-
Search Results
-
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ሥነ-ምግባርን ጠብቀው ከመሥራትና ማህበረሰቡን ከማስተማር ይልቅ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን እያባባሱ መሆኑን ባለሙያዎች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በበኩሉ መገናኛ ብዙሃኑ የሚሠሯቸውን የዘገባ ስህተቶች እና አባባሽ ይዘቶች እንዲያስተካክሉ በቃልና በደብዳቤ እያሳወቅኩ ነው ይላል።
ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚፅፉት አቶ በፍቃዱ ኃይሉ “የክልል መገናኛ ብዙሃን ወገንተኝነት እና ለገዥው ቡድን አጎብዳጅነት” እንደሚታይባቸው አንስተው፤ ብዙ ፖለቲካዊ ዘገባዎችን እና ትርክቶችን በተዛባ መልኩ የሚያቀርቡ እንደሆኑ ነው የገለጹት።
ዘውግ-ተኮር የሆኑ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሙያዊ ስነምግባርን ጠብቀው ያለመዘገብ፣ ሀቅን እንዳለ ያለማቅረብና ሚዛናዊ አለመሆን እንደሚስተዋልባቸው የሚናገሩት አቶ በፍቃዱ ኃይሉ፥ ይህ ደግሞ በሀገሪቱ ግጭት በሚስተዋልበት ወቅት የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ እንዳይዘግቡ አድርጓቸዋል ነው ያሉት።
አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ስህተት የሚፈጽሙት ባለማወቅ መሆኑን ገልጸው፥ ከዚህ ዓይነት ስህተት እንዲወጡ መጀመሪያ በማስተማር የተለየ ሁኔታ ሲያጋጥም በተጨባጭ ማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ይገባልም ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃኑ የሕዝብ ማስተማሪያ አልያም የጦር መሣሪያ የመሆን ዕድል ስላላቸው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ሀሳባቸውን በመስጠት፤ የኢትዮጵያ የብሮድካስት ባለሥልጣልም የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህርና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ አቶ ሃይማኖት ጌታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን አዘጋገብ “ፅንፍ ይዞ እየተጓዘ” መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህም ለግጭት አባባሽ እየሆነ ነው ይላሉ።
በተለይ አንዳንድ “የፅንፍ ፖለቲካ” የሚያራምዱ ግለሰቦች የራሳቸውን መገናኛ ብዙሃን በመክፈት የሚፈልጉትን “ፅንፈኛና የጥላቻ አጀንዳ” እያሰራጩ መሆኑን ተናግረዋል። በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን በኩል ደግሞ “ሕዝብ ሲሞት እና ጉዳት ሲደርስበት ተከታትሎ ከመዘገብና መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ መንግሥትን እየጠበቁ የመዘገብ አዝማሚያ ይታይባቸዋል” ነው ያሉት።
መገናኛ ብዙሃኑ አስቀድመው የስጋት ትንተናዎችን በሚዛናዊነት በማቅረብ ግጭትን የመከላከል ሚና እየተወጡ አይደለም ያሉት አቶ ሃይማኖት፥ ብሮድካስት ባለስልጣንም ለመገናኛ ብዙሃኑ የተሰጣቸው ነጻነት እንዳይታፈን ጥንቃቄ በማድረግ፤ በተሳሳተ መንገድ እየሄዱ ባሉት ላይ የእርምት እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንደወሰን አንዱዓለም “የሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ በተረበሸ ቁጥር መገናኛ ብዙሃኑም አብረው መታመማቸው ከፍተኛ ችግር አስከትሏል” ነው ያሉት።
አብዛኛው መገናኛ ብዙሃን ሕዝብን ከሕዝብ፣ ክልልን ከክልል፣ መንግሥትን ከሕዝብ የሚያራርቁ ዘገባዎችን እየሠሩ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፥ ለሕዝብ የሚጠቅሙ ማኅበራዊ፣ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና ሌሎች የሕይወት መልኮችን ትተው ፖለቲካ ላይ ብቻ የመጠመድ ችግር ይታይባቸዋል ነው ያሉት።
