Search Results for 'የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ'

Home Forums Search Search Results for 'የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ'

Viewing 15 results - 16 through 30 (of 49 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    ቴሌብር የሞባይል ገንዘብ አ ገልግሎት ምረቃ በተመለከተ የቀረበ ጋዜጣዊ መግለጫ ― ኢትዮቴሌኮም

    ኩባንያችን “ቴሌብር” የተሰኘ፣ ለማኅበረሰባችን ምቹ እና ሁሉን አካታች የሆነ የገንዘብ ማስተላለፊያ እና የመገበያያ ዘዴ የሆነውን፣ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎቱን (mobile money service) ለመጀመር አስፈላጊ ዝግጅቶችን አጠናቆ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም አገልግሎቱ መጀመሩን ሲያበስር በታላቅ ደስታ ነው!

    በሀገራችን በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውና በኩባንያችን የሚሰጥ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ከተደራሽነትና ለአጠቃቀም እጅግ ቀላል ከመሆኑ አኳያ ለማኅበረሰባችን የብስራት ዜና ሲሆን፤ ሕዝባችንን ለማገልገል ካለን ጽኑ ፍላጎት አንጻር ለኩባንያችን ትልቅ ስኬት ነው።

    የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በሀገራችን ያለውን የፋይናንስ አካታችነት ክፍተት በማጥበብ፣ ዜጎች ባሉበት ሆነው ፈጣንና ቀላል በሆነ ዘዴ እንዲሁም በአነስተኛ የግብይት ወጪ የተሻለ የፋይናንስ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታን ያመቻቻል። የፋይናንስ አካታችነት /financial inclusion/ ሁሉንም የፋይናንስ አገልግሎቶች ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ ፅንሰ ሀሳብ ሲሆን፤ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ ዓይነተኛ መፍትሔ ነው። ቴሌብር የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ጤናማ የገንዘብ ፍሰት ከመፍጠሩም ባሻገር፥ ቁጠባን በማሳደግ፣ ድህነትን በመቀነስ፣ ሥራ ፈጣሪነትንና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት እንዲሁም ገንዘብ የሚታተምበትን ወጪ በመቀነስና ኢኮኖሚን በማሳደግ የሕዝባችንን ሁለንተናዊ እድገትና ተጠቃሚነትን ያሳድጋል።

    ኩባንያችን ለቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ መዋዕለ-ንዋይ በማፍሰስ የዘረጋውን መጠነ ሰፊ መሠረተ ልማት በመጠቀም ወደ ደንበኞቹ ቅርብ ከመሆኑ አኳያ ለኅብረተሰባችን ተጨማሪ እና ከፍተኛ አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥር አገልግሎት ማስጀመሩ በሀገራችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲሁም ለኅብረተሰባችን የዕለት ተዕለት ኑሮ መሻሻል ጉልህ አስተዋጽዖ ይኖረዋል።

    ኩባንያችን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎትና ተያያዥ የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ለውድ ደንበኞቹና ለሁሉም ማኅበረሰብ ለማቅረብ የፍቃድ ጥያቄውን ካቀረበበት ወቅት ጀምሮ ሰፊ የዝግጅት ሥራዎችን ያከናወነ ሲሆን፤ በተለይም በኢንዱስትሪው የተመረጠና የተሻለ የሞባይል ገንዘብ ቴክኖሎጂን ሥራ ላይ ለማዋል፣ ተገቢ ፖሊሲዎችን እና አሠራሮችን ለመተግበር፣ ሰፊውን ወኪል ኔትወርክ (ngent network) ለማንቀሳቀስ እና ከቴሌኮም እና ከፋይናንስ ኢንዱስትሪዎች የተሻሉ ልምዶችን በመቀመር በቂ ዝግጅት በማድረግ በዋናነት የባንክ አገልግሎት ማግኘት ያልቻሉ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችና በገጠር የሚገኙ ዜጎችን የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ ጥረቶችን በማድረግ ለዛሬው ስኬት በቅቷል።

    አገልግሎቱን ለማኅበረሰባችን በማቅረብ ሂደት ውስጥ በርካታ ተቋማት የሚሳተፉ ሲሆን፤ በተለይም በሀገራችን ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የፋይናንስ እና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች እንዲሁም አገልግሎቱን ለደንበኞቻችን ቅርብ ለማድረግ የሚያስችሉ ከኩባንያችን ጋር ልዩ ውል ያላቸው ዋና ወኪሎች /master agents/ እና በእነዚህ ዋና ወኪሎች የተመለመሉ እስካሁን ባለው ከ1,600 በላይ ወኪሎች /agents/ ዋነኛ ተሳታፊዎች ናቸው። የአገልግሎት ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ የወኪሎችን ቁጥር በየወሩ በማሳደግ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ15ሺህ በላይ ለማድረስ እየተሠራ ይገኛል።

    ቴሌብርን በመጠቀም ገንዘብ ከማስተላለፍ፣ ከመቀበልና ከመክፈል በተጨማሪ ግብይት ለመፈጸም የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር ከተለያዩ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጋር አብረን እየሠራን ሲሆን፤ ለአብነት ያህል ውሀና ፍሳሽ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ገቢዎች፣ ሱፐር ማርኬቶች፣ ነዳጅ ማደያዎች፣ እርዳታ ድርጅቶች፣ ካፌዎችና ሬስቶራንቶች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ የህትመት ሚዲያዎች እና ሌሎችም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚገኙበት ሲሆን አገልግሎቱ ክፍያ መቀበልና መፈጸም ያስችላቸዋል።

    ከዚህ በተጨማሪም ደንበኞቻችን ከውጭ ሀገር የሚላክላቸውን ገንዘብ ቴሌብር የሞባይል ገንዘብ አገልግሎትን በመጠቀም በቀላሉና በአነስተኛ ወጪ ለመቀበል የሚያስችላቸው አገልግሎት ለማስጀመር ከዓለም አቀፍ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ጋር የኢንቴግሬሽን ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፤ ኩባንያችን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ፈቃድ ካገኘ አጭር ጊዜ ከመሆኑ አኳያ ከድርጅቶቹ ጋር ያሉ ሂደቶችና ፎርማሊቲዎችን አጠናቆ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አገልግሎቱን መስጠት ይጀምራል።

    በቀጣይም ቴሌብር የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ለማኅበረሰባችን ሁለንተናዊ ለውጥና መሻሻል ከፍተኛ ሚና ያላቸው እንዲሁም የፋይናንስ አገልግሎት ከማግኘት ባሻገር ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የሞባይል አነስተኛ ብድር፣ የቁጠባ አገልግሎትና ተያያዥ የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበርና አስፈላጊ ቅደመ ሁኔታዎችን በማሟላት የሚያስጀምር ይሆናል።

    የቴሌብር አገልግሎት በሀገራችን የፋይናንስ አገልግሎት ላይ የሚታየውን ውስንነት ወይም የፋይናንስ አካታችነት ክፍተት በማጥበብ ሰፊ ሚና የሚጫወት ሲሆን አሁን ላይ 35% ብቻ የሆነውን የፋይናንስ አካታችነት ወደ 60% ለማሳደግ ግብ አስቀምጠን እየሠራን ሲሆን በተለይም ከኮቪድ-19 ጋር በተገናኘ የገንዘብ ንክኪን ለመቀነስ የቴሌብር አገልግሎት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።

    ቴሌብር የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶች ያሉት አገልግሎት ሲሆን በተለይም የሀገራችንን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ጉልህ ሚና ለመጫወት በዘርፉ ላይ ድርሻና ሚና ያላቸውን አካላት በማሳተፍ ተቀናጅቶ በመሥራት በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ ከ40% እስከ 50% ያህሉን ጠቅላላ የሀገራችን የኢኮኖሚ ግብይትና የገንዘብ ፍሰት በቴሌብር እንዲከናወን አቅደን እየሠራን እንገኛለን።

    በዚህ አጋጣሚ ቴሌብር የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት የበለጠ ፍሬ እንዲያፈራና የሀገራችንን የዲጅታል ፋይናንስ ፍላጎት ለማሟላት እና ዲጅታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት ከግብ ለማድረስ በኢኮሲስተሙ ሚና ያላቸው ባለድርሻ አካላት በተለይም የፋይናንስ ተቋማት፣ የንግድ ድርጅቶችና አገልግሎት ሰጭ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆናችሁ ተቋማት አብራችሁን እንድትሠሩ ጥሪያችንን በአክብሮት እናቀርባለን።

    ኢትዮቴሌኮም

    ቴሌብር

    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡታጅራ ከተማ ወስጥ ያስገነባውን የባንኩ ዲስትሪክት ህንፃ ሳይጠናቀቅ በመተው
    ወደ ሌላ አካባቢ እንዲዛወር መደረጉ አግባብነት የሌለው ነው ተባለ

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጉራጌ ማኅበረሰብን ነዋሪዎችን እና አጎራባች ከተሞችን ታሳቢ በማድረግ በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር የባንኩን ዲስትሪክት ለመክፈት ከውሳኔ ደረሶ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ከጫፍ ሲደርስ ዲስትሪክቱን ወደሌላ አካባቢ ማዛወሩ ተገቢ አለመሆኑ ተገለፀ።

    የጉራጌ ማኅበረሰብ ከጥንት ጀምሮ እሴቱ የሆነውን የቁጠባ ባህል ፍላጎት እና የልማት ተነሳሽነት ተከትሎ የቡታጅራ ከተማ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በከተማዋ መሀከል ላይ ዋናውን መስመር ተከትሎ ባንኩ ቅርንጫፍ እንዲከፍት ቦታውን አመቻችቶ ባቀረበው መሠረት ቅርንጫፉን ከፍቶ አሁን አራት አድርሷል።

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡታጅራ ከተማ ቅርንጫፍ ባለበት ስፍራ ለጉራጌ ማኅበረሰብ በዞኑ ለሚኖሩ ማኅበረሰቦች እና ለአጎራባች ከተሞች የሚያገለግል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲስትሪክት ለመክፈት ከውሳኔ በመድረስ፥ ህንፃም ገንብቶ ለማጠናቀቅ ከጫፍ ባደረሰበት ሰዓት ማዕከሉን ወደ ሌላ አካባቢ ማዛወሩ ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ማኅበረሰቡ ቅሬታውን እያቀረበ ይገኛል።

    የባንኩ ማኔጅመንት ባስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መሠረት ለጉራጌ እና ለአካባቢው ከተሞች በማዕከልነት የባንኩ ዲስትሪክት አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበት ውሳኔ በማሳለፍ በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር የጀመረውን የዲስትሪክት መቀመጫነት ወደ ሌላ አካባቢ ማዛወሩ የአካባቢውን ማኅበረሰብ የማይመጥን ውሳኔ መሆኑን ማኅበረሰቡ ያነሳል።

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአመራር (ማኔጅመንት) አባላትም የመጀመሪያ ውሳኔያቸውን በማጽናት በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር የባንኩን ዲስትሪክት በማስቀጠል ባለበት የማያጸኑ ከሆነ የዞኑን ማኅበረሰብ በባንኩ ላይ ያለውን ደንበኝነት የሚሸረሽርና ደንበኝነታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድርም ከግምት ውስጥ ያላስገባ ውሳኔ መሆኑን ማኅበረሰቡ ይገልፃል።

    ባንኩ የራሱ የሆነ አሠራር አለው በማንኛውም ዓይነት በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ጣልቃ ገብነት ውሳኔውን በመሻር ዲስትሪክቱን ማዛወሩ ቅቡልነት የሌለው አሠራር መሆኑን በማስገንዘብ፤ ባንኩ በመጀመሪያው (በቀደመው) ወሳኔው ፀንቶ በተጀመረበት ስፍራ ማስቀጠል እንደሚገባም በመግለጽ ማኅበረሰቡ ያሳስባል።

