Search Results for ' የኢትዮጵያ ቡና'

Home Forums Search Search Results for ' የኢትዮጵያ ቡና'

Viewing 3 results - 46 through 48 (of 48 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    የስንፈተ ወሲብ መድኃኒቶች እንደአግባቡ ከሆነ በሀኪም ትዕዛዝ የሚሰጡ መሆናቸውን በመግለጽ፥ ነገር ግን በሕገ-ወጥ መንገድ ያለሀኪም ትዕዛዝ ለኅብረተሰቡ የሚያሰራጩ ሕገ-ወጥ የመድኃኒት ተቋማት እንዳሉ ተጠቅሟል።

    አዲስ አበባ – የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ፈዋሽነቱና ደኅንነቱ ያልተረጋገጠ በንግድ ስሙ “ቪጋ፣” “ቪጎ” እና “ፊካ” (ቪጎ 50፣ ቪጎ 100/ Vigo50/100፣ ቬጋ 50፣ ቬጋ 100/Vega 50/100፣ ፊካ 50፣ ፊካ 100/Fika 50/100) የተሰኙ የወሲብ ማነቃቂያ መድኃኒቶች (የስንፈተ ወሲብ መድኃኒቶች) በሕገ-ወጥ መንገድ በሀገር ውስጥ መሰራጨታቸውንና በተጠቃሚዎች ላይም የጤና እና የኢኮኖሚ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን አስታወቀ።

    ባስልጣን መሥሪያ ቤቱ ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተገለጸው በድህረ-ገበያ ቅኝት በተደረገው የቁጥጥር ሥራ ለማወቅ እንደተቻለው በተቋሙ ያልተመዘገቡና ጥራት እና ደኅንነነታቸው ያልተረጋገጡ እንዲሁም በሕገ-ወጥ መንገድ ወደሀገር ውስጥ የገቡት የስንፈተ ወሲብ (የወሲብ ማነቃቂያ) መድኃኒቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመገኘታቸው ህብረተሰቡ ምርቶቹን ከመጠቀም ራሱን እንዲቆጥብና ጥንቃቄ እንዲያደርግ ባለስልጣን መስሪያቤቱ አሳስቧል።

    ከዚህ በተጨማሪ ችግሩን የከፋ የሚያደርገው የስንፈተ ወሲብ መድኃኒቶች እንደአግባቡ ከሆነ በሀኪም ትዕዛዝ የሚሰጡ መሆናቸውን በመግለጽ፥ ነገር ግን በሕገ-ወጥ መንገድ ያለሀኪም ትዕዛዝ ለኅብረተሰቡ የሚያሰራጩ ሕገ-ወጥ የመድኃኒት ተቋማት እንዳሉ የተደረሰበት ስለሆነ ህብረተሰቡ መሰል ተግባር ሲፈጸም ከተመለከተ በነጻ የስልክ መስመር 8482 በመደወል ለባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ እንዲያሳውቅ አስገንዝቧል።

    የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱን መግለጫ በመጥቀስ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደዘገበው ከላይ የተጠቀሱት ሕገ-ወጥ መድኃኒቶች ለስንፈተ ወሲብ (ፈዋሽነት (በሌላ አባባል፥ ለወሲብ ማነቃቂያነት) ጥቅም ላይ እየዋሉ ሲሆን፥ በአዲስ አበባ፣ በዲላ፣ በወላይታ፣ በወራቤ፣ በሆሳዕና፣ በሀዋሳ፣ በደሴ፣ በኮምቦልቻ እና በጎንደር በስፋት እየተሰራጩ ነው። እነዚህ ሕገ-ወጥ መድኃኒቶች በህብረተሰቡ ላይ እይሳደሩ ያለው ዘርፈ ብዙ ጫና እና ተጽዕኖዎች ከፍተኛ ነው። እንደዘገባው ከሆነ ይህ እጅግ አሳሳቢ ችግር በስፋት ከተከሰተ ሁለት ዓመትና ከዚያ በላይ ቢሆነውም በአሁኑ ጊዜ የተጠቃሚው ቁጥር እየጨመረና እያስከተለ ያለውም ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። መግለጫውን መስጠት ያስፈለገውም ስርጭቱ በመስፋፋቱ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ እና በድርጊቱ ላይ የሚሳተፉም ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ለማሳሰብ ነው።

