Home › Forums › Semonegna Stories › ሳይቃጠል በቅጠል – በጋራ ሀገራችን ላይ ያጠላውን የመበታተንና የሕዝብ ለሕዝብ እልቂት ለመቀልበስ የመፍትሄዎች አካል እንሁን!
Tagged: ነአምን ዘለቀ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 1 month ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
November 7, 2019 at 11:41 pm #12545SemonegnaKeymaster
“ሀገራችንን ኢትዮጵያን አጣብቆ የያዘውን መንግሥታዊ ኃይል ቢዳከም፣ እነዚህ የታሪክም የፓለቲካ መሠረት ያላቸው ልዩ ልዩ ቅራኔዎች በየቦታው ቢፈነዱ፣ በሕዝብ መካከል የእርስ በእርስ ግጭቶች ቢበራከቱ በብዙ አቅጣጫና ውስብስብ የብሄር ቅራኔዎች፣ ሌሎች ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና፣ ማኅበራዊ ችግሮች የተጠመደች ሀገራችንና የኢትዮጵያ ሕዝብ ወዴት ሊወስዱ እንደሚችሉ ከግምት ማስገባት አስፈላጊና ወሳኝ ይሆናል።”
ሳይቃጠል በቅጠል
በጋራ ሀገራችን ላይ ያጠላውን የመበታተንና የሕዝብ ለሕዝብ እልቂት ለመቀልበስ የመፍትሄዎች አካል እንሁን!
(ነአምን ዘለቀ)በሀገር ውስጥ ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በሙሉ፣ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የልዩ ልዩ የቋንቋና ባህል ማኅበረሰቦችን ለምትወክሉ ልሂቃንና ምሁራን፣ የሃይማኖትና የፓለቲካ ድርጅቶች መሪዎች፣ በሀገር ውስጥና በዲያስፓራ ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖች፣ አክቲቪስቶች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳታፊዎች በሙሉ፦
ሰሞኑን በአገራችን በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ አካባቢዎች በደረሱ ጥቃቶች ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊና ንጹሃን ወንድሞች፣ እህቶች፣ አባቶች፣ እናቶች፣ አዛውንት፣ ሕጻናት ሳይቀሩ፣ የሃይማኖት አገልጋዮች ጭምር በግፍ ተገድለዋል፣ ቆስለዋል፣ ተፈናቅለዋል። አብያተ ክርስቲያናትና መስጊዶችም ተቃጥለዋል። ብዙ ግፍ ተፈጽሟል። ሕይወታቸውን ላጡ ንጹሃን ዜጎች ወገኖቼና ለቤተሰቦቻቸው፣ ለዘመዶቻቸው በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰማኝን ጥልቅ ሃዘን እገልጻለሁ።
የሰው ልጆችን ከእንስሳት የሚለየን ረቂቅ ሕሊናን፣ ርሕራሄን፣ ሰብዓዊነት ነው። ከአራት አስር ዓመታት በላይ በተሰበኩ፣ ላለፉት በርካታ ወራት ደግሞ በተካረሩና ጥላቻን መሠረት ባደረጉ የተዛቡና ቁንጽል የታሪክና የፓለቲካ ትርክቶች ሳቢያ ለደረሰው እጅግ አሳዛኝ ጥቃትና የኢትዮጵያውያን ሕይወት መቀጠፍ የራሳቸው ሚና እንደነበራቸው የሚያጠያይቅ አይደለም።
