Search Results for 'የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ'

Home Forums Search Search Results for 'የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ'

Viewing 15 results - 31 through 45 (of 49 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራር አባላት ፊቤላ ኢንዱስትሪያል በማስገንባት ላይ የሚገኘውን ግዙፍ የምግብ ዘይት ፋብሪካን ጎበኙ

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራር አባላት ፊቤላ ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በማስገንባት ላይ የሚገኘውን ግዙፍ የምግብ ዘይት ፋብሪካን ጎበኙ። ፋብሪካው በተያዘው በጀት ዓመት ተመርቆ ምርት እንደሚጀምር በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፋይናንስ በማድረግ እየተሳተፈበት የሚገኘውና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቡሬ ከተማ በኢትዮጵያዊው ባለሃብት አቶ በላይነህ ክንዴ የተገነባው የዘይት ፋብሪካ በዓመት 500 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት የሚያመርት ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍጆታን ከ50 እስከ 60 በመቶ መሸፈን የሚያስችልና ለዘይት ግዥ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማዳን የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረውም ተገልጿል።

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሚሰማሩና ለበርካቶች የሥራ ዕድል ለሚፈጥሩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ብድር የሚያቀርብ ሲሆን፥ በቡሬ ከተማ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ ወጥቶበት በመገንባት ላይ ለሚገኘው የምግብ ዘይት ፋብሪካም ባንኩ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ማቅረቡን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንትና የጉብኝት ቡድኑ አስተባባሪ አቶ ሙሉነህ አቦዬ ይገልፃሉ።

    በቡሬ ከተማ በ30 ሄክታር መሬት ላይ ግንባታው ተገባዶ የማሽን ተከላ ሥራው እየተጠናቀቀ የሚገኘው ይህ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ከአንድ ወር በኋላ ወደ ምርት እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን፥ ከ2500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።

    በአቶ በላይነህ ክንዴ በመገንባት ላይ ያለው ፋብሪካው፥ የሀገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍጆታን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚሸፍን በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል። በሀገር ውስጥ ያለውን የምግብ ዘይት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ወደ ዘርፉ መግባታቸውን የገለጹት አቶ በላይነህ ክንዴ፥ ፋብሪካው ወደ ምርት ሲገባ የውጭ ምንዛሬ በማዳን በኩል ፋይዳው የጎላ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

    በመገንባት ላይ ያለው ትልቅ የምግብ ዘይት ፋብሪካ አካባቢው ከሱዳን ጠረፍ እስከጃዊ አኩሪ አተር፣ ኑግ፣ ሰሊጥ፣ ሱፍ፣ ስንዴና በቆሎ በከፍተኛ ደረጃ ትርፍ አምራች በመሆኑ ምርቶቹን በግብአትነት በመጠቀም የምግብ ዘይት በከፍተኛ ደረጃ በማምረት የአገሪቱን ከ50 እስከ 60 በመቶ ፍላጎት እንደሚሸፍንም ነው አቶ በላይነህ የጠቆሙት።

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በቡሬ ከተማ በመገንባት ላይ ለሚገኙት ሌሎች አምራች ኢንዱስትሪዎች ፋይናንስ በማድረግ ላይ ሲሆን፣ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚገኙና በአምራች ኢንዱስትሪው ለተሰማሩ የግል ኢንቨስተሮች ፋይናንስ በማድረግ ላይ እንደሚገኝና ይህን ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ሙሉነህ አቦዬ አስታውቀዋል።

    በቡሬ ከተማ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ምርት ለመግባት በዝግጅት ላይ ያለው ፊቤላ ኢንዳስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የዘይት ፋብሪካ በ2006 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን የጀሪካን፣ የማሸጊያ፣ የሳሙና፣ የማርጋሪንና የካርቶንን ጨምሮ ሰባት የተለያዩ ፋብሪካዎችን በውስጡ ይዟል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ፊቤላ ኢንዱስትሪያል

    Anonymous
    Inactive

    አቶ አቤ ሳኖ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሾሙ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – አቶ አቤ ሳኖ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሾሙ። አቶ አቤ ከየካቲት 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ነው ባንኩን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ የተመደቡት።

    የካቲት 26 ቀንም ከቀድሞ የባንኩ ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባጫ ጊና እና ከሌሎች የባንኩ የሥራ አመራር አባላት ጋር ትውውቅና የሥራ ርክክብ አድርገዋል። በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት አቶ ባጫ ጊና በኃላፊነት ቆይታቸው የሥራ አመራሮችና ሠራተኞች ላደረጉላቸው እገዛና ትብብር ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፥ ከአዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ጋርም በትጋትና በትብብር በመሥራት ለተሻለ ውጤት እንዲሠሩም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

    አዲስ የተሾሙት የባንኩ ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቤ ሳኖ በበኩላቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ ሥራ የጀመሩበትና በወጣት እድሜያቸው በኃላፊነት መምራት ወደቻሉበት ባንክ መምጣታቸው የሚጠበቅባቸውን ለማበርከት እንደሆነ ገልፀዋል። አቶ አቤ ሳኖ ከዚህ በፊት ከሁለት ዓመታት ከፍ ላለ ጊዜ ያህል (ከጥር ወር 1998 ዓም እስከ ኅዳር ወር 2001 ዓ.ም.) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በፕሬዝዳንትት ማገልገላቸው ይታወሳል። የዚያን ጊዜ የአንጋፋው ባንክ ፕሬዝዳንት ሆነው ሲሾሙ የ30 ዓመት ወጣት ነበሩ። ይህም ሁኔታም የሥራ ልምዳቸውን ጥያቄ ውስጥ በማስገባት በዘርፉ በተሰማሩ ብዙ ግለሰቦች ዘንድ ጥርጣሬንና አግራሞትን ፈጥሮ ነበር።

    አቶ አቤ አክለውም በድጋሚ ኃላፊነቱን ተረክበው እንዲሠሩ ምክንያት የሆናቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞችን ከልብ መውደዳቸውና ሠራተኛው ለእርሳቸው የነበረው አክብሮትና ፍቅር እንደሆነ ገልፀዋል። ባንኩ ለሀገር የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ከፍ ለማድረግ ከአመራሩና ሠራተኛው ጋር በመሆን የአቅማቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል።

    ከሐምሌ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የባንኩ ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ባጫ ጊና ሀገራቸውን በዲፕሎማሲው ዘርፍ ለማገልገል ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ ነው አቶ አቤ ሳኖ ባንኩን እንዲመሩ በኃላፊነት የተመደቡት።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    —–
    ሌሎች ዜናዎች፦

    አቶ አቤ ሳኖ Abe Sano

    Anonymous
    Inactive

    የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ‹‹ሸገር ባንክ›› የተሰኘ ባንክ ለመመሥረት እንቅስቃሴ ጀመሩ

