነት ይዞ በመንቀሳቀስ ከሚመለከተው ባለድርሻ አካላት ጋር ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባም አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

    ለተከታታይ አምስት ቀናት የቆየውን የምክክር መድረክ የተካፈሉ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው በሚችሉት አቅም ሁሉ ህብረተሰቡን ለማገልገል ፍቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    ተጨማሪ ዜና፦ ኢትዮጵያዊው ባለሃብት አቶ በላይነህ ክንዴ እያስገነቡ ያሉት የምግብ ዘይት ፋብሪካ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል

    አቶ ወዳጅ ምስክር ከሰሜን ወሎ ዞን፣ ወይዘሮ በላይነሽ አሻግሬ ደግሞ ከደቡብ ጎንደር ፋርጣ ወረዳ በምክክር መድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎች ናቸው። ከውይይቱ በቂ ግብዓት እንዳገኙ ነግረውናል። ተሳታፊዎቹ እንደተናገሩት ወቅቱን መሰረት ያደረገ የገጠር መሬት አጠቃቀም ስልጠና መውሰዳቸው ለቀጣይ የተጣለባቸውን የሕዝብ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ዝግጁ እንደሚያደርጋቸው ለአብመድ ጋዜጠኞች አረጋግጠዋል።

    በመዝጊያ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ገዱ አንዳርጋቸው የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ቢሮ ከወረዳ እስከ ክልል ድረስ ተቋማዊ በሆነ መንገድ ሥራውን በአግባቡ ለመወጣት ጥረት እያደረገ ያለ ተቋም መሆኑን አውስተው፥ መሬት ሀብት እና የማንነት መገለጫ መሆኑን በመረዳት የኃላፊነት ስሜት በተሞላበት መንገድ ሲንቀሳቀስ ለቆየው ለተቋሙ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ ሥራው አድካሚ መሆኑን በመጥቀስ ወደ ዘመናዊ የመረጃ ቋት ለማስገባት ተቋሙ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል።

    ከገጠር መሬት ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ ማንኛውም ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚችለው በመድረኩ ላይ የተሳተፈው ባለሙያ ነው፤ በተለይ በምዕራብ ቆላማው የክልሉ አካባቢዎች ለበርካታ ዘመናት ጥሩ አሠራር ያልነበረባቸውን ቦታዎች በዚሁ ተቋም ውስጥ በተሰማሩ ሙያተኞች እና አመራሮች አማካኝነት ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተካከል ተችሏል ብለዋል።

    በከተሞች ዙሪያ የሚኖሩና ትኩረት የማያገኙ አርሶ አደሮች ጥቅማቸው እና መብታቸው እንዲከበር በማድረግ በኩል ትልቅ ሥራ ተሰርቷል፤ ተገፍተው ለነበሩ አርሶ አደሮች በተገቢው መንገድ ካሳ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

    ምንጭ፦ የአማራ መገናኛ ብዙሀን ድርጅት (አብመድ)

    ገዱ አንዳርጋቸው

    Semonegna
    Keymaster

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ ተዘጋጅቷል፤ የትምህርት ዘመኑን የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊና ጤናማ ለማድረግ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፤ በሁሉም ካምፓሶች የህፃናት ማዋያ ማዕከላትን ለማቋቋም በዝግጅት ላይ ነው።

    አርባ ምንጭ (ኢዜአ/AMU)– አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ መዘጋጀቱን ፕሬዚዳንቱ ገለጹ። ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊና ጤናማ ለማድረግ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ተወያይቷል።

    የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት ነባርና አዲስ ተማሪዎችን በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያሰለጥናል። ከነዚህም ከ6ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች አዲስ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።

    ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲገቡ በማኅበራዊ ሕይወታቸው ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ጉዳዮች ላይ የክህሎት ትምህርት እንደሚሰጥም አመልክተዋል።

    ዩኒቨርሲቲው ጥቅምት 11 እና 13 ቀናት የነባር ተማሪዎች ቅበላ የሚያከናውን ሲሆን፣ ጥቅምት 15 ና 16 ቀናት 2011 ዓ.ም ደግሞ አዲስ ገቢዎችን እንደሚቀበል ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

    ተማሪዎቹ ከአቀባበል ጀምሮ በመማር ማስተማር ሂደት ችግሮች እንዳያጋጥማቸው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ያስረዱት ዶክተር ዳምጠው፣ ከግቢ ውጭ ችግር እንዳያጋጥማቸው የከተማው ነዋሪዎች ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

    ◌ ተመሳሳይ ዜና፦ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በትምህርት ጥራትና ለኅብረተሰቡ ንጹህ ውሃ ለማቅረብ እየሠራ ነው

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፖለቲካ፣ ኃይማኖትና ከትምሀርት ጋር ግንኙነት በሌላቸው ጉዳዮች የጸዳ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

    የአርባ ምንጭ ከተማ የሰላም ፎረም አባል አቶ ገረሱ በየነ በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ተግባሩን ለማከናወን እንዲያስችለው የሰላም ፎረም እንዲያቋቁም አሳስበዋል።

    ሌላኛው የሀይማኖት አባት መጋቢ ካሳዬ በየነ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው አካባቢ እየተስፋፉ የመጡትን የሺሻ፣ የጫትና የመጠጥ ቤቶች ጉዳይ እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል።

    የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ኤዞ ኤማቆ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከውሃና ከኤሌክትሪክ መቆራረጥ ጋር የሚያጋጥሙትን ችግሮችን ለማስወገድ እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲው አካባቢ የሚታዩ ሕገ ወጥ የሺሻ፣ የመጠጥና ጭፈራ ቤቶችን በመቆጣጠርና በመከታተል እገዛ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

    በውይይቱ ላይ የሀይማኖት አባቶች፣ የከተማው የሰላም ኮሚቴ አባላት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

    ከዚሁ ጋር በተያያዘ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2011 በጀት ዓመት በሁሉም ካምፓሶች የህፃናት ማዋያ ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ገልጸዋል። ዳይሬክቶሬቱ ማዕከላቱን በቅርበት እንዲከታተል ኃላፊነት የተሠጠው ሲሆን በያዝነው በጀት ዓመት የቢሮ መጠሪያውን ወደ ‹‹ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት›› እንደሚቀይርም አስታውቋል።

    የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህለ እንደገለፁት በፌዴራል የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀፅ 48(6) መሠረት ሴት የመንግስት ሠራተኞች ከወሊድ በኋላ ወደ ሥራ ገበታቸው ሲመለሱ በሚሠሩበት ተቋም ውስጥ ህጻን ልጆቻቸውን በቅርበት እየተንከባከቡና እየተከታተሉ መደበኛ ሥራዎቻቸውን እንዲያከናውኑ ለማገዝ የህፃናት ማቆያ ማቋቋም አስፈላጊ ነው። በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 36(1) መሠረት ህጻናት ከወላጆቻቸው ማግኘት የሚገባቸውን ተገቢውን እንክብካቤ የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።

    የህፃናት ማቆያዎቹ መቋቋም ዓላማዎች ከሆኑት ውስጥ እናቶቻቸው በሥራ ምክንያት በአቅራቢያቸው ባለመኖራቸው ምክንያት በህፃናት ጤንነትና ደህንነት ላይ የሚደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቀነስ፣ በመንግስት ተቋማት ውስጥ የተሰማሩ እናት ሠራተኞች በህጻን ልጆቻቸው ምክንያት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚፈጥሩትን ክፍተቶች መሙላት፣ በሴት ሠራተኞች ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን መቀነስ እና ውጤታማነታቸውን ማሳደግ ጥቂቶቹ ናቸው።

    የህፃናት ማዋያዎቹ ከመደበኛው የሥራ መግቢያ ሰዓት  እስከ ሥራ መውጫ ሰዓት ድረስ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን የመኝታ፣ የማረፊያ፣ የመጫወቻ፣ የምግብ ማብሰያ፣ የመመገቢያ አቅርቦትና አገልግሎት እንዲሁም የእንክብካቤ፣ የቅርብ ክትትል እና የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና አገልግሎቶችን አካቷል።

    እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ አገልግሎቱን ለማግኘት ወላጆች የማንነት መግለጫ መታወቂያ ማቅረብ የሚኖርባቸው ሲሆን የህፃናቱን ምግብ በተመለከተ ከማቆያ ማዕከሉ ጋር በሚደረግ ስምምነት ወላጆች አዘጋጅተው ማቅረብ አልያም ተመጣጣኝ ክፍያ ፈጽመው የማዕከሉን አቅርቦት መጠቀም ይችላሉ። የማዕከሉን የውስጥ ግብዓት ከማሟላት ጀምሮ ተንከባካቢ ሞግዚት የመቅጠሩ ተግባር የዩኒቨርሲቲው ይሆናል።

    ወ/ሪት ሠናይት እንደገለጹት በህፃናት ደህንነት ላይ የወጡትን ህግጋት መሠረት በማድረግ በህፃናት ጤንነት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ከሚችሉ ኬሚካሎች፣ ብናኞች፣ ድምፅ ያላቸው የማምረቻ ቦታዎችና መሠል ጎጂ ነገሮች የራቀ የህፃናት ማቆያ ለመገንባት ዩኒቨርሲቲው የቦታ መረጣ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። የህፃናት ማቆያ ማዕከላቱ ህንፃዎች የመኝታ፣ የመጫወቻና የንፅህና መጠበቂያ ክፍሎችን የሚያካትቱ ይሆናል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ኢትዮጵያውያን የፋሽን ዲዛይነሮች ለዓለም ገበያ የኢትዮጵያን ምርት ይዘው ሲወጡ ምርቱን ብቻ ሳይሆን ሜድ ኢን ኢትዮጵያ በሚለው ሳያሜ ኢትዮጵያዊነትንም በማስተዋወቅ ደረጃ ጉልህ አስተዋጽዖ አያደረጉ እንደሆነ እንደሚሰማቸው ይናገራሉ።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ)– ኢትዮጵያውያን ዲዛይነሮች በኢትዮጵያ የተመረተ ሜድ ኢን ኢትዮጵያ በተሰኘው መለያ አገራቸውን ለማስተዋወቅ ተስፋ ሰንቀዋል።

    ዲዛይነር ሳምራዊት መርሲኤሓዘን ኢትዮጵያ ውሰጥ የተሰራ ሜድ ኢን ኢትዮጵያ የተሰኘ መለያን የያዙ ቦርሳዎችና ሌሎች የቆዳ ውጤቶችን በማምረት አገሯን የማስተዋወቅ ራዕይ ይዛ እየሰራች ትገኛለች።

    በእንስሳት ሃብት ከአፍሪካ ቀዳሚ እየተባለች ለዘመናት የምትታወቀው ኢትዮጵያ ከቆዳ ውጤቶች እምብዛም አለመጠቀሟ ዲዛይነር ሳምራዊትን ያስቆጫታል። እንደ እርሷ አገላለጽ አሁንም ቢሆን በቁጭት ከተሠራ በእንስሳት ሃብት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ በተመረቱ የቆዳ ውጤቶች አገርን ለማስጠራት ጊዜው አልረፈደም።

    ለዚህ የእርሷ የቆዳ ቦርሳ፣ ምንጣፍና ሌሎች ምርቶች ተደራሽ በሆኑባቸው አገራት ያለውን ተቀባይነት በማንሳት ታብራራለች። ለዓለም ገበያ የኢትዮጵያን ምርት ይዛ ስትወጣ ምርቱን ብቻ ሳይሆን ሜድ ኢን ኢትዮጵያ በሚለው ሳያሜ ኢትዮጵያዊነትንም እየሸጠች መሆኑን እንደሚሰማት ነው የተናገረችው።

    ሥራዋን ከጀመረች ስድስት አመታትን ያስቆጠረችው ዲዛይነሯ፤ ጀርመን፣ ጃፓንና ሆላንድ ምርቷን ከምታቀርብባቸው አገሮች መካከል ሲሆኑ በቀጣይም የዱባይና እንግሊዝ ገበያን ለመድረስ ዕቅድ አላት።

    የውጭ ገበያን ሰብሮ ለመግባት መጀመሪያ የራሳችንን መቀበልና የራሳችንን ማድነቅ መጀመር አለብን የሚል ሃሳብም አንስታለች።

    በቆዳ ምርቶች ያደጉ አገሮች ለዲዛይን፣ ለአሠራርና አጨራረስ የሚጠቀሙበትን ዘዴ ልምድ በመውሰድ መወዳደር አለብን የሚል እሳቤም አላት ዲዛይነር ሳምራዊት።

    “በውጭ ባህል ጥገኛ ከመሆን የብሔር ብሔረሰቦችን የአለባበስ ስርዓት ከዓለም አቀፍ ፍላጎት ጋር በማመጣጠን መለያ በማድረግ ልንታወቅበት የምንችል የገበያ ዘርፍ ነውም” ስትል ትገልጻለች።

    የቀደምት ኢትዮጵያውያን እናቶች መገለጫ ከሆነው “ፈትል” በተሠሩ የአገር ባህል ልብሶችም ኢትዮጵያን ለዓለም ለማስተዋወቅ ተስፋ ማድረጋቸውን “የፈትል ዲዛይነር” ሽያጭ ሠራተኛ ወጣት ፌቨን ተስፋዬ ትናገራለች።

    የኢትዮጵያ ፈትል በማንኛውም ሰዓት ሊለበስ በሚችል መልኩ በማምረት አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች አገሮች ምርቱን ካገኙ በጉጉት እንደሚወስዱ ታዝባለች። ልብሱ የተሠራበት ጥሬ እቃ ከፈትል መሆኑ በተለያዩ አገራት አድናቆትን እያገኘና ባህልን እያስተዋወቀ መሆኑንም ፌቨን ትናገራለች።

    ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ዲዛይነር ቁንጅና ተስፋዬ ዘወትር የሚለበሱ የኢትዮጵያን ባህል የሚገልጹ ልብሶችን በመሥራት ለአገር ውስጥና ለውጪ ገበያ በማቅረብ ላይ ትገኛለች።

    ቪድዮ፦ የኢትዮጵያ አልባሳትና ባህላዊ ዲዛይኖች የዓለም ገበያን ሰብረው እንዲገቡ ለማድረግ ብዙ መሠራት አለበት

    የምትሠራቸው አልባሳት የኢትዮጵያን አንዱን ብሔረሰብ አለባበስ በሚገልጽ መልኩ በመሆናቸውም በእያንዳንዱ ልብስ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን ባህል እያስተዋወቀች መሆኗን ተናግራለች።

    ከዚህ በፊት በዓለም ላይ የተሰሩት የአለባበስ ዲዛይኖች እየተደጋገሙ በመሆናቸውና አሁን አሁን እነሱ በሠሩት ዲዛይን መሠረት ዓለም ወደ አፍሪካ ፊቱን እያዞረ መሆኑን በመግለጽ ይህን ዕድል አገራችንን ለማስተዋወቅ መጠቀም አለብን የሚል አስተያየትም ሰጥታለች።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ሜድ ኢን ኢትዮጵያ

    Semonegna
    Keymaster

    ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ለ13ኛ ጊዜ በሚያካሂደው ዓመታዊ የኪነ ህንጻ አውደ ርዕይ “ኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን” በሚል መሪ ሀሳብ ከጥቅምት 8 ቀን እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቲያትር ይካሄዳል።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በየዓመቱ የሚያካሂደው ዓመታዊ የኪነ ህንጻ አውደ ርዕይ ጥቅምት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ይጀመራል።

    ለ13ኛ ጊዜ በሚካሄደው አውደ ርዕዩ “ኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን” በሚል መሪ ሀሳብ በብሔራዊ ቲያትር ይካሄዳል።
    የዩኒቨርሲቲው የኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን የትምህርት ክፍል ሃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ገብረጻዲቅ ለኢዜአ እንደገለጹት አውደ ርዕዩ የትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች የሥራ ውጤቶቻቸውን የሚያቀርቡበት ነው።

