Home › Forums › Semonegna Stories › የጉራጌ ሕዝብ ከ158 ዓመታት በፊት…
- This topic has 1 reply, 2 voices, and was last updated 2 years, 6 months ago by
Semonegna.
-
AuthorPosts
-
November 24, 2022 at 12:16 pm #54494
Semonegna
Keymaster“ጀፎረ”/”ጀፎሮ” ― የጉራጌዎች ውብ ስፍራ
ጀፎረ (በአንዳንድ አካባቢዎች “ጀፎሮ” ተብሎ ይጠራል) ውብ፣ ጽዱና ማራኪ በአባቶች ባህላዊ ዕውቀትና ጥበብ የተከሸነ፣ ሰፊ አረንጓዴ ጎዳና፣ በግራና በቀኙ በልምላሜያቸው ተውበው በሚታዩ እፀዋቶች የታጠረ፣ ማራኪ በሆኑ በባህላዊ እደ ጥበብ በተሽቆጠቆጡ ቤቶች የታጀበ፣ በየመሀሉ ላይ እንደ ሊባኖስ ዝግባ የገዘፉ ዛፎች ያሉት፣ ወደ መንደሩ ለሚገባ ሁሉ ለአእምሮ እፎይታን፣ ለነፍስ ደግሞ እርካታን የሚያጎናጽፍ የጉራጌዎች ልዩ ስፍራ ነው።
ጀፎረ በጉራጌ ማኅበረሰብ ዘንድ ልዩ ታሪክ እንዳለው ይነገርለታል። ጀፎረ አገልግሎቱ ሁለገብ ነው። ለመንደሮች ውበት መላበስ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
ጀፎረ ማለት የመንደር ወይም የጎጥ ነዋሪዎች የጋራ መጠቀሚያ፣ መተላለፊያ፣ መግቢያ እና መውጫ፣ ሰፊ መሰብሰቢያ፣ ጠዋት ከብቶች ከመሰማራታቸው በፊት ማታ ደግሞ ወደ ቤታቸው ከመግባታቸው በፊት ለማቆሚያነት የሚያገለግል የጋራ ስፍራ ማለት ነው።
ጀፎረ የጎኑ ስፋት 100-150 ሜትር፣ ርዝመቱ በመሃል የሚያልፍ ገደል፣ ደን፣ ወንዝ እስከሌለ ድረስ ሳይቋርጥ ይቀጥላል። ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የሚለካው በዘፈቀደ ሳይሆን በባህሉ በተመረጡ አባቶች ወይም “የዥር ዳነ” የመሬት ልኬት ዳኞች አማካኝነት መሆኑን የዘርፉ አጥኚዎች ይናገራሉ።
የጉራጌ ማኅበረሰብ ለጀፎረ ትልቅ ትኩረት ከመስጠቱ የተነሳ ጀፎረ ላይ የተተከለ የዛፍ ቅርንጫፍ፣ አፈር ወይም ሌሎችንም ነገሮች ይዞ ወደ ግል ቤት ማስገባት ክልክል ነው።
ጀፎረ በርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች አሉት። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያክል፦ ሰው ሲሞት የለቅሶ ሥነ ሥርዓት ይከወንበታል፤ ሰርግ ሲኖር የሙሽሪትና የሙሽራው አጃቢዎችና ዘመዶች በባህላዊ ዘፈን በማጀብ ይሞጋገሱበታል፤ ባህላዊ የእርቅ ሥነ ሥርዓት ይከናወንበታል፤ ሕፃናት ይጫወቱበታል፤ በቅሎና ፈረስ ይገራበታል፤ ወጣቶች የገና ጨዋታ ይጫወቱበታል፤ ወንዶችና ሴቶች የደቦ ሥራ ለመሥራት ቁጭ ብለው ይመካከሩበታል፤ በመስቀል በዓል አዛውንት ወይም የቀዬው ሽማግሌዎች፣ ጎልማሶች እና ወጣቶች በደመራው ሥነ ሥርዓት ላይ ተሰብስበው ይመራረቁበታል፤ አባቶች በርጩማቸውን ይዘው በመውጣት ንፁህ አየር ይቀበሉበታል።
ይህ “የመንደር አደባባይ” ለከብቶች መዋያነትም ያገለግላል። በተለይ በክረምት ወራት ከሰኔ እስከ መስከረም የግርጌ ሳር ከከብቶች መብልነት አልፎ ለቤት ክዳን መክደኛነት እስኪደርስ ድረስ እንደማስተንፈሻ ግልጋሎት መስጠት ሌላኛው የጀፎረ ተጨማሪ ጠቀሜታው ነው።
በጉራጌ ብሔረሰብ እያንዳንዱ የመንደሩ ነዋሪ ጀፎሮን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት አለበት። የመንደሩ ማኅበረሰብ በዘመቻ መልክ በመውጣት በባለቤትነት ስሜት ጀፎሮን ያፀዳል።
የጀፎረ መኖር ለእንሰት ተክል እድገት፣ ለቡናና ለሌሎች የጓሮ አትክልት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው። በተለይም ከብቶች ጀፎረ ላይ ስለሚሰማሩ እነዚህ የጓሮ አትክልቶች በከብቶች እንዳይበሉና እንዳይረገጡ ጉልህ አገልግሎት ይሰጣል።።
በመሆኑም ጀፎረ/ጀፎሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በመረዳት በተለይ ወጣቱ አባቶች ጠብቀው ያቆዩልንን ሀብታችንን በመንከባከብ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት በመወጣት እንዲህ ዓይነቱን ውብ ባህላችንን እንጠብቅ በማለት መልዕክታችንን በማስተላለፍ በጉራጌ ዞን የቸሃ ወረዳ ጀፎርን በዚህ መልኩ የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቃኝቶታል።
ምንጭ፦ የጉራጌ ዞን የመንግሥት ግንኙነት ጉዳዮች መምሪያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.