እነዚህን አሰቃቂና ዘግናኝ ድርጊቶች የፈጸሙ ሁሉ ተጠያቂ መሆን አለባቸው፣ መንግሥት እነዚህን ኢ-ሰብዓዊ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች በሕግ ፊት ማቅረብ አለበት።
ከጥቂት ወራት በፊት በልዩ ልዩ ሚዲያዎች በተደጋጋሚ ሃሳቤን ለመግለጽ እንደሞከርኩት ከአንዳንድ የኦሮሞና የአማራ፣ የሕብረ ብሔር ኢትዮጵያውያን ልሂቃን፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ ሚዲያዎችና ሶሻል ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶች፣ የብሔርም የሕብረ ብሔርም የፓለቲካ ድርጅት መሪዎች ሲሰነዘሩ የቆዩ ትንኮሳዎች፣ ጠብ አጫሪ ተግባራት፣ እንቅስቃሴዎች በልዩ ልዩ ማኅበረስቦች መካከል ለዘመናት የነበረውን ተጋምዶ፣ ትስስር፣ ትብብር፣ ፍቅር፣ ወልዶ ተዋልዶ አብሮ መኖር የነበረውን እንዳልነበር እያራከሰ እያኮሰሰ የደረሰበትን አሳዣኝ ዝቅጠት ከንፈር እየመጠጥን ስንታዘብ ሰንብተናል። በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ፣ እልህ ተጋብተውም እንዱ እንዱን ለመብለጥ የቃላት ጦርነቶችና፣ ከሁሉም ጎራ የሚሰራጩ የተዛቡ ትርክቶች፣ በሶሻል ሚዲያ የቃላት ሰይፍ መማዘዝ፣ ጥላቻን በሕዝብ መካከል መርጨት በስፋት ሲደረጉ የቆዩበት ሁኔታ፣ በስፋት በተሰራጩ የታሪክም የፓለቲካም የተዛቡ ትርክቶች፣ እጅግ ሲጋነኑ የነበሩ ቁንጽል መረጃዎች፣ በሰፊው የተዛመቱ የፈጠራ ወሬዎችን ጨምሮ በማኅበረሰቡ መካከል፣ በተለይም ለዘመናት ኢትዮጵያን እንደ ሀገር በመገንባት ትልቅ ድርሻ ያላቸውን በኦሮሞና የአማራ ሕዝቦች መካከል ትልቅ ክፍተት እንዲፈጠር፣ የተወሰኑ የሕዝብ ክፍሎች ውስጥም ጥላቻ አየሰፋ፣ እየተጠናከረ እንዲመጣ አፍራሽ አሰተዋጽኦ በማድረግ ከሰሞኑ ለተቀሰቀስው ከጥላቻ የመጣ ጥቃት፣ እጅግ አሳዛኝና እሰቃቂ ድርጊቶች ሚና እንደነበራቸው መታወቅ ያለበት ይመስለኛል።
በተለይ በሕዝብ ቁጥር ትልቅ በሆኑት ብሔሮች በአማራና በኦሮሞ መካከል ቅራኔን፣ ጥላቻን፣ ጥርጣሬን የሚያጠናክሩ ትንኮሳዎች፣ በየመድረኩ፣ በጀርመን በእሥራኤል፣ በሌሎችም የዲያስፓራ የተቃውሞ ሰልፎች የተሰነዘሩ የጥላቻ፣ እንዱ ሌላውን በንቀት የሚያንኳስሱ ቃላቶችና ድርጊቶች፣ የተሳሳቱና የተዛቡ ትርክቶች በስፋት ሲካሄዱ እንደነበር የሚካዱ ሊሆኑ አይችሉም። ከዚህ አፍራሽና እጅግ ስስና ተሰባሪ የሆነውን የሀገሪቱን ሁኔታ፣ ተዋናዮቹ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ፣ ከግለሰቦች ጀርባ የሚገኙ የዶ/ር መረራ ጉዲናን አጠቃቀም ለመዋስ “የሚጋጩ ህልሞች” እንዲሁም ቅዠቶች፣ ሃሳቦችና ትርክቶች፣ በእነዚህ ትርክቶች ዙሪያም የተሰለፉ ሚሊዮኖች መኖራቸውን እነዚህ ሚዲያዎች፣ ሶሻል ሚዲያዎችና፣ አክቲቪስቶችና የፓለቲካ ልሂቃን ከግምት ውስጥ ሊያስገቡት አልቻሉም፤ ለማስገባትም አልተፈለገምም ነበር።የሴራ መልዕክቶች፣ ባልተጣሩና ለማጣራትም ምንም ጥረት ባልተደረገባቸው በዜና መልክ የሚቀርቡ የፈጠራም የተጋነኑም ወሬዎች በተለይ ሀገር ውስጥ በመሬት ላይ ለሚገኘው የገፈቱ ቀማሽ ሰላማዊ ሕዝብ የማይበጀው መሆኑ መረዳት ያስፈልግ ነበር።