    አውደ ርዕዩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ ዘርፉ ኢንዱስትሪ ከመቀላቀላቸው በፊት ሥራዎቻቸውን ለኅብረተሰቡ፣ ለመንግስት ተቋማትና ለዘርፉ ባለድርሻ አካላት በማቅረብ ልምድ የሚቀስሙበት እንደሚሆን አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ተማሪዎቹ እርስ በእርስ እንዲማማሩም መልካም አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል።

    የተሻለ አቅም ያላቸው ተማሪዎች ወደ ሥራ ዓለም ሲገቡ በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት ከመቅረፍ አንጻር አስተዋጽዖ እንደሚያበረክቱም ነው አቶ ቴዎድሮስ ያስረዱት።

    አውደ ርዕዩ በየዓመቱ ሲካሄድ በአማካይ እስከ ሁለት ሺህ ሰው እንደሚጎበኘውና ዘንድሮም ከአንድ ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚጎበኙት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

    ALSO: EVENT: The 9TH ADDISBUILD: International Construction, Steel, Construction Machinery & Infrastructure Exhibition

    በአውደ ርዕዩ የዩኒቨርሲቲው የዘንድሮ የትምህርት ክፍሉ 60 ተማሪዎች የሥራ ፕሮጀክቶቻቸውን እንደሚያቀርቡና የተሻለ ሥራ ያቀረቡ ተማሪዎች የኢትዮጵያ የኪነ ህንጻ ባለሙያዎች ማኅበር (Association of Ethiopian Architects) በሚያዘጋጀው ዓመታዊ ውድድር እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል።

    በዚህ አውደ ርዕይ ሌሎች የመንግስትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደሚሳተፉም ተናግረዋል።

    በብሔራዊ ቲአትር አዳራሽ የሚካሔደው አውደ ርዕይ ከጥቅምት 8 ቀን እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል።

    ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ከሚሰጣቸው የትምህርት ዘርፎች አንዱ “ኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን” ሲሆን በዚሁ ትምህርት ዘርፍ ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ (bachelors degree) አስተምሮ ያስመርቃል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    አዲሱ የካቢኔ አባላት ሹመት የቀረበው የአስፈፃሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ እንደገና ለማሻሻል የቀረበውን አዲስ ረቂቅ አዋጅ በምክር ቤቱ መፅደቁን ተከትሎ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  አስታውቋል።

    አዲስ አበባ – የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ20 አዳዲስ የካቢኔ አባላት ሹመት ውስጥ 50 በመቶ ሴቶች ሆነው እንዲያገለግሉ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የቀረበውን ሹመት ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ አፀደቀ።

    የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሚሾሙት 20 ካቢኔዎች ውስጥ 10 ሴቶች ሆነው በተሰጣቸው ኃላፊነት እንዲያገለግሉ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

    አዲሱ የካቢኔ አባላት ሹመት የቀረበው የአስፈፃሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ እንደገና ለማሻሻል የቀረበውን አዲስ ረቂቅ አዋጅ በምክር ቤቱ መፅደቁን ተከትሎ ነው።

    በዚህም መሠረት የሹመቱ ዋና መስፈርት ብቃት፣ የትምህርት ዝግጅትና ለውጥን የመምራት አቅም መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ከሚሾሙት ካቢኔዎች 50 በመቶ (በቁጥር፥ ወይም ከ20ዎቹ 10 ሴት) ካቢኔዎች መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

    ይህም በኢትዮጵያ ምናልባትም በአፍሪካ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑም በምክር ቤቱ ተገልጿል።

    በዚህ በተደረገው የካቢኔ ሹመት ለውጥ ውስጥ ከዚህ በፊት “የፐብሊክ ሰርቪስ እና ሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር” ተብሎ ይጠራ የነበረው ሚኒስቴር ተለውጦ አሁን “ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን” (Civil Service Commission) በሚል እንደተተካ ታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ ሶስት ኮሚሽኖችም በአዲስ መልክ ተካተዋል፤ እነዚህም (1) የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን (Job Creation Commission)፣ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን (Environment, Forestry and Climate Change Commission) እና የፕላንና እድገት ኮሚሽን (Plan and Development Commission) ናቸው።

    አዲስ በተዋቀረው ካቢኔ ውስጥ የተሰየሙት ባለስልጣናትና የተሰየሙበት ስልጣን ዝርዝር

    1. ዶ/ር ሂሩት ካሳው ― የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር
    2. ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም ― የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
    3. ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ― የሰላም ሚኒስቴር
    4. ዶ/ር ሳሙኤል ሆርቃ ― የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር
    5. ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ― የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር
    6. አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ― ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ
    7. አቶ አህመድ ሺዴ ― የገንዘብ ሚኒስቴር
    8. ዶ/ር አሚን አማን ሐጎስ ― የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር
    9. ወ/ሮ አዳነች አበበ ― የገቢዎች ሚኒስቴር
    10. ኢ/ር አይሻ መሀመድ ሙሳ ― የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር
    11. አቶ ኡመር ሁሴን ― የግብርና ሚኒስቴር
    12. ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ― የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
    13. ወ/ሮ የዓለምፀጋይ አስፋው — የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር
    14. ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ― የትራንስፖርት ሚኒስቴር
    15. አቶ ጃንጥራር አባይ ― የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር
    16. ዶ/ር ኢ/ር ጌታሁን መኩሪያ ― የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
    17. ዶ/ር ጥላዬ ጌጤ ― አምባዬ የትምህርት ሚኒስቴር
    18. ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ― የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
    19. ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ-እግዚአብሔር ― የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
    20. ዶ/ር ፍፁም አሰፋ ― የፕላን ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የካቢኔ አባላት ሹመት

    Semonegna
    Keymaster

    ሱማሌላንድ ውስጥ የሚገኘው የበርበራ ወደብ በባለቤትነት ደረጃ የኤምሬቱ ዲፒ ወርልድ 51 በመቶ፣ የሶማሌላንድ አስተዳደር 30 በመቶ እና የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ 19 በመቶ ድርሻ አላቸው።

    አዲስ አበባ (ሶማሌላንድ ሰን/ ኢዜአ) – ኢትዮጵያ 19 በመቶ ባለድርሻ የሆነችበት የሶማሌላንድ የበርበራ ወደብ ግንባታ ተጀመረ።

    ጥቅምት 1 ቀን 2011 ዓ.ም የግንባታ ማስጀመር ሥነ ስርዓቱ ሲካሄድ በሥነ ስርዓቱ ላይ የሶማሌላንድ አስተዳድር እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች ተካፍለዋል።

    መቀመጫውን ዱባይ ያደረገው ዲፒ ወርልድ (DP World) የተባለው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (UAE) ኩባንያ በ420 ሚሊዮን ዶላር የበርበራ ወደብ ግንባታን ለማካሄድ ውል ገብቶ ሥራውን ጀምሯል።

    በስምምነቱ መሠረት በወደቡ ግንባታ የኤምሬቱ ዲፒ ወርልድ 51 በመቶ፣ የሶማሌላንድ አስተዳደር 30 በመቶ እና የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ 19 በመቶ ድርሻ ይዘዋል ተብሏል።

    ከግንባታ በኋላ የሶማሌላንድ መንግስት፣ የኢትዮጵያ መንግስት እና ዲፒ የበርበራ ወደብ ላይ ያላቸው ውል ለ30 ዓመት የሚቆይ መሆኑንም ተመልክቷል።

    የሶማሌ ላንድ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ (Muse Bihi Abdi) በሥነ ስርዓቱ ላይ እደንደተናገሩት የበርበራ ወደብ ግንባታ እውን መሆን የሶማሌላንድ ኢኮኖሚን ከማነቃቃት ባሻገር ለቀጠናው የንግድና ኢኮኖሚ ትስርስር ፋይዳው የጎላ ነው።

    በተያያዘ ዜና ሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ የሚገነባው የኢትዮጵያ ንግድ ሎጂስቲክስ ፕሮጀክት የዲዛይን ጥናት እየተጠናቀቀ መሆኑን የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን ገለጸ።