ባለስልጣኑ የመገናኛ ብዙሃኑን ሥራዎች መዝኖ እርምጃ ለመውሰድ ከዚህ ቀደም የነበረውን ፖለቲካዊ መስፈርት በመቀየር ሙያዊ መመዘኛ ማዘጋጀቱን ጠቁመው፥ በመስፈርቱ መሠረት ድክመትና ጥንካሬ ተለይቶ እንዲያስተካክሉት ለተወሰኑ መገናኛ ብዙሃን ደብዳቤ መላክ መጀመሩንም ገልጸዋል።
“ሀገሪቱ ለውጥ ላይ ናት በሚል መገናኛ ብዙሃኑ የነውጥ አራጋቢ ሆነው እንዲቆዩ መፍቀድ አይገባም” ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፥ የፖለቲካ ሁኔታ በተረበሸ ቁጥር ሚዲያው አብሮ መረበሽ እንደለሌበትና በቅርቡ በሚወጣው የመገናኛ ብዘሃን አዋጅ ግልፅ ድንበር እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
የፖለቲካ አመራሮች በቦርድም ሆነ በሚዲያ መሪነት እንዳይሰየሙ በረቂቅ አዋጁ መቀመጡን አንስተው፥ መገናኛ ብዙሃኑ ከባለሥልጣኑ ጋር እንደ ‘አይጥ እና ድመት’ ከሚተያዩ እርስ በራሳቸው የሚተራረሙበት፣ የሚነጋገሩበትና የሚደጋገፉበት የመገናኛ ብዙሃን ካውንስል መቋቋሙንም ነው የገለጹት።
“በልቅነት እየሠሩ ያሉትን ለማረም ሲባል በነጻነት ላይ ያሉት መጎዳት የለባቸውም” ያሉት አቶ ወንደወሰን፥ ችግሩን ለማረምና ሁለቱን ለመለየት ከውይይትና ከአቅም ግንባታ ጀምሮ በቀጣይ በሕግ የተጠና የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተናግረዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ (ABH Partners) የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እና አምስት የሥራ ኃላፊዎቹ ላይ ጉዳት አድርሰውብኛል በሚል በመሠረተው የ174.6 ሚሊዮን ብር ክስ ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረቡ።
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን ጋዜጣ) – የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ (HERQA) እንዲሁም አምስት የሥራ ኃላፊዎቹ በድርጅቱ ላይ ላደረሱትና ለሚደርሰው ጉዳት የ174.6 ሚሊዮን ብር ተከፍሎ እስከሚያልቅ ከሚታሰብ ሕጋዊ ወለድ ጋር ክስ እንዳቀረበባቸውና ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ፍርድ ቤት እንደቀርቡ ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ (ጥምረት ለተሻለ ጤና) /ABH Partners/ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል አማካሪ ድርጅት አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ማርቆስ ፈለቀ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፥ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ከማምራቱ በፊት ኤጀንሲው የድርጅቱን መልካም ሥምና ዝናን በማጠልሸቱ ይቅርታ እንዲጠይቅና ችግሩን እንዲያርም ቢጠየቅም ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም።
በዚህም ድርጅቱ ነሐሴ 23 ቀን 2011 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሐ-ብሔር ስድስተኛ ምድብ ችሎት የመዝገብ ቁጥር 241863 ክስ ለመመሥረት ተገዷል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴን ጨምሮ አምስት የሥራ ኃላፊዎችም ተከሰዋል።