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ የጉራጌና የአካባቢዋ ማኅበረሰብም የኢትዮጵያ አንድ አካል ነው፤ ልማትም ይሻል፤ የዚህን ማኅበረሰብ ስሜት ከግምት ውስጥ ባለማስገባት የተጀመረና ለማጠናቀቅ ከጫፍ የደረሰን ልማት ማዛወር በምንም ዓይነት አስተሳሰብም ሆነ አመለካከት ተቀባይነት የሌለው ውሳኔ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ሲል ማኅበረሰቡ ይገልጻል።

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቡታጅራ ከተማ

    Anonymous
    Inactive

    በኢትዮጵያ አዲስ የ200 ብር ኖት ይፋ ተደረገ፤ ነባሮቹ የ10፣ የ50 እና የ100 ብር የገንዘብ ኖቶችም ተቀይረዋል

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ኢትዮጵያ ነባሮቹን የ10፣ የ50 እና የ100 ብር የገንዘብ ዓይነቶች (የገንዘብ ኖቶች) ሙሉ ለሙሉ መለውጧን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አስታወቁ። በተጨማሪም አዲስ የ200 ብር ኖት መቅረቡንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። እንዲሁም የ5 ብር ገንዘብ ኖት ባለበት ቀጥሎ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ሣንቲም እንደሚቀየርም ተገልጿል።

    እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፥ ነባሮቹን የገንዘብ ኖቶች በመተካት ለግብይት የሚሆን አዲስ የገንዘብ ኖት መጠቀም እንደምትጀምር መስከረም ሦስት ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ተደርጓል።

    እነዚህ አዲስ የገንዘብ ኖቶች ለሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍን፣ ሙስናን እና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠርና ለመቀልበስ ይረዳሉ ብለዋል።

    በአዲሶቹ የገንዘብ ኖቶች ላይ የተካተቱት ምስጢራዊ ምልክቶችና መለያዎች የገንዘብ ኖቶቹን አመሳስሎ ለማተም የሚደረጉ ሕገ ወጥ ጥረቶችንም ለማስቀረት እንደሚያግዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አክለው ገልጸዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት መልዕክት (እንግሊዝኛ) እንዲህ ይነበባል፦

    Ethiopia today unveils new Birr notes for 10, 50 & 100 denominations, with introduction of a new Birr 200 note. The new notes will curb financing of illegal activities; corruption & contraband. Enhanced security features on the new notes will also cease counterfeit production.

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ የገንዘብ (የብር) ኖቶች ለውጡን ተከትሎ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር ዝግጅት ተደርጓል። በተለያዩ ጎረቤት ሀገራት የኢትዮጵያ የብር ኖቶች ክምችት መኖሩን የጠቀሱት ዶ/ር ይናገር፥ ለብር ለውጡ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል። ለዚህም ከጸጥታና የደህንነት አካላት ጋር በመነጋገር የመቆጣጠርና የማምከን ተግባራት እንደሚከናወኑ ገልጸዋል። በተለይ በድንበር አካባቢ የሚገኙ ባንኮችም በብር ኖቶች ለውጡ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እንዳይጋለጡ ጥብቅ ክትትል ይደረጋል ብለዋል።

    ዶ/ር ይናገር የብር ኖቶች ቅያሬውን ለማከናወን ማንኛውም ግለሰብ የብር ኖቶቹን ራሱ በባንክ መቀየር ሲገባው፥ በሌላ ግለሰብ (በውክልና) የገንዘብ ኖት ለውጥ ማከናወን የማይችል መሆኑንም ተናግረዋል።

    በ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን የብር ኖት መታተሙንና የመጠባበቂያ ክምችት እንዲኖር ተጨማሪ የብር ኖቶች እየታተሙ መሆኑን ዶ/ር ይናገር አመልክተዋል። ባለፉት ጥቂት ወራት አዳዲሶቹን የብር ኖቶች ወደ ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የማጓጓዝ ሥራ መሠራቱንና አሮጌውን ገንዘብ መቀየር የሚያስችል በቂ ክምችት እንዳለ ገልጸዋል።

    ካፒታል ኢትዮጵያ ሳምንታዊ ጋዜጣ በግንቦት ወር 2012 ዓም እንደዘገበው፥ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር (EBA) በነበሩት የብር ኖቶች ላይ ለውጥ እንዲደረግ መጠየቁን ገልጾ ነበር። ማኅበሩ በአሁኑ ጊዜ በብር ኖቶች መበላሸት ምክንያት ከ113 ቢሊዮን ብር በላይ ከባንክ አገልግሎት ውጪ እንደሆነ በመጥቀስ፥ የሚታየውን የብር ኖቶች ከገበያ/ ከአገልግሎት ውጪ መሆን ችግር ለመቅረፍ የብር ኖቶችን መቀየር አስፈላጊነት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ (NBE) አስገንዝቦ ነበር።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሌሎች ዜናዎች፦

    የ200 ብር ኖት

    Semonegna
    Keymaster

    ሸገር ፓርክ በትልቅ ሥነ-ሥርዓት ተመርቋል

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአዲስ አበባን ከተማ የቀይራል ተብሎ የሚጠበቀው ሸገር ፓርክ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት በአዲስ ዓመት ዋዜማ ጳጉሜን 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ባለስልጣናት እና ጥሪ የተደረገላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች እና የተለያዩ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም በተገኙበት ተካሂዷል።

    ሸገር ፓርክ የኢትዮጵያን ሕብረ ብሔራዊነት በሚያሳይ መልኩ የተገነባ ሲሆን፥ በውስጡ የተፈጥሮ እጽዋትንም ያካተተ ነው። ፓርኩ የኢትዮጵያን ቀደምት ታሪክ በማሳየት የወደፊት ብሩህ ተስፋን የሚያሳይ የወዳጅነት ፓርክ እንደሆነ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።

    ግንባታው ከአንድ ዓመት በፊት የተጀመረው ሸገር ፓርክ በቻይና ግዙፉ የግንባታ ሥራ ተቋራጭ ኩባንያ “China Communications Construction Company (CCCC)” የተገነባ ነው።

    በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በፓርኩ ግንባታ አስተዋጽኦ ላደረጉ የቻይና የተለያዩ ኩባንያዎች ትልቁን የወዳጅነት ሽልማት አበርክተዋል። በግንባታው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ኢትዮጵያዊያንም እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

    ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሸገር ፓርክ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ካደረጉት ንግግር የተወሰዱ ነጥቦች፡-

    • አዲስ አበባ ይህን ፓርክ ማግኘቷ ስሟንና ደረጃዋን ከፍ ያደርገዋል፤
    • ይህ እና ሌሎች ፓርኮች የከተማይቱንና የሀገራችንን ገፅታ ያስውቡታል፤
    • ፓርኩ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤
    • ፓርኩ ተባብሮ መሥራት የሚያስገኘውን ውጤት ማሳያ ነው፤
    • ሸገር ፓርክ ከመሃል ሀገር ሳንወጣ ሩቅ ቦታ የተጓዝን የሚያስመስለን ፓርክ ነው፤
    • ከተለምዶው የተለየ ነገር ማየት አድማሳችንን ያሰፋዋል፤
    • [በግሌ] ይህ ፓርክ በዚህ ፍጥነት ለምረቃ ይበቃል ብዬ አላሰብኩም ነበር፤
    • በፓርኩ በሚገኘው የአበባ ማፍያ ስፍራ ከዓይናችን ጠፍተው የቆዩ አበቦችን ሳይቀር ማስተዋል ችያለሁ፤
    • ውበትን መሻት ካለንበት ሀኔታ ጋር አይፃረርም፤
    • አገራችንን የማስዋብ ጥረታችንን ከሌሎች የልማት ጥረቶቻችን ጋር ጎን ለጎን ካስኬድነው በአጭር ጊዜ የአገራችንን ገፅታ መቀየር እንችላለን፤
    • በፕሮጀክቱ የተሳተፉ ሁሉም አካላት የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሸገር ፓርክ

    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የበረራ ትኬትን በኤሌክትሮኒክ ክፍያ ዘዴ አማካኝነት አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ስምምነት አደረገ
    ደንበኞች የ‘ጉዞጎ’ (GuzoGo) መተግበሪያን በመጠቀም የሀገር ውስጥ እና ዓለምአቀፍ የበረራ ትኬቶችን መግዛት የሚችሉበት አሠራር ተዘርግቷል

    አዲስ አበባ – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሶልጌት ትራቭል (Solgate Travel) የበረራ ትኬት ሽያጭ በኤሌክትሮኒክ ክፍያ ሥርዓት ለማከናወን የሚያስችላቸውን ስምምነት ነሐሴ 29 ቀን 2012 ዓ.ም በተካሄደ ይፋዊ ሥነ-ሥርዓት ፈጽመዋል።

    በስምምነቱ መሠረት ደንበኞች የሲቢኢ ብር (CBE Birr) እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁሉም ቅርንጫፎች አማካኝነት ክፍያቸውን መፈፀም የሚያስችል የ‘ጉዞጎ’ (GuzoGo) መተግበሪያን በመጠቀም የሀገር ውስጥ እና ዓለምአቀፍ የበረራ ትኬቶችን መግዛት የሚችሉበት አሠራር መዘርጋቱን ነው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ዮሐንስ ሚሊዮን የገለፁት።

    ደንበኞች በረራቸውን ለማስመዝገብና የትኬት ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለው የ‘ጉዞጎ’ (GuzoGo) የሞባይል መተግበሪያን ከድረ-ገጽ በማውረድና የሞባይል ስልካቸው ላይ በመጫን አገልግሎቱን ማግኘት ያስችላልም ነው የተባለው።

    በስልካቸው ላይ የጉዞጎ መተግበሪያን ያልጫኑ፣ ለቸኮሉ ወይም በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች መጠቀም ላልቻሉ ተጓዦች ወደ 7473 የጥሪ ማዕከል በመደወል የጉዞ ቦታ ማስያዝና ትኬት መቁረጥ የሚቻልበት አሠራር መዘርጋቱም ነው የሶልጌት ትራቭል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ሽፈራው የገለጹት። ወደ 7473 የስልክ ጥሪ ማእከል በመደወል የሚፈልጉትን በረራ በማስመዝብ ክፍያቸውን በሲቢኢ ብር ወይም በባንኩ ቅርንጫፎች በማከናወን የትኬት ግዥ መፈጸም እንደሚችሉ አቶ ቴዎድሮስ ጠቁመዋል።

    በቀጣይ ደንበኞች አገልግሎቱን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሞባይል እና የኢንተርኔት ባንክ አገልግሎቶች አማካኝነት ማግኘት የሚችሉበት አሠራር በቅርቡ የሚተገበር መሆኑን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን ተጓዥ ደንበኞች ‘የጉዞጎ’ (GuzoGo) መተግበሪያን በመጠቀም የሀገር ውስጥ የሆቴል ክፍል ማስያዝ (reservation) የሚችሉበት አገልግሎቱን ለመጀመር መዘጋጀታቸውን  ነው የጉዞጎ ሥራ አስኪያጅ አቶ በእርሱፈቃድ ጌታቸው በስምምነት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የገለጹት።

    ሶልጌት ትራቭል የኤሌክትሮኒክ የክፍያ ዘዴን በመተግበር የአየር ትኬት ሽያጭ አገልግሎት ለመስጠት ኢትዮጵያ ውስጥ በረራ ካላቸው 10 አየር መንገዶች የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኤመሬትስ (Emirate)፣ ሉፍታንዛ (Lufthansa)፣ ኳታር ኤርዌይስ (Qatar Airways)፣ ተርኪሽ ኤርላይንስ (Turkish Airlines)፣ ኬንያን ኤርዌይስ (Kenyan Airways)፣ ፍላይ ዱባይ (Fly Dubai)፣ ገልፍ ኤር (Gulf Air)፣ ኢጅፕትኤር (EgyptAir) እና ሳኡዲያ (Saudia) አየር መንገዶች ጋር እየሠራ በመሆኑ አገልግሎቱን የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርገው ኃላፊዎቹ ገልጸዋል።

