Search Results for 'ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ'

Home Forums Search Search Results for 'ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ'

Viewing 4 results - 16 through 19 (of 19 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    ጅማ ዩኒቨርሲቲ ባስገነባው የህክምና ማዕከል ምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ ለዓመታት ያስተማራቸውን 331 የህክምና ዕጩ ምሩቃን እና በተለያዩ መስኮች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ 2ሺህ የድህረ ምረቃ መርሀ ግብር ተማሪዎችን ያስመርቃል።

    ጅማ (ሰሞነኛ)– ጅማ ዩኒቨርሲቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የፌድራልና የክልል መንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የህክምና ማዕከሉን ኅዳር 29 ቀን 2011 ዓም እንደሚያስመርቅ ተዘግቧል።

    የህክምና ማዕከሉ 800 (ስምንት መቶ) አልጋዎች ያሉት ሲሆን፥ በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል ከ20 ሚሊየን በላይ ሰዎች የህክምና አገልግፍሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ተብሏል። ማዕከሉ እንደ ደቡብ ሱዳን ላሉ ጎረቤት ሀገራትም አገልግሎት ለመስጠት ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ መሆኑን ተነግሯል።

    ዩንቨርሲቲው ያስገነባው ይህ የህክምና ማዕከል በህክምና እና ጤናው ዘርፍ የምርምር፣ የማስተማሪያ፣ እንዲሁም የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል መሆኑም ነው የተገለጸው። በዚህም ጅማ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሲነጻጸር ልቆ የሚታይበትን የማኅበረሰብ ተኮር (community-based) ትምህርትና ምርምር ይበልጥ ያገለብትለታል ተብሎ ይታመናል።

    Ethio-American Doctors Group (EADG): Building a regional healthcare system & medical tourism

    ዩንቨርሲቲው በህክምና ማዕከሉ የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ ለዓመታት ያስተማራቸውን 331 የህክምና ዕጩ ምሩቃን እና በተለያዩ መስኮች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ 2ሺህ የድህረ ምረቃ መርሀ ግብር ተማሪዎችን እንደሚያስመርቅም ታውቋል።

    በተመሳሳይ መልኩ ዩንቨርሲቲው ያስገነባው 40 ሺህ ያህል ተመልካቾችን ማስተናገድ የሚችለው ስታዲየም፣ ሲቭክ አዳራሽ፣ መንገዶችና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች ይመረቃሉ ተብሏል። የሲቪክ አደራሹ በርካታ ተሰብሳቢዎችን በአንዴ የሚያስተናግድና የተለያዩ ኮንፈረንሶችን በተመሳሳይ ጊዜ ለማካሄድ የሚያስችሉ የተለያዩ ክፍሎች እንዳሉትም ተነግሯል። ከዚህ ጋር ተያይዞ እንደተዘገበው ይህ የሲቭክ አዳራሽ ከተማዋን የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ ስለመሆኑም ነው የተገለጸው።

    ምንጭ፦ ኢቢሲ / ኤፍ.ቢ.ሲ. / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    ጅማ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ማዕከል


    Semonegna
    Keymaster

    ጂንካ ዩኒቨርሲቲ እስካሁን ድረስ በ14 የትምህርት ክፍሎችን በመክፈት ተማሪዎችን እያስተማረ መሆኑንና የኒቨርሲቲው የትምህርት ክፍሎቹን ወደ 41 ለማሳደግ ዕቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑንም የኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ተናግረዋል።

    ጂንካ፣ ደቡብ ኦሞ ዞን (ዋልታ) – ጂንካ ዩኒቨርሲቲ በ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን 1ሺ 500 አዳዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

    የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ገብሬ ይንቲሶ ለዋልታ እንደገለጹት በዘንድሮ የበጀት ዓመት እና የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን ቅበላ የተሳካ ለማድረግ በሁለት ዘርፍ የተከፈሉ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ።

    የኒቨርሲቲው የዘንድሮ ዓመትን የመማርና ማስተማር ሂደቱን ለማስጀመር የመምህራን ዝግጅትን ጨምሮ የተማሪዎች የአገልግሎት መስጪያ ተቋማት የሆኑት ቤተ መጽሐፍትና የመመዝገቢያ ሥፍራዎች በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ የማስቻል ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል ፕሬዚደንቱ።

    በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት መስጪያ ህንጻዎች ግንባታ መዘግየታቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር ገብሬ አዳዲስ ተማሪዎችን በጊዚያዊ የመጠሊያ ህንጻዎች እንዲገቡ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል። የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮ ዓመት የተማሪዎች የመግቢያ ቀንም እስካሁን አለመቆረጡን ፕሬዚደንቱ አያይዘው ገልጸዋል።

    ጂንካ ዩኒቨርሲቲ እስካሁን ድረስ በ14 የትምህርት ክፍሎችን በመክፈት ተማሪዎችን እያስተማረ መሆኑንና የኒቨርሲቲው የትምህርት ክፍሎቹን ወደ 41 ለማሳደግ ዕቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑንም ፕሬዚደንቱ አብራርተዋል።