ኤጀንሲው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ (ABH Partners) ጋር በጥምረት የሚሠሩትን ሥራ እንደማያውቀው ቢያስተባብልም፤ ሁለቱ ተቋማት ውል ተፈራርመው ሥራውን ሲጀምሩ በወቅቱ የነበሩት የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በቦታው ተገኝተው መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተው እንደነበር ዶ/ር ማርቆስ አስታውሰው፤ “ይህም መንግሥት አያውቀውም የሚለውን ሐሳብ ትክክል እንዳልሆነ አመላካች ነው። ከወራት በፊት ትምህርት የሚሰጥበትን ቦታ ተገኝተው የጎበኙ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታዎች ግን ‘ሥራው የዩኒቨርሲቲውን አቅም ለማዳበር ያገዘ ነው’ ሲሉ አሞካሽተውታል። ለጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመስጠት የመምህራን ፍልሰት እንዲቀንስ አዎንታዊ አስተዋፅዖ ማበርከቱንና ለትምህርት ጥራት እንዲተጋ የሚያግዙ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውንም ሚኒስቴሩ ምስክርነቱን በደብዳቤ ሰጥቷል” ብለዋል።
ሚኒስቴሩ፥ የዚህ መሰል የግሉ ዘርፍና የመንግሥት አጋርነት ለትምህርት ጥራትም ሆነ ተደራሽነት ሚናው የላቀ መሆኑን በመግለጽ፥ ለዚህ ሊበረታታ ለሚገባው ድርጅት አገራዊ ፋይዳውን በማየት የግንባታ መሬት በመስጠት ትብብር እንዲደረግላቸው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የትብብር ደብዳቤ እንደፃፈላቸውም ጠቁመዋል።
ሚኒስቴሩ ለዩኒቨርሲቲውና ለድርጅቱ ምስክርነት በመስጠት ከመንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ ሲያደርግ፥ ኤጀንሲው ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 ከሰጠው ሥልጣን ውጪ “ዩኒቨርሲቲው ከዋናው ግቢ ውጪ በአዲስ አበባ የሚሰጠው ትምህርት ዕውቅና የለውም፤ ሕጋዊም አይደለም” በማለት እግድ ማስተላለፉ “ባለፉት ሰባት ዓመታት የት ነበረ?” የሚል ጥያቄንም የሚጭር እንደሆነ ዶ/ር ማርቆስ አብራርተዋል።
ጅማ ዩኒቨርሲቲ የማስተማር ሥራውን ሊሰራ፤ አማካሪ ድርጅቱ ደግሞ አስተዳደራዊ ድጋፍ ሊሰጥ በገቡት ስምምነት መሠረት ዩኒቨርሲቲው አዲስ አበባ ባለው ካምፓስ ምንም ዓይነት የመንግሥት ድጋፍ ሳይደረግለት ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ ሙሉ ድጋፍ በማድረግ ለመማር-ማስተማሩ አስፈላጊ ግብዓቶችን አሟልቶ በውሉ መሠረት ግዴታውን ሲወጣ መቆየቱንም ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከዋናው ግቢ ውጪ ማስተማርም ሆነ ከሌሎች አካላት ጋር በትብብር መሥራት እንደማይችል ኤጀንሲው ቢገልጽም፣ በዩኒቨርሲቲው እንደገና ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 240/2003 ግን ዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ከሚገኝበት ጅማ ከተማ ውጪ በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ክፍሎችን እንዲሁም የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ሊያቋቁም እንደሚችል ተደንግጓል።
በተመሳሳይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዋጅ ዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኳቸውን ለማሟላት ድጋፍ ሊሰጣቸው ከሚችል ከማንኛውም ተቋም ጋር መሥራት እንደሚችሉ ይደነግጋል። በዚህም በአዋጁ ያልተከለከለን ሥልጣን ኤጀንሲው በደብዳቤ መሻሩ ተገቢነት እንደሌለው ዶ/ር ማርቆስ ገልፀዋል። በመሆኑም ለቀጣይ የትምህርት ዘመን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንና ተማሪዎችና የተማሪ ወላጆች በሁኔታው መደናገጥ እንደማይገባቸው ተናግረዋል።
የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ (ቁጥር 650/2001) አንቀጽ 93፣ ንዑስ አንቀጽ አንድ አገልግሎት በሌሎች ወገኖች እንዲሰጥ ስለማድረግ ይደነግጋል። በዚህም ማንኛውም የመንግሥት ተቋም ተገቢና ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ሆኖ ሲያገኘው የድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶችን በሌሎች አገልግሎት አቅራቢዎች እንዲሰጥ ሊያደርግ እንደሚችል አስቀምጧል።