    አዲስ አበባ (ሪፖርተር ጋዜጣ)– የኦሮሚያ ክልልን በፕሬዚዳንት ከመመራት ባሻገር የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችን በሚኒስትርነት ያስተዳደሩትና በስደት ከኢትዮጵያ ውጭ የነበሩት አቶ ጁነዲን ሳዶ ‹‹ሸገር ባንክ›› የተባለ አዲስ ባንክ ለማቋቋም እንቅስቃሴ በመጀመር የባንኩን የአክሲዮን ሽያጭ አስጀምረዋል።

    አቶ ጁነዲን ‹‹ሸገር ባንክ›› በሚል መጠሪያ የሰየሙትን ባንክ ለማቋቋም የተሰባሰበውን አደራጅ ኮሚቴ በአስተባባሪነት እየመሩ ሲሆን፣ ባንኩን ለመመሥረት የሚያስፈልገውን ካፒታል ለማሟላት ከተለያዩ ባለሀብቶች ጋር ከመከሩና አክሲዮን የሚገዙ በርካቶችን ከጎናቸውን ካሰለፉ በኋላ ወደ ካፒታል ማሰባሰብ ሥራ መግባታቸው ይጠቀሳል።

    ከሸገር ባንክ የአክሲዮን ሽያጭ በተሠራጨው መረጃ መሠረት፣ እንደ ሕጉ አግባብ አንድ አክሲዮን የአንድ ሺሕ ብር ዋጋ ይኖረዋል። አንድ ባለአክሲዮን ከአሥር አክሲዮኖች ጀምሮ መግዛት ይችላል ተብሏል። ባንኩን በተያዘው ዓመት መጨረሻ  ሥራ ለማስጀመር መታቀዱን ከአደራጅ ኮሚቴው ለመረዳት ተችሏል። ሸገር ባንክን ለመመሥረት አቶ ጁነዲን ጨምሮ 150 አደራጆች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ሲገለጽ፣ ካፒታል በማሰባሰቡ ረገድ ባንኩ ውጭ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሠራም ተጠቅሷል። የባንኩን አብላጫ ድርሻም በገጠሩ ኅብረተሰብ ላይ ትኩረት በማድረግ የአክሲዮን ሽያጩ እንደሚከናወን ይጠበቃል።

    የ‹‹ሸገር ባንክ›› አደራጆች፣ ከባንኩ ጋር ለመሥራት ፈቃደኛ የሆኑና ታዋቂ ግለሰቦችን በማካተት ሐሙስ፣ የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል የባንኩን አቅጣጫ የሚያመላክት ትንታኔ አቅርበዋል።

    በዚሁ ወቅትም የባንኩ የአክሲዮን ሽያጭ እንደተጀመረ ተገልጾ፣ ከታዋቂ ግለሰቦች መካከል ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ፣ አቶ ጁነዲን ሳዶ፣ አቶ ጌቱ ገለቴ፣ አቶ ድንቁ ደያስና ሌሎችም ተገኝተዋል። የተለያዩ ከተሞችን የሚያስተዳድሩ ኃላፊዎችና  ከንቲባዎች እንዲሁም አባ ገዳዎች ተሳትፈዋል።

    በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት ባንክ ለማቋቋም 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስፈልጋል። ይህንን ተከትሎም የሸገር ባንክ የተፈቀደ ካፒታል እስከ ሁለት ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ተገልጿል። የባንኩ አደራጆች ቢሮ ቦሌ መንገድ ላይ በሚገኘው ጌቱ ኮሜርሻል ሕንፃ ላይ መከፈቱም ታውቋል።

    የሸገር ባንክ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጁነዲን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲያቅፍ እንደሚደረግ በተለይ ግን ለገበሬው ክፍልና በተለያዩ ከተሞች በአነስተኛ ንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑና ተደራሽ የፋይናንስ አቅርቦቶችን እንዲያገኙ ይታሰባል። ባንኩ የገጠሩን ክፍል ከከተማው ጋር በማስተሳሰር የገቢ ምንጩ እንዲሰፋ የማገዝ ዓላማ እንዳለውም አቶ ጁነይዲ ጠቅሰዋል።

    ሙሉ ታሪኩን ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ያንብቡ

    ሸገር ባንክ

    Semonegna
    Keymaster

    የሀገሪቱ ንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሁነኛ ደጋፊ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2019 የግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ ሽልማት አሸናፊ ሆነ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2019 የግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ ሽልማት አሸናፊ ሆነ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊ የሆነው “በምርጥ የንግድ ባንክ” ምድብ ነው።

    ባንኩ በተለያዩ ዘርፎች ከቀረቡ ባንኮች ጋር ተወዳድሮ ነው “ምርጥ ንግድ ባንክ” /Best Commercial Bank/ ሽልማት አሸናፊ መሆን የቻለው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ምርጥ ባንኮች ደረጃ እያገኘ የመጣ ሲሆን ለዚህ ዓለም አቀፍ ሽልማት ሲበቃ ይህ የመጀመሪያው ነው።

    ሽልማቱ ግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ በሚያወጣቸው መስፈርቶች ተመሥርቶ የሚካሄድ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዚህ ሽልማት አሸናፊ ለመሆን ካስቻሉት መስፈርቶች መካከል ለበርካታ ዓመታት በትርፋማነት መቀጠሉ፣ ተደራሽነቱ በፍጥነት እያደገ መሄዱ፣ የደንበኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩ፣ ለልማት ሥራዎች የሚያስፈልግ የፋይናንስ አቅርቦት ማሳደጉ፣ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በሚገባ መወጣቱና ሌሎች የባንክ አገልግሎቶችን በተሟላ ሁኔታ መስጠት መቻሉ እንደሆነም ተጠቅሷል።

    ባንኩ የአገሪቱን ቁልፍ የልማት ሥራዎች እየደገፈና ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የጤና፣ ትምህርት፣ አካባቢ ጥበቃና ሌሎችም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በግንባር ቀደምትነት ለመደገፍና በመሳተፍ ለአገራችን ልማት አጋር መሆኑን በተጨባጭ ያስመሰከረ መሆኑ ዓለም አቀፍ ሽልማቱን በቀዳሚነት እንዲያገኝ እንዳስቻለው ነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ባጫ ጊና የገለፁት።

    በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ከሆኑ ሥራዎች መካከል የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት ማሳደግ የሚያስችሉ ግዙፍ ኘሮጀክቶችን ፋይናንስ በማድረግ ባለፉት ዓመታት በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዲከናወኑ አድርጓል። ለኃይል ማመንጫ ኘሮጀክቶች በርካታ ገንዘብ በማቅረብ ግንባታዎች እንዲከናወኑ በማድረግ ላይ መሆኑም ነው የተገለፀው።