    በባለስልጣኑ የመድኃኒት ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ እንዳለ እንደገለጹት፤ ባለስልጣኑ ባከናወነው የክትትልና ቁጥጥር ስራ በደቡብ ክልል ‹‹ቪጋ› እና ‹‹ቪጎ›› የተባለውን ጨምሮ በህገወጥ መንገድ የገቡ መድኃኒቶች ሲሸጡ የተደረሰባቸው ከ30 በላይ የሚሆኑ የግል መድኃኒት ቤቶች የክልሉ ተቆጣጣሪ አካል እርምጃ እንዲወስድ ስም ዝርዝራቸውን አሳውቋል። በከሚሴና በደሴም በተመሳሳይ የተሰማሩ ወደ 20 ድርጅቶች እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረጉን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

    ባለስልጣኑ በተለያየ ጊዜ በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መድኃኒቶችን ከፍትህ አካላትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመውጫ በሮች ላይ ቁጥጥር በማድረግ ህገወጦችን በመከላከል ረገድ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ቢሆንም የህብረተሰብ ተሳትፎ መኖር እንዳለበት አመልክተዋል። ህብረተሰቡ ያለ ሀኪም ትዕዛዝ ከመውሰድ እንዲቆጠብና ህገወጥነትንም እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል።

    በባለስልጣኑ የመድኃኒት ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብደላ ቃሶ ባለስልጣኑ ፈዋሽነታቸውና ጥራታቸው የተረጋገጠ መድኃኒቶችን ህብረተሰቡ በቀላሉ የሚለይበትን አሠራር ዘርግቶ ችግሩን ለመቅረፍ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል። ተገልጋዮች ከዚህ በኋላ ሕጋዊና ሕጋዊ ያልሆኑ መድኃኒቶችን በባለስልጣኑ ድረ-ገጽ (http://www.mris.fmhaca.gov.et) ማየት እንደሚችሉና በድረ-ገጹ ላይም ስለመድኃኒቱ ዝርዝር የሆነ መረጃ እንደሚያገኝ አመልክተዋል። ቀደም ሲል እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ይወስድ የነበረውን መድኃኒቶችን በዓይነትና በብዛት የመመዝገብ ሥራም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    የስንፈተ ወሲብ መድኃኒቶች

    Semonegna
    Keymaster

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ ተዘጋጅቷል፤ የትምህርት ዘመኑን የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊና ጤናማ ለማድረግ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፤ በሁሉም ካምፓሶች የህፃናት ማዋያ ማዕከላትን ለማቋቋም በዝግጅት ላይ ነው።

    አርባ ምንጭ (ኢዜአ/AMU)– አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ መዘጋጀቱን ፕሬዚዳንቱ ገለጹ። ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊና ጤናማ ለማድረግ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ተወያይቷል።

    የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት ነባርና አዲስ ተማሪዎችን በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያሰለጥናል። ከነዚህም ከ6ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች አዲስ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።

    ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲገቡ በማኅበራዊ ሕይወታቸው ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ጉዳዮች ላይ የክህሎት ትምህርት እንደሚሰጥም አመልክተዋል።

    ዩኒቨርሲቲው ጥቅምት 11 እና 13 ቀናት የነባር ተማሪዎች ቅበላ የሚያከናውን ሲሆን፣ ጥቅምት 15 ና 16 ቀናት 2011 ዓ.ም ደግሞ አዲስ ገቢዎችን እንደሚቀበል ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

    ተማሪዎቹ ከአቀባበል ጀምሮ በመማር ማስተማር ሂደት ችግሮች እንዳያጋጥማቸው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ያስረዱት ዶክተር ዳምጠው፣ ከግቢ ውጭ ችግር እንዳያጋጥማቸው የከተማው ነዋሪዎች ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

