-
Search Results
-
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ ደንበኞቹ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳባቸው በባንክ እንዲከፍሉ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የተፈፀመው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባንክ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ደረጄ ፉፋ አማካኝነት ነው።
◌ ኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ተሸካሚ ላይ የተዘረጋውን ገመድ በጋራ ለመጠቀም ተስማሙ
የመግባቢያ ስምምነቱ ዋና ዓላማ በመጀመሪያው ምእራፍ 27 ሺህ የሚሆኑ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀሙ እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳባቸውን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል እንዲከፍሉ ለማስቻል እና በቀጣይም በአፈጻጸም ሂደቱ የተገኙ ተሞክሮዎችን በማካተት በመላ ሀገሪቱ ያሉ ደንበኞች ላይም ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር አስታውቀዋል።
ተቋሙ ቀድሞ ይጠቀምበት የነበርውን የፍጆታ ሂሳብ አሰባሰብ ስርዓት በመቀየር፣ ቀልጣፋና በዘመናዊ ቴክኖሎጅ የታገዘ አገልግሎት ለደንበኞቹ ለመስጠት እንደሚስያችለው አክለው ገልፀዋል። ይህም በመሆኑ ተቋሙ፣ ባንኩና ደንበኞች የፍጆታ ሂሳብ ለመክፍል ይፈጠር የነበረውን የገንዘብና የጉልበት ብክነት በከፍተኛ ደረጃ ስለሚቀንሰው፤ ሦስቱም አካላት ተጠቃሚ ይሆናሉ ሲሉ ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የተናገሩት።
◌ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ዕውቀቶችና ልምዶች የተገኙበትና በምስራቅ አፍሪካ በርዝመት ቀዳሚውን ስፍራ የያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ህንጻ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባንክ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ደረጄ ፉፋ በበኩላቸው፥ ዘመናዊ የክፍያ ስርዓት መዘርጋቱ ደንበኞች ሳይጉላሉ ካሉበት ስፍራ ሆነው ክፍያ በባንኩ አማካኝነት በቀላሉ ለመክፍል እንደሚያስችላቸው ገልፀዋል። ሲያጋጥሙ የነበሩ የአከፋፈል ስርዓት ችግሮችን እንዲቀርፍ ያስችላል፤ ደንበኞችም ያጠፉት የነበረውን ጊዜና የሚያጋጥማቸው ውጣ ውረድ ይቀንስላቸዋል ሲሉ ነው አክለው የተናገሩት።
በስምምነቱ መሠረት እነዚህ ደንበኞች በቂ ግንዛቤ በተለያዩ አማራጮች ካገኙ በኋላ በያዝነው ዓመት ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ እንዲሁም የዚህን ጅምር ሥራ ውጤታማነት ከታየ በኋላ ሁሉም ደንበኞች በተመሳሳይ መልኩ ክፍያ እንዲፈፅሙ በቀጣይ አንደሚደረግ ተገልጿል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- ቤልካሽ ኢትዮጵያ ሄሎማርኬት እና ሄሎሾፕ የተሰኙ ሁለት የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ገፆችን ሊያስጀምር ነው
- የጣልያን መንግስት አዲስ አበባን ከምፅዋ የሚያገናኘውን የባቡር ምስመር ፕሮጀክት ጥናት ወጪ ለመሸፈን ተስማማ
- አዳማ ከተማ ውስጥ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው እና ጥቅም ላይ የማይውሉ መድኃኒቶችን ማስወገጃ ማዕከል ተገነባ
- ኬር ኢትዮጵያ በ7 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ወጭ ያስገነባውን የምርምርና የስልጠና ማዕከል ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስረከበ
- የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራዎችን በአዲስ ኃይል ወደቀድሞ ፍጥነት ለመመለስ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ለተቀናጀ የግብርና-ኢንዱስትሪ ፓርኮች ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ15 ሚሊዮን የአሜርካ ዶላር (420 ሚሊዮን ብር) ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ኢትዮጵያ እና ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማቶችን በገንዘብ የሚደግፈው የአፍሪካ ልማት ባንክ ለተቀናጀ የግብርና-ኢንዱስትሪ ፓርኮች ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ15 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራረሙ።