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሶልጌት ትራቭል ጋር የፈጸመው ስምምነት የባንኩን ደንበኞች የዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት አካል ሲሆን፥ ባንኩ ከውሃና ፍሳሽ አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት፣ ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ ከመልቲቾይስ ኢትዮጵያ፣ ከክፍለ ከተሞች፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከሌሎች የመንግሥትና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በመተባበር በተለያዩ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ዘዴዎች አገልግሎቱን እያቀረበ እንደሚገኝ ይታወቃል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

    GuzoGo

    Semonegna
    Keymaster

    በግማሽ ቢሊዮን ብር የተገነባው ኃይሌ ሪዞርት አዳማ ተመረቀ
    ተቃጥለው የነበሩ የሻሸመኔ እና ዝዋይ የኃይሌ ሪዞርቶችና ሆቴሎች ወደሥራ እንደሚመለሱም ተገለጸ

    አዳማ (አዲስ ዘመን) – በአዳማ ከተማ በ500 ሚሊዮን ብር በሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ “ኃይሌ ሪዞርቶች እና ሆቴሎች” (Haile Resorts & Hotels) ኢንቨስትመንት የተገነባው ዘመናዊው ኃይሌ ሪዞርት አዳማ ተመረቀ።

    ነሐሴ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የሆቴሉ ባለቤት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ እንደገለጸው፥ አዲሱ ኃይሌ ሪዞርት አዳማ በአጠቃላይ 300 ለሚሆኑ ዜጎችና የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባሻገር ከፍተኛ ጥረት ባለው አገልግሎት ሕብረተሰቡን ለማገልገል የቆመ ነው ብሏል።

    ለሀገር ጎብኚዎች በምቹ የቦታ አቀማመጡና ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቱ ሆቴሉን ተመራጭ እንደሚያደርገው የጠቆመው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ፥ ሪዞርቱ 106 የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎች፣ ሁለት ደረጃቸውን የጠበቁ የመመገቢያ አዳራሾች እንዲሁም ባሮችና ሌሎች ደረጃቸውን የጠበቁ የስብሰባ አዳራሾች እንዳሉትም ገልጿል።

    “ኃይሌ ሪዞርቶች እና ሆቴሎች” ድርጅት ፈተናዎች ቢገጥሙትም በምሥራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ ለመሆን ተጨማሪ ሪዞርቶችን ለመክፈት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን የጠቆመው ሻለቃ ኃይሌ፥ በቅርቡም በአዲስ አበባ፣ በወላይታ ሶዶ፣ በኮንሶ፣ በደብረ ብርሃን፣ በጎርጎራ እና በተቀሩት የኢትዮጵያ ክፍሎች እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ሆቴሎችና ሪዞርቶችን ከፍቶ ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሠራ መሆኑንም ተናግሯል።

    በቅርቡ የቃጠሎ ጉዳት የደረሰባቸው የሻሸመኔ እና ዝዋይ የኃይሌ ሪዞርቶችና ሆቴሎች በቅርቡ ወደ ቀደመ ሥራቸው እንደሚመለሱም አትሌት ኃይሌ ተናግሯል። መንግሥት ለሪዞርቶቹ ከለላ ከመስጠት አልፎ ሥራ በማስጀመር ሂደቱ አስፈላጊውን ትብብር እንዲደርግም ጠይቋል።

    ሪዞርቶችና ሆቴሎች ለአንድ ሀገር የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የላቀ ድርሻ እንዳላቸው የጠቀሰው ሻለቃ ኃይሌ፥ በእነዚህ መሠረተ ልማቶች ላይ አሉታዊ ክፍተት ሲያጋጥም መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ ችግሩን ካልፈታው ኢንቨስትመንቱ ሊጎዳ እንደሚችል ጠቁሟል። ውድመት የደረሰባቸው ሁለቱ ሪዞርቶችና ሆቴሎችም የሕዝብ ገንዘብ በመሆናቸው በአስቸኳይ ወደሥራ እንደሚመለሱ አመላክቷል።

    እንደሻለቃ አትሌት ኃይሌ፥ ገለፃ በተለይ ኃይሌ ሪዞርት ዝዋይ በፍጥነት ወደሥራ እንዲመለስ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፤ በእነዚህ ሪዞርቶች እና ሆቴሎች ውስጥ ሲሠሩ የነበሩና በአሁኑ ወቅት ከሥራ ውጪ የሆኑ ሠራተኞችን ወደሥራ ለመመለስ ከመንግሥት እገዛ ይጠበቃልም ብሏል። የሆቴሎቹን መከፈት እውን ለማድረግ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥትና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋርም እየሠራ መሆኑን ተናግሯል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    ኃይሌ ሪዞርት አዳማ

    Anonymous
    Inactive

    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን።
    የሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ እና ግድያውን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ ዞኖች
    ተቀነባብረው በተፈጸሙ ጥቃቶች የተጎዱ ኦርቶዶክሳውያንን መርዳትንና መልሶ ማቋቋምን አስመልክቶ
    ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ

    አማን አማን እብለክሙ ከመ ትበክዩ ወትላህዉ አንትሙ፤ ወዓለምሰ ይትፌሣሕ፤ ወአንትሙሰ ተኃዝኑ፤ ወኃዘንክሙ ፍሥሐ ይከውነክሙ = እውነት እውነት እላችኋለኹ፤ እናንተ ታለቅሳላችኹ፤ ሙሾም ታወጣላችኹ፤ ዓለም ግን ደስ ይለዋል፤ እናንተም ታዝናላችኹ፤ ነገር ግን ኃዘናችኹ ወደ ደስታ ይለወጣል።” (ዮሐ.16፥20) ሃጫሉ ሁንዴሳ ስመ ጥምቀቱ ኃይለ ገብርኤል፣ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት በአዲስ አበባ መገደሉ ይታወሳል። ቤተ ክርስቲያን፥ በዚያ ድንገተኛ የልጇ ግድያ ከባድ ኃዘን ተሰምቷታል። ኾኖም፣ በግድያው የተሰማትን ኃዘን ለመወጣት ጊዜ ሳይሰጣት፣ ኃዘንተኛነቷ ተረስቶ እና እንደ ጠላት ተቆጥራ፣ በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች በክርስቲያን ልጆቿ ላይ ዘግናኝ ፍጅት እና መከራ ተፈጸመባቸው።

    በኦርቶዶክሳዊነታቸው ብቻ በአሠቃቂ መልኩ በገጀራ ተቀሉ፤ በቆንጨራ ተቆራረጡ፤ በጦር ተወግተው በጩቤ ተዘከዘኩ፤ በሜንጫ ተተለተሉ፤ በዱላ ተቀጥቅጠው እና በደንጊያ ተወግረው ተገደሉ፤ አስከሬናቸው በጎዳና እየተጎተተ ሲንገላታ ዋለ፤ ለቀናት በየቦታው ወድቆ የቆየው የሰውነት ክፍላቸው ለከርሠ አራዊት ሲሳይ ኾነ፤ ሴቶች፥ በልጆቻቸው፣ በአባቶቻቸው እና በባሎቻቸው ፊት ተደፈሩ፤ ለዘመናት የደከሙበት ቤት ንብረታቸው፣ በጥናት እና በጥቆማ እየተለየ ከተዘረፈ በኋላ ቀሪው ጋዝ እየተርከፈከፈበት በእሳት እየጋየ ወደመ፤ ብዙዎች ከሞቀ ቀዬአቸው ተፈናቅለው የክረምቱን ጨለማ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን በሚገኙ መቃብር ቤቶች እና አዳራሾች፣ በልዩ ልዩ መንግሥታዊ ተቋማት እንዲሁም፣ በግሰለቦች ቤቶች ተጠልለው ለማሳለፍ ተገደዱ፤ ለአስከፊ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቡናዊ ቀውሶች ተዳረጉ።

    ቤተ ክርስቲያናችን፣ ይህንኑ የተቀነባበረ ጥቃት እንደሰማች፣ ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በቋሚ ሲኖዶስ የሐዘን መግለጫ አውጥታለች፤ በአገር ውስጥ እና በውጭ በሐዘንና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ስታመለክት ከርማለች፤ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትም፥ “አጥፊዎችን አንታገሥም፤ ተገቢውን ፍትሕ እንሰጣለን፤ የተጎዱትን እንክሳለን፤” ብለው ቃል የገቡትን ይፈጽሙ እንደ ኾነ በማለት በትዕግሥት ጠብቃ ነበር። ኾኖም፣ ዜጎችን ከጥቃት አስቀድሞ የመከላከል እና የመጠበቅ፣ ፍትሕን የማስፈንና ተጎጂዎችን በአግባቡ የመካስ ሓላፊነታቸውን በወቅቱ እና በብቃት ሲወጡ አላየችም።

    በጉዳዩ ላይ የተወያየው ቋሚ ሲኖዶስም፣ በየሥፍራው በአካል ተገኝቶ የደረሰውን ጉዳት የሚያጠና ዐቢይ ኮሚቴ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እንዲቋቋም መመሪያ ሰጥቷል። በዚኽም መሠረት ዐቢይ ኮሚቴው፣ ተጎጂዎችን፥ በጊዜያዊነት ለመርዳት እና በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ንኡሳን ኮሚቴዎችን አደራጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል።

    ዐቢይ ኮሚቴው ባወጣው መርሐ ግብር፣ የሥራው መጀመሪያ ያደረገው፣ ጥቃቱ የተፈጸመባቸውን አካባቢዎች በዝርዝር በመለየት፣ ተጎጅዎችን የማጽናናት እና መረጃ የማሰባሰብ ጉዞ ማካሔድ ነበር። ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ መንፈሳውያን ማኅበራትንና በርካታ የብዙኃን መገናኛዎችን ጨምሮ 260 ያኽል ልኡካን የተሳተፉበት ይኸው ጉዞ፣ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች ውስጥ በስድስት አህጉረ ስብከት የሚገኙ 25 ወረዳዎችን የሸፈነ ነበር።

    የዐቢይ ኮሚቴው ልኡካን፣ ተጎጂዎችንና በማነጋገር እና ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች በመጎብኘት ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት፣ የልጃችን የኃይለ ገብርኤልን ግድያ ተከትሎ፣ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች፣ የመንግሥትን መዋቅር ተገን ያደረጉ የእምነት እና የብሔር ጽንፈኞች አስቀድመው ከተደራጁ ኀይሎች ጋራ በመቀናጀት የፈጸሙት ስልታዊ እና አረመኔያዊ ጥቃት ዋና ዒላማ፣ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን እንደነበሩ ተረጋግጧል።

    ከሰኔ 22 ቀን ምሽት ጀምሮ እስከ ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ሦስት ተከታታይ ቀናት በተፈጸመው በዚያ ጥቃት፥ ከ67 በላይ ምእመናን በግፍ እና በአሠቃቂ ኹኔታ ተገድለዋል፤ 38 ምእመናን ቋሚ(ከባድ)፣ 29 ምእመናን ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ከሰባት ሺሕ በላይ ምእመናን ከመኖሪያቸው ከመፈናቀላቸው ባሻገር፣ በተለያየ ደረጃ ለሚገለጽ ሥነ ልቡናዊ እና ሥነ አእምሯዊ ቀውስ ተዳርገዋል፤ ከአምስት ቢልዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረታቸውንም በዘረፋ እና በቃጠሎ ማጣታቸውን፣ ከዐቢይ ኮሚቴው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።