ያደራጁት ኃይል በእጃቸው በሌለበት፣ አማራጭ ራዕይና ፕሮግራም ባላዘጋጁበት፣ አገርን ሊያረጋጋ፣ ሕዝብን ከጥቃት ሊከላከል የሚችል ወታደራዊና የጸጥታ ኃይሎችን ባላሰለጠኑበት፣ በማይመሩበት፣ ለዚህ ደግሞ መንግሥታዊ አቅሙም፣ ችሎታም፣ ስትራቴጂካዊ ጥናቶች ሆነ ቅደመ ዝግጅቶች ማንም ምንም በወጉ ባላሰቡበት፣ ባልተዘጋጁበት ሁኔታ በስልጣን ላይ የሚገኘውን ብዙ ተግዳሮቶች የገጠመው ነገር ግን ለውጥን ለማምጣት ደፋ ቀና ሲል የቆየውን የለውጡን አመራር በከፍተኛ ርብርብ ለማዋከብና ለመሸርሸር የተሄደበት ርቀት ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ይመስለኛል።
ሀገራችንን ኢትዮጵያን አጣብቆ የያዘውን መንግሥታዊ ኃይል ቢዳከም፣ እነዚህ የታሪክም የፓለቲካ መሠረት ያላቸው ልዩ ልዩ ቅራኔዎች በየቦታው ቢፈነዱ፣ በሕዝብ መካከል የእርስ በእርስ ግጭቶች ቢበራከቱ በብዙ አቅጣጫና ውስብስብ የብሄር ቅራኔዎች፣ ሌሎች ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና፣ ማኅበራዊ ችግሮች የተጠመደች ሀገራችንና የኢትዮጵያ ሕዝብ ወዴት ሊወስዱ እንደሚችሉ ከግምት ማስገባት አስፈላጊና ወሳኝ ይሆናል። እንደ ሀገር መኖር አለመኖር፣ እንደ ሀገር መቀጠል ወይንም አለመቀጠል የምንችልበት ወይንም የማንችልበት የታሪክ መጋጠሚያ ላይ ደርሰናል። በአንድ አካባቢ የሚጀመር እሳት፣ ወደ ሌላ አካባቢ ሊዛመት እንደሚችል ወደ ሰደድ እሳት ሊያድግ፣ ሊሸጋገር ወደሚችል ደረጃ እንደሚደርስ ብዙ እውቀትና ማሰብ የሚፈልግ አይመስለኝም። በሌላም በኩል ደግሞ የእርስ በእርስ ግጭቶች እየተቀጣጠሉ፣ አድማሳቸው እየሰፋ ሊሄድ እንደሚችል፣ በአንድ አካባቢ የተነሳ ግጭትና የግጭቱ ጥቃት ስለባ የሆኑ ወገኖች በሌላ አካባቢ በሚገኙ የአጥቂዎች ወገኖች ላይ የብቀላ ጥቃት፣ የብቀላ ብቀላ አድማሱ አየሰፋ፣ እየተዛመተ፣ ማንም ምድራዊ ኃይል ሊቆጣጠረው ወደማይችል ምድራዊ ሲኦል ሊለወጥ የማይችልበት ምክንያት አይኖርም።
ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፦