የፋይናንስ ስምምነቱን የፈረሙት በኢትዮጵያ በኩል የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ሲሆኑ በአፍሪካ ልማት ባንክ በኩል ደግሞ የባንኩ የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አብዱል ካማራ (ዶ/ር) ናቸው።
ዋና መቀመጫነቱ በአቢጃን ከተማ (አይቮሪኮስት) የሆነው የአፍሪካ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው በኢትዮጵያ በግብርና – ኢንዱስትሪ (agro-industry) ዙርያ እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ነው። ድጋፉ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ እና በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስታት ስር እየተገነቡ ላሉ አራት ኢንዱስትሪ ፓርኮችን እንደሚውል ተገልፃል።
ፕሮጀክቱ ሦስት ዋና ዋና ክፍሎችን ለመደገፍ የሚውል ሲሆን በኢንዱስትሪ ፓርኮች መሠረተ-ልማትን ለማሳደግ፣ በዘላቂነት የግብርና-ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ እንዲኖር ለማሰቻል እና በፕሮጀክት አስተዳደርና አተገባበር ላይ ለአራቱ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት እና ለንግድ እና ኢንዱስትሪ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለማከናውን ይውላል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በፊርማ ሥነ-ሥርዓት ወቅት እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካለቸው የአፍሪካ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የተለያዩ መርሀ ግብሮችን ነድፋ እየተንቀሳቀሰች የምትገኝ ሲሆን፥ በተለይም ሁሉን አቀፍ እድገት እንዲኖር ማስቻል፣ ድህነት ቅነሳ እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር የማደረግ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ ልማት በስፋት ለመግባት እያደረገች ላለው ጥረት የአፍሪካ ልማት ባንክ እያደረገው ላለው ድጋፍ ምስጋናቸው አቅርበዋል።ባለፈው ወር የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ የዘረጋቸውን መሠረታዊ አገልግሎቶች ማሻሻያ መርሀ ግብር (Basic Services Transformation Program) ለመደገፍ 123 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል።
ምንጭ፦ የገንዘብ ሚኒስቴር
——
ተጨማሪ ዜናዎች፦- አንበሳ የከተማ አውቶቡስ በአንዳንድ አካባቢዎች አገልግሎቱን በማቋረጡ ተገልጋዮች ለችግር ተዳርገዋል
- የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የፎረንሲክ ምርመራ በጋራ ለማከናወን ተስማሙ
- የጅማ–አጋሮ–ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በተገኙበት በይፋ ተጀመረ
- ሐረር የሚኖሩ የጉራጌ ህብረተሰብ አባላት በመስቃንና ማረቆ ወረዳ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ100,000 ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ
- የዱባይ አቡዳቢው ኤግል ሒልስ በአዲስ አበባ ለገሀር የተቀናጀ የመኖሪያ፣ አገልግሎት መስጫና የመዝናኛ ስፍራ ሥራውን ጀመረ
አዲስ አባባ – የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም በይፋ ገንዘብ መሰብሰብ መጀመሩን የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሁለት ወር በፊት ለኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ የትረስት ፈንዱ እንዲቋቋም ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበው እንደነበረ ይታወሳል።
በይፋ የተቋቋመው ትረስት ፈንድ ጥቅምት 12 ቀን ገንዘብ መሰብሰብ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አማካሪ ምክር ቤት ተቋቁሞ በይፋ ሥራ እንዲጀምር ላደረጉት ትጋትና ጥረት አባላቱን በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም አመስግነዋል።
በአሁኑ ወቅት በትረስት ፈንዱ ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ እንዳለና ከዚህም በኋላ ብዙ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።
———————————————-
———————————————-