    የሀገሪቱ ንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዋና ደጋፊ ከሆኑ ድርጅቶች መካከል ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፥ በየዓመቱ ለግብርና ግብዓቶች አቅርቦት፣ ለክልሎች ፋይናንስ ማቅረቡ፣ ለሀገር ውስጥ ከሚያቀርበው ከፍተኛ መጠን ካለው ብድር በተጨማሪ ለህብረተሰቡ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የመድኃኒት፣ የምግብ ዘይት፣ ስንዴ፣ ስኳርና ቅባት ሌሎች የፍጆታ እቃዎችና የፋብሪካ ግብአቶች ከውጪ እንዲገቡ በማገዝ እየሠራ መሆኑም ለአሸናፊነቱ አስተዋፅኦ ማበርከቱ ተገልጿል። አቶ ባጫ ጊና አክለውም ሽልማቱ ባንኩ በቀጣይ ያለውን አገልግሎት ለማሳደግና በሌሎች ዘርፎችም ተሸላሚ ለመሆን የሚያነሳሳ መሆኑን ገልፀዋል።

    ግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ በ2019 ካዘጋጃቸው የውድድር ምድቦች መካከል፦

    • Best Commercial Bank – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
    • Best Islamic Bank – የአፍጋኒስታኑ Islamic Bank of Afghanistan፣
    • Best Innovative Bank – የአርመኑ InecoBank፣
    • Best Digital Bank – የቦትስዋናው FNB Botswana፣
    • Best Customer Service Bank – የባህሬኑ BBK፣
    • Best Retail Bank – የግብጹ National Bank of Egypt፣

    ከአሸናፊ ምርጥ ዝርዝሮች መካከል ይጠቀሳሉ። በተለያዩ ዘርፎች ያሸነፉ የባንኮችን ዝርዝር ለማየት እዚህ ጋር ይጫኑ። ከዚህ ቀደም የግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ ሽልማት አሸናፊ ከነበሩ ሀገራት መካከል ካናዳ፣ ሩስያ፣ ቻይና፣ ፖርቹጋል፣ ህንድ፣ ኢንዶኒዥያ፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጀሪያ ይጠቀሳሉ።

    ግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ መቀመጫነቱ ለንደን ከተማ (እንግሊዝ) የሆነ ንግድና ኢንዱስትሪ ዘገባዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የህትመት ድርጅት ነው።

    ንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ

    Anonymous
    Inactive

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በሀገራችን ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ የክፍያ ሥርዓቶችን በማስተዋወቅ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የዲጂታል ማዕከል ከፈተ።

    ይህ የዲጂታል ማዕከል በቀን ከ300 ሺ ሰው በላይ በሚንቀሳቀስበትና ከፍተኛ የደንበኞች ፍሰት ባለበት መገናኛ አካባቢ፣ የባንኩ ህዳሴ ህንፃ ላይ ነው የተከፈተው።

    በዲጂታል ማዕከሉ መክፈቻ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የባንኩ ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ባጫ ጊና እንዳሉት፥ ማዕከሉ ከሃያ በላይ የገንዘብ መክፈያና መቀበያ ማሽን በአንድ ቦታ በማስቀመጥ ደንበኞች በቀላሉ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሀገራችንን የክፍያ ሥርዓት ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ፋና ወጊ መሆኑን ገልፀው፥ በተመሳሳይ ሁኔታ ከ16 ዓመታት በፊት የኤቲኤም ማሽንን (ATM) በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀውና አገልግሎት ላይ ያዋለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆኑም አቶ ባጫ አስታውሰዋል።

    በዲጂታል ማዕከል ውስጥ ከተቀመጡ በርካታ ኤቲኤሞች መካከል ሁለቱ ገንዘብ ገቢና ወጪ ማድረግ እንዲችሉ ተደርገው የተዘጋጁ መሆናቸውን ፕሬዝዳንቱ ገልፀው፣ በቀጣይ ተመሳሳይ ገንዘብ ገቢና ወጪ የሚያደርጉ ከ100 በላይ ተጨማሪ ኤቲኤሞችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚቀመጡ መሆኑን አስታውቀዋል።

    ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ፥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚሰጣቸው የባንክ አገልግሎቶች ጥራታቸውን ጠብቀውና የደንበኞችን ፍላጎት አሟልተው እንዲሰጡ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ። ይህ የተገለጸው ባንኩ የ6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸሙን በዝርዝር ገምግሞ በቅርንጫፎች እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶችን ተዘዋውሮ ከተመለከተ በኋላ ነው።

    አቶ ባጫ ጊና የገነተ ጽጌ፣ ቸርችል፤ ፍልዉሃ እና ጥላሁን አባይ ቅርንጫፎችን ከተመለከቱ በኋላ እንደተናገሩት፥ ቅርንጫፎች እየሰጧቸው የሚገኙ የባንክ አግልግሎቶች ቀላል፣ ቀልጣፋና ለደንበኞች ምቾት መስጠት ላይ አተኩረው መሥራት ይገባቸዋል።

    የባንክ አገልግሎት ሁልጊዜም እየዘመነና ድካምን እየቀነሰ መሄዱን ያስታወሱት አቶ ባጫ ጊና፥ ባንኩም በፍጥነት እየተለዋወጠ ከሚሄደው ዓለም ጋር አብሮ የሚራመድ አገልግሎት ማቅረብ ይገባል። ለዚህም ባንኩ ለቅርንጫፎች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ለደንበኞቹ የሚመጥን አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ጥረት እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

    ከግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ጎን ለጎን በቅርንጫፎች እየተሰጡ የሚገኙ አገልግሎቶችን በአካል ተዘዋውሮ ምልከታ በማድረግና አስፈላጊውን የቁሳቁስና የሰው ኃይል በማሟላትና ስልጠና በመስጠት ክፍተቶችን መሸፈንና አገልግሎቶቹ በጥራት እንዲሰጡ የሚደረገው ጥረት በሁሉም የባንኩ ቅርንጫፎች ተጠናክሮ እንደሚሠራ ከጉብኝታቸው በኋላ ገልጸዋል።

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአንድ ወር የሚቆይ “የአገልግሎት ጥራት መሻሻል እናመጣለን” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ የሚገኘው ንቅናቄ ያለበትን ሁኔታ የአመራር ቡድኑ የተመለከተ ሲሆን፥ ከደንበኞች ከተሰጡ አስተያየቶች ለመረዳት እንደተቻለው ባንኩ አገልግሎቶቹን ጥራታቸውን በጠበቀ መልኩ በመስጠት የሚታወቅ በመሆኑ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የጥራት መጓደሎችን በትኩረት ማስተካከል እንደሚገባው ለአመራር ቡድኑ ጠቁመዋል።

    ጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም. የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ ቡድኖች ተከፋፍለው በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ቅርንጫፎችን በመመልከት ክፍተት በታየባቸው ቅርንጫፎች ፈጣን ማስተካከያ እንዲያደርጉ አቅጣጫ በመስጠት ነው የዕለቱን ምልከታቸውን ያጠናቀቁት።