ዛሬ ትላንት አይደለም። ትላንት የሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ የአብዛኛው የዲያስፓራ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ትኩረትና የትግሉ ግብ፣ የትግሉም ዒላማ በሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሲዘወር በነበረ ግፈኛና ጨካኝ አገዛዝ ላይ ያነጣጠረ እንደነበር የሚካድ አይደለም። ከጎንደር እስከ ሐረር፣ ከባሌ ዶሎ እስከ ወሎ፣ ከሐረር እስከ ባሕር ዳር የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኦሮሞ እሰክ አማራው፣ ከጋምቤላ እሰከ ሶማሌ፣ ከአዲስ አባባ እስከ አምቦ ትግሉ ከመንግሥት ኃይሎች፣ ከጨቋኝና ግፈኛ ገዥዎችና የመጨቆኛ መሥራሪያዎቻቸው፣ ተቋማቶቻቸው ጋር ሲያፋፍም የነበረ፣ አለፍ ካለም የእነሱ ጥቂት ደጋፊዎች ላይ ያነጣጠረ እንደነበር የማይረሳ ነው።
ዛሬ ግን ቅራኔው፣ ግጭቱ፣ ጥላቻው የጎንዮሽ በሕዝብ መካከል ሆኗል፤ በማኅበረሰቦች መካከል ሆኗል። ትልቁ አደጋ ይህ ከሰሞኑ የተከሰተውና ነጥሮ የወጣው እውነታ ከዚህ ጋር የተያያዘ መሆኑ የሚያጠራር፣ የሚያሻማ ሊሆን አይችልም። ዛሬ ቅራኔው ለዘመናት አብረው በኖሩ ማኅበረሰቦችና በሕዝብ መካከል መሆኑ ነው። ይህ እውነታ በስፋትና በጥልቀት በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚታይ እጅግ አደገኛ ሂደት መሆኑ ግልጽ አየሆነ ነው።
ይህን ልዩና እጅግ አስጊ ሁኔታ ለመለወጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ፣ ዘዴዎች፣ ብልሃቶች ይጠይቃል። መንግሥታዊ የማድረግ አቅም የመኖር አለመኖር ብቻ ሳይሆን የመንግሥት እርምጃዎች፣ የመንግሥት ድርጊቶች ሊፈጥሩ የሚችሉትን አሉታዊ የሆነ የአንድ ወይንም የሌላ ወገን የአጸፋ ምላሽ ለመቋቋም የሚያስችል፣ ያልተጠበቁ ትላልቅ አደጋዎች በሕዝብ ላይ እንዳይደርሱም እስቀድሞ ችግሮቹ በቀጥታ የሚመለከታቸውና ከችግሩ ጋር ተፋጠው የሚገኙ የመንግሥት መሪዎችና ልዩ ልዩ የመንግሥታዊ ተቋማት ሃላፊዎች ሊደረግ ብቻ የሚችል የቢሆንስ ትንታኔም የሚያስፈልገው ነው። የመንግሥት መሪዎች ወደ ስልጣን ያመጣቸው ፓርቲና ሕዝብ ውስጥ ያላቸው ቅቡልነት፣ ስትራቴጂካዊ አስተሳሰብ ዝግጁነት፣ በየጊዜው የሚፈተሽ ዕቅድና ይህንኑ የማስፈጸሚያ/የ ማድረግ አቅም የሚሰጡ ልዩ ልዩ የመሣሪያዎች ሳጥን በአግባቡና በብቃት ማዘጋጀትን የሚጠይቁ ናቸው። ድርብርብና በየደረጃው የሚከናወኑ ተግባራት ያሉበት ውስብስብ ሁኔታ ነው። በመንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ በአገር ሽማግሌዎች፣ በሃይማኖት አባቶች፣ በልሂቃን፣ በልዩ ልዩ ኃይሎችና ባለድርሻዎች በጋራም፣ በተናጠልም ሥራዎችን ይጠይቃሉ።