    ◌ ተመሳሳይ ዜና፦ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በትምህርት ጥራትና ለኅብረተሰቡ ንጹህ ውሃ ለማቅረብ እየሠራ ነው

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፖለቲካ፣ ኃይማኖትና ከትምሀርት ጋር ግንኙነት በሌላቸው ጉዳዮች የጸዳ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

    የአርባ ምንጭ ከተማ የሰላም ፎረም አባል አቶ ገረሱ በየነ በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ተግባሩን ለማከናወን እንዲያስችለው የሰላም ፎረም እንዲያቋቁም አሳስበዋል።

    ሌላኛው የሀይማኖት አባት መጋቢ ካሳዬ በየነ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው አካባቢ እየተስፋፉ የመጡትን የሺሻ፣ የጫትና የመጠጥ ቤቶች ጉዳይ እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል።

    የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ኤዞ ኤማቆ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከውሃና ከኤሌክትሪክ መቆራረጥ ጋር የሚያጋጥሙትን ችግሮችን ለማስወገድ እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲው አካባቢ የሚታዩ ሕገ ወጥ የሺሻ፣ የመጠጥና ጭፈራ ቤቶችን በመቆጣጠርና በመከታተል እገዛ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

    በውይይቱ ላይ የሀይማኖት አባቶች፣ የከተማው የሰላም ኮሚቴ አባላት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

    ከዚሁ ጋር በተያያዘ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2011 በጀት ዓመት በሁሉም ካምፓሶች የህፃናት ማዋያ ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ገልጸዋል። ዳይሬክቶሬቱ ማዕከላቱን በቅርበት እንዲከታተል ኃላፊነት የተሠጠው ሲሆን በያዝነው በጀት ዓመት የቢሮ መጠሪያውን ወደ ‹‹ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት›› እንደሚቀይርም አስታውቋል።

    የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህለ እንደገለፁት በፌዴራል የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀፅ 48(6) መሠረት ሴት የመንግስት ሠራተኞች ከወሊድ በኋላ ወደ ሥራ ገበታቸው ሲመለሱ በሚሠሩበት ተቋም ውስጥ ህጻን ልጆቻቸውን በቅርበት እየተንከባከቡና እየተከታተሉ መደበኛ ሥራዎቻቸውን እንዲያከናውኑ ለማገዝ የህፃናት ማቆያ ማቋቋም አስፈላጊ ነው። በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 36(1) መሠረት ህጻናት ከወላጆቻቸው ማግኘት የሚገባቸውን ተገቢውን እንክብካቤ የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።

    የህፃናት ማቆያዎቹ መቋቋም ዓላማዎች ከሆኑት ውስጥ እናቶቻቸው በሥራ ምክንያት በአቅራቢያቸው ባለመኖራቸው ምክንያት በህፃናት ጤንነትና ደህንነት ላይ የሚደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቀነስ፣ በመንግስት ተቋማት ውስጥ የተሰማሩ እናት ሠራተኞች በህጻን ልጆቻቸው ምክንያት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚፈጥሩትን ክፍተቶች መሙላት፣ በሴት ሠራተኞች ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን መቀነስ እና ውጤታማነታቸውን ማሳደግ ጥቂቶቹ ናቸው።

    የህፃናት ማዋያዎቹ ከመደበኛው የሥራ መግቢያ ሰዓት  እስከ ሥራ መውጫ ሰዓት ድረስ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን የመኝታ፣ የማረፊያ፣ የመጫወቻ፣ የምግብ ማብሰያ፣ የመመገቢያ አቅርቦትና አገልግሎት እንዲሁም የእንክብካቤ፣ የቅርብ ክትትል እና የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና አገልግሎቶችን አካቷል።

    እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ አገልግሎቱን ለማግኘት ወላጆች የማንነት መግለጫ መታወቂያ ማቅረብ የሚኖርባቸው ሲሆን የህፃናቱን ምግብ በተመለከተ ከማቆያ ማዕከሉ ጋር በሚደረግ ስምምነት ወላጆች አዘጋጅተው ማቅረብ አልያም ተመጣጣኝ ክፍያ ፈጽመው የማዕከሉን አቅርቦት መጠቀም ይችላሉ። የማዕከሉን የውስጥ ግብዓት ከማሟላት ጀምሮ ተንከባካቢ ሞግዚት የመቅጠሩ ተግባር የዩኒቨርሲቲው ይሆናል።