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስካሁን ከ1,560 በላይ በሚሆኑ ቅርንጫፎች፣ ከ23.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ደንበኞችን ማፍራት የቻለ ሲሆን፣ ከ3,000 በላይ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች፣ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ለኤቲኤም ካርድ ተጠቃሚ ደንበኞች አገልግሎት እየሰጠ ያለ አንጋፋና በሀገሪቱ ትልቁ ባንክ ነው።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ


    Semonegna
    Keymaster

    ብርሃን ባንክ የ10ኛ ዓመት የምሥረታ ክብረ በዓሉን ሲያከብር ለኢትዮጵያ ልብ ህሙማን ሕፃናት መርጃ ድርጅት የ3 ሚሊዮን ብር እንዲሁም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአጥንት ህክምና ክፍል የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ብርሃን ባንክ የ10ኛ ዓመት የምሥረታ ክብረ በዓሉን ህዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በተለያዩ ሥነ-ሥርዓቶች በስካይላይት ሆቴል በደማቅ ሁኔታ አክብሯል። በዝግጅቱ ባንኩ ለአገልሎት ክፍት ከሆነበት ከከፈረንጆች ጥቅምት (October) ወር 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ ያሉ የተለያዩ ዋነኛ ስኬቶቹን በማወደስ፣ የወደፊት ጊዜያትን ደግሞ በጠንካራ አቅም ሊጓዝ እንዳቀደ ነው ያስረዳው። የእለቱ ዝግጅት በሦስት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያነጣጠረ ሆኖ በተለያዩ መርሃግብሮች በስኬት ተጠናቅቋል።

    ከተለያዩ የህትመት እና ኤሌክተሮኒክስ ሚዲያ ተቋማት ተጋብዘው በቀረቡ የሚዲያ አካላት በተዘጋጀው የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ እና የባንኩ ፕሬዚዳንት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ እስከ 11፡45 ድረስ ተከናውኗል። በማስከተልም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ወንበሮቻቸውን እንደያዙ በመድረኩ ላይ በእውቅ የሙዚቃ ተጫዋቾች አማካኝነት ድንቅ የሆነ የቫዮሊን የሙዚቃ ኮንሰርት ለታዳሚያኑ ቀርቧል። ይህንንም ተከትሎ በአርቲስት ሃረገወይን አሠፋ የመድረክ አጋፋሪነት ለእንግዶቹ የሚቀርበው የአዳራሽ ውስጥ ዝግጅቱ በይፋ ተጀመረ። አርቲስት ሃረገወይን የባንኩን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ካቀረበች እና አጠር ያለ የ10 ዓመታት የባንኩን የአመሰራረት አፅመ ታሪክ በአጭሩ አቅርባ መድረኩን እንዲረከቧት እና የእለቱን የክብር እንግዶች ወደ መድረክ እንዲጋብዙ የባንኩን ፕሬዚዳንት አቶ አብሃም አላሮን ወደ መድረኩ ጋበዘች።

    የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አብሃም አላሮ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት እንዲያስተላልፉ የብሔራዊ ባንክ ገዥ የሆኑትን ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ወደ መድረክ ጋብዘው ገዥው ባንኩ በርካታ ባለአክሲዮኖችን በመያዝ ቀዳሚው የንግድ ባንክ መሆኑን ገልፀው ለመላው የባንኩ ማህበረሰብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አቅርበዋል። በማስከተልም የቀረበው የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጉማቸው ኩሴ የእንኳን አደረሳችሁ እና እንኳን ደስ ያላችሁ መልክት ሲሆን፥ ሰብሳቢው በመልዕከታቸው የባንኩን ስኬቶች በማወደስ ቀጣይ ሥራዎችን በተሻለ አቅም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ እምነታቸውን ገልፀዋል። ይህ ዝግጅት እንዲህ ባለው መልኩ ቀጥሎ በባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አብርሃም አላሮ አጠር ያለ የኢትዮጵያ ባንኮችን ታሪክ እና እድገት እንዲሁም ብርሃን ባንክ በ10 ዓመታት ዕድሜው ያሳየውን የአፈፃፀም ጉዞን የሚያሳይ ጥናት ቀርቧል። ፕሬዚዳንቱ ባንኩ ከምሥረታው ጀምሮ በተለያዩ ልኬቶች ያስመዘገባቸው ስኬቶቹ እጅግ አመርቂ እና ፍሬያማ የሚባሉ መሆናቸውን አብራርተው በቀጣይም እነኚህ ስኬቶቹ በላቀ መልኩ አሸብርቀው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

    በማስከተል የቀረበው ለባንኩ መመሥረት እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች ባንኩን ከምሥረታው ጀምሮ ላገዙ መሥራቾች፣ አመራሮች እንዲሁም ላለፉት አስር ዓመታት በባንኩ ላገለገሉ ሠራተኞች የእውቅና እና የምስጋና ስጦታዎችን የማበርከት ሥነ-ሥርዓት ነበር። ከምስጋና የምስክር ወረቀት (certificate) ጀምሮ 13 ሠራተኞቹን ጨምሮ ለተለያዩ ባለድርሻዎች በወርቅ በተሠሩ ስጦታዎች ተበርክቶላቸዋል። ይህንኑ መርሀ ግብር ተከትሎ ብርሃን ባንክ ለኢትዮጵያ ልብ ህሙማን ሕፃናት መርጃ ድርጅት የ3 ሚሊዮን ብር እንዲሁም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአጥንት ህክምና ክፍል 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። ይህንኑ ስጦታ የማዕከላቱ ተጠሪዎች ዶክተር ሄለን በፈቃዱ (የልብ ሕሙማን ህፃናት ድርጅትን በመወከል) እና ዶክተር ብሩክ ላምቢሶ (የአጥንት ህክምና ክፍልን በመወከል) ከባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ እጅ ተቀብለዋል። ይሀንን ስጦታ ሲቀበሉም ድጋፉ በሚደረግላቸው እና የህክምና ወጪዎቻቸውን መሸፈን በማይችሉ አቅመ ደካማ ህፃናት እና አረጋውያን ስም አመስገነው ገንዘቡን ሙሉ በሙሉ ለታለመለት ዓላማ እንደሚያውሉ ከምስጋና ጋር ቃል ገብተዋል።

    በዝግጅቱ መጨረሻ ላይም የባንኩ ቀጣይ የንግድ ምልክት ወይም መለያ ምልክት ሆኖ የሚያገለግለውን አዲስ አርማ ለታዳሚያን ተዋውቆ የዕለቱ ዝግጅት በእራት መርሀ ግብር በደማቅ ሁኔታ ተገባዷል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ብርሃን ባንክ

    Semonegna
    Keymaster

    ባንዲራ ይዛችሁ ወጥታችኋል በማለት ክርስቲያኖችን የሚያዋክቡ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተጠየቀ
    ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚሞክሩ ጽንፈኞች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ እንዲቆም የሚያግዝ እና ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት ሙያዊ ትንተና የሚያቀርብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ጉባኤው ጠይቋል።