    ባለስልጣኑ አስመጪዎች፣ ላኪዎችና የተለያዩ ደንበኞች በሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ የሚደርስባቸውን መጉላላት ለመቀነስ አሰራሩን ዘመናዊ ለማድረግ የሞጆ ሎጂስቲክስ ማዕከልን ሊገነባ መሆኑ ይታወቃል።

    ተመሳሳይ ዜና፦ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ የአሰብ እና የምጽዋ ወደቦችን መጠቀም ለመጀመር ዝግጅቷን እያጠናቀቀች ነው

    በዚህም ባለስልጣኑ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ሐምሌ 2017 ከዓለም ባንክ የዲዛይን ፈቃድ አግኝቶ በመጀመሪያ የዲዛይን ጥናቱ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው።

    በማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን የኢትዮጵያ ንግድ ሎጂስቲክስ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ዶክተር መንግስት ኃይለማርያም እንዳሉት፤ ግንባታው የሚከናወነው ከዓለም ባንክ በተገኘ 150 ሚሊዮን ዶላር ነው። የዓለም ባንክ ይህንን ገንዘብ ለኢትዮጵያ በክሬዲት መልክ የሰጠው እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር መጋቢት 31 ቀን 2017 ነበር።

    ግንባታው እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2022 እንደሚጠናቀቅና የዲዛይን ጥናቱም በተያዘለት የጊዜ ገደብ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

    በዲዛይን ጥናቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ ዓለም ባንክን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከተደረገበት በኋላ ሁለተኛው የግንባታ ምዕራፍ ይጀምራል ብለዋል።

    ግንባታው ሲጠናቀቅም በሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ ያለውን አሰራር ወደ ኤሌክትሮኒክስ በመቀየር ቀልጣፋ፣ ፈጣንና ዘመናዊ አሠራር ይኖረዋል ነው ያሉት።

    የሞጆ ደረቅ ወደብ የመሰረተ ልማት አቅርቦት እጥረት፣ የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ችግርና የተሟላ የኤሌክትሮኒክስ ስርዓት ችግር እንዳለበት ገልጸዋል።

    በመሆኑም የሚገነባው የኢትዮጵያ ንግድ ሎጂስቲክስ ፕሮጀክት እነዚሀን ችግሮች በዘመናዊና በተቀናጀ መንገድ ማከናወን ያስችላል ብለዋል።

    ምንጭ፦ ሶማሌላንድ ሰን እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    የበርበራ ወደብ

    Semonegna
    Keymaster

    በጥቅምት ወር ዓም የጸደቀው የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ የፊልም ኢንዱስትሪውን ዘርፍ በአግባቡ እንዲያሳድገው ከተፈለገ የማስፈጸሚያ ሰነድ ሊዘጋጅለት ይገባልበሀገሪቱ ውስጥ በፊልም ሥራ ላየ እንደተሰማሩ ባለሙያዎች ማብራሪያ።

    በጌትነት ተስፋማርያም (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

    አዲስ አበባ – የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ ዘርፉን በአግባቡ እንዲያሳድገው ከተፈለገ የማስፈጸሚያ ሰነድ ሊዘጋጅለት እንደሚገባ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ገለጹ።

    የኢትዮጵያ ፊልም ሠሪያዎች ማህበር የቀድሞ ፕሬዚዳንት አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ እንደገለጸው፤ የዘርፉን ችግሮች ለማቃለል የሚያስችል አ ሠራር ይኖረዋል የተባለው ፖሊሲ ባለፈው ዓመት ጸድቋል። ነገር ግን ፖሊሲው ዝርዝር ጉዳዮችን የማይዝ በመሆኑ እያንዳንዱን የዘርፉን ችግሮች ሊቀርፍ የሚችል የማስፈጸሚያ ሰነድ ሊዘጋጅ ይገባል።

    እንደ አርቲስት ደሳለኝ ገለጻ፤ የፊልም ኢንዱስትሪው ለአምስት መቶ ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠር የሚችል መሆኑን በጥናት ተረጋግጧል። ነገር ግን እስካሁን በአግባቡ ስላልተሠራበት ውጤቱ እምብዛም ነው። ከአጠቃላይ የአገሪቷ ገቢ ውስጥ ያለው ድርሻም ዝቅተኛ ነው። የፊልም ፖሊሲው አስፈጻሚ አካል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ካለው የሰው ኃይል፣ የፊልም ጥበብ ዕውቀት ችግር እና አደረጃጀት አኳያ ዘርፉን በሚገባው ልክ እያገዘ አይደለም። በመሆኑም የፊልም ባለሙያዎች ዋነኛውን ድርሻ በመውሰድ ለፖሊሲው ማስፈጸሚያ ስትራቴጂ ለማውጣት ሌት ከቀን መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

    የፊልም ባለሙያው ዮናስ ብርሃነ መዋ በበኩሉ፤ እንደ አንድ የፊልም ባለሙያ ፖሊሲው ሲጸድቅ በኢንዱስትሪው ያሉት ችግሮች ይቀረፋሉ ብሎ እንደጠበቀ ገልጿል። ዝርዝር ጉዳዮችን ለማስተካከል እና ወጥ አሠራር ለማምጣት የማስፈጸሚያ ሰነዱ የግድ መዘጋጀት እንዳለበት ባለሙያዎች ሊገነዘቡ እንደሚገባ ተናግሯል። የማስፈጸሚያ ሰነዱንም ለማዘጋጀት የሚያስችል ቡድን ከባለድርሻ አካላት ተውጣጥቶ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን በር በየጊዜው በማንኳኳት ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርቧል።

    የኢትዮጵያ የፊልም ሠሪዎች የዘርፍ ማኀበር ፕሬዚዳንት አቶ ቢንያም አለማየሁ እንደገለጸው፤ የማስፈጸሚያ ሰነዱ ቢዘጋጅ በመጀመሪያ ኢንዱስትሪው በማደጉ ተጠቃሚ የሚሆነው ባለሙያው ነው። በመሆኑም አርቲስቶች፣ ዳይሬክተሮች እና በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚሳተፉ ግለሰቦች ሳይሰለቹ ለፖሊሲው የማስፈጸሚያ ሰነዱ ዝግጅት መሥራት አለባቸው። በዘርፉ ያለውን የዕውቀት፣ የገቢ እና የአሠራር እድገት ለማስመዝገብ ማስፈጸሚያ ሰነዱ ቁልፍ ሥራ መሆኑን በመረዳት ማንኛውም ባለሙያ በንቃት ሊሳተፍ እንደሚገባ ገልጿል።

    የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ሰላም ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ የፊልም ሠሪዎች የዘርፍ ማኅበር በጋራ ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ፊልም ፖሊሲ ትግበራ ላይ ያተኮረ ውይይት ሰሞኑን በብሔራዊ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አዳራሽ ማካሄዱ ይታወሳል። በውይይቱ መጨረሻ ከ20 ያላነሱ በኪነጥበቡ ላይ ተሳትፎ ያላቸው በጎፈቃደኛ ባለሙያዎች የፊልም ፖሊሲው ማስፈጸሚያ ሰነድ ለማዘጋጀት በሚደረገው ጥረት ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ተመርጠዋል።

    እንደ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ፥ የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ በኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. መጽደቁ ይታወሳል።

    በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀውን የፊልም ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ሙሉ ዶሴ (ፋይል) በፒ.ዲ.ኤፍ (PDF) እዚህ ጋር ያገኙታል

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ

    Semonegna
    Keymaster

    ዩኒቨርሲቲው ለሠራተኞቹ ያስተላለፋቸው መኖርያ ቤቶች ስቱዲዮ፣ ባለ አንድ መኝታ፣ ባለ ሁለት መኝታ እና ባለ ሦስት መኝታ ሲሆኑ ሠራተኞቹ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሠራተኝነት እስካሉ ድረስ ቤቶቹን በነጻ ይገለገሉባቸዋል።

    ነቀምቴ (ኢዜአ) – ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸውን መኖርያ ቤቶች ለሠራተኞቹ አስረከበ።