    የጥቃቱን አስከፊነት በዚኽ መልኩ የተረዳው ዐቢይ ኮሚቴው፣ ተጎጅዎችን በአፋጣኝ ባሉበት ለመርዳት እና በዘላቂነት ለማቋቋም ይቻል ዘንድ፣ አደረጃጀቱን በዐዲስ መልክ በማጠናከር ተልእኮውን በአጭር ጊዜ ለማከናወን የሚያስችለውን ስልት ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የጉዳቱን መጠን በነፍስ ወከፍ ደረጃ የመለየት ሥራ እየሠራ ሲኾን፣ በዚኽም መነሻነት፣ ርዳታው በቀጥታ ለተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው እንዲደርስ ይደረጋል፤ በዘላቂነት ለማቋቋምም ኹኔታዎችን ያመቻቻል።

    ዐቢይ ኮሚቴው፣ በጉዳት ጥናት መረጃው መሠረት፣ ጊዜያዊ ርዳታን ከማድረስ እና ከመልሶ ማቋቋም ባሻገር፣ መንግሥት በአስቸኳይ ሊፈጽማቸው የሚገቡ ተግባራት አሉ ብሎ ያምናል፤ እነዚኽም፤

    1. ተጎጅዎች በሃይማኖታቸው በደረሰባቸው ስልታዊ እና ዘግናኝ ጥቃት የተነሣ፣ በከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ላይ እንደሚገኙ በቀረበው ሪፖርት እና ማስረጃ አረጋግጠናል። በወቅቱ ያሉበት ኹኔታ፣ ለኮሮና ቫይረስ እና ለሌሎችም ተላላፊ በሽታዎች የሚያጋልጣቸው እንደኾነ ለመታዘብ ተችሏል። በመኾኑም፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና የፌዴራል መንግሥት፣ የኦርቶዶክሳውያን ኢትዮጵያውያንን በሕይወት የመኖር እና ሀብት የማፍራት ሰብዓዊ እና ዜግነታዊ መብቶችን በማስከበር፣ የደኅንነት እና የኑሮ ዋስትና በአፋጣኝ እንዲያረጋግጥላቸው ቤተ ክርስቲያናችን አጥብቃ ታሳስባለች።
    2. መንግሥት፥ ጥቃቱን ያቀዱትን፣ የፈጸሙትንና ያስተባበሩትን ኀይሎች እንዲሁም፣ የተጣለባቸውን ሓላፊነት ወደ ጎን በማለት ጥቃቱን በዝምታ የተመለከቱትን በመዋቅሩ ውስጥ ያሉትን ሹማምንት እና የጸጥታ አካላት የኾኑ አጥፊዎችን፣ በቁጥጥር ሥር በማዋል እና በሕግ ተጠያቂ በማድረግ ፍትሕ ርትዕ እስከ መጨረሻው እንዲያሰፍን ታሳስባለች። በዚኽ ረገድ፣ መንግሥት፣ ከጥቃቱም በኋላ ቢኾን፣ ሕግን ለማስከበር እያደረገ ያለውን ጥረት፣ ቤተ ክርስቲያን በቅርበት የምትከታተለውና የምታደንቀውም ነው፤ ለውጤታማነቱም፣ ማናቸውንም የበኩሏን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መኾኗን ትገልጻለች።
    3. በአሳዛኝ ኹኔታ በደል እና ግፍ የተፈጸመባቸው ኾነው እያለ፣ በጥቃቱ ምንም ሱታፌ የሌላቸው ንጹሐን ዜጎች፣ በኦርቶዶክሳዊነታቸው ብቻ ታስረው እየተንገላቱ በመኾኑ፣ ጉዳያቸው በጥንቃቄ ታይቶ ከእስር እንዲፈቱ ታሳስባለች።
    4. አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የፖሊቲካ ፓርቲዎች፥ የግፉዓን ሰማዕታቱን መጠቃት፣ አላግባብ ለቡድናዊ እና ፖሊቲካዊ ትርፍ በመጠቀም በሐዘናችን ከመሣለቅ እንዲቆጠቡ፤ መንግሥትም፣ ተገቢውን ክትትል በማድረግ እንዲያስታግሥ ቤተ ክርስቲያን አበክራ ታሳስባለች።
    5. ከወርኀ ሰኔው ጥቃት በፊትም ኾነ በኋላ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎችም ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች፣ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ በተደጋጋሚ እየደረሱ የሚገኙ ስልታዊ የኾኑ ግልጽ ተጽዕኖዎች እና ጥቃቶች፣ በዐይነት እና በመጠን እየጨመሩ መጥተዋል። አብዛኞቹ የክልል መንግሥታት፣ ለውይይት ባሳዩት በጎ ፈቃድ፣ ጥቃቱንና ተጽዕኖውን በተወሰነ ደረጃ ለመግታት ቢቻልም፣ በተለይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የወቅቱ አስተዳደር ግን፣ የቀረበለትን በጋራ ችግሮችን የመፍታት ጥያቄ ችላ በማለት እና ባለመቀበል ቤተ ክርስቲያናችንን በተደጋጋሚ አሳዝኗታል። በክልሉ የተወሰኑ አህጉረ ስብከት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ያገደው ሕገ ወጥ ቡድን፣ ለቤተ ክርስቲያን በሕግ የተሰጧትን መብቶች ከመጋፋት ጀምሮ የአስተዳደር መዋቅሯን እስከ ማፍረስ የተዳፈረው፣ ክልላዊ መንግሥቱ ለቤተ ክርስቲያን ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ባለመስጠት በሚያሳየው ቸልተኝነት እንደ ኾነ ለመረዳት አያዳግትም። በመኾኑም፣ የትላንቱን ችግር ለማከም፣ ይልቁንም ነገ በከፋ መልኩ ሊመጣ ያለውን ለማስቀረት እንዲቻል፣ በጋራ ከመሥራት ውጪ መፍትሔ የለም፤ ብለን እናምናለን። ስለዚህ ክልላዊ መንግሥቱ፣ ጥያቄያችንን ተቀብሎ በጋራ ለመሥራት ዝግጁ እንዲኾን ቤተ ክርስቲያናችን አጥብቃ ታሳስባለች።
    6. በ2012 ዓ.ም. መባቻ፣ በአንድ ቀን 97 ዜጎች እና ምእመናን ካለቁበት የወርኀ ጥቅምቱ ጥቃት እንዲሁም የወርኀ ጥር የበዓለ ጥምቀት አከባበር ወቅት ከተፈጸሙ ግድያዎች እና ዘረፋዎች ጀምሮ፣ በልዩ ልዩ የአገራችን አካባቢዎች፣ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ እየደረሱ ያሉ ግፎችንና በደሎችን መንግሥት አጣርቶ ለፍርድ እንዲያቀርብ፣ ውጤቱንም በይፋ ለሕዝብ እንዲገልጽ ቤተ ክርስቲያናችን አጥብቃ ትጠይቃለች።
    7. ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን፣ ለአገር ሰላም እና ለሕዝብ አንድነት ባበረከተችው አስተዋፅኦ፣ በገነባችው የተቀደሰ ባህል እና ባወረሰችው ዘርፈ ብዙ እሴት፣ በኢትዮጵያውያን ኹሉ ልትከበር እና ልትወደድ የሚገባት ናት። ከሞላው ጸጋዋ እና በረከቷ ያልተቋደሰ ኢትዮጵያዊ ይኖራል ተብሎ የማይገመት በመኾኑ፣ የኹሉ እናት እና ባለውለታ ናት ብለን እናምናለን።

    ኾኖም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየደረሱ ያሉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች፣ አብዝቶ እንደሚነገረው፣ “በሽግግር ወቅት የሚያጋጥሙ” ተብለው ብቻ የሚታለፉ ሳይኾኑ፣ የተሳሳቱ ርእዮተ ዓለማዊ ትርክቶችንና ጂኦ-ፖለቲካዊ ዳራዎችን መነሻ በማድረግ በተቀነባበረ እና በተደራጀ ስልት የሚፈጸሙ ኦርቶዶክሳውያንን የ‘ማጽዳት’ እንቅስቃሴዎች እንደኾኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየኾነ መምጣቱን ቤተ ክርስቲያናችን ትገነዘባለች፤ በአጭር ጊዜ ሳይታረም በዚኹ ከቀጠለም፣ የከፋ ፍጻሜ ሊያስከትል እንደሚችል ከወዲሁ ታስገነዝባለች።

    ስለዚህም፣ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት፥ በእኒህ ስሑት አስተሳሰቦች እና ሐሳዊ ትርክቶች ማሕቀፍ፣ ኾነ ተብሎ የሚፈጸም ኦርቶዶክሳውያንን የማሣቀቅ እና የማዳከም ሃይማኖት ተኮር ጥቃትን አስቀድሞ በመከላከል፣ ፍትሕን በማስፈን፣ ተጎጂዎችን በአግባቡ በመካስ እና በማቋቋም፣ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ በአጽንዖት ታሳስባለች።

    የተወደዳችኹ ተጎጂ ምእመናንና ምእመናት የመንፈስ ልጆቻችን፤

    የግፍ ጥቃቱ የደረሰባችኹና በአሁኑ ወቅት በዐጸደ ቤተ ክርስቲያን አዳራሾች እና በግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች ተጠልላችኹ እንደምትገኙ ይታወቃል። ይህ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችኹ የተቀበላችኹት መከራ፣ በቤተ ክርስቲያናችን የሰማዕታት መዝገብ በወርቅ ቀለም ተጽፎ የሚኖር ነው። በግፈኞች ፊት ለማዕተበ ክርስትናችኹ ታምናችኹ ባሳያችኹት ጽናት እና በከፈላችኹት መሥዋዕት፣ የአገራችኹን ህልውና እና አንድነት ታድጋችኋል፤ የቤተ ክርስቲያናችኹን ልዕልና አስመሰክራችኋል። ይኸውም፣ ለትውልድ አብነት ኾኖ በምሳሌነት ሲነገር የሚኖር በመኾኑ፣ እናት ቤተ ክርስቲያናችኹ ኮርታባችኋለች። ለወደፊትም፣ መላው ኢትዮጵያውያንና ኦርቶዶክሳውያን፣ በሚያስፈልጋችኹ ኹሉ ከጎናችኹ ይቆማሉ፤ ብቻችኹን እንዳልኾናችኹም ቤተ ክርስቲያን ታረጋግጥላችኋለች። ዛሬ ባገኛችኹ መከራ ግፍ አድራሾች ቢደሰቱም፣ በጊዜው ጊዜ ፍትሕን በሕግ ተጎናጽፋችኹ እንባችኹ እንደሚታበስ እና ኃዘናችኹ ወደ ደስታ እንደሚለወጥ ቤተ ክርስቲያናችን ታምናለች።

    በአገር ውስጥ እና በውጭ የምትገኙ የተወደዳችኹ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

    አሠቃቂው ጥቃት ከደረሰበት ሰዓት ጀምሮ፣ በኢትዮጵያዊ ነባር አስተምህሮ እና የአብሮነት ባህል እርስ በርስ በመረዳዳት፣ ዓለም አቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ያሳደረው ከባድ የኑሮ ጫና ሳይበግራችኹ እና ርቀት ሳይገድባችኹ የጥቃቱን ሰለባዎች ለመታደግ እና መልሶ ለማቋቋም ያደረጋችኹትንና በማድረግ ላይ ያላችኹትን ልዩ ልዩ አስተዋፅኦ፣ ቤተ ክርስቲያናችን በከፍተኛ አንክሮ ትመለከታዋለች፤ የጎሣ እና የእምነት ልዩነት ሳይገድባችኹ እስከ ሞት ደርሳችኹ ላደረጋችኹት ሰብዓዊ እና ኢትዮጵያዊ ርዳታ እና ድጋፍ፣ ልዑል እግዚአብሔር ዋጋችኹን ይከፍላችኹ ዘንድ ዘወትር ትጸልያለች።