የኢትዮጵያን ሰላምና፣ ደህንነት፣ መረጋጋት የሚፈልጉ ዜጎች ሁሉ ይህን አስጊና አደገኛ በሕዝባችን ደህንነት፣ በሕዝባችን አብሮነት፣ በኢትዮጵያ ሃገራዊ ህልውና ላይ የተደነቀረ ከባድ አደጋ ለመሻገር ከተፈለገ ይህን አደጋ ከሚያባብሱ፣ ከሚቀጣጥሉ ቃላት፣ ቅስቀሳዎች፣ ቁንጽልና በቅጡ ያልታሰቡባቸው፣ ያልተጠኑም በርካታ የሀሰትም ወሬዎች፣ የተዛቡና በምንም መልኩ መቼም ሙሉና ሁለንተናዊ እይታን ሊሰጡ የማይችሉ ትርክቶች በሚዲያና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ከማሰራጨት መቆጠብ የግድ ይሆናል። በምትኩ የሚዲያዎች ሚና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ መስጠት፣ ማኅበረሰቦች እንዲቀራረቡ የበኩላቸውን ሚና መጫወት ያለባቸው ይመስለኛል። ግጭት ሳይሆን ውይይት፣ ቅራኔን ሳይሆን መግባባት እንዲመጣ ገንቢ ጥረቶች ማድረግ የሁሉም የፓለቲካ ልሂቃንና የሚዲያዎች፣ በሀገር ቤትም በውጭ ሀገርም የሚገኙ የብሄርም የሕብረ ብሄርም ዓላማ ያነገቡ አክቲቪስቶች ታሪካዊ ሃላፊነት ነው ብዬ አምናለሁ። በተለይም እሳቱ የማይደርስባቸው፣ በእነሱም በቤተሰቦቻቸው፣ በዘመዶቻቸው ላይ ጭምር ሊደርስ የሚችል የማይመስላቸው በውጭም በሀገር ውስጥም የሚገኙ የየብሔሩ ልሂቃን፣ የየብሔሩና በሕብረ ብሔርም ኢትዮጵያዊነትና ዜግነት ፓለቲካ የተደራጁ አክቲቪስቶች ሁሉ ቆም ብለው ማሰብ የሚገባቸው ወቅት አሁን መሆኑን በጥብቅ ለማሳሰብ እፈልጋለሁ።
የሚቀጥለው እሳት ወደ ሰደድ እሳት እንዳያመራ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ለትላልቆቹ የፓለቲካ ልዩነቶች መፍትሄ ማፈላለግ ያስፈልጋል። የተጀመረው አዝጋሚና ብዙ ተግዳሮቶች የገጠመው የለውጥ ሂደት ከእናካቴው እንዳይቀለበስ ሁሉም የድርሻውን ማበርከት አለበት ብዬ አምናለሁ። ይህን አጋጣሚ ለመጠቀም ያቆበቆቡ፣ ይህን ሁኔታ ለመጠቀም ሰሞኑን በሀዘን የተመለከትነውን ጥቃት በማጦዝ፣ በማራገብ ጮቤ የረገጡ፣ ልዩ ልዩ ዘዴዎችንም በመጠቀም ከተለያዩ የፓለቲካም፣ የሚዲያም ተዋናዮች ጀርባም በመሆን ቅራኔዎችና ችግሮች እንዲሰፉ፣ እንዲባባሱ የእነማን ዘርፈ ብዙ ጥረት እንደሆነ የሚጠቁሙ በርካታ መረጃዎች በየጊዜው እንደሚያሳዩ ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ይመስለኛል። ከመሸጉበት ለማንሰራራት፣ ብሎም የኢትዮጵያን ሃገረ መንግሥት ማዕከል ዳግም ለመቆጣጠር ያላቸውን ቀቢጸ-ተስፋ ዕውን ለማድረግ፣ የለመዱትንም ግፈኛ መንግሥታዊ ሽብርና መንግሥታዊ ዘረፋ በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኪሳራ ለማስቀጠል ሙከራቸውን ከማድረግ ወደ ኋላ የማይሉ እኩይና ከታሪክ የማይማሩ ያረጁ ያፈጁ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን የፓለቲካ አስተሳሰብ ጋር እራሳቸውን ማለማመድ፣ ካለፈው ወንጀሎቻቸውና ውድቀታቸው መማር የማይችሉ ድኩማን የፓለቲካ ድርጅች እንዳሉ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍንትው ብሎ የሚታይ ሃቅ ነው ብዬ እገምታለሁ።