    የዩኒቨርሲቲው የመሠረተ ልማትና የሕንፃ ግንባታ ዳይሬክተር ዶክተር ደረጄ አደባ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የመኖርያ ቤት ለሌላቸው ሠራተኞቹ የቤት ባለቤት ለማድረግ ያስገነባቸውን 134 መኖሪያ ቤቶች ትናንት አስረክቧል። ለመኖሪያ ቤቶቹ ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም ገልጸዋል።

    ከዚህ በተጨማሪ በ1999 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ የተጀመሩና በገንዘብ እጥረት ምክንያት ግንባታቸው የተቋረጡ 10 ሕንፃዎችን በመግዛት ሠራተኞቹን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን፥ ሕንጻዎቹ ሲጠናቀቁ 150 የሚሆኑ የተቋሙን ሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸውንም ዶክተር ደረጄ አክለው ገልጸዋል።

    ዶክተር ደረጄ እንዳሉት መኖርያ ቤቶቹ ስቱዲዮ፣ ባለ አንድ መኝታ፣ ባለ ሁለት መኝታ እና ባለ ሦስት መኝታ ሲሆኑ ሠራተኞቹ በተቋሙ እስካሉ ድረስ ቤቶቹን በነጻ ይገለገሉባቸዋል።

    ከዩኒቨርሲቲው ሠራተኞቹ መካከል መምህር ተስፋዬ ፍቃዱ በሰጡት አስተያየት ተቋሙ በግል የኪራይ ቤት ሲንከራተቱ ይገጥማቸው ከነበረው ችግር እንደተፈታላቸው ተናግረዋል። በግል ተከራይቶ መኖር ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዳሉት ገልጸው በአከራዩና በተከራይ መካከል ቅሬታ በተፈጠረ ቁጥር ይደርስባቸው በነበረው መጉላላት ይማረሩ እንደነበር ገልጸዋል።

    መምህር እሱባለሁ ዳባ በበኩላቸው የግል ቤት በተከራዩበት ወቅት ከውሃና መብራት ክፍያ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጭቅጭቅና ግጭት ውስጥ ይገቡ እንደነበር አስታውሰዋል።

    በተመሳሳይ፦ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪዎች በርካታ መርሀ ግብሮችን ከፈቱ

    በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው በኩል የመኖሪያ ቤት ችግራቸው መፈታቱ የትምህርትና የምርምር ሥራቸውን ተረጋግተው ለማከናወን እንደሚያስችላቸው ጠቁመው በተቋሙ በኩል ለተደረገላቸው የመኖርያ ቤት ስጦታ መስጋናቸውን አቅርበዋል።

    መኖርያ ቤት ማግኘታቸው ከዚህ ቀደም ለግለሰብ ይከፍሉት የነበረውን የቤት ኪራይ ወጪ ከመቀነሱ ባለፈ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በማኅበራዊ ጉዳዮች እንዲተሳሰሩ የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት ደግሞ መምህር ኤልያስ ቱጁባ ናቸው። መምህሩ እንዳሉት ሠራተኞች አንድ አካባቢ መሆናቸው ለትራንስፖርት አገልግሎትና ለኢንቴርኔት አገልግሎት ምቹ ሁነታ ከመፍጠር አኳያ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

    ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ከዚህን ቀደም ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመኖርያ ቤት ሕንፃ በማስገንባት ከ60 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞቹ ማሰረከቡ የተቋሙን መረጃ ያሳያል።

    በየካቲት ወር 1999 ዓ.ም የተቋቋመው ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት 82 በመጀመሪያ (bachelors)፣ በሁለተኛ (masters) እና በዶክትሬት ዲግሪዎች ተማሪዎችን እንደሚያስተምር የዩኒቨርሲቲው ድረ ገጽ ያስረዳል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ወለጋ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 የስኳር ፋብሪካ የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጨምሮ የተለያዩ የክልል፣ የፌደራል እና የውጭ ሀገር ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 የስኳር ፋብሪካ መርቀው ከፈቱ።

    በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ንብረትነት በተገነባው በዚሁ ፋብሪካ የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ የኤርትራው ፕሬዝዳንት አማካሪ የማነህ ገብረአብ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁየቻይና ልማት ባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ቡ ዪ እንዲሁም የደቡብ ክልል ርዕስ መስተዳደር አቶ ሚሊዮን ማቲዮስን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናትም ተገኝተዋል።

    ከቻይና ልማት ባንክ በተገኘው 8 ቢሊዮን ብር ብድር የተገነባው ይህ ፋብሪካ በቻይናው ቻይና ኮምፕላንት ግሩፕ ተቋራጭነት የተገነባ ሲሆን የሙከራ ምርቱን ዛሬ ይጀምራል። ፋብሪካው የሙከራ ሥራውን የሚጀምረው ከ2ሺህ እስከ 3ሺህ ቶን ሸንኮራ አገዳ በመፍጨት ነው።

    ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ መሥራት ሲጀምር በቀን ከ8 ሺህ እስከ 10 ሺህ ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም የሚኖረው ሲሆን የዓለም ገበያን ፍላጎት መሠረት በማድረግም ጥሬ ስኳር (raw sugar)፣ ነጭ ስኳር (plantation white sugar) እና የተጣራ ስኳር (refined sugar) ማምረት ይችላል። ከሁለት ወር በፊት በተደረገው ፍተሻ የፋብሪካው ማምረቻ ማሽኖች ወደ ምርት ለመሸጋገር ዝግጁ መሆናቸው ተረጋግጠዋል።

    በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ስር በሚገኙ አራቱም ፋብሪካዎች በ100 ሺህ ሄክታር በላይ የሸንኮራ አገዳ ለማልማት የመስኖ መሠረተ ልማት ተከናውኗል፤ እስካሁንም ባለው ሂደት 30ሺህ ሄክታር መሬት የመስኖ ውሃ እንዲያገኝ ማድረግ ተችሏል። የመስኖ ውሃ ካገኘው መሬት ውስጥም 16ሺህ ሄክታር በሚሆነው መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ መተከሉም ተገልጿል።

    ዜና፦ ቬሎሲቲ አፓረልዝ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመርያ የሆነውን የግል የኢንዱስትሪ ፓርክ ሊገነባ ነው።

    የአሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት ስኳር ፋብሪካ ወደ ምርት በተሸጋገረበት በመጋቢት ወር 2008 ዓ.ም የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ፋብሪካ ግንባታ በይፋ መጀመሩ ይታወሳል። ግንባታውም የተከናወነው ከቻይና ልማት ባንክ በተገኘ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ነው።

    ፕሮጀክቱ ወደ አገልግሎት መግባቱ በአገሪቱ ስኳር ወደ ማምረት የተሸጋገሩ ፋብሪካዎችን ቁጥር ወደ ስምንት (ወንጂ ሸዋ፣ መተሐራ፣ ፊንጫአ፣ ከሰም፣ ተንዳሆ፣ አርጆ ዲዴሳ፣ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 እና 3) ያደርሰዋል።

    በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ስር ከሚገነቡት አራት የስኳር ፋብሪካዎች አንዱ የሆነው ይህ ፋብሪካ፤ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የኦሞ ወንዝን በሚያዋስኑት በከፋና ቤንች ማጂ ዞኖች መሃል ይገኛል።

    ኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ከተቋቋመ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ከ110 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 የስኳር ፋብሪካ ተመረቀ

     

    Semonegna
    Keymaster

    እንደ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጻ፥ እስካሁን ባለው ተሞክሮ የአንድ ፓርክ ግንባታ ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ይጠናቀቃል፤ በዚህ መሠረት  አሁን በግንባታ ላይ ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ይጠናቀቃሉ።

    አዲስ አበባ – እስከ አሁን ወደ ምርት የገቡትን አራቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮችና በቅርቡ የተመረቀውን የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጨምሮ በ2012 ዓ.ም ማጠናቀቂያ 15 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ማምረት እንደሚገቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

    የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽንና ማኔጅመንት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን በተለይ እንደተናገሩት፤ እስካሁን የሀዋሳ፣ የቦሌ ለሚ ቁጥር አንድ አይሲቲ፣ የመቐለ እና ኮምቦልቻ ፓርኮች ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ ገብተዋል። ከቀናት በፊት የተመረቀውን የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጨምሮ የጅማና የደብረ ብርሃን በሁለት ወራት ውስጥ ወደ ሥራ ይገባሉ።