    ወ/ሪት ሠናይት እንደገለጹት በህፃናት ደህንነት ላይ የወጡትን ህግጋት መሠረት በማድረግ በህፃናት ጤንነት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ከሚችሉ ኬሚካሎች፣ ብናኞች፣ ድምፅ ያላቸው የማምረቻ ቦታዎችና መሠል ጎጂ ነገሮች የራቀ የህፃናት ማቆያ ለመገንባት ዩኒቨርሲቲው የቦታ መረጣ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። የህፃናት ማቆያ ማዕከላቱ ህንፃዎች የመኝታ፣ የመጫወቻና የንፅህና መጠበቂያ ክፍሎችን የሚያካትቱ ይሆናል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ለ13ኛ ጊዜ በሚያካሂደው ዓመታዊ የኪነ ህንጻ አውደ ርዕይ “ኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን” በሚል መሪ ሀሳብ ከጥቅምት 8 ቀን እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቲያትር ይካሄዳል።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በየዓመቱ የሚያካሂደው ዓመታዊ የኪነ ህንጻ አውደ ርዕይ ጥቅምት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ይጀመራል።

    ለ13ኛ ጊዜ በሚካሄደው አውደ ርዕዩ “ኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን” በሚል መሪ ሀሳብ በብሔራዊ ቲያትር ይካሄዳል።
    የዩኒቨርሲቲው የኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን የትምህርት ክፍል ሃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ገብረጻዲቅ ለኢዜአ እንደገለጹት አውደ ርዕዩ የትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች የሥራ ውጤቶቻቸውን የሚያቀርቡበት ነው።

    አውደ ርዕዩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ ዘርፉ ኢንዱስትሪ ከመቀላቀላቸው በፊት ሥራዎቻቸውን ለኅብረተሰቡ፣ ለመንግስት ተቋማትና ለዘርፉ ባለድርሻ አካላት በማቅረብ ልምድ የሚቀስሙበት እንደሚሆን አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ተማሪዎቹ እርስ በእርስ እንዲማማሩም መልካም አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል።

    የተሻለ አቅም ያላቸው ተማሪዎች ወደ ሥራ ዓለም ሲገቡ በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት ከመቅረፍ አንጻር አስተዋጽዖ እንደሚያበረክቱም ነው አቶ ቴዎድሮስ ያስረዱት።

    አውደ ርዕዩ በየዓመቱ ሲካሄድ በአማካይ እስከ ሁለት ሺህ ሰው እንደሚጎበኘውና ዘንድሮም ከአንድ ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚጎበኙት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

    ALSO: EVENT: The 9TH ADDISBUILD: International Construction, Steel, Construction Machinery & Infrastructure Exhibition

    በአውደ ርዕዩ የዩኒቨርሲቲው የዘንድሮ የትምህርት ክፍሉ 60 ተማሪዎች የሥራ ፕሮጀክቶቻቸውን እንደሚያቀርቡና የተሻለ ሥራ ያቀረቡ ተማሪዎች የኢትዮጵያ የኪነ ህንጻ ባለሙያዎች ማኅበር (Association of Ethiopian Architects) በሚያዘጋጀው ዓመታዊ ውድድር እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል።

    በዚህ አውደ ርዕይ ሌሎች የመንግስትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደሚሳተፉም ተናግረዋል።

    በብሔራዊ ቲአትር አዳራሽ የሚካሔደው አውደ ርዕይ ከጥቅምት 8 ቀን እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል።

    ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ከሚሰጣቸው የትምህርት ዘርፎች አንዱ “ኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን” ሲሆን በዚሁ ትምህርት ዘርፍ ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ (bachelors degree) አስተምሮ ያስመርቃል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ

Viewing 3 results - 46 through 48 (of 48 total)