የትረስት ፈንድ አማካሪ ምክር ቤቱ የፈንዱን አቅምና ውጤታማነት ለማሻሻል በትጋት መሥራት እንዳለበትም ዶክተር አብይ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ የሚሰጡትን የተወሰነ ገንዝብ በአንድ ወይም በሁለት ጊዜ ጠቅልለው በመክፈል በጣም ወሳኝ ለሚባሉ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገውን ድጋፍ እንዲያፋጥኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።
በቀን ከአንድ ዶላር በላይ መስጠት ለሚችሉ ዜጎች ድጋፋቸውን በፍጥነት እንዲያድርጉና ዓለም አቀፉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ ከትረስት ፈንድ ምክር ቤቱ ጋር ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ዶክተር አብይ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የዳይሬክተሮች ቦርድ የተመረጡ ሲሆን ስም ዝርዝራቸው በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግም መጠቆማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የላከው መግለጫ ያስረዳል።
ፈንዱ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማቀናጀትና የልገሳውን ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚያስችል እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን የባንክ ሒሳብ ቁጥሩም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000255726725 (አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ) ነው። ከዚህ የባንክ የሒሳብ ቁጥር በተጨማሪ ተቋሙ በኢንተርኔትም ገንዘብ እንደሚያሰባስብና ኦፊሴላዊ ድረ ገጹም “https://www.ethiopiatrustfund.org” እንደሆነ ክስር በተመለከተው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ባደረጉት ንግግር ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።
በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በቀን ቢያንስ 1 የአሜሪካ ዶላር በመለገስ ለተለያዩ የልማት ሥራዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቃቸው የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ተቋም ምክር ሰጪ ካውንስል መግለጫ (ጥቅምት 10 ቀን 2011 ዓ.ም)
የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዳያስፖራ ፈንድ ተቋም ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም (October 22, 2018) ለሕዝብ መዋጮ መሰብሰቢያ ይከፈታል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ፈንድ ተቋም ምክር ሰጪ ካውንስል (ኢዲቲኤፍ) ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም (October 22, 2018) ለሕዝብ መዋጮ መሰብሰቢያ ያዘጋጀዉን ዝግጅት ለሕዝብ ይፋ አድርጎ ሥራዉን በኦፊሴላዊ ድረ-ገጽ https://www.ethiopiatrustfund.org እንደሚጀምር በደስታ ያስታዉቃል።
ባለፉት ሳምንታት ካውንስሉ የዲያስፖራ ፈንዱን ሕጋዊና መንግስታዊ ደንቦችን በተከተለ መንገድ ፈንዱን ለመመስረት በትጋት ሠርቷል።
የፈንዱ ካውንስል ምክር ቤት በዓለም ያሉ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ በቀን 1 ዶላር ለህዝብ አርዳታ አዋጡ ያሉትን ጥሪ ተመልከቶ መዋጮ ለመስጠትና ፈንዱን በስራ ላይ ለማዋል ከፍ ያለ ጉጉት አንዳላቸው ይገነዘባል።
ይህን ፍላጎት ለሟሟላትና ፈንዱን በሥነ ስርዓት ሥራ ማስጀመር ምክር ቤቱ ለትርፍ ያልተቋቋመ የበጎ አድራጎት ድርጅት ማቋቋም የባንክ ሂሳብ ቁጥር መክፈት ከኢንተርኔት ክፍያ ስርዓቶች እና ሌሎች የፋይናንስ መድረኮችን ጋር መደራደር አና የተለያዩ ደንቦችን ሟላትና አስተዳደራዊ እና የአፈፃፀም ሂደቶችን ለመቆጣጠር እና ግልጽነትን ለማረጋገጥ ምክር ቤቱ እነዚህን ሥራዎች በፍጥነት መወጣት ችሏል።
ካውንስሉ ዓለምአቀፍ ዲያስፖራዎች ማኅበረሰቦች ለፈንዱ ላሳዩት መታገስና የማያወላዉል ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋናዉን ያቀርባል።
ካውንስሉ የኢትዮጵያ ዲያስፖራን የኢትዮጵያ ወዳጆች እና ሌሎች ነፃነት ዲሞክራሲ ሰብአዊ መብቶችን እና መልካም አስተዳደርን በኢትዮጵያ ማበልፀግ የሚፈልጉን ሁሉ በቀን 1 ዶላር መዋጮቻቸዉን በአንድ ጊዜ በጠቅላላው 365 የአሜሪካን ዶላር እንዲከፍሉ ባክብሮት ይጠይቃል። ይህንም በማድረግ አስፈላጊ ፕሮጀክቶችን ባፋጣኝ ለማስጀመር ይቻላል።
ስለ ፈንዱ ለመማር እና መዋጮ ለማድረግ ወድዚህ ድህረ ገፅ ይሂዱ (ይጫኑ) https://www.ethiopiatrustfund.org/