    አዳዲስ የሚከፈቱት የትምህርት ዘርፎችም በደቡብ ኦሞ ዞን የሚታዩ የሙያ ክፍተቶችን ለመሙላት በሚያስችል መልኩ የሚከፈቱ መሆኑም ተገልጿል።

    የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ዓመት 1ሺህ 100 ያህል ተማሪዎችን የተቀበለ ሲሆን በዘንድሮ ዓመት 1ሺ500 አዳዲስ ተማሪዎችን በመቀበል በአጠቃላይ ተማሪዎችን 2ሺህ 600 ለማድረስ እየሠራ ይገኛል።

    በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል (ደብብሕክ)፣ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ጂንካ የሚገኘው ጂንካ ዩኒቨርሲቲ በ2010 ዓ.ም. በትምህርት ሚኒስቴር ስር ከተከፈቱት 11 አዳዲስ የሕዝብ ዩኒቨርሲቲዎች (public universities) አንዱ ነው።

    ምንጭ፦ ዋልታ

    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    ጂንካ ዩኒቨርሲቲ

     

    Semonegna
    Keymaster

    ዩኒቨርሲቲው ለሠራተኞቹ ያስተላለፋቸው መኖርያ ቤቶች ስቱዲዮ፣ ባለ አንድ መኝታ፣ ባለ ሁለት መኝታ እና ባለ ሦስት መኝታ ሲሆኑ ሠራተኞቹ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሠራተኝነት እስካሉ ድረስ ቤቶቹን በነጻ ይገለገሉባቸዋል።

    ነቀምቴ (ኢዜአ) – ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸውን መኖርያ ቤቶች ለሠራተኞቹ አስረከበ።

    የዩኒቨርሲቲው የመሠረተ ልማትና የሕንፃ ግንባታ ዳይሬክተር ዶክተር ደረጄ አደባ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የመኖርያ ቤት ለሌላቸው ሠራተኞቹ የቤት ባለቤት ለማድረግ ያስገነባቸውን 134 መኖሪያ ቤቶች ትናንት አስረክቧል። ለመኖሪያ ቤቶቹ ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም ገልጸዋል።

    ከዚህ በተጨማሪ በ1999 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ የተጀመሩና በገንዘብ እጥረት ምክንያት ግንባታቸው የተቋረጡ 10 ሕንፃዎችን በመግዛት ሠራተኞቹን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን፥ ሕንጻዎቹ ሲጠናቀቁ 150 የሚሆኑ የተቋሙን ሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸውንም ዶክተር ደረጄ አክለው ገልጸዋል።

    ዶክተር ደረጄ እንዳሉት መኖርያ ቤቶቹ ስቱዲዮ፣ ባለ አንድ መኝታ፣ ባለ ሁለት መኝታ እና ባለ ሦስት መኝታ ሲሆኑ ሠራተኞቹ በተቋሙ እስካሉ ድረስ ቤቶቹን በነጻ ይገለገሉባቸዋል።

    ከዩኒቨርሲቲው ሠራተኞቹ መካከል መምህር ተስፋዬ ፍቃዱ በሰጡት አስተያየት ተቋሙ በግል የኪራይ ቤት ሲንከራተቱ ይገጥማቸው ከነበረው ችግር እንደተፈታላቸው ተናግረዋል። በግል ተከራይቶ መኖር ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዳሉት ገልጸው በአከራዩና በተከራይ መካከል ቅሬታ በተፈጠረ ቁጥር ይደርስባቸው በነበረው መጉላላት ይማረሩ እንደነበር ገልጸዋል።

    መምህር እሱባለሁ ዳባ በበኩላቸው የግል ቤት በተከራዩበት ወቅት ከውሃና መብራት ክፍያ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጭቅጭቅና ግጭት ውስጥ ይገቡ እንደነበር አስታውሰዋል።

    በተመሳሳይ፦ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪዎች በርካታ መርሀ ግብሮችን ከፈቱ

    በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው በኩል የመኖሪያ ቤት ችግራቸው መፈታቱ የትምህርትና የምርምር ሥራቸውን ተረጋግተው ለማከናወን እንደሚያስችላቸው ጠቁመው በተቋሙ በኩል ለተደረገላቸው የመኖርያ ቤት ስጦታ መስጋናቸውን አቅርበዋል።

    መኖርያ ቤት ማግኘታቸው ከዚህ ቀደም ለግለሰብ ይከፍሉት የነበረውን የቤት ኪራይ ወጪ ከመቀነሱ ባለፈ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በማኅበራዊ ጉዳዮች እንዲተሳሰሩ የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት ደግሞ መምህር ኤልያስ ቱጁባ ናቸው። መምህሩ እንዳሉት ሠራተኞች አንድ አካባቢ መሆናቸው ለትራንስፖርት አገልግሎትና ለኢንቴርኔት አገልግሎት ምቹ ሁነታ ከመፍጠር አኳያ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

    ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ከዚህን ቀደም ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመኖርያ ቤት ሕንፃ በማስገንባት ከ60 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞቹ ማሰረከቡ የተቋሙን መረጃ ያሳያል።

    በየካቲት ወር 1999 ዓ.ም የተቋቋመው ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት 82 በመጀመሪያ (bachelors)፣ በሁለተኛ (masters) እና በዶክትሬት ዲግሪዎች ተማሪዎችን እንደሚያስተምር የዩኒቨርሲቲው ድረ ገጽ ያስረዳል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ወለጋ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በዶክትሬት ዲግሪ አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮችን ከፍተው ተማሪዎችን ይቀበላሉ።

    ደብረ ብርሃን/ባህር ዳር – ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ (2011 ዓ.ም) የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ ዲግሪ (bachelor degree) አራት በሁለተኛ ዲግሪ (master degree) አስራ ሁለት መርሃ ግብሮችን እንደሚከፍት አስታወቀ።

    የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ጌትነት አሸናፊ ለኮሙኒኬሽን ጉዳዮች እንደገለጹት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን አስራ ስድስት አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮችን ይከፍታል።

    ዶክተር ጌትነት አሸናፊ እንዳሉት የትምህርት ክፍሎቹ ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያና ሁለተኛ ድግሪ ዲግሪ የሚሰጣቸውን የትምህርት መርሀ ግብሮች የመጀመሪያ ድግሪ ከ49 ወደ 53 እንዲሁም 34 የነበረውን የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሀ ግብር ወደ 46 ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።

    ከተመሠረተ 11 ዓመት የሞላው ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ሰዓት ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ መስኮች እያስተማረ ይገኛል።

    በተመሳሳይ ዜና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ፣ በበሁለተኛ እና በዶክትሬት (doctorate) ዲግሪ በሚከፍታቸው 18 አዳዲስ የትምህርት መስኮች ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ። ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት ከ8 ሺህ 700 በላይ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበልም አስፈላጊው ዝግጅት ማድረጉም ተጠቁሟል።

    የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር እሰይ ከበደ ዛሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ተቋሙ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ አዳዲስ የትምህርት መስኮችን በመክፈት አገራዊ እድገቱን በእውቀት ለማገዝ እየሠራ ነው።

    በተያዘው የትምህርት ዘመንም ሁለት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ 12 የሁለተኛ ዲግሪና አራት የዶክትሬት ዲግሪ የትምህርት መስኮችን ከፍቶ 250 ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

    ዶክተር እሰይ እንዳሉት ህግ፣ መሬት አስተዳደር፣ ጤና፣ ቴክኖሎጂ፣ ጨርቃጨርቅ፣ ትምህርት፣ ፖለቲካል ሳይንስና የመሳሰሉት የትምህርት መስኮች አዲስ የሚከፈቱባቸው ናቸው። “የተሳካ የመማር ማስተማር ተግባር ለማካሄድም ቀደም ብሎ የሥርአተ ትምህርት ቀረጻ መደረጉንና የመምህራን ቅጥርም ሆነ ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል” ብለዋል።

    የኒቨርሲቲው በአፋን ኦሮሞ ትምህርትም በዚህ ዓመት አጋማሽ መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሥርአተ ትምህርት ቀረጻ ሥራ ማካሄዱንና የመምህራን ቅጥር እየፈጸመ መሆኑን ዶክተር እሰይ አስታውቀዋል።

    ተቋሙ በህክምናው ዘርፍ የተሻለ እውቅት ያላቸው ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ “የተሻለ የማስተማርም ሆነ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት አዲስ የማስተማሪያ ሆስፒታል ገንብቶ የ170 መምህራንን በመቅጠር ላይ ነው” ብለዋል።

    ዩኒቨርሲቲው በመደባኛው የትምህርት መርሀግብር ብቻ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ከ8 ሺህ 700 በላይ አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምርም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አያይዘው ገልጸዋል።

    በተለይም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ዩኒቨርሲቲ እየወረደ የመጣውን የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ የተሻለ አቅም ያላቸውን መምህራን በመመደብ፣ ቤተ ሙከራዎችንና ቤተ መጻህፍትን በማደረጀት ጥራትን ለማምጣት እየሠራ መሆኑንም ገልፀዋል። ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን አጠናቀው ከመውጣታቸው በፊትም አጠቃላይ የጥራት መለኪያ ፈተና እንዲወስዱም እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

    ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመደበኛውና መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት መርሃ ግብሮች ዓመታዊ የተማሪ የቅበላ አቅሙ በአሁኑ ወቅት ከ50 ሺህ በላይ ደርሷል።

    ምንጭ፦ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር ጌትነት አሸናፊ (ፎቶ፦ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ)

Viewing 4 results - 16 through 19 (of 19 total)