    —–

    አዲስ አበባ (ማኅበረ ቅዱሳን) – የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ዓርማ አድርጋ ስትጠቀምበት የኖረችውን እና አሁንም የምትጠቀምበትን ባንዲራ ለበዓል ይዛችሁ ወጥታችኋል፤ በቤተ ክርስቲያን ጣሪያ እና ጉልላት ላይ ቀብታችኋል በማለት ምእመናንን የሚያዋክቡ፣ ወጣት ክርስቲያኖችን የሚያስሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተጠየቀ።

    በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያንን ተቀማጭ ገንዘብ ከንግድ ባንክ አውጥታችሁ እኛ በምንፈልገው ባንክ አስቀምጡ በማለት የሚያስገድዱ በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የሚገኙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ያስጠነቀቀው 38ኛው የመንበረ ፓትርያርክ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ቅዳሜ ጥቅምት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በተጠናቀቀበት ዕለት ነው።

    ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት ርዕዮተ ዓለም ቀርጸው፣ የሐሰት ታሪክ ፈጥረው በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚነዙ አቀጣጣዮችን (‘አክቲቪስት’/ ‘activist’ ነን ባዮች) እና ፖለቲከኞችን እኩይ ድርጊት መቃወም እንደሚገባ ጉባኤው በመግለጫ አሳውቋል።

    ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚሞክሩ ጽንፈኞች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ እንዲቆም የሚያግዝ እና ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት ሙያዊ ትንተና የሚያቀርብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ጉባኤው ጠይቋል።

    የሕግ ባለሙያዎች የተካተቱበት ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚደርስ ኮሚቴ በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቋቋም ጉባኤው አሳስቦ አገራዊ ለውጡ ተስፋ የሰጠ ቢሆንም በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለው እኩይ ተግባር ቤተ ክርስቲያንን እያሳዘናት እና እያሳሰባት መሆኑንም አስገንዝቧል።

    በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈጸመውን ጥፋት በሰላማዊ መንገድ በሽምግልና እና በውይይት ለመፍታት ጥረት ማድረግ የሚገባ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ መደረግ እንደሚኖርበትም አሳስቧል።

    የጥምቀት እና የመስቀል በዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን ሙሉ በሙሉ ነጥቀው፣ አንዳንድ ጊዜም ቆርሰው ለሌሎች የሚሰጡ አካላትን እኩይ ድርጊት አጥብቆ የተቃወመው መግለጫው በአገር ውስጥም በውጭም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለመፈታተን የሚሞክሩ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን እኩይ ድርጊት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥበብ እና በትዕግሥት ማሳለፉ የሚያስደንቅ መሆኑን ገልጧል።

    ምንጭ፦ ማኅበረ ቅዱሳን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ባንዲራ ይዛችሁ ወጥታችኋል

    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እንዳሳወቀው፥ የተጠናቀቁ የባቡር ፕሮጀክቶችን ወደ ተግባር ለማስገባት የኤሌክትሪክ ኃይል አለመኖር ጉልህ ችግር መፍጠሩንና፣ እየተከናወኑ ባሉ ፕሮጀክቶችና ታላላቅ ተግባራት ላይ መስተጓጎልን አስከትሏል።

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የተጠናቀቁ የባቡር ፕሮጀክቶችን ወደ ተግባር ለማስገባት የኤሌክትሪክ ኃይል አለመኖር እክል መፍጠሩን የኢትዮዽ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታውቋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበኩሉ ችግሩ ኮርፖሬሽኑ ለመሠረተ ልማት የሚያስፈልገውን ክፍያ ባለመፈጸሙ የተፈጠረ መሆኑን ገልጿል።

    በቱርኩ ሥራ ተቋራጭ ያፒ መርኬዚ እየተሠራ ያለውና ግንባታው ከ97 በመቶ በላይ የደረሰው የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ፕሮጀክት እየተጠናቀቀ ቢሆንም የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመኖሩ የሙከራ ጉዞ ለማድረግ አለመቻሉን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ ገልጸዋል።

    እንደ አቶ ደረጃ ገለጻ ያለቁት ፕሮጀክቶች ወደሥራ ቢገቡ ወደ ጅቡቲ ወደብ በሚደረገው ጉዞ የሚወስደውን ጊዜ ከ50 በመቶ በላይ በመቀነስ የወጪ ገቢ ንግድን ያቀላጥፋሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን የባቡር መስመሩ የሚያልፍበት አካባቢ ኅብረተሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከፍ ይላል። ስለዚህም የኤሌክትሪክ ችግር ቶሎ እልባት ቢያገኝ መልካም ነው ብለዋል።

    የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሞገስ መኮንን በበኩላቸው እንዳሉት፥ ድርጅታቸው መሠረተ ልማቱን ዘርግቶ ኃይል የማቅረብ ሥራ ይሠራል። ለመሠረተ ልማት ዝርጋታው የሚያስፈልገው ወጪ ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይሉን በሚፈልገው ድርጅት የሚሸፈን ይሆናል። የኢትዮጵያ ምድር ባቡርም ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ የሚሆነውን ክፍያ ባለመፈጸሙ የኤሌክትሪክ ኃይል ሊያገኝ አለመቻሉን አቶ ሞገስ ገልጸዋል።

    የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ ግን ይህ የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የበጀት እጥረት ሲገጥመው በመጨረሻ ያመጣው ሃሳብ እንጂ የቀድሞ አሠራሩ እንዲህ አልነበረም ብለዋል።

    እንደ አቶ ደረጀ ገለጻ፥ ‘በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ውሃ ስትፈልግ ከለገዳዲ ጀምረህ መስመር አትዘረጋም፤ ራሱ ድርጅቱ መሠረተ ልማቱን ይሰራልሃል። የኤሌክትሪክ ኃይልም ከዚህ የተለየ አይደለም፤ የመሠረተ ልማት ዝርጋታውንም ሆነ የኃይል አቅርቦቱን የሚያከናውነው ራሱ ነው’ ብለዋል።

    ምንጭ፡- አዲስ ዘመን / ኢቢሲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን


    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያቀረበውን ይህን ከወለድ ነፃ የዳያስፖራ የቤት መግዣ የፋይናንስ አገልግሎት በውጭ የሚኖሩ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሌሎች በዚህ አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ኢትዮጵያ ውስጥ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግ የሚያስችል ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ይፋ አደረገ። አገልግሎቱ ሙስሊሙን ህብረተሰብ ጨምሮ ሌሎች የወለድ አገልግሎትን የማይፈልጉ ዳያስፖራዎችም እንዲጠቀሙበት የተዘጋጀ ነው።