    የቦሌ ለሚ ቁጥር ሁለት፣ የባህር ዳር፣ የድሬዳዋና የቂሊንጦ ፋርማስቲዩካል ፓርኮች በተያዘው በጀት ዓመት የሚጠናቀቁ መሆናቸውን ገልፀው ከዚህ በተጨማሪ የአይሻ፣ የአረርቲ የአሶሳና ሠመራ ፓርኮች በዚሁ ዓመት ግንባታቸውን ለመጀመር የአዋጭነት ጥናቶቻቸው ተጠናቆ ወደ ስምምነት እየተገባ መሆኑን ተናግረዋል። እስካሁን ባለው ተሞክሮ የአንድ ፓርክ ግንባታ ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ይጠናቀቃል ያሉት ኃላፊው ሌሎቹም በዚሁ መሠረት በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ይጠናቀቃሉ ብለዋል።

    ተያያዥ ዜና፦ ቬሎሲቲ አፓረልዝ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመርያ የሆነውን የግል የኢንዱስትሪ ፓርክ ሊገነባ ነው።

    ፓርኮቹ የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርቱ ቢሆንም በዋናነት መንግሥት በኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ባስቀመጠው መሠረት በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ፣ በህክምና መገልገያዎችና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። እነዚህ ዘርፎች በአነስተኛ ካፒታል የሚንቀሳቀሱ ሲሆን ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉም ናቸው። በተጨማሪም ፓርኮቹ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ከማበረታታት ባሻገር የውጭ ባለሀብቶችን በስፋት ለመሳብ የሚያስችሉ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።

    እንደ አቶ ሽፈራው ገለፃ፤ ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ በውጭ ምንዛሬ የሚገቡትን ምርቶች የሚተኩና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ የሚያሳድጉ ይሆናሉ። በዚህ ረገድ የቂሊንጦ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በመድኃኒት ምርት፣ የድሬዳዋና የአዳማ ደግሞ በኮንስትራክሽን ማቴርያልና ከውጭ የሚገቡ ኬሚካሎችን በአገር ውስጥ ለመተካት የተያዙ ሲሆን፤ በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የሚሰማሩት የወጪ ንግድ ላይ የሚያተኩሩ እንደሆኑም ገልፀዋል።

    በ2006 ዓ.ም. የተቋቋመው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን (IDPC) ሀገሪቱ ውስጥ በመንግስት ውጪ የሚገነቡትናና ወደ ሥራ የገቡትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች በበላይነት ይቆጣጠራል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬሥ ድርጅት

    የኢንዱስትሪ ፓርኮች

    Semonegna
    Keymaster

    በመቀሌ ከተማ በ147 ሚሊዮን ብር ካፒታል ሙሉ ብርሃን ኢንዱስቱሪና ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ያቋቋመው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

    መቀሌ (ኢዜአ) – በ147 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ገመድ ተሸካሚ የኮንክሪት ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካ ምርት ማከፋፈል መጀመሩን አስታወቀ።

    “ሙሉ ብርሃን ኢንዱስቱሪና ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር” በሚል የተቋቋመው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

    የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አቶ እሥራኤል ብርሃኑ ለኢዜአ እንደገለጹት ፋብሪካው በአገር አቀፍ ደራጃ ያለውን የኮንክሪት ምሶሶ ችግር ለመፍታት ታሳቢ ተደርጎ የተቋቋመ ነው።

    ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት በቀን እስከ 90 የሚደርስ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ ምሶሶዎችን በማምረት ላይ ሲሆን በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር በቀን እስከ 300 የተለያዩ ደረጃ ያላቸው ምሶሶዎችን የማምረት አቅም እንደሚኖረው ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

    ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመነጋገር ፋብሪካው ምርቶቹን ለትግራይአማራአፋር ክልሎች ማከፋፈል መጀመሩን አቶ እሥራኤል አስታውቀዋል።

    ፋብሪካው ከአገር ውስጥ ስሚንቶ፣ አሸዋና ጠጠር የሚጠቀም ሲሆን ለምሶሶው መሥሪያ የሚውሉ ብረቶችን ከውጭ በማስገባት ለአገልግሎት ያውላል።

    ፋብሪካው በሚያመርተው ምርት መንግስት በከተማና በገጠር የኤሌክትሪክ ሽፋን ለማዳረስ እያከናወነ ላለው ሥራ አጋዥ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

    የክልሉ መንግስት በቦታ አቅርቦትና ብድር በማመቻቸት እገዛ እንዳደረገላቸው የገለጹት አቶ እሥራኤል ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት እንዲችል ከውጭ ለሚመጡ ጥሬ ዕቃዎች መግዣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።

    በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የትግራይ ቅርንጫፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ገብረመድህን የኮንክሪት ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ምርቶች ማምረት መጀመሩን ተናግረዋል።

    የኮንክሪት ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካው በመቀሌ ማምረት መጀመሩ ከአሁን ቀደም ከአዲስ አበባ ለማጓጓዝ ለትራንስፖርት ይወጣ የነበረውን ወጪ ይቀንሳል ብለዋል።

    ከፍትኛ የኤሌክትሪክ ምሶሶዎች ለ20 ዓመታት ዋስትና ያላቸው መሆኑን የገለጹት ሥራ አስፈፃሚው ካሁን በፊት ለአገልግሎት ይውሉ የነበሩ የባህርዛፍ ምሶሶዎች በጉዳት ምክንያት ያደርሱ የነበሩትን አደጋና የኤሌክትሪክ መቆራረጥ የሚቀንስ ነው።

    የትግራይ ክልል ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሃፍቶም ፋንታሁን እንደገለጹት የምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካው በመቀሌ ከተማ ለተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ቦታ ከተሰጣቸው ባለሀብቶች መካከል በፍጥነት ወደ ማምረት ሥራ መሸጋገር መቻሉ በአርያነቱ እንዲቀመጥ የሚያደርገው ነው።

    የትግራይ ክልል የተረጋጋ ሰላም ያለው በመሆኑ በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን የጽህፈት ቤት ኃላፊው ገልጸዋል።

    በመካኒካል ምህንድስና የተመረቀው ወጣት አማኑኤል ሀይሉ በፋብሪካው በመቀጠር በወር 6ሺህ ብር የወር ደሞዝ እየተከፈለው ይሠራል። በፋብሪካው የሥራ እድል በማግኘቱ ደስተኛ መሆኑን የሚናገረው ወጣት አማኑኤል ገቢ ማግኘት መጀመሩ ከቤተሰብ ጥገኝነት ወጥቶ የራሱን ቤተሰብ ለመመስረት መቻሉን ገልጿል።

    ወጣት ዙፋን ኪዳኑ በበኩሏ “ማኅበሩ በዘርፉ ኢንቨስት በማድረጉ የአካባቢውን ወጣቶች የሥራ አድል ተጠቃሚ አድርጎናል” ብላለች።

    በትግራይ ክልል በ2010 ዓ.ም 24 ቢልዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 1ሺህ 328 ባለሀብቶች በሥራ እንዳሉ ከክልሉ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመልክታል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    የኤሌክትሪክ ምሶሶ

    Semonegna
    Keymaster

    የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት የሚሰጥበት ጊዜ ተራዘመ

    የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት የሚሰጥበት ቀን መራዘሙን የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ።

    ክትባቱ በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች በጥቅምት ወር እና ከስድስት ወራት በኋላ ደግሞ ለሁለተኛ ዙር ሊሰጥ ታቅዶ ነበር። በቢሮው የክትባት መርሃ ግብር የቴክኒክ አማካሪ አቶ ሙሉጌታ አድማሱ እንደገለፁት ለክትባት የሚሆነው መድሃኒት በመዘግየቱ ምክንያት ክትባት የሚሰጥበት ቀን ወደ ህዳር 5/2011 ዓ.ም ተራዝሟል።

    በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚሰጠው የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ዉጤታማነት በአማራ ክልል በሁሉም ዞኖች እና ወረዳዎች ለጤና ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱንም አቶ ሙሉጌታ ነግረውናል። ከጤና ጥበቃ ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው በክልሉ ከ4 መቶ 50 ሺህ በላይ ልጃገረዶች ክትባቱን ይወስዳሉ። እድሜያቸው 14 ዓመት የሆናቸው ልጃገረዶች ብቻ የክትባቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ለማወቅ ተችሏል።

    የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እድሜያቸው ከ9 እስከ 14 ዓመት የሆናቸው ልጃገረዶችን የግብረ ስጋ ግንኙነት ከመፈጸማቸው በፊት ከበሽታው ለመከላከል ሲባል በዓለማቀፍ ደረጃ ይሰጣል። ይሁን እንጅ በኢትዮጵያ ደረጃ ለሁሉም ልጃገረዶች የሚበቃ መድኃኒት ገዝቶ ማቅረብ ባለመቻሉ ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት ላይ ክትባቱ እንደሚሰጥ ጤና ጥበቃ ቢሮው ገልጿል።

    Semonegna
    Keymaster

    ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በዶክትሬት ዲግሪ አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮችን ከፍተው ተማሪዎችን ይቀበላሉ።

    ደብረ ብርሃን/ባህር ዳር – ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ (2011 ዓ.ም) የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ ዲግሪ (bachelor degree) አራት በሁለተኛ ዲግሪ (master degree) አስራ ሁለት መርሃ ግብሮችን እንደሚከፍት አስታወቀ።

    የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ጌትነት አሸናፊ ለኮሙኒኬሽን ጉዳዮች እንደገለጹት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን አስራ ስድስት አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮችን ይከፍታል።

    ዶክተር ጌትነት አሸናፊ እንዳሉት የትምህርት ክፍሎቹ ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያና ሁለተኛ ድግሪ ዲግሪ የሚሰጣቸውን የትምህርት መርሀ ግብሮች የመጀመሪያ ድግሪ ከ49 ወደ 53 እንዲሁም 34 የነበረውን የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሀ ግብር ወደ 46 ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።

    ከተመሠረተ 11 ዓመት የሞላው ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ሰዓት ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ መስኮች እያስተማረ ይገኛል።

    በተመሳሳይ ዜና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ፣ በበሁለተኛ እና በዶክትሬት (doctorate) ዲግሪ በሚከፍታቸው 18 አዳዲስ የትምህርት መስኮች ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ። ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት ከ8 ሺህ 700 በላይ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበልም አስፈላጊው ዝግጅት ማድረጉም ተጠቁሟል።

    የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር እሰይ ከበደ ዛሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ተቋሙ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ አዳዲስ የትምህርት መስኮችን በመክፈት አገራዊ እድገቱን በእውቀት ለማገዝ እየሠራ ነው።

    በተያዘው የትምህርት ዘመንም ሁለት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ 12 የሁለተኛ ዲግሪና አራት የዶክትሬት ዲግሪ የትምህርት መስኮችን ከፍቶ 250 ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

    ዶክተር እሰይ እንዳሉት ህግ፣ መሬት አስተዳደር፣ ጤና፣ ቴክኖሎጂ፣ ጨርቃጨርቅ፣ ትምህርት፣ ፖለቲካል ሳይንስና የመሳሰሉት የትምህርት መስኮች አዲስ የሚከፈቱባቸው ናቸው። “የተሳካ የመማር ማስተማር ተግባር ለማካሄድም ቀደም ብሎ የሥርአተ ትምህርት ቀረጻ መደረጉንና የመምህራን ቅጥርም ሆነ ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል” ብለዋል።

    የኒቨርሲቲው በአፋን ኦሮሞ ትምህርትም በዚህ ዓመት አጋማሽ መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሥርአተ ትምህርት ቀረጻ ሥራ ማካሄዱንና የመምህራን ቅጥር እየፈጸመ መሆኑን ዶክተር እሰይ አስታውቀዋል።

    ተቋሙ በህክምናው ዘርፍ የተሻለ እውቅት ያላቸው ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ “የተሻለ የማስተማርም ሆነ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት አዲስ የማስተማሪያ ሆስፒታል ገንብቶ የ170 መምህራንን በመቅጠር ላይ ነው” ብለዋል።

    ዩኒቨርሲቲው በመደባኛው የትምህርት መርሀግብር ብቻ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ከ8 ሺህ 700 በላይ አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምርም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አያይዘው ገልጸዋል።

    በተለይም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ዩኒቨርሲቲ እየወረደ የመጣውን የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ የተሻለ አቅም ያላቸውን መምህራን በመመደብ፣ ቤተ ሙከራዎችንና ቤተ መጻህፍትን በማደረጀት ጥራትን ለማምጣት እየሠራ መሆኑንም ገልፀዋል። ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን አጠናቀው ከመውጣታቸው በፊትም አጠቃላይ የጥራት መለኪያ ፈተና እንዲወስዱም እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

    ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመደበኛውና መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት መርሃ ግብሮች ዓመታዊ የተማሪ የቅበላ አቅሙ በአሁኑ ወቅት ከ50 ሺህ በላይ ደርሷል።

    ምንጭ፦ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር ጌትነት አሸናፊ (ፎቶ፦ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ)

    Semonegna
    Keymaster

    የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል (በተለምዶው አማኑኤል ሆስፒታል) ኢትዮጵያ ውስጥ የአዕምሮ ህክምና የሚሰጥ ትልቁ ሆስፒታል ሲሆን፥ የተቋቋመውም በጣልያኖች እ.ኤ.አ በ1937 ዓ.ም አካባቢ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። 

    አዲስ አበባ – በየዓመቱ እ.ኤ.አ ጥቅምት 10 ቀን የሚከበረውን የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአገራችን ለ26ኛ ጊዜ “ወጣቶች እና የአዕምሮ ጤና በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ” በሚል መሪ ቃል የተለያዩ ምሁራን፣ የህክምና ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም የሆስፒታሉ ሠራተኞች በተገኙበት መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም በአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ በድምቀት ተከበረ።

    የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች የተከበረ ሲሆን ቀኑን አስመልክቶ የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዳኦ ፈጆ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ “ወጣቶች ብዙ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት የዓለም መረጃ መረብ ላይ በመጠመድ የሳይበር ወንጀልን በመለማመድ፤ ይህንኑ የመገናኛ መረብ በመጠቀም ህዝብን ወደ አልተፈለገ የእርስ በርስ ግጭቶች ውስጥ በማስገባት እና ከዚህም ሲያልፍ ከማኅበረሰቡ ባህልና ሞራል ውጭ የሆኑ ባዕዳን ቪዲዮዎችን በመመልከት ላይ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

    አያይዘውም ራሳቸውን የሚያጠፉና በአደንዛዥ እፅ ሱስ ስር እየወደቁ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱ እማኝ የሚያሻው ጉዳይ እንዳልሆነ በመጥቀስ በዚህ አዙሪት ውስጥ የሚያልፉት ደግሞ አብዛኛውን ወጣቶች መሆናቸው እጅግ አስደንጋጭ ነው ብለዋል። ዋና ሥራ አስኪያጁ እንደገለፁት አብዛኛው የአዕምሮ ህመሞች በወጣትነት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚከሰቱ መሆናችውና ወጣቶቹ ደግሞ ስለ አዕምሮ ጤና ያላቸው ግንዛቤ እና አስተምህሮ አናሳ መሆኑ ይበልጥ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል ሲሉ አክለዋል።

    በመጨረሻም “ይህ ቀን ወጣቶቻችን እንዴት ጠንካራ፣ ችግር ፈች፣ ከሱስ አዙሪት፣ ከእርስ በርስ ግጭቶች፣ ከእፅ ተጠቃሚነት እና ከልክ ያለፈ የኢንተርኔት ተጠቃሚነት (substance abuse and internet overload) ሰብረው መውጣት የሚችሉበትን መፍትሄ የምናፈላልግበትና የምንመክርበት ጊዜው አሁን ነው” በማለት ለታሳታፊዎቹ መልእክታቸውን በአንክሮ አስተላልፈዋል።