    በሌላ በኩል፣ በክርስቲያናዊ የትብብር መንፈስ፣ በኦርቶዶክሳውያን ላይ የደረሰው ጉዳት ተሰምቷችኹ፣ ጥቃቱን በማውገዝ አጋርነታችኹን በመግለጫ እና በልዩ ልዩ ድጋፎች ላሳያችኹ የዓለም ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የከበረ ምስጋናዋን ታቀርብላችኋለች።

    አሁንም፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተጠናክሮ የተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት፣ ተጎጅዎችን ለመርዳት እና በዘላቂነት ለማቋቋም እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ፥ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ እና በሞያ እንድትድገፉ፤ እንዳስፈላጊነቱም በቀጣይነት ለሚያስተላልፈው ጥሪ ንቁ ምላሽ ለመስጠት እንድትዘጋጁ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን። በዚኹ አጋጣሚ፣ በአገር ውስጥ እና በውጭ የምትኖሩ ምእመናን፥ ድጋፍ እና አስተዋፅኦ ማድረግ ያለባችኹ፣ በቋሚ ሲኖዶስ የተቋቋመው የርዳታ አሰባሳቢ አካል በከፈታቸው የባንክ ሒሳብ ቁጥሮች ብቻ መኾኑን እናስታውቃለን።

    ቸሩ እግዚአብሔር፥ ለአገራችንና ለዓለም ሰላምን፣ ለሕዝባችን አንድነትን፣ በግፍ ለተገደሉት ልጆቻችን ዕረፍተ ነፍስንና ለቤተ ክርስቲያናችን መጽናናትን እንዲሰጥልን እንለምናለን።

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር
    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት

    ~~~

    ዐቢይ ኮሚቴው የከፈታቸው የባንክ ሒሳብ ቁጥሮች፡–

    በኦርቶዶክሳዊነታቸው ምክንያት በግፍ ለተፈናቀሉ ክርስቲያኖች መርጃ እና ማቋቋሚያ
    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጭር ቁጥር፦ 8080
    ሕብረት ባንክ የሒሳብ ቁጥር፦ 1601811299653018
    ወጋገን ባንክ የሒሳብ ቁጥር፦ 0837771210101
    ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የሒሳብ ቁጥር፦ 3359601000003
    ዓባይ ባንክ የሒሳብ ቁጥር፦ 146211349291701

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት

    ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ

    Semonegna
    Keymaster

    ኢትዮ ሊዝ ከሰባት ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው የእርሻ ሜካናይዜሽን መሣሪያዎች ለገበሬዎች አስረከበ

    አዲስ አበባ – በኢትዮጵያ በሊዝ ፋይናንስ ዘርፍ በመሰማራት የመጀመርያው የውጭ ኩባንያ የሆነው ኢትዮ ሊዝ የተሰኘው የአሜሪካ ኩባንያ 16 ኮምባይነሮችን ለአርሶ አደሮች እና ለማኅበራት አስረከበ። የግብርና ሜካናይዜሽን መሣሪያዎቹን ወደ አገር ውስጥ ያስገባው የኢትዮጵያ መንግሥት በግብረናው ዘርፍ ለማዘመን የያዘውን ስትራቴጂ ለመደገፍ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ ጋር ያደረውን ሰምምንት ተከትሎ ሲሆን፥ ስምምነቱም እነዚህን ውድ የሆኑ የግብርና ማቀነባበሪያ መሣሪያዎችን መግዛት የማይችሉትን አርሶ አደር ገበሬዎችን በአጭር ጊዜ ባለቤት የሚያደርግ ይሆናል።

    በዚህኛው ዙር የተካሄደው ርክክብ እስካሁን ድረስ ያስረከባችውን የግብርና መሣሪያዎች ቁጥር ወደ አንድ መቶ ያደረሰ ሲሆን፥ አጠቃላይ ወጪያቸው ከ7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው። ከእነዚህም በተጨማሪ ኩባንያው በመጪው መስከረም እና በጥቅምት ወራት (2013 ዓ.ም.) ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ተጨማሪ መሣሪያዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚያስፈልጉትን ሥራዎች እያከናወነ ይገኛል።

    የኢትዮ ሊዝ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ግሩም ፀጋዬ በርክክቡ ውቅት እንደተናግሩት፥ “በተከታታይ ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባናቸው ያሉት የግብርና መሣሪያዎች ኩባንያችን የሀገሪቱን የግብርና ዘርፍ የማዘመን ዕቅድ ለማሳካት የበኩሉን እየሠራ እንደሆነ የሚያሳይ ሲሆን፥ በዚህም እንቅፋት የሆነውን የውጭ ምንዛሪ እጦት መፍታት ችለናል” በማለት አስረድተዋል።

    አቶ ግሩም አክለውም፥ “ዘላቂነት ያለው ግብርናን ማዘመን ሥራ  የአርሶ አደሩን አቅም በመገንባት ረገድ ቁልፍ ሚና ሊጫወትና ምርታማነትን እና ገቢን ሊያሻሽል እንዲሁም የምግብ ዋስትናን እና አኗኗር ለማሻሻል ይረዳል” ብለዋል። የኢትዮ ሊዝ አርሶ አደሮች ከመደገፍ በተጨማሪ ለኦፕሬተሮች፣ ለረዳቶች ኦፕሬተሮች እና ለተለያዩ ባለሙያዎች፣ የሥራ ዕድልን የሚፈጥር እንደሆነ በሻሽመኔ ከተማ በተደረገው ርክክብ ላይ ተነግሯል።

    አትዮ ሊዝ አፍሪካን አሴት ፋይናንስ ካምፓኒ (African Asset Finance Company/AAFC) በተሰኘ የአሜሪካ ኩባንያ በ400 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተመሠረተ ኩባንያ ነው። ኩባንያው ለእርሻ፣ ለሕክምናና አምራች ኢንዱስትሪ የሚውሉ ዘመናዊ መሣሪያዎች በኪራይ ለማቅረብ የሚያስችለውን የሥራ ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም. አግኝቷል።

    ኢትዮ ሊዝ የካፒታል እቃዎችን እንደአስፈላጊነቱ በመለየት እና በመግዛት፣ አስፈላጊ ጥገናዎችን እና አግባብነት ባለው ሁኔታ አገልግሎት ላይ መዋላቸውን የመቆጣጠር ኃላፊነት ይኖረዋል። በተጨማሪም ተከራዩ ወይንም አገልግሎቱን ያገኘው አካል መሣሪያዎችን መግዛት የሚችልበትን መንገድ ያመቻቻል። ኢትዮ ሊዝ ወደሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ፥ ለግብርና፣ ለጤና፣ ለኃይል አቅርቦት (energy)፣ ለምግብ ማቀነባበር (food processing) አገልግሎት ሰጪዎች የካፒታል እቃዎችን አቅርቧል። ድርጅቱ እስካሁን ከ60 በላይ ከሚሆኑ ደንበኞች ጋር የካፒታል እቃዎች አቅርቦት ስምምነት አድርጓል።

    ስለ ኢትዮ ሊዝ
    ኢትዮ ሊዝ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል የሊዝ ፋይናንስ አቅራቢ ኩባንያ ሲሆን፥ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቶ እ.አ.አ በ2017 የአፍሪካ አሴት ፋይናንስ ኩባንያ አካል በመሆን ሥራው ጀምሯል። ኩባንያው በአፍሪካ የሊዝ አገልግሎት ያልተዳረሰባቸውን ገበያዎች ለማገልገልና አቅምን ያገናዘበ ብድር ለማቅረብ የሚሠራ ኩባንያ ነው። ለበለጠ መረጃ http://www.ethiolease.com ይጎብኙ።

    ስለ አፍሪካን አሴት ፋይናንስ ካምፓኒ (AAFC)
    የአፍሪካ አሴት ፋይናንስ ኩባንያ (AAFC) ዋና መቀመጫውን በአሜሪካ ኒው ዮርክ በማድረግ በተለያዩ ሀገራት ያሉ ኩባንያዎች የፋይናንስ አቅርቦት አገልግሎት ይሰጣል። በመላው አፍሪካም የደንበኞችን ፍላጎትና አቅምን መሰረት ያደረገ የቁስ ውሰት አገልግሎቶችን ይሰጣል። ለበለጠ መረጃ http://www.aafc.com ይጎብኙ።

    ኢትዮ ሊዝ

    Anonymous
    Inactive

    በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለቱሪስት ብቻ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች ሄሎ ታክሲ በተባለ ድርጅት አማካኝነት በይፋ ተመርቀው ሥራ ጀመሩ

    አዲስ አበባ (ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር) – ኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ የሚገጣጥማቸውና በሄሎ ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ታክሲዎች በሸራተን አዲስ ሆቴል በኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ሒሩት ካሳው በይፋ ተመርቀዋል።

    የኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሶሎሞን ሙሉጌታ፥ “ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ የቱሪዝም ሀብት ያላትና የተስፋ ምድር በመሆኗ ለቱሪስት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎችን ቀድመን ለማዘጋጀት ችለናል” ብለዋል።

    የሄሎ ታክሲ መሥራችና ባለቤት አቶ ዳንኤል ዮሐንስ በበኩላቸው፥ “ሄሎ ታክሲ በቀጣይም ቱሪስቱን በአውሮፕላን ወደ ቱሪስት መዳረሻዎች ለማድረስና አመርቂ አገልግሎት ለመስጠት 50% ዝግጅቱን አጠናቋል” ብለዋል።

    ሄሎ ታክሲ ከዚህ ቀደም 40 ታክሲዎችን አስመርቆ በይፋ ሥራ ያስጀመረ ሲሆን፥ አሁን ደግሞ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የቱሪስት ታክሲ ወደ አገልግሎት በማስገባት ሥራውን ጀምሯል። ሄሎ ታክሲ ከዚህ ቀደም በታክሲ አገልግሎት ተሰማርተው መኪኖቻቸው አሮጌ በመሆናቸው ከአገልግሎት ውጭ ለሆኑባቸው አሮጌውን መኪና በመቀበልና በአዲስ በመተካት የታክሲ ባለቤቶችን እየታደገ ያለ ድርጅት መሆኑም ተገልጿል። የተሰበሰቡ አሮጌ ታክሲዎችም ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመንጃ ፍቃድና ተግባራዊ የመኪና ጥገና መማሪያ እንዲሆኑ፤ ከዚያም ሲያልፍ የዋጋ ተመን ወጥቶላቸው ወደ ማቅለጫ ገብተውና ለውጭ ገበያ ተሽጠው ገቢ እንዲያስገኙ ሥራ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል።

    የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስተር ክብርት ዶ/ር ሒሩት ካሳው፥ “መንግሥት የታክሲ ሞተሮች ከቀረጥ ነጻ ሆነው ወደ ሀገራችን እንዲገቡ የወሰነው ግብር መሰብሰብ አቅቶት ሳይሆን፥ አሮጌ መኪኖችን በአዲስ ተተክተው የአየር ብክለት እንዲቀንስ፣ ሀገር ውስጥ ሲገጣጠሙም ተጨማሪ የሥራ ዕድል ስለሚፈጥሩ፣ ዜጎቻችንም በሀገራቸው ሠርተው እንዲከብሩ፣ ስርቆት የሚፀየፍ ጥሩ አገልጋይ እንድትሆኑ ነው” ብለዋል።

    ሚኒስትሯ አክለውም፥ ታክሲዎችን በአዲስ እንደቀየራችሁ ሁሉ አስተሳሰባችሁንና ሕይወታችሁን በመቀየር ለቱሪስቶቻችንም ቀድሞ መረጃ በመስጠት ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ የሀገራችንን ገፅታ እንድትገነቡ አሳስባለሁ ብለዋል።

    የክህሎትና የአገልግሎት አሰጣጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ለታክሲ ሹፌሮች ይሰጣል ያሉት ሚኒስትሯ፥ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሕጋዊ አሠራርን መከተል እና ለረዥም ዓመታት በአሮጌ መኪና ጭስ የተበከለችውን ሀገራችንን በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብራችን ችግኝ በመትከልና በማልማት ማኅበራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አደራ እላለሁ ብለዋል።