በተመሳሳይ በጅማ ዩኒቨርሲቲ እንደገና ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ (ቁጥር 240/2003) በአንቀጽ ሦስት መሠረት የዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ጅማ ከተማ ሆኖ በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ክፍሎችን፣ የምርምርና የሕብረተሰብ አገልግሎት ማዕከሎችን ሊያቋቁም እንደሚችል ተቀምጧል።
ባለፉት 15 ቀናት ኤጀንሲው “የትብብር ሥልጠና ትክክል ባለመሆኑ እንዲያቆሙ” በሚል ሚኒስቴሩ በደብዳቤ ማሳወቁን መግለጹ ይታወሳል። በዚህ መልኩ ሲሠሩ የነበሩ የጅማ፣ የደብረ ማርቆስ፣ የባህር ዳር እና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲዎች እንደታገዱ አሳውቋል።
ሆኖም ጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ ሥራቸውን በመቀጠላቸው “አደብ ሊገዙ ይገባል” ብሎም ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ኤጀንሲው በተቋማቱ በመማር ላይ ያሉትን ተማሪዎች ዝርዝር እንዲላክለት የጠየቀ ሲሆን፤ ተመርቀው የወጡ ተማሪዎች ዕጣ ፈንታ ግን ቀጣይ ውይይት እንደሚያስፈልገው አሳውቆ ነበር።
ምንጭ፦ አዲስ ዘመን ጋዜጣ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ዓላማው ክልሉን ለማተራመስና የህዝቡን ህልውና አደጋላይ ለመጣል ያለመ መሆኑን ገልጸው፥ በአሁኑ ወቅት የፌዴራል መንግስት ሁኔታውን የማስተካከልና ክልሉን የማረጋጋት ትዕዛዝ እንደተሰጠው አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መደረጉን በኢፌዴሪ ጠቅላይ የሚኒስቴር ፅህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ። አቶ ንጉሱ ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት ላይ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) በሰጡት መግለጫ በክልሉ መንግስት ላይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደርጓል።
በተደራጀ ሁኔታ በመንግስት መዋቅር ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የተሞከረው የተደራጀ እንቅስቃሴ ከሽፏል ነው ያሉት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ።
የአማራ ክልል ወደ መረጋጋት እየመጣ ባለበትና እና ሕዝቡ ቀደም ሲል ያነሳ የነበረውን የህግ የበላይነት ጥያቄ ለመመለስ እየተሠራ ባለበት ወቅት የተሰነዘረው ጥቃት የክልሉ መንግስት ብቻ ሳይሆን የአማራ ሕዝብ ላይ የተሞከረ ነው ብለዋል።
ሙከራው ክልሉን ለማተራመስና የህዝቡን ህልውና አደጋላይ ለመጣል ያለመ መሆኑን ገልጸው፥ በአሁኑ ወቅት የፌዴራል መንግስት ሁኔታውን የማስተካከልና ክልሉን የማረጋጋት ትዕዛዝ እንደተሰጠው ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ በመግባት ይህን መሰሉን ተግባር የመግታት ሥራ እንደሚሠራና ህብረተሰቡም አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጸረ-ህገ መንግስትና መፈንቅለ መንግስቶች እንዲሁም በታጠቁ ኃይሎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጸው፥ ክልሉን ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በትብብር እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ንጉሱ ጥላሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ቴለቭዥን ጋዜጠኛ ጋር ያደረጉትን አጭር ቃል ምልልስ እዚህ ጋር በመጫን ያዳምጡ።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- አቶ አዲሱ አረጋ፥ ያ’ኔ!