    በዝግጅቱ ላይ ቀኑን አስመልክቶ የአዕምሮ ጤና ምንነት፤ በአዕምሮ ጤና ላይ የማኅበረሰቡ የግንዛቤ ደረጃ ፤ በአገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የስርጭት ሁኔታ እንዲሁም ወጣቶች እና የአዕምሮ ጤና በአሁኑ ወቅት ምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስፔሻሊስት በሆኑት በዶ/ር ሙሃመድ ንጉሴ እና በዶ/ር ዮናስ ላቀው ለተሳታፊዎቹ ገለፃ ቀርቧል። በመቀጠልም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በእንግድነት የተገኙት ፕሮፌሰር አታላይ ዓለም እንደተናገሩት በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየንተሰራፋ የመጣውን የአዕምሮ ጤና ችግር ለመቀነስና መፍትሄ ለማበጀት መንግስት፤ ባለድርሻ አካላት እና ሚዲያዎች የአንበሳውን ድርሻ ሊወስዱ እንደሚገባ ገልፀዋል።

    በመጨረሻም በተለያየ የአዕምሮ ህመም ተጠቂ ሆነው አማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ ህክምና ተደርጎላቸው በመልካም ጤና ላይ የሚገኙ ሶስት ፈቃደኛ ግለሰቦች ሆስፒታሉን ከማመስገን ባለፈ በአዕምሮ ጤና ላይ የነበራቸውን ግንዛቤ እና ልምድ ለተሳታፊዎች ያካፈሉ ሲሆን በመልእክታቸውም የአዕምሮ ህመም እንደማንኛውም ህመም ውጤታማ ህክምና ያለው መሆኑን በማስተላለፍ በማኅበረሰቡ ዘንድ ስለ አዕምሮ ህመም ያለውን የተዛባ ግንዛቤ ለመቅረፍ መንግስት እና ህዝብ በጋራ ሊሰሩ እንዲሚገባ አስተላልፈዋል።

    ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስር የሚተዳደረው የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል (በተለምዶው አማኑኤል ሆስፒታል) ኢትዮጵያ ውስጥ የአዕምሮ ህክምና የሚሰጥ ትልቁ ሆስፒታል ሲሆን፥ የተቋቋመውም በጣልያኖች እ.ኤ.አ በ1937 ዓ.ም አካባቢ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሆስፒታሉ ዘርፈ ብዙ ማስፋፋቶችን እያከናወነ ሲሆን፥ በየካቲት ወር 2009 ዓ.ም. በሆስፒታሉ ስር ሆኖ የየካ ኮተቤ ሆስፒታል የአዕምሮ ህክምና መስጠት ጀምሯል

    ምንጭ፦ የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል

    አማኑኤል ሆስፒታል

    Semonegna
    Keymaster

    አደጋ የተጋረጠበትን የቡናውን ኢንዱስትሪ በጥናትና ምርምር ታገዞ ከአደጋ መታደግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሠረታዊ ዓላማ ነው የሚሉት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቃልኪዳን ነጋሽ፥ ዲላ ዩኒቨርሲቲ የበኩሉን ሚና ለመጫወት የቡና ምርምር ማዕከል በማቋቋም በዘርፉ የአርሶ አደሩን ህይወት መቀየር የሚችል ውጤታማ የምርምር ሥራዎችን ይሠራል።

    ዲላ (ዲዩ) – ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከደቡብ ክልል ቡና አበጣሪዎች፣ አጣቢዎችና አቅራቢዎች ዘርፍ ማኅበር ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።

    የቡና ኢንዱስትሪ በዓለም ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ዘርፍ ከመሆኑ ባሻገር ከ2.25 ቢሊዮን ሲኒ በላይ ቡና በየቀኑ እንደሚጠጣ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ ፍላጎት እየጨመረ ቢመጣም አቅርቦቱ እየቀነሰ መምጣቱ እንዳሳሰባቸው የዘርፉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ለዚህም የአየር ንብረት ለውጥና ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን ለምርት መቀነስ በምክንያትነት ይጠቀሳል።

    ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ምድር ብቻ ሳትሆን በዘርፉ የዕውቀት መሠረትም ናት። 25 በመቶ የሚሆነው የሀገራችን ህዝብ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ህይወቱ በቡና ላይ የተመሠረተ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ ከምታመርተው ቡና ዘጠና በመቶውን የደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች ይሸፍናሉ።

    የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ የነበረው ቡና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ከፍተኛ የምርት መቀነስ አሳይቷል። የቡና በሽታ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የእርሻ መሬት መስፋፋት፣ የደን ጭፍጨፋና ሰደድ እሳት፣ የአቅም ውስንነትና የግንዛቤ እጥረት ለቡና ምርት መቀነስ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

    ከውሃ ቀጥሎ በብዛት የሚጠጣው ቡና በዓለም የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት በነዳጅ ብቻ ይቀደማል። በሀገራችን ደግሞ ከፍተኛውን ደረጃ ይይዛል።

    አደጋ የተጋረጠበትን የቡናውን ኢንዱስትሪ በጥናትና ምርምር ታገዞ ከአደጋ መታደግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሠረታዊ ዓላማ ነው የሚሉት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቃልኪዳን ነጋሽ በዩኒቨርሲቲው የቡና ምርምር ማዕከል መቋቋሙ በዘርፉ የአርሶ አደሩን ህይወት መቀየር የሚችል ውጤታማ የምርምር ሥራዎችን ለመሥራት ያስችለናል ብለዋል።

    በጌዴኦ፣ ጉጂና ሲዳማ ዞኖች የቡና ምርታማነት መቀነስን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምሮች በመሥራት አርሶ አደሮችን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው ይሠራል ያሉት ፕሬዚዳንቱ በቀጣይም ዘርፉን ለማሳደግ የቡና ትምህርት ክፍል መክፈት፣ የምርምር መፅሔት ማሳተምና ለሚሰሩ ምርምሮች የበጀትና ሃሳብ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

    ዲላ ዩኒቨርሲቲ በጌዴኦ ዞን ከ3 ሄክታር በላይ መሬት ተረክቦ የቡናን ምርት በጥራትና በመጠን ከፍለ ማድረግ የጥናትና ምርምር ሥራ መጀመሩን የተናገሩት የምርምርና ስርፀት ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር መምህር ዳርጌ ፀጋዬ የአየር ንብረት ለውጥ፣ በሽታና ዕድሜ ለምርት መቀነስ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።

    የቡና ምርምር ማዕከል መቋቋሙ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያግዛል ያሉት መምህር ዳርጌ፥ በሽታን የሚቋቋሙ ምርጥ ዝርያዎችን በሳይንሳዊ መንገድ በማባዛት ያረጁና በበሽታ የተጠቃውን ቡና ለመተካት እየተሠራ ነው ብለዋል።

    የደቡብ ክልል ቡና አበጣሪዎች፣ አጣቢዎችና አቅራቢዎች ዘርፍ ማኅበር ፕሬዚዳንትና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ አባል አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ በበኩላቸው ከዩኒቨርሲቲው ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው በቡና ጥራት፣ምርት መቀነስና በአባላት ተጠቃሚነት ላይ የተደቀነውን ችግር በሳይንሳዊ መንገድ መፍትሄ ለመስጠት ያግዛል ብለዋል።

    የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ኢንዱስትሪውን በመደገፍ የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ የጎላ ነው ያሉት አቶ ዘሪሁን በቡና ምርት ላይ ከምርት እስከ ግብይት ድረስ የሚያግጥሙ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ምርምር መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል።

    የምርምር ሥራዎቹም በአዳዲስ ፈጠራ፣ በትምህርትና ስልጠና እንዲሁም ከሀገሪቱ፣ ከኢንዱስትሪውና የአባላት ፍላጎት ጋር የተጣጣመ የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት በተለይ በዘርፉ የሴቶችን ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚያስችል ሥራ ለመሥራት ያግዛል ብለዋል አቶ ዘሪሁን።

    ምንጭ፦ ዩኒቨርሲቲው

    ዲላ ዩኒቨርሲቲ

Viewing 15 results - 691 through 705 (of 730 total)