    በመጨረሻም ክብርት ወ/ሮ ቡዜና አልኸድር የኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ፥ ለታክሲ አገልግሎት ማኅበራቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንዲሳተፉ የችግኝ ስጦታ ያበረከቱ ሲሆን፥ ከሄሎ ታክሲ ድርጅት ጋርም በቱሪስት የታክሲ አገልግሎት ዙሪያ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

    የኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ ተወካይ አቶ ሸምሰዲን አብዱራህማን በኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል ተደራሽ የሚሆኑ ለ110 ሥራ አጥ ወጣቶች በ100% ብድር የሚሰጡ ሄሎ ታክሲዎችን፣ አስር የቱሪስት አምቡላንሶችን፣ በ59 ቋንቋዎች የማስተርጎም ሥራ የሚሠሩ ሃምሳ ማሽኖችን ለክብርት ዶ/ር ሒሩት ካሳው አስረክበዋል።

    የሄሎ ታክሲ ባለቤት አቶ ዳንኤል ዮሐንስ በኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል ተደራሽ የሚሆኑ ለ250 ሰዎች አሮጌ ታክሲያቸውን ብቻ ሰጥተው አዲስ ታክሲ እንዲረከቡ የሚያስችል ስጦታ ያቀረቡ ሲሆን፥ የታክሲ ማኅበራትም ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የምስጋና ስጦታ ለክብርት ዶ/ር ሒሩት ካሳው አበርክተዋል።

    ምንጭ፦ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሄሎ ታክሲ ኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ

    Anonymous
    Inactive

    የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባባር ኢትዮጵያን ማስቻል (Enabling Ethiopia) የተባለ የ5 ዓመት ፕሮጀክት ጀመረ

    አዲስ አበባ – የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኢትዮጵያን ማስቻል (Enabling Ethiopia) የተባለ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባባር ጀመረ። የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽንና ማስተርካርድ ፋውንዴሽን በጋራ የጀመሩት የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ፈጠራን በማበረታታት፣ አካታችና አነቃቂነትን መሠረት በማድረግ ፖሊሲዎችን በማሻሻል በኢትዮጵያ የተጀመረውን የሥራ ፈጠራ እንቅስቃሴ የሚደግፍ ነው። ለዚህ ፕሮጀክት ማስተርካርድ ፋውንዴሽን የ11.8 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

    “ኢትዮጵያን ማስቻል” (Enabling Ethiopia) ፕሮጀክት ሲቀረጽ የሀገሪቱን የ5 ዓመት የሥራ ፈጠራ መሪ ዕቅድ ለማሳካት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ታምኖበት ነው። ፕሮጀክቱ ሀገሪቱን የሥራ ፈጠራ አጀንዳ እና የኮሚሽኑን አምስት ዓመት ስትራቴጂ ለመተግበር እንዲያግዝ ሆኖ የተቀረጸ ነው። እ.ኤ.አ በኦክቶበር 2019 የተጀመረው የኮሚሽኑ የአምስት ዓመት የሥራ ዕድል ፈጠራ መሪ ዕቅድ በግል ዘርፉና በፌደራል እንዲሁም በክልሎች ደረጃ ያሉ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በተናበበ መልኩ አስፈላጊውን ግብዓት በማቅረብ፣ ኢንቨስትመንትን በማመቻቸት በ 2015 (እ.ኤ.አ) 14 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ያለመ ነው።

    በዚህ ፕሮጀክት የረጅም ጊዜ ዕቅድ ለሥራ ፈጠራ ምቹ ምህዳር መፍጠር፣ አስፈላጊ የሰው ኃይል ካፒታልን ማዳበር እና ማክሮ ፖሊሲዎች ሥራ ፈጠራን እንዲያበረታቱ ማስቻል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራባቸዋል።

    ኢትዮጵያን ማስቻል ለ50 ሺህ ሴቶችና ወጣቶች በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የሥራ ዕድል በማመቻቸት የመሪ ዕቅዱን አፈጻጸም ያግዛል። በተጨማሪም ለሥራ ዕድል ፈጠራ ተገቢውን ትኩረት የሚሰጡ ማክሮ ፖሊሲዎች እንዲቀረጹና አፈጻጸማቸውም ቀልጣፋ እንዲሆን የአቅም ግንባታ እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ፣ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ግንባታውን በማገዝ እንዲሁም ሃብት በማሰባሰብ ሥራዎች ላይ የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል።

    ኢትዮጵያን ማስቻል ትኩረት ላልተሰጣቸው የማኅበረሰብ አካላት ማለትም የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ለሚሠሩት ሥራ ክፍያ የማያገኙ በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች፣ ስደተኞችና አካል ጉዳተኞችን ለመርዳት ዓላማ ያደረገ ነው። ፕሮጀክቱ የወጣቶችን ክህሎት ከማዳበር በተጨማሪ 200 ለሚሆኑ እምቅ ኃይል ያላቸው ሥራ ፈጣሪዎች ህልማቸውን እንዲያሳኩ ድጋፍ ያደርጋል።

    “ኢትዮጵያን ማስቻል ስሙም እንደሚያመለክተው ለበርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች መልካም አጋጣሚ ነው። በተለይም ትኩረት ያልተደረገባቸው ነገር ግን ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሥራ እንዲኖራቸውና ገቢ እንዲያገኙም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። በተጨማሪም ፕሮጀክቱ አዳዲስ ዕድሎችን ለማመቻቸት እና ለሥራ ፈጣሪዎች ፣ ለድርጅቶችና ለግሉ ሴክተር እንቅፋቶችን ለማስወገድ ትኩረት ፈጠራ ትብብርና ልህቀትን በመጠቀም ለሴቶችና ለወጣቶች ደህንነቱ የተጠበቀ ፣ የተከበረ እና አስደሳች የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ይተጋል” በማለት ዶ/ር ኤፍሬም ተክሌ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር የፕሮጀክቱን አስፈላጊነት ገልጽዋል።

    ፕሮጀክቱ የሚተገበረው በሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን መሪነት ሲሆን የፌዴራልና የክልል መንግሥታት፣ የኢንተርፕራይዝ ልማት አካላት እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ ተቋማትና የግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር ነው።

    “ይህ ፕሮጀክት በ2030 (እ.ኤ.አ) ለ10 ሚሊዮን ወጣቶች የተከበሩና አስደሳች የሥራ ዕድሎችን ለማመቻቸት ከተቀረጸው የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ወጣት አፍሪካ በሥራ ላይ ፕሮጀክት ጋር አብሮ የሚሄድ ሲሆን፥ ከኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ጋር ባለን ትብብር የኢትዮጵያ ወጣቶች እድገት እንዲያስመዘግቡና የሚያደርጉት አስተዋጽኦ በጉልህ እንዲታይላቸው የሚያደርግ ነው” በማለት አቶ አለማየሁ ኮንዴ ኮይራ፣ የማስተርካርድ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ገልጸዋል።

    • ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን
      የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን እ.ኤ.አ በ2018 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በጸደቀው ደንብ ቁጥር 435/2011 መሠረት ተጠሪነቱ ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆኖ የተቋቋመ መንግሥታዊ ተቋም ነው። ኮሚሽኑ በሁሉም የሥራ ዘርፎች የሥራ ዕድል ፈጠራ አጀንዳን የማስተዳደር ፣ የማቀናጀት እና የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን በዚህም በመላ ሀገሪቱ የሚፈጠሩ ሥራዎች ዘለቄታ ያላቸው እንዲሆኑ እ.ኤ.አ በ2020 ዓ.ም ሦስት ሚሊዮን ፣ በ2025 ዓ.ም 14 ሚሊዮን ፣ በ 2030 ደግሞ 20 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ በማመቻቸትና ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም በፖሊሲና ስትራቴጂ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ክትትል እና አቅም ግንባታ፣ በትብብርና ኢንቨስትመንት፣ በኢኖቬሽንና በመረጃ ትንተና እና ሥርዓት ማበልጸግ ላይ ትኩረት በማድረግ እስከ ሚያዝያ 2012 (እ.ኢ.አ) ድረስ 2.4 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ አድርጓል።

    ስለ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን የበለጠ መረጃ ለማግኘት ድረ-ገጹንና ማኅበራዊ ሚድያዎቹን ይጎብኙ፦
    https://www.jobscommission.gov.et
    https://twitter.com/Jobs_FDRE
    https://www.facebook.com/JobsCommissionFDRE/

    • ማስተርካርድ ፋውንዴሽን
      ማስተርካርድ ፋውንዴሽን (Mastercard Foundation) ሁሉም ሰው የመማር እና የመበልፀግ ዕድል ሊያገኝ የሚችልበት ዓለም እንዲኖር ይመኛል። ለዚህም ፋውንዴሽኑን ዋነኛ ተልዕኮውን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ ሰዎች የትምህርት ልህቀት እና የፋይናንስ አካታችነትን ማሻሻል ነው። በዓለማችን ካሉ ታላላቅ ፋውንዴሽኖች መሐከል አንዱ የሆነው የማስተርካርድ ፋውንዴሽን አፍሪካ ላይ ዋነኛ ትኩረቱን ያደርጋል። እ.ኤ.አ በ2006 በማስተርካርድ ኢንተርናሽናል አማካኝነት ቢመሠረትም በአሁኑ ወቅት ራሱን በቻለ የቦርድ አመራር ስር ይተዳደራል። ማስተርካርድ ፋውንዴሽን በቶሮንቶ፥ ካናዳ እንዲሁም በኪጋሊ፥ ሩዋንዳ  ፅሕፈት ቤቶች አሉት።

    ስለ ማስተርካርድ ፋውንዴሽን የበለጠ መረጃ ለማግኘት ድረገጹንና ማህበራዊ ሚድያዎቹን ይጎብኙ፦
    http://www.mastercardfdn.org
    http://twitter.com/MastercardFdn

    ምንጭ፦ ማስተርካርድ ፋውንዴሽን

    ኢትዮጵያን ማስቻል (Enabling Ethiopia)

    Anonymous
    Inactive

    ኢትዮጵያ ውስጥ በግዙፍነቱ ቀዳሚ የሆነው ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ

    አዲስ አበባ (ፋና) – በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባውና በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ የሚያመርተው ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ። በፋብሪካው ምርቃ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በምረቃው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ፋብሪካው የዳቦ ፋብሪካ ብቻ ሳይሆን በምግብ ራሳችንን የመቻል ፍላጎታችንን፣ ከድህነት የመውጣት ጥማትን እና የብልፅግና ጎዳናን አመላካች ነው ብለዋል።

    በኢትዮጵያ በ10 ወራት ፋብሪካ ገንብቶ ማጠናቀቅ የሚታሰብ አልነበረም፤ በተለይም ለሚድሮክ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ ሚድሮክ ከነበረበት ድክመት ተላቆ ፋብሪካውን በዚህ ፍጥነት ማጠናቀቅ መቻሉ ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ነው ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አክለውም መንግሥት በቀጣይ ሁለት ዓመታት ስንዴን ከውጭ ማስገባት የማቆም ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ፤ ለዚህም የሙከራ ምርቶች መጀመራቸውን አስታውቅዋል። ስንዴ ማምረት ብቻ ሳይሆን ምርቶቹን ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ መቀየር አስፈላጊ መሆኑንም የገለፁ ሲሆን፥ ለዚህም ለግሉ ዘርፍ ጥሪ መቅረቡን አስታውቅዋል።

    መንግሥት ላቀረበው ጥሪ ሼክ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ፈጣን ምላሽ መስጠታቸውን በመግለፅ፥ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ እውን እንዲሆን በማድረጋቸውም ምስጋናቸውን ያቀረቡላቸው ሲሆን፥ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሌም ከጎናቸው እንደሆነ አረጋግጠዋል።