- ከዴሞክራሲና ከነጻነት ጋር የተቆራኙ እሴቶች
- አቶ አዲሱ አረጋን ነጻ ያወጣችው የእስክንድር ፌስታል
- ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተቀሰቀሰ ረብሻ የአንድ ተማሪ ህይወት አለፈ
- ብርሃኑ ነጋ የመረጠውን ሕይወት ለመምረጥ የጨዋ ልጅ መሆን ይጠይቃል፣ የህሊና ሰው መሆን ይጠይቃል፣ ራስን ማክበር ይጠይቃል
በአሁኑ ጊዜ የግዕዝ ቋንቋን ትምህርት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚሰጥባቸው መካከል መቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ ደሴ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ አክሱም ዩኒቨርሲቲ እና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የየኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ፌ.ዲ.ሪ.) ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከብሔራዊ ቤተ መፃሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ፣ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ቅዱስ ያሬድ ጥንታዊ ብራና ጽሑፎች ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ከሰኔ 1-2 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ “ግዕዝ እና ሥነ-ፈውስ” በሚል መሪ ቃል በመቐለ ከተማ ለሚካሄደው 5ኛውን የግዕዝ ጉባኤ ቀንን አስመልክቶ መረጃውን አስቀድሞ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ጋዜጣዊ መግለጫ በሚኒስቴሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ግንቦት 26 ቀን 20011 ዓ.ም. ተሰጥቷል።
ጋዜጣዊ መግለጫውን በጥምረት የሰጡት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቋንቋና የባህል እሴቶች ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው፣ የብሔራዊ ቤተ መፃሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ፣ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ቅዱስ ያሬድ ጥንታዊ ብራና ጽሑፎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሐጎስ አብርሃ ናቸው።
እንደኃላፊዎቹ መግለጫ፥ በግዕዝ ቋንቋ ውስጥ ያሉ ሀገር በቀል ዕውቀቶች በርካታ በመሆናቸው ልንማርበት፣ ልንጠቀምበትና ልትውልድ በማሸጋገር ወደ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ማምራት ይቻላል። በመሪ ቃሉ “ግዕዝ እና ሥነ-ፈውስ” ስንል እንደየባህሉ ሥነ-ልቦናን፣ ፀሎትን፣ ሥነ-ቃልን ለማወቅና መዳንን የሚያበረታታታ ሀገር በቀል ዕውቀት መሆኑንማወቅ ስላለብን፣ ብሎም ስለግዕዝ ያለንን ግንዛቤ ለማስፋት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
እንዲሁም በሀገራችን በርካታ ጥንታዊ የጽሑፍ ሀብቶቻችን የምናገኝበት በግዕዝ ቋንቋ የተፃፉ በመሆኑ፣ ጥንታዊ የስልጣኔ መገለጫ ሆኖ የሚያገለግል ነው። በአሁኑ ጊዜ የግዕዝ ቋንቋን ትምህርት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚሰጥባቸው መካከል መቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ ደሴ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ አክሱም ዩኒቨርሲቲ እና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። በሀገራችን በግዕዝ ቋንቋ በተሠሩ ሥራዎች ላይ እስካሁን የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት 750,000 በብራና ላይ የተፃፉ መጽሕፍት መኖሩ ታውቋል።
ምንጭ፦ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ እና ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በደብረ ብርሃን ከተማ ሃውልት ሊቆምላቸው ነው
- ጉዞ ዓድዋ ― ታላቁ የዓድዋ ድልን የሚገባው የታሪክ ማማ ላይ ለመስቀል የሚጥር ኢትዮጵያዊ ማኅበር
- የወልድያ ዩኒቨርሲቲ እና ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በትብብር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የትምህርት መስክ ሊጀምሩ ነው
- ሀገር በቀል የመድኃኒት አምራቾች መሠረታዊ ችግሮች በጥናት ሊለዩ ይገባል ― የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ
- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት ኤጀንሲ አሠራሩን ለማዘመን ከእንግሊዝ ሀገር አቻው ጋር ውይይት ተደረገ
ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከዓርብ ጀምሮ እስካሁን በውል ባልታወቀ ምክንያት የተቀሰቀሰው ግጭት እስከዛሬ (ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም.) ድረስ አለመረጋጋቱን ተማሪዎቹ ገልጸዋል።
ደብረ ማርቆስ (ቢቢሲ አማርኛ)– በአማራ ክልል ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተፈጠረ ግጭት አንድ ተማሪ መሞቱን ተማሪዎች ለቢቢሲ ገለጹ። ሟች ሰዓረ አብርሃ እንደሚባልና የሦስተኛ ዓመት የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል (economics department) ተማሪ እንደነበረ ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል።
በዩኒቨርስቲው ከዓርብ ጀምሮ የተቀሰቀሰው ግጭት እስከዛሬ (ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም.) ድረስ አለመረጋጋቱን ተማሪዎቹ ገልጸዋል።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ደሳለው ጌትነትም በተቋሙ ከባለፈው አርብ (ግንቦት 16 ቀን) 12 ሰዓት ጀምሮ ግጭቶች መኖራቸውን አረጋግጠዋል።
በዚህም አርብ ግንቦት 16 ላይ 3 ልጆች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረው ልጆቹ አሁን ሆስፒታል ይገኛሉ ብለዋል። የተጎዱት ተማሪዎች በባህር ዳር እና አዲስ አበባ ሪፈራል ተጽፎላቸው ወደዚያው መወሰዳቸውንም ጨምረው ያስረዳሉ። በግጭቱ ሁለት ተማሪዎች በድንጋይና በስለት ጉዳት እንደደረሰባቸው የዓይን እማኞቹ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በተፈጸመበት ጥቃት ምክንያት አንደኛው ተማሪ ወዲያውኑ ህይወቱ ማለፉንና ሌላኛው ተማሪ ደግሞ ለሕክምና እርዳታ ወደ ባህር ዳር መወሰዱን ከተማሪዎቹ ለመረዳት ተችሏል።
የረብሻውን ምክንያት እስካሁን ማረጋገጥ አልቻልንም ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አርብ ዕለት ተሳትፎ የነበራቸውን የተወሰኑ ልጆች ፖሊስ ተከታትሎ ከግቢ ውጭ ይዟቸው ፖሊስ ጣቢያ ስለሚገኙ ጉዳያቸው እየተጣራ ነው በማለት የግጭቱ መንስዔ ከዚያ በኋላ ተጣርቶ የሚታወቅ ይሆናል ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት በዩኒቨርሲቲው አዳራሽ የተጠለሉ ተማሪዎች እንዳሉ የተገለፀ ሲሆን ትላንት የሟችን አስክሬን ለመሸኘት የተሰበሰቡ ተማሪዎችም “ትምህርቱ ይቅርብን ወደ መጣንበት መልሱን” በማለት ለዩኒቨርሲቱው ፕሬዚዳንት ጥያቄ ማቅረባቸውን ነግረውናል።
የዚህን ዜና ተጨማሪ መረጃ ቢቢሲ አማርኛ ላይ ማንበብ ይቀጥሉ።
ከዚያው ከአማራ ክልል ሳንወጣ፥ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በምዕራብ እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ለተፈናቀሉ ወገኖች ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት (አብመድ) ዘግቧል። በቀጣይም ከ967 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።
ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ለአብመድ በጻፈው ደብዳቤ እንዳመላከተው ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ከዚህ በፊት በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በኩል የ1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። አሁን ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች 967ሺህ 786 ብር ከወር ደመወዛቸው አዋጥተው ድጋፍ አድርገዋል።
የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም በሚደረገው አገራዊ እና ክልላዊ የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደት ተማሪዎችም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከታቸውንም ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።
ከዚህ በፊት ሠራተኞች እና ዩኒቨርሲቲው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋሙ አንድ ሚሊዮን ብር በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በኩል ድጋፍ ማድረጉም ታውቋል።
ምንጮች፦ ቢቢሲ አማርኛ እና አብመድ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
Search Results for 'ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ'
Viewing 7 results - 1 through 7 (of 7 total)
Viewing 7 results - 1 through 7 (of 7 total)