    የባንኩ የጥራት ቁጥጥር ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እመቤት መለሰ አዲሱን ከወለድ ነፃ የዳያስፖራ ፋይናንስ አገልግሎት አስመልክተው በሰጡት አስተያየት “ለመኖሪያ ቤት መግዣ የሚውለው ከወለድ ነፃ የዳያስፖራ ፋይናንስ አገልግሎት ከዚህ ቀደም ከቀረቡትና ዳያስፖራውን ከሚመለከቱ የባንክ አገልግሎቶች በተለየ መንገድ ይተገበራል” ብለዋል።

    ዳያስፖራው ወዲዓ’ህ የቁጠባ ሒሳብን በመጠቀም ቢያንስ 20 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ በእንግሊዝ ፓውንድ፣ በአሜሪካን ዶላርና በዩሮ መቆጠብ ከቻለ፣ የፋይናንስ ጥያቄውን ለባንኩ በማቅረብ መስተናገድ እንደሚችል ወይዘሮ እመቤት ተናግረዋል።

    ግንባታው የተጠናቀቀና ጅምር ቤት ለመግዛት የሚውለው የፋይናንስ አገልግሎት በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የመኖሪያ ቤት ችግር እንቅፋት እንዳይሆንባቸው ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ታስቦ ለዳያስፖራው የተዘጋጀ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት ነው። የፋይናንስ አገልግሎቱን መስፈርቶች ማሟላት የሚችሉ ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ወይም በሚኖሩበት አገር በሚገኝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ቀርበው የወዲዓ’ህ ቁጠባ ሒሳብ በመክፈት መቆጠብ የሚችሉ ሲሆን፣ ለአገልግሎቱ የሚያስፈልገውን ቅድመ ክፍያ በአንድ ጊዜ ወይም በተለያዩ ጊዜያት በመቆጠብ መክፈል ይችላሉ። ለቤት መግዣ የሚውለውን ፋይናንስ እስከ 20 ዓመት በሚደርስ የቆይታ ጊዜ ከፍለው መጨረስ እንዲችሉም ተመቻችቷል።

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያቀረበውን ይህን ከወለድ ነፃ የዳያስፖራ የቤት መግዣ የፋይናንስ አገልግሎት በውጭ የሚኖሩ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሌሎች በዚህ አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ እንዲጠቀሙበት ወይዘሮ እመቤት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    ከወለድ ነፃ


    Anonymous
    Inactive

    አሁን የተወሰደውን እርምጃ በማፋጠን ጣቢያውን በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል የመለዋወጫ አቅርቦት ስምምነትም ጣቢያውን ከገነባው ኩባንያ ጋር በመፈራረም ወደ ሥራ መገባቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብርሃም በላይ ተናግረዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በተከዜ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ከነበሩት አራት ተርባይኖች ሦስቱ ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብርሃም በላይ አስታወቁ።

    በተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት ዶ/ር አብርሃም፥ ለጣቢያው በተሰጠው ትኩረትና በተወሰደው የማስተካከያ እርምጃ ቀደም ሲል በአንድ ተርባይን ብቻ ኃይል ያመነጭ የነበረው ጣቢያው በአሁኑ ሰዓት ሦስት ተርባይኖቹ ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ገልፀዋል።

    አሁን የተወሰደውን እርምጃ በማፋጠን ጣቢያውን በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል የመለዋወጫ አቅርቦት ስምምነትም ጣቢያውን ከገነባው ኩባንያ ጋር በመፈራረም ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

    እንደ ዶ/ር አብርሃም በላይ ገለፃ፥ በኃይል ማመንጫው የተከሰቱ ችግሮች በወቅቱ ተለይተው መፍትሄ እንዲያገኙ ባለመደረጉ ተቋሙ ተጨማሪ ወጪ ለማውጣት ተገዷል። በመሆኑም ተመሳሳይ ችግር በሌሎች የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እንዳያጋጥም ትምህርት ሊወሰድበት እንደሚገባም አንስተዋል።

    ዶ/ር አብርሃም ከጣቢያው ሠራተኞች ጋር የተወያዩ ሲሆን በተቋሙ እየተካሄዱ ያሉ የለውጥ ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

    ተቋሙ የተሻለ አቅም እንዲኖረው እና በአገልግሎት ጥራቱ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችሉ የሰው ሃብት ልማት ሥራዎች እየተሠሩ በመሆኑ የተቋሙ ሠራተኞች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

    ተቋሙ ዋናው የኦፕሬሽን ተልዕኮውን ለማሳካት የሚያስችሉ የተልእኮ ግልፅነት የመፍጠር፣ የኮርፖሬት ቢዝነስ አስተሳሰብ የመገንባት፣ አገልግሎት የሚሰጡ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ የማስገባት፣ የግሪድ ሞደርናይዜሽን፣ የሀብት አስተዳደርና የፋይናንስ ስርዓቱን የማዘመን የለውጥ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውም በውይይቱ ተብራርቷል።

    በ2002 ዓ.ም. ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የተከዜ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የደጋን ቅርፅ ያለው ሲሆን በግንባታው ዘርፍ በአፍሪካ ጉልህ የኢንጂነሪንግና ዲዛይን ፋይዳ ካላቸው አስር የውሃ ኃይል ማመንጫዎች ውስጥ አንዱ ያደርገዋል።

    185 ሜትር ከፍታና 710 ሜትር ርዝመት ያለው የተከዜ ግድብ 300 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን በዓመት በአማካይ 1431 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ያመነጫል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶር አብርሃም በላይ


    Anonymous
    Inactive

    ተማሪዎች እና መምህራን 123ኛውን የአድዋን ድል እየዘከሩ ነው
    —–

    ‹‹3ቱ የካቲቶች›› የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ እስከ የካቲት 30 ይቆያል

    የ‹መለከት አፀደ ሕጻናትና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት› ተማሪዎች በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥር በሚገኘው በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል በመገኘት 123ኛውን የአድዋን ድል እየዘከሩ ነው፡፡

    የአድዋን ድል በማስመልከትም ያዘጋጁትን ቴአትር አቅርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የልጆች ክፍል አዘጋጆች በቦታው ተገኝተው የተማሪዎቹን ጉብኝትና ቴአትር ቀረጻ አድርገዋል፡፡

    ሕጻናቱ ባቀረቡት ቴአትር ላይ አገር ስለመውደድ፣ ስለፍቅር እና የፆታ እኩልነትን አስመልክተው አስተማሪ ጭብጦችን አንስተዋል፡፡

    ‹‹3ቱ የካቲቶች›› የተሰኘው የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ እስከ የካቲት 30 ስለሚቆይ ሁላችሁም እንድትጎበኙት ተጋብዛችኋል፡፡

    —————————-
    አድራሻች፡- የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ ከፒያሳ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በሚወስደው መንገድ፣ ሆስፒታሉ አካባቢ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጉለሌ ቅርንጫፍን አልፎ በሚገኘው ቅያስ 500 ሜትር ገባ ብሎ፡፡

    ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ

    Semonegna
    Keymaster

    ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ከየካቲት 10 ቀን 2003 (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችንና አባል ለመሆን ብቁ የሚያድርጓትን የማሻሻያ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የሚያስችላትን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየሠራች መሆኑን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የባለ ብዙ ዘርፍ የንግድ ግንኙነትና ድርድር ዳይሬክተር አቶ ሙሴ ምንዳዬ የዓለም ባንክ የንግድና ክልላዊ ትብብር ዳይሬክተር ጋር ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሂደትን እና የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና ስምምነትን ለማጽደቅ እያደረገች ባለው እንቅስቃሴ ዙሪያ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተወያዩበት ወቅት ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እና በድርድሩ ሂደት የሚገጥሟትን ችግሮች ተቋቁማ ወደ ድርጅቱ እንድትቀላቀል ለማድረግ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

    ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ብታስመዘግብም የግል ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስት ያለው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው

    አቶ ሙሴ አያይዘው በአሁኑ ወቅት መንግስት በተለይም በአገልግሎት ንግድ ሰጭ ተቋማት ላይ እየሠራቸው ያሉት የማሻሻል (ሪፎርም) ሥራዎች እና የቴሌኮም ድርጅትን የቁጥጥር/ርጉላቶሬ/ መስሪያ ቤት የተለያዩ ዘርፎች ለግሉ ሴክተር ለማስተላለፍ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁ ሀገሪቷ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገውን ድርድር ሊያግዝ የሚችል መልካም አጋጣሚ ነው ያሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም. 4ኛውን የሥራ ቡድን ስብሰባ ለማካሄድ የተለያዩ ዶክመንቶችን የማዘጋጀት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

    በዓለም ባንክ የማክሮ፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ዳይሬክተር ወ/ሮ ካሮሊን ፍረንድ (Caroline Freund) በበኩላቸው ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በዓለም የንግድ ድርጅት ድርድር እና በአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ዙሪያ የሚሠራቸው ሥራዎች መልካም መሆናቸውን ገልጸው ወደፊት ለሚደረጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድርኮች እንዲሁም ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ ቢሮና መሠረተ- ልማት እንዲኖር ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

    እ.ኤ.አ. ጥር 1 ቀን 1995 በ124 አገራት የአባልነት ፊርማ የተመሠረተውን የዓለም ንግድ ድርጅት (World Trade Organization)፣ በአሁኑ ሰዓት ዋና መቀመጫውን ጄኔቭ ከተማ፣ ስዊዘርላን አድርጎ 164 አገራትንም በአባልነት አቅፏል።ኢትዮጵያም የዚህ ድርጅት አባል ለመሆን ከየካቲት 10 ቀን 2003 (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችንና አባል ለመሆን ብቁ የሚያድርጓትን የማሻሻያ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች።

    ምንጭ፦ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    የዓለም ንግድ ድርጅት


    Anonymous
    Inactive

    100 የአሊያንስ ትራንስፖርት አውቶቢሶች ከስራ ታገዱ
    —–
    አንድ መቶ ያህል የአሊያንስ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ንብረት የሆኑ የከተማ አውቶቡሶች ከስራ ታገዱ፡፡ አውቶቡሶቹ የታገዱት በባንክ የብድር አከፋፈል ስርዓት ላይ በተፈጠረ አለመግባባት እንደሆነም ታውቋል፡፡

    ባለፈው ረቡዕ ከሰዓት በኋላ የአሊያንስ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢና አባላት በጌትፋም ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አክሲዮን ማህበሩ በገባው ውል መሰረት ብድሩን በየወሩ ለመክፈል በአገሪቱ ላይ የተፈጠረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ አውቶቡሶቹ የሚያስፈልጋቸውን የመለዋወጫ እቃ ከውጭ ለማስመጣት በነበረ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና ተያያዥ ችግሮች እንቅፋት በመሆናቸው በውል መሰረት መክፈል አለመቻላቸውንና በዚህም ምክንያት አበዳሪያቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቶዎቹ አውቶቡሶች ስምሪት ላይ እንዳይውል ከጥር 28 ጀምሮ እግድ ማውጣቱን ተናግረዋል፡፡

    ከ2500 በላይ ባለ አክሲዮኖች እና ከ600 በላይ ሰራተኞች ያሉት አሊያንስ ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር፤ በ2005 ዓ.ም 25 ያህል አውቶቡሶችን በመግዛት የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የገለፁት የቦርድ ሰብሳቢው ዶ/ር አዲል አብደላ፣ መንግሥት በ2008 ዓ.ም 500 ያህል የከተማ አውቶቡሶች በግል አንቀሳቃሾች ወደ አዲስ አበባ ገብተው በአዲስ አበባና በዙሪያው ላሉ ከተሞች አገልግሎት እንዲሰጡ የቀረጥ ነፃና የብድር አቅርቦት ባመቻቸበት ወቅት 300 ያህል አውቶቡሶች እንዲገዙ ከመንግስት ፈቃድ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡

    ይሁን እንጂ በወቅቱ የነበራቸው አቅም ከ100 አውቶቡሶች በላይ ማስመጣት ባለመቻሉ መቶዎቹን ብቻ በብድር ገዝተው ወደስራ እንዲሰማሩ መደረጉን ገልፀው ባንኩ የ6 ወር የእፎይታ ጊዜ ቢሰጣቸውም አውቶቡሶቹ ወደ አገር ገብተው ከማለቃቸው በፊት የእፎይታ ጊዜው እንዳለቀና አውቶቡሶቹ በቅጡ ስራ ሳይጀምሩ ባንኩ ብድር ክፈሉ በማለቱ ከሌሎች በጀቶችም ከሌላም እያመጡ መክፈል መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
    “መቶዎቹ አውቶቡሶች የመንግስት ፕሮጀክቶችና ራሱ መንግስት ታሪፍ ያወጣላቸው እንጂ በንግድ ታሪፍ የሚሰሩ አይደሉም” ያሉት የአክሲዮን ማህበሩ የቦርድ አባላት በአሁን ጊዜ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ለባንኩ ደብዳቤ በመፃፍ፣ ጉዳዩን የሚያጣራ ኮሚቴ በማቋቋምና ራሳቸውም ከባንኩ ጋር በመወያየት ጉዳዩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

    ምንጭ፦ አዲስ አድማስ ጋዜጣ

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና የውጪ ምንዛሬ እጥረት ለሀገር በቀል የመድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ አምራቾች እውነተኛ ፈተና መሆን አለመሆናቸው በገለልተኛ አካል ሊጠና ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ባለድርሻ አካላት ተናገሩ።

    ጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም ከሀገር ውስጥ አምራቾች በተደረገው ውይይት የ6 ወር የመድኃኒት አቅርቦት አፈፃፀም 25% መሆኑን ተከትሎ ለአቅርቦቱ ዝቅተኛ አፈፃፀም በተደጋጋሚ በምክንያትነት የሚሰጡት የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በገለልተኛ አካል ተጠንቶ ድጋፍ የሚያስፈልገውን በመደገፍ የሚያጭበረብረውን በማጣራት እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል ሲሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ገልፀዋል።

    ኤጀንሲው ለሀገር ውስጥ አምራቾች በቅድሚያ ክፍያ እንዲሁም 25 በመቶ ጨረታ ላይ እንዲወዳደሩ እንደሚደግፉ የተጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ አሁንም አምራቾች መድኃኒቶችን በበቂ መጠን ጥራት ማቅረብ አለመቻላቸው አጠራጣሪ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

    ◌ News: Humanwell Healthcare Group inaugurates Humanwell Pharmaceutical Ethiopia PLC in Chacha town

    እንደአስተያት ሰጪዎች ገለጻ ሀገር በቀል አምራቾች ኤጀንሲው የሚሰጣቸው የቅድሚያ ክፍያ ሒሳብ በአግባቡ ቃላቸውን ለመተግበር እያዋሉት መሆኑ ወይም ሌላ ዓላማ መዋሉ ሊጠና ይገባል ብለዋል። አክለውም የሚሰጠውን ገንዘብ ለሌላ የግል ንግድ እየተጠቀሙበት መሆኑን ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልጸዋል።

    በተያያዘ ዜና የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች በአዳማ ከተማ የግማሽ ዓመት አቅድ አፈጻጸም ላይ እንዳሉት ሀገር በቀል የመድኃኒት አምራቾች ኤጀንሲው በሚያቀርበው ገንዝብ ለግል አቅራቢዎች ትርፍ ለማሳደድ እንደሚያውሉት መረጃ አለ ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም የሚደረገው ድጋፍ በአግባቡ የመያጠቀሙበት ከሆነ በሂደት እየለዩ እርምጃ ለወሰድ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

    ከዚሁ ውይይት በተጨማሪ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ የጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል አቅርቦቱን የበለጠ ለማሻሻል ብቻውን መስራቱ ውጤታማ ሊያደርገው እንደማይችል የኤጀንሲው የግዥ ትንበያና ገበያ ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብይ ክፍሎም አብራርተው የሀገር ውስጥ አምራቾቹ ሊያስቡበት እንደሚገባም አቶ አብይ አክለው ገልፀዋል።

    ◌ News: SanSheng Pharmaceutical PLC inaugurated in the Eastern Industry Zone in Dukem, Ethiopia

    የአገር ውስጥ አምራቾች አፈፃፀማቸውን መፈተሽ እንዳለባቸውና አፈፃፀማቸው ዝቅ ባለ ቁጥር በመድኃኒት እጦት የሚያልፈውን የሰው ሕይወት ሊያስቡ እንደሚገባ የመድኃኒትና የህክምና መሣርያዎች ግዢ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ጎይቶም ጊጋር ገልፀዋል።

    የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ሣሙኤል ኃይሉ በበኩላቸው በአሁኑ ሠዓት የመድኃኒት እጥረት እንደ ቀልድ የሚታይ ጉዳይ አይደለም ብለዋል።

    አቅርቦቱ ዝቅ እንዲል ካደረጉ ምክንያቶች መካከል የውጭ ምንዛሬና የመብራት መቆራረጥ በዋናነት በውይይቱ የተጠቀሱ ሲሆን ኤጀንሲው ይህን ለማስተካከል አፈፃፀማቸውን ለመለካት የሚያስችል ነጥቦችን የያዘ ረቂቅ ሰነድ (KPI) ቀርቦ የጋራ ማድረግ ተችሏል።

    በመጨረሻም ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ ባንክ፣ የኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መገኘታቸው በቀጣይ ችግሩን በመቅረፍ የሕብረተሠቡን የመድኃኒት ፍላጎት ለማሟላት ያስችላል ብለዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ


    Semonegna
    Keymaster

    መቀዛቀዝ የታየበትን የህዝባዊ ተሣትፎ ለማነቃቃት የተለያዩ መድረኮችን በቀጣይነት እንደሚያዘጋጅ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሣትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ገልጸዋል።

    አዲስ አበባ (ዋልታ)– የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሣትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ባለፉት 6 ወራት 484 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታውቋል።

    ጽህፈት ቤቱ በበጀት ዓመቱ እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ ሲሆን በቀጣይ የተጠናከረ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንደሚንቀሳቀስ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር እና የህዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ባዘጋጁት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጿል።

    መቀዛቀዝ የታየበትን የህዝባዊ ተሣትፎ ለማነቃቃት የተለያዩ መድረኮችን በቀጣይነት እንደሚያዘጋጅ የህዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ገልጸዋል።

    ቪዲዮ፦ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ድጋፍ ዙሪያ ከኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት ጋር የተደረገው ውይይት

    ከዚሁ ጋር በተያያዘም ጥር 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ከንቅናቄ መድረኮች አንዱ የሆነው ሁሉም የዳያስፖራ አካላት የሚገኙበት መድረክ በራስ ሆቴል መድረክ አዘጋጅቶ ከተለያዩ ሀገራት ከመጡ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ጋር በቀጣይነት እና በተሻለ ሁኔታ ግድቡን ሊደግፉ በሚችሉበት መንገድ ላይ ውይይት አድርጓል።

    ዳያስፖራው ባለፉት ሰባት ዓመታት 46 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን ሃገሪቱ ካላት ዲያስፖራ ቁጥር አንጻር ድጋፉ አነስተኛ መሆኑ ተጠቁሟል። በመሆኑም በተለይም በምዕራብ አውሮፓ የሚገኙ ዲያስፖራዎች የሚጠበቅባቸውን ያህል ድጋፍ ስላላደረጉ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ የዳያስፖራ ማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ስዩም አስታውቋል።

    ለዚህም ዳያስፖራው ለህዳሴው ግድብ አዲስ የዳያስፖራ ተሳትፎ ንቅናቄ ለመፍጠር እና በዳያስፖራው ዘንድ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ያለውን ብዥታ ለማጥራት መድረክ ፈጥሮ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ እንደነበርና፣ የራስ ሆቴሉ ውይይትም የዚሁ ዋነኛ አካል እንደነበር ተገልጿል። በተመሳሳይ ሁኔታም በዕለቱ የተለያዩ የህዝብ አደረጃጀቶች የሚሳተፉበት የንቅናቄ መድረክ በካፒታል ሆቴል ተካሂዶ ነበር።

    ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሁለት ዓመት በኋላ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር የተገለጸ ሲሆን ከአራት ዓመት በኋላ ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

    ምንጭ፦ ዋልታ ሚዲያ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦  

    ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ


Viewing 15 results - 31 through 45 (of 49 total)