እነዚ ህይሎች የራሳቸውን ጥቅምና ያጡትን የበላይነትና ፈላጭ ቆራጭነት ከማየት በስቲያ፣ በሕዝብ ላይ ጭነው ከነበሩት የበላይነት ባሻገር ለሕዝብ መከራ፣ ለሰው ልጆች ጉስቁልና ቁብ የማይሰጣቸው ናቸው። የሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን ደምና እንባ ለ27 ዓመታት አንደ ጎርፍ እንዲፈስ ያደረጉት እነዚህ የፓለቲካ ዓመታት ይህን እኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት የጋራ አገራችን ኢትዮጵያ አገራዊ ትርምስ ውስጥ ብትገባ ፈጽሞ የማይጨነቁበት መሆኑን ሲጀምሩም የተነሱበት የፓለቲካ ዓላማ፣ ታሪካቸው፣ እስካሁንም የቀጠሉበት አንደበታቸው፣ የተካኑበት መሰሪነትና ተንኮል ያረጋግጣል። “እኛ የኢትዮጵያ አዳኞች ነን” በሚል ሽፋንና ነገር ግን የማዕከላዊ መንግሥትን ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ቀቢጸ-ተስፋቸው እሁንም በትዕቢትና በትምክህት ተወጥረው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ አገራችንን ወደ ሁለንተናዊ ትርምስ ጎዳና ሊያስገባ የሚችል ዕድል እንዳንሰጣቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት በጽኑ አምናለሁ።
የኢትዮጵያ ምድር ከጥንት ከሺህ ዓመታት በፊት ዛሬ የሚገኙ ሕዝቦች ያልነበሩበት፣ አንዱ በአንድ ዘመን ከደቡብ ተነስቶ ሌሎችን ማኅበረሰቦች አስገብሮ መሬት ሲይዝ፣ በሌላ ዘመን ሌላው ይህኑ አጸፋ ሲያደርግ፣ ሲስፋፋ፣ በአመዛኙ ደግሞ የየብሔሩ ገዢዎች፣ በዓለም ላይ እንደነበሩ ገዥዎች ሁሉ የተደረጉ ሂደቶች ናቸው። ሌሎች የዓለም ሃገሮች ከተመሠረቱበት የሀገራት ምሥረታ ሂደት ምንም የሚለየው የለም። ባርያ ፈንጋዩና አስገባሪው ደግሞ የአንድ ብሔር አንድ ቋንቋ የሚናገሩ ብቻም አልነበሩም። በልዩ ልዩ የታሪክ ምዕራፎች የየማኅበረሰቡ/ብሄሩ ንጉሶችና ገዢዎች፣ አስገባሪዎች፣ ተስፋፊዎች በመሆን ተፈራርቀዋል። የልዩ ልዩ ብሔሮች/ማኅበረሰቦች ገዢዎች ከመሃል ወደ ደቡብ፣ ከደቡባዊ ከምሥራቃዊ ኢትዮጵያ ተነስቶ እስከ መሃላዊ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እስከ ሲሜናዊና ሰሜን ምሥራቃዊ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዝመት በመስፋፋት ሲፈራረቁበት የቆዩበት የረጅም ዘመናት ሂደት ነው። የረጅም ዘመናት ታሪካችን እያንዳንዱ ማኅበረሰብና በየዘመኑ፣ በሰፊው የታሪካችን ምዕራፎች የነበሩ የብሔርም የሕብረ-ብሔርም ገዥዎች በቀደሙት ዘመናት አጣኋቸው ያላቸውን መሬቶች ለማስመለስ ዳግም በኃይል ሲስፋፋ የነበረበት ውጥንቅጥና አባይን በጭልፋ እንደሚባለው ረጅምና ተጽፎ ያላለቀ፣ ተጽፎም ሊያልቅ የማይችል፣ የብዙ ዘመናት የመጥበብ፣ የመስፋት ሂደቶችና ተደጋጋሚ ኡደቶች ብቻም አልነበሩም። የንግድ ልውውጥ፣ የማኅበራዊ ግንኙነቶች፣ የቋንቋና ባህል መወራርስና