ልዩ ማስታወሻ – የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በሚል ስም አንዳንድ በግል የተደራጁ ሰዎች ገንዘብ ለመሰብሰብ ጥረት እንደሚያደርጉ የፈንዱ ምክር ቤት ይረዳል። ነገር ግን ኦፊሴላዊ የሆነው በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እ.ኤ.አ. ነሐሴ 9, 2018 በካውንስሉ የተቋቋመው ኤድቲኤ (EDTF) ብቸኛና መደበኛ በሕግ የታወቀው ነው።
ሱማሌላንድ ውስጥ የሚገኘው የበርበራ ወደብ በባለቤትነት ደረጃ የኤምሬቱ ዲፒ ወርልድ 51 በመቶ፣ የሶማሌላንድ አስተዳደር 30 በመቶ እና የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ 19 በመቶ ድርሻ አላቸው።
አዲስ አበባ (ሶማሌላንድ ሰን/ ኢዜአ) – ኢትዮጵያ 19 በመቶ ባለድርሻ የሆነችበት የሶማሌላንድ የበርበራ ወደብ ግንባታ ተጀመረ።
ጥቅምት 1 ቀን 2011 ዓ.ም የግንባታ ማስጀመር ሥነ ስርዓቱ ሲካሄድ በሥነ ስርዓቱ ላይ የሶማሌላንድ አስተዳድር እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች ተካፍለዋል።
መቀመጫውን ዱባይ ያደረገው ዲፒ ወርልድ (DP World) የተባለው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (UAE) ኩባንያ በ420 ሚሊዮን ዶላር የበርበራ ወደብ ግንባታን ለማካሄድ ውል ገብቶ ሥራውን ጀምሯል።
በስምምነቱ መሠረት በወደቡ ግንባታ የኤምሬቱ ዲፒ ወርልድ 51 በመቶ፣ የሶማሌላንድ አስተዳደር 30 በመቶ እና የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ 19 በመቶ ድርሻ ይዘዋል ተብሏል።
ከግንባታ በኋላ የሶማሌላንድ መንግስት፣ የኢትዮጵያ መንግስት እና ዲፒ የበርበራ ወደብ ላይ ያላቸው ውል ለ30 ዓመት የሚቆይ መሆኑንም ተመልክቷል።
የሶማሌ ላንድ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ (Muse Bihi Abdi) በሥነ ስርዓቱ ላይ እደንደተናገሩት የበርበራ ወደብ ግንባታ እውን መሆን የሶማሌላንድ ኢኮኖሚን ከማነቃቃት ባሻገር ለቀጠናው የንግድና ኢኮኖሚ ትስርስር ፋይዳው የጎላ ነው።
በተያያዘ ዜና ሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ የሚገነባው የኢትዮጵያ ንግድ ሎጂስቲክስ ፕሮጀክት የዲዛይን ጥናት እየተጠናቀቀ መሆኑን የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን ገለጸ።
ባለስልጣኑ አስመጪዎች፣ ላኪዎችና የተለያዩ ደንበኞች በሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ የሚደርስባቸውን መጉላላት ለመቀነስ አሰራሩን ዘመናዊ ለማድረግ የሞጆ ሎጂስቲክስ ማዕከልን ሊገነባ መሆኑ ይታወቃል።
ተመሳሳይ ዜና፦ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ የአሰብ እና የምጽዋ ወደቦችን መጠቀም ለመጀመር ዝግጅቷን እያጠናቀቀች ነው
በዚህም ባለስልጣኑ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ሐምሌ 2017 ከዓለም ባንክ የዲዛይን ፈቃድ አግኝቶ በመጀመሪያ የዲዛይን ጥናቱ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው።
በማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን የኢትዮጵያ ንግድ ሎጂስቲክስ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ዶክተር መንግስት ኃይለማርያም እንዳሉት፤ ግንባታው የሚከናወነው ከዓለም ባንክ በተገኘ 150 ሚሊዮን ዶላር ነው። የዓለም ባንክ ይህንን ገንዘብ ለኢትዮጵያ በክሬዲት መልክ የሰጠው እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር መጋቢት 31 ቀን 2017 ነበር።
ግንባታው እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2022 እንደሚጠናቀቅና የዲዛይን ጥናቱም በተያዘለት የጊዜ ገደብ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዲዛይን ጥናቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ ዓለም ባንክን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከተደረገበት በኋላ ሁለተኛው የግንባታ ምዕራፍ ይጀምራል ብለዋል።
ግንባታው ሲጠናቀቅም በሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ ያለውን አሰራር ወደ ኤሌክትሮኒክስ በመቀየር ቀልጣፋ፣ ፈጣንና ዘመናዊ አሠራር ይኖረዋል ነው ያሉት።
የሞጆ ደረቅ ወደብ የመሰረተ ልማት አቅርቦት እጥረት፣ የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ችግርና የተሟላ የኤሌክትሮኒክስ ስርዓት ችግር እንዳለበት ገልጸዋል።
በመሆኑም የሚገነባው የኢትዮጵያ ንግድ ሎጂስቲክስ ፕሮጀክት እነዚሀን ችግሮች በዘመናዊና በተቀናጀ መንገድ ማከናወን ያስችላል ብለዋል።
ምንጭ፦ ሶማሌላንድ ሰን እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)