    መሰል የዳቦ ማምረቻዎችን ከአዲስ አበባ ውጪ በክልል ከተሞችም ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑን እና ለዚህም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሌሎች ከተሞች መሰል መለስተኛ የዳቦ ፋብሪካዎችን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሯን አስታውቀዋል። በተጨማሪም የዱባይ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ዛይድ አልናህያንም ከፍ ያለ ፋብሪካ ቃል መግባታቸውን እና ይህም በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

    እነዚህ አሁን የተገነቡ እና ወደ ፊት የሚገነቡ ፋብሪካዎች በቀን ዳቦ ለማግኘት ለሚያዳግታቸው ሕፃናት ዳቦ እንዲያገኙ የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ።

    “አዲስ አበባን፣ ክልሎችን፣ ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን እንለውጣለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ “ኢትዮጵያ የጀመረችውን በሙሉ ታጠናቅቃለች፤ ይህም በየአደባባዩ እየጮኸች ሳይሆን ሪቫን እየቆረጠች ነው” ብለዋል።

    ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማም፥ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተገንብቶ እውን እንዲሆን ለተሳተፉ አካላት መስጋና አቅርበዋል። የሸገር ዳቦ ፋብሪካ መገንባት የከተማውን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና ይቀንሳል ያሉት ኢ/ር ታከለ፥ በቀጣይም የከተማዋ ነዋሪዎችን ጥያቄ የሚመልሱ ሥራዎችን በማቀድ ወደ ሥራ መገባቱብንም አስታውቅዋል።

    የሚድሮክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብነት ገብረ መስቀል በበኩላቸው፥ ሜድሮክ ኢትዮጵያ ለአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ነዋሪ ሕዝብ በከፍተኛ ጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ አምርቶ ማቅረብ እንዲቻል ሸገር ዳቦ ፋብሪካን ገንብቶ ለፍሬ አብቅቷል ብለዋል።

    በ41 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ፋብሪካው፥ የዳቦ እና የዱቄት ፋብሪካ፣ የሻይ ቅጠል ማቀነባበሪያ እና 120 ሺህ ኩንታል ስንዴ ማከማቸት የሚያስችል 4 ጎተራ እንዳለው አስታውቀዋል። በ6 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካው በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ የሚያመርት መሆኑን እና በቀን በሶስት ፈረቃ እስከ 2 ሚሊየን ዳቦ የሚያመርት መሆኑ ገልፀዋል።

    ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ግንባታው በአጠቃላይ በ900 ሚሊዮን ብር ወጪ መከናወኑን ያስታወቁት አቶ አብነት፥ አጠቃላይ ወጪውም በሚድሮክ እህት ኩባንያዎች የተሸፈነ መሆኑንም አስታውቅዋል። ፋብሪካው ከምርት እስከ ማከፋፈል ሂደት ቁጥራቸው 3 ሺህ 400 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል።

    ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት

    ሸገር ዳቦ ፋብሪካ

    Anonymous
    Inactive

    ኢትዮጵያ ውስጥ በግዙፍነቱ ቀዳሚ የሆነው ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ

    አዲስ አበባ (ፋና) – በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባውና በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ የሚያመርተው ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ። በፋብሪካው ምርቃ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በምረቃው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ፋብሪካው የዳቦ ፋብሪካ ብቻ ሳይሆን በምግብ ራሳችንን የመቻል ፍላጎታችንን፣ ከድህነት የመውጣት ጥማትን እና የብልፅግና ጎዳናን አመላካች ነው ብለዋል።

    በኢትዮጵያ በ10 ወራት ፋብሪካ ገንብቶ ማጠናቀቅ የሚታሰብ አልነበረም፤ በተለይም ለሚድሮክ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ ሚድሮክ ከነበረበት ድክመት ተላቆ ፋብሪካውን በዚህ ፍጥነት ማጠናቀቅ መቻሉ ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ነው ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አክለውም መንግሥት በቀጣይ ሁለት ዓመታት ስንዴን ከውጭ ማስገባት የማቆም ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ፤ ለዚህም የሙከራ ምርቶች መጀመራቸውን አስታውቅዋል። ስንዴ ማምረት ብቻ ሳይሆን ምርቶቹን ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ መቀየር አስፈላጊ መሆኑንም የገለፁ ሲሆን፥ ለዚህም ለግሉ ዘርፍ ጥሪ መቅረቡን አስታውቅዋል።

    መንግሥት ላቀረበው ጥሪ ሼክ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ፈጣን ምላሽ መስጠታቸውን በመግለፅ፥ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ እውን እንዲሆን በማድረጋቸውም ምስጋናቸውን ያቀረቡላቸው ሲሆን፥ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሌም ከጎናቸው እንደሆነ አረጋግጠዋል።

    መሰል የዳቦ ማምረቻዎችን ከአዲስ አበባ ውጪ በክልል ከተሞችም ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑን እና ለዚህም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሌሎች ከተሞች መሰል መለስተኛ የዳቦ ፋብሪካዎችን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሯን አስታውቀዋል። በተጨማሪም የዱባይ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ዛይድ አልናህያንም ከፍ ያለ ፋብሪካ ቃል መግባታቸውን እና ይህም በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

    እነዚህ አሁን የተገነቡ እና ወደ ፊት የሚገነቡ ፋብሪካዎች በቀን ዳቦ ለማግኘት ለሚያዳግታቸው ሕፃናት ዳቦ እንዲያገኙ የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ።

    “አዲስ አበባን፣ ክልሎችን፣ ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን እንለውጣለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ “ኢትዮጵያ የጀመረችውን በሙሉ ታጠናቅቃለች፤ ይህም በየአደባባዩ እየጮኸች ሳይሆን ሪቫን እየቆረጠች ነው” ብለዋል።

    ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማም፥ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተገንብቶ እውን እንዲሆን ለተሳተፉ አካላት መስጋና አቅርበዋል። የሸገር ዳቦ ፋብሪካ መገንባት የከተማውን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና ይቀንሳል ያሉት ኢ/ር ታከለ፥ በቀጣይም የከተማዋ ነዋሪዎችን ጥያቄ የሚመልሱ ሥራዎችን በማቀድ ወደ ሥራ መገባቱብንም አስታውቅዋል።

    የሚድሮክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብነት ገብረ መስቀል በበኩላቸው፥ ሜድሮክ ኢትዮጵያ ለአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ነዋሪ ሕዝብ በከፍተኛ ጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ አምርቶ ማቅረብ እንዲቻል ሸገር ዳቦ ፋብሪካን ገንብቶ ለፍሬ አብቅቷል ብለዋል።

    በ41 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ፋብሪካው፥ የዳቦ እና የዱቄት ፋብሪካ፣ የሻይ ቅጠል ማቀነባበሪያ እና 120 ሺህ ኩንታል ስንዴ ማከማቸት የሚያስችል 4 ጎተራ እንዳለው አስታውቀዋል። በ6 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካው በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ የሚያመርት መሆኑን እና በቀን በሶስት ፈረቃ እስከ 2 ሚሊየን ዳቦ የሚያመርት መሆኑ ገልፀዋል።

    ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ግንባታው በአጠቃላይ በ900 ሚሊዮን ብር ወጪ መከናወኑን ያስታወቁት አቶ አብነት፥ አጠቃላይ ወጪውም በሚድሮክ እህት ኩባንያዎች የተሸፈነ መሆኑንም አስታውቅዋል። ፋብሪካው ከምርት እስከ ማከፋፈል ሂደት ቁጥራቸው 3 ሺህ 400 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል።

    ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት

    ሸገር ዳቦ ፋብሪካ

    Anonymous
    Inactive

    ሲቢኢ ኑር (CBE Noor) ― የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሚሰጠው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ራሱን የቻለ ስያሜና አርማ ሥራ ላይ አዋለ

    አዲስ አበባ (CBE) – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሚሰጠው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ‘ሲቢኢ ኑር’ (CBE Noor) የተሠኘ ስያሜና አርማ ሥራ ላይ ማዋሉን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ግንቦት 28 ቀን 2012 ዓ.ም በተዘጋጀ የማስተዋወቂያ መርሀ-ግብር ላይ ይፋ አድርገዋል።

    ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን በተጠናከረ መልኩ ለሕብረተሰቡ ለማዳረስ እየተገበረ ካለው መጠነ ሰፊ የማሻሻያ ተግባራት ጋር ተያይዞ አዲሱ ስያሜና አርማ ሥራ ላይ መዋሉን አቶ አቤ ሳኖ በመርሀ ግብሩ ላይ ተናግረዋል።

    አዲሱን ስያሜ እና አርማ በማዘጋጀት ሂደት በርካታ አማራጮች የቀረቡ መሆኑን አቶ አቤ አስታውሰው፥ ‘ኑር’ የሚለው አረብኛ ቃል ‘የብርሀን ፍንጣቂ’ የሚለውን ትርጓሜ የያዘ ሲሆን በአማርኛ መኖር የሚለውን መልካም ተስፋን የሚያመለክት በመሆኑ ለአገልግሎቱ ፈላጊዎች ተስፋን የሚሰጥ እንዲሁም ባንኩ ያለውን ራዕይ አመላካች ቃል ስለሆነ የባንኩ የሸሪዓ አማካሪዎችና የባንኩ ከፍተኛ የሥራ አመራር አስተያየት ሰጥተውበት ስያሜው መመረጡን ገልፀዋል።

    ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱን ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን የተናገሩት አቶ አቤ፥ በእምነታቸው ምክንያት ወለድ ለማይፈልጉ ደንበኞች አገልግሎቱን እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ባንኩ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን አክለው ገልፀዋል።

    የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እ.ኤ.አ. በ2011 ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መመሪያ ማውጣቱን ተከትሎ እ.ኤ.አ. ከህዳር 2013 ጀምሮ በተመረጡ 23 ቅርንጫፎች በተለየ መስኮት አገልግሎቱ መሰጠት መጀመሩን በንግግራቸው ያስታወሱት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት፥ በአሁኑ ጊዜ በ1574 በላይ ቅርንጫፎች በመስኮት ደረጃ እንዲሁም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ ለመስጠት በተከፈቱ ከ53 በላይ ቅርንጫፎች አማካኝነት አገልግሎቱ በመሰጠት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

    ባንኩ የሸሪዓ መርህን የሚከተሉ የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን ለሕብረተሰቡ በማድረስ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ አቤ እ.ኤ.አ. ግንቦት 2020 መጨረሻ ድረስ በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ 30.3 ቢሊዮን ብር መድረስ መቻሉን አመላክተዋል።

    አቶ አቤ በገለፃቸው፥ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን የሚጠቀሙ ደንበኞች ብዛትን 2.7 ሚሊዮን መድረሱንና ባንኩ በተለያዩ የሥራ መስኮች ለተሰማሩ ደንበኞች 3 ቢሊዮን ብር የፋይናንስ አገልግሎት ማቅረቡን አስረድተዋል።

    አቶ አቤ ባንኩ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት፣ ዕውቅናና አመኔታን ያተረፉ፣ በዘርፉ በቂ የትምህርት ዝግጅት፣ ጥልቅ ዕውቀትና የካበተ ልምድ ያላቸው አምስት አባላት ያሉት የሸሪዓ መማክርት ኮሚቴ እ.ኤ.አ. ከ2019 ጀምሮ ሰይሟልም ነው ያሉት።

    የሸሪዓ አማካሪዎችን መሰየሙ ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱን የሸሪዓ እሴትን በጠበቀ መልኩ ለመስጠት እንዳስቻለው የገለፁት አቶ አቤ የሸሪዓ መርህ መከበሩን የሚያረጋግጡ የውስጥ ቁጥጥር አሠራሮችን የመተግበር፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሂሳብ መዝገብ የመለየት እና መመሪያዎችን የማርቀቅ ተግባርም ማከናወኑን አክለው ገልፀዋል።

    አቶ አቤ በንግግራቸው መጨረሻ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለደንበኞቹ የተሻለ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የማቅረብ ትልቅ አላማ እንዳለው እና በቀጣይ የቁጠባ እና የፋይናንስ አማራጮቹን በማስፋት፣ አዳዲስ አሠራሮችን በመተግበር እና ይበልጥ ዘመናዊ በማድረግ የባንክ አገልግሎቱን ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል አመቺና ተስማሚ በሆነ መልኩ ለማቅረብን ያለውን ቁርጠኝነት ገልፀው፥ ደንበኞችና መላው ሕብረተሰብ የወቅቱ የጤና ስጋት ከሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እራስንና ቤተሰብን በመጠበቅ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በሆነዉ ሲቢኢ ኑር (CBE Noor) ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሸሪዓ መርህን በመከተል በሚሰጠው ‘ሲቢኢ ኑር’ (CBE Noor) በተሰኘው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት፦

      • ከወለድ ነፃ የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎት
      • ለበይክ የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎት (ለሀጅ እና ኡምራ ተጓዦች)
      • ዘካ የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎት (ዘካ ለሚያወጡ)
      • የፋይናንስ አገልግሎት
      • የዓለም አቀፍ ንግድ ድጋፍ
      • የዳያስፖራ የቤት መግዣ/መሥሪያ ብድር እና
      • ሌሎችንም አገልግሎቶች

    ከ50 በላይ በሆኑ አገልግሎቱን ብቻ ለመሥጠት በተከፈቱ ቅርንጫፎች እና ከ1574 በላይ በሆኑ ቅርንጫፎች በተለየ መስኮት ይሰጣል፡፡

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    CBE Noor

    Anonymous
    Inactive

    የሠራተኞቻቸውን ደመወዝ የቀነሱ እና ከሥራ ያሰናበቱ 14 ሆቴሎች ተለይተው ታወቁ – የኢትዮጵያ የሆቴል ባለሙያዎች ማኅበር

    አዲስ አበባ (ኢፕድ) – የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን የሥራ መቀዛቀዝ ምክንያት በማድረግ የሠራተኞቻቸውን ደመወዝ ያልከፈሉ፣ የቀነሱ እና ሠራተኞቻቸውን ከሥራ ያሰናበቱ 14 ሆቴሎች መለየታቸውን የኢትዮጵያ የሆቴል ባለሙያዎች ማኅበር አስታወቀ።

    የኢትዮጵያ የሆቴል ባለሙያዎች ማኅበር የኮምኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እጅጉ እንደሻው ግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደገለጹት፥ መንግሥት የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉን ለመደገፍ ድጎማ ቢያደርግም አንዳንድ ሆቴሎች ሠራተኞቻቸውን እያሰናበቱ፣ እንዲሁም ደመወዛቸውን እያስቀሩና እየቀነሱ ነው።

    ሆቴሎችን መለየት የተቻለው ማኅበሩ በመሠረተው የቴሌግራም የመገናኛ ዘዴ መሆኑን ጠቁመው፥ ሠራተኞች የደረሰባቸውን ችግርና ሥራ የለቀቁበትን ደብዳቤ ይዘው መጥተዋል። ማኅበሩ የተገኙ የደብዳቤ ማስረጃዎችን በመያዝ ለኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር ኮንፌዴሬሽን ማሳወቁን አቶ እጅጉ አመልክተዋል።

    “ተበድረን ለሠራተኛ አንከፍልም፤ መንግሥት እንደሚያደርግ ያድርጋችሁ” ያሉ ሆቴሎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ እጅጉ፥ መንግሥት ያወረደውን መመሪያና ድጎማ ተፈፃሚ የሚያደርጉ አሠራሮችን እንዲያመቻች አሳስበዋል።

    እንደ አቶ እጅጉ ገለጻ፥ የሆቴል ሠራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት አያገኙም፤ የሚከፈላቸው ደመወዝ በፊትም አነስተኛ ነበር። በዚህ ወቅት የደንበኛ ጉርሻም አያገኙም። የትራንስፖርት ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል:: ከአነስተኛ ደመወዛቸው ላይ ግብር ይቆረጥለታል:: በመሆኑም መንግሥት ለእንዲህ አይነት ሠራተኞች የግብር ቅናሽ ወይም ምኅረት እንዲያደርግላቸውና ሙሉ ደመወዛቸውን እንዲያገኙ አሳስበዋል።

    የኢትዮጵያ የሆቴል ባለሙያዎች ማኅበር ፀሐፊ አቶ ክፍሉ ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው፥ ሆቴል ያለሠራተኛ ባዶ ህንፃ ማለት እንደሆነ ገልፀው፥ “የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜያዊ ነው፤ ነገ ያልፋል። ልምድ ያላቸውን የሆቴል ሠራተኞች ማሰናበት ለባለሀብቱም ለአገርም ክስረት ነው” ብለዋል።

    የሆቴል ሠራተኛ ዲፕሎማት እንደመሆናቸው በአግባቡ ካልተያዙ የሠራተኞች ዕጣ ለባለሀብቱም እንደሚተርፍ አመልክተው፥ “በዚህ ወቅት የተባረረ ሠራተኛ ነገ ቀን ሲወጣ ‘ና!’ ቢባል የሚመጣበት ሞራል አይኖረውም። የሆቴል ሠራተኛ ደንበኛን የሚያረካው በደስታ ሲሠራ ነው” ሲሉም አቶ ክፍሉ ተናግረዋል።

    በኢትዮጵያ የሆቴል ባለሙያዎች ማኅበር የሥልጠና እና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ሥዩም እንደገለጹት፥ በሌሎች ሀገራት እንኳን ያልተደረገውን የኢትዮጵያ መንግሥት ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ድጋፍ አድርጓል። ይህ ዓይነት ድጋፍ በሌሎች ዘርፍ አልተደረገም። መንግሥት ያደረገው ድጋፍ ግን ከታች ባለው የአፈፃፀም ችግር ክፍተት ታይቶበታል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢፕድ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    የኢትዮጵያ የሆቴል ባለሙያዎች ማኅበር የኮምኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እጅጉ እንደሻው

    Semonegna
    Keymaster

    መንግሥት የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመግታት የሚወሰዱ አዳዲስ እርምጃዎችን ይፋ አደረገ

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) ስርጭትን ለመከላከል ከተቋቋመው ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጣ ኮሚቴ ጋር ያለውን የክንውን ሁኔታ እና ተጨማሪ መመሪያዎች እንዲሁም <ኮቪድ-19>ን ለመከላከል እና ስርጭቱን ለመግታት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን አስመልክቶ በኢንተርኔት አማካኝነት (virtually) ውይይት አድርገዋል።

    እስከ ዛሬ መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ አጠቃላይ ኮቪድ-19 የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 16 በመጨመሩ፣ ቫይረሱ በፍጥነት እየተዛመተ እንዳይሄድ ለመግታት ሲባል በቂ የመከላከል ሥራዎች መሠራታቸውን ለማረጋገጥ፣ የፌደራል መንግሥት በስፋት የቅድመ-ጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ተመልክተዋል።

    ከውይይቱ በኋላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የሚከተሉትን ተጨማሪ ቁልፍ እርምጃዎች ይፋ ያደረጉ ሲሆን ጥሪም አቅርበዋል።

    በዚህም መሠረት፦

    1. ከዛሬ (መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም.) ከሰዓት ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ የሚደርሱ እና ለለይቶ መከታተያ በተዘጋጁት ሆቴሎች ለመቆየት አቅም የሌላቸው መንገደኞች ወደ አዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ተዛውረው ከውጪ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ መንገደኞች ለ15 ቀናት ተለይተው እንዲቆዩ የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ የሚያደርጉ ይሆናል።
    2. ከዛሬ አንስቶ ለተጨማሪ ሁለት ሳምንታት ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማትን ጨምሮ፣ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው የሚቆዩ ይሆናል።
    3. በገበያ ስፍራዎች እና በሀይማኖት ተቋማት ውስጥ ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ በጥብቅ ተፈጻሚ ሊደረጉ ያስፈልጋል። የፌደራል መንግሥት አስከፊ ብሔራዊ አደጋ በሚከሰት ጊዜ ሀይማኖታዊ ስብሰባዎች እንዲቋረጡ የማድረግ ሕገመንግሥታዊ መብት አለው። ሆኖም፣ በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉትን እርምጃዎች ተግባራዊ ከመደረጋቸው በፊት፣ ዜጎች የማኅበራዊ ርቀት መመሪያን ተግባራዊ እንዲያደርጉ በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል።
    4. ሁኔታው ተጨማሪ ድጋፍን የሚጠይቅ ከሆነ ሁሉም ጡረታ የወጡ እንዲሁም በትምህርት ላይ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ለብሔራዊ ግዳጅ እንዲዘጋጁ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
    5. የተለያየ መጠን እና ዓይነት ያላቸው መገልገያዎችን የያዙ ከ134 በላይ ተቋማት ለለይቶ መከታተያ፣ ለይቶ ማቆያ እና ሕክምና እንዲሆኑ ተለይተዋል። ስለዚህ፣ መንግሥት ሁሉም ዜጎች እንደ አልጋዎች፣ ፍራሾች፣ አንሶላዎች፣ የመተንፈሻ ቬንትሌተሮች እና ሌሎች ከሕክምና ጋር ተያያዥነት ያላቸው እና የሌላቸው መገልገያዎችን ለማሰባሰብ በመሥራት ላይ የሚገኘውን የብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ ያቀርባል።
    6. የማክሮ-ኢኮኖሚ ንዑስ ኮሚቴው ኢኮኖሚው ዘርፉን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አማራጮችን ለመቀየስ በልዩ ልዩ ዘርፍ ከተሠማሩት አበይት የኢንደስትሪ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትን ሲያካሂድ ቆይቷል። ይህንኑ ተከትሎም፣ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የሚከተሉት እርምጃዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ፡-
      • የ<ኮቪድ-19> ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስፈልጉ የገቢ ዕቃዎች እና ግብአቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ይደረጋል።
      • የፋይናንስ ዘርፉን ጤንነት አስጠብቆ የመቀጠል እና ባንኮች በ<ኮቪድ-19> ቫይረስ ለተጎዱ ደንበኞቻቸው ጊዜያዊ የብድር እፎይታ እና ተጨማሪ ብድር ለመስጠት እንዲያስችላቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ 15 ቢሊየን ብር ለግል ባንኮች ይሰጣል።
      • የውጪ ምንዛሬ የሚያስፈልጋቸው እና የ<ኮቪድ-19> ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ዕቃዎችን እና ግብዓቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለሚያስገቡ አስመጪዎች ባንኮች ቅድሚያ በመስጠት እንዲያስተናግዱ ይደረጋል።
      • በፋይናንስ አገልግሎት የተነሳ ገጽ ለገጽ መገናኘት እና የብር ንክኪን ለመቀነስ እንዲቻል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሞባይል አማካኝነት የሚደረግ ክፍያ እና ገንዘብ የማስተላለፍ ጣሪያውን ከፍ ያደርጋል።
      • የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለውጭ ገበያ በሚቀርብ አበባ ላይ የጣለው ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ገደብ በጊዜያዊነት እንዲነሳ ተደርጓል። ኩባንያዎች የተሻለ የገንዘብ ፍሰት እንዲኖራቸው ለማስቻል፣ የገቢዎች ሚኒስቴር የተጨማሪ እሴት ታክስ አመላለስ ሂደቱን በተለየ መልኩ እንዲያፋጥን ይደረጋል።
      • የ<ኮቪድ-19> ወረርሽኝን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የሸቀጦች እጥረት እና አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠር በንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር የጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

    ምንጭ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

    ኮቪድ-19

Viewing 15 results - 16 through 30 (of 49 total)