መዳቀል የነበሩበትም ሂደት ነበር። ለዳር ድንበርና ለሕዝብ ክብር ለኢትዮጵያ አገራዊ ግንባታ በኦሮሞም፣ በአማራም፣ በአፋር፣ በትግሬ፣ በወላይታ፣ ጉራጌ በሌሎችም የቋንቋና የባህል ማኅበረሰቦች ባፈሯቻቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሀገራዊ እርበኞች፣ አንጸራቂ ጀብድ በፈጸሙ፣ ታላላቅ ጀግኖችና የጦር መሪዎች መስዋዕትነት የተገነባ ሕብረ-ብሔራዊ ኢትዮጵያ ማንነትና ሃገራዊነት የታሪክ ሂደትም ነው። ይህ ውስብስብ የታሪክ ሂደት በ150 ዓመት ታሪክ ትንሽ አጭር መነጽር ሊታጠር፣ ሊገደብ የማይችል ሰፊ የዘመናት የታሪክ ባህርን በጭልፋ በሰፈረ፣ እጅግ ቁንጽል የሆነ የነፍጠኛ የሰባሪ የገባር/የአስገባሪ ትርክትና እንድምታ የማያይወክለው፣ የማይገልጸው ሰፊና ጥልቅ የሆኑ የታሪኮቻችን ገመዶችና ክሮች የልዩ ልዩ ማኅበረስቦች መስተጋብሮች፣ ግንኙነቶችና፣ የሂደቶች ውጤት ነው።
ዋናው፣ ትልቁ ሃቅ ግን ከዚህም ከዚያም ወገን ማንም የታሪካችን ሙሉ እውቀት፣ ሙሉ መረጃ እንኳን በዚህኛው በወዲያኛውም ሕይወቱ ሊኖረው አይችልም። ታላላቆቹና በዓለም ደረጃ የሚታወቁት የታሪክ ጸሐፍት እነ አርኖልድ ቶዬንቢ (Arnold J. Toynbee)፣ ኤድዋርድ ጊበን (Edward Gibbon)፣ ዘመናዊና ትላልቅ ስም ያላቸው ኒያል ፊርግሰን (Niall Ferguson)፣ ፈርናንድ ብራውዴል (Fernand Braudel)፣ ሌሎችም ታዋቂ የታሪክ አጥኚዎች የሀገራቸውንም ሆነ የዓለምን ታሪክ በሚመለክት የጻፏቸው ሁሉንም የታሪክ ምዕራፎች፣ ሁሉንም ታሪካዊ ክንውኖች፣ ሁሉንም ታሪካዊ መረጃዎች፣ ሁሉንም ታሪካዊ ሂደቶች አጣርተው በሙሉ፣ ፍጹም በሆነ እውቀት/ዩኒቨርሳል የታሪክ ዘይቤም የታሪክ ሙሉ እይታ ሊኖራቸው እንደማይችል የታወቀ ሃቅ ነው። የብዙ አገሮች ታላላቅ የታሪክ ጸሐፊዎች በእያንዳንዱ የታሪክ ምዕራፍ አስከ ዛሬ የሚወዛገቡባቸው በርካታ የታሪክ ኩነቶች፣ የታሪክ ትርጓሜዎች፣ የታሪክ ዘይቤዎች እንዳሉ ራሱ የኢትዮጵያን ታሪክ በራሳቸው ልክ ለሚፈልጉት የፓለቲካ አጀንዳ ቀንጭበውና ቆንጽለው የሚያቀርቡ የየብሔሩ ልሂቃን የሚያጡት ሃቅም አይደለም።
እነዚህ አጨቃጫቂ፣ አወዛጋቢ የሆኑት በሁሉም ወገን ቁንጽል የሆኑና ማንም በምንም መልኩ ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ እንደበርክታ የታሪክም የማኅበራዊ ሳይንስ የመነጩ ጥናትችና ትርክቶች ሙሉ እይታ፣ ሙሉ እውቀት፣ ሙሉ ግንዛቤ፣ እንደሌላቸው ይታወቃል። የተፈጥሮ ሳይንስ በተለይም ከአንስታይን የሬላቲቪትይ የፊዚክስ ቲዎሪ (Albert Einstein’s Relativity Theory) ግኝት በኋላ ሁሉን አዋቂና ሁሉን ተንባይ ነኝ የሚለው ማንነቱ ላይ በደረሰብት ቀውስ ሳቢያ የሳይንሱ ማኅበረሰብ የሚቀበለው በአመዛኙ ፍጹም የሆነ፣ ሙሉ የሆነ እውቀት፣ ዩኒቨርሳል የሆነ እርግጠኝነት፣ የትንበያ አቅምም እንደሌለ ነው። ሌሎች ታላላቅ የሳይንስ ፈላስፎች ኢ-እርግጠኝነት (Uncertainty principle) የሚል ስያሜ የሰጡት የተፈጥሮ ሳይንስ ንጉስ የሆነው ፊዚክስ ተፈጥሮን ሙሉ በሙሉ፣ ሁሉን ለማወቅና የሚሆነውንም ለመተንበይ የማይችል፣ በእጅጉ ያለውን ውሱንነት ያጠናከሩ፣ ልዩ ልዩ የእውቀት ዘርፎችም ከኢኮኖሚክስ እስከ የፓለቲካ ሳይንስ የእውቀት ዘርፎች ጠቅላይ ሊሆኑ፣ ሙሉና የወድፊቱንም በፍጹም እርግጠኝነት ሊተነብዩ እንደማይችሉ፣ ልዩ ልዩ የእውቀት ዘርፎች በተወሰነ አውድ፣ በተወሰነ ካባቢ ውሱን ለሆነ ግንዛቤና እውቀት፣ ለውሱን ችግሮች መፍቻ ዘይቤዎች/መሣሪያዎች ብቻ እንደሆኑ፣ የወደፊቱም የመተንብይም ሆነ ያልፈውን የታሪክም የማኅበረሰብን ውጥንቅጦች በሁለንተዊና ጠቅላይ/ዩኒቨርሳል በሆነ መልኩ ለማወቅ እንደማይቻል እንዱ ሌላውን ሲገለብጡ፣ የኖሩ ንደፈ ሃሳቦች፣ ጽንሰ ሃሳቦች (theories)፣ የዓለም እይታዎች (paradigms)፣ ልዩ ልዩ የማኅበረሰባዊና የተፈጥሮ ሳይንስ ፍልስፍናዎች፣ እንዲሁም የዘይቤዎች (methods/models) የትየለሌ መሆናቸው የሚያረጋግጡት ይህንንኑ ነው። በብዙዎች ዘንድ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ግንዛቤና መግባባት የተደረሰ ይመስለኛል።
ስለዚህ የኢትዮጵያ ልሂቃን በተለይ በፓለቲካው ትልቅ ሚና ያላችሁ የታሪክና የህብረተሰቡን ችግሮች ሁሉ በሚመለከት አለን የምትሉት ግንዛቤ ውሱንነት መቀበል። ትህትና ብትህውትነት (humbleness and humility) እኛ ሁሉን እናውቅለታለን ብለው ለሚገምቱት ሕዝብና ማኅበረሰብም የተሻለው ምልከታ ይመስለኛል። ምክንያቱም ፍጹም እወቀት፣ ፍጹማዊ እውነት አለኝ ለማለት በማይቻልበት እጅግ ሰፊና ጥልቅ የተፈጥሮ፣ የታሪክ፣ የማህብረሰብም ሂደቶች፣ ጉራማይሌዎች፣ ጓዳ ጎድጓዳዎች፣ ጉራንጉሮች፣ ዥጉርጉር ሁኔታዎችና ሂደቶች የነበርን ሕዝቦች በመሆናችን። የሰው ልጆች ሕይወትም ሆነ የዓለም ሕዝቦች ታሪክ አካል የሆነ የኢትዮጵያ ታሪክ (ታሪኮች) ግራጫ ቀለም ያላቸው እንጂ ነጭና ጥቁር ባለመሆናቸው የኋላ ታሪኮቻችን፣ የሚጋጩ ትርክቶች ያን ወይንም ይህን ቁንጽል የታሪክ ጠብታ ይዞ ሙሉ እውቀት ባለቤት ነኝ፤ በሞኖፖል እውቀት እኔ ጋር ብቻ የሚል ስሜት ያላቸው የየብሄሩ ልሂቃን ቁንጽ የታሪክ ትርጉሞች/ትርክትን መሠረት አድርገው የሚሰነዘሩ ሽኩቻዎች የሕዝብ፣ የማኅበረሰብ ቅራኔዎች፣ ጥላቻና፣ ግጭቶች፣ ጥቃቶች መንስዔም እየሆነ የመጣበት ይህ እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ እሁን ላይ መቆም ይገባዋል። ለአገርና ለሕዝብ የተሻለው፣ የሚበጀው መንገድም ይህ ይመስለኛል። ሁለተኛው አማራጭ ሕዝብን ማጫረስ፣ ሀገርን ማፍረስ፣ ሁሉም በእሳት የሚጫወት ተዋናይ በሰደድ እሳቱ ወላፈን እራሱም ሆነ በምድር ላይ የሚገኙ የሚወዳቸውም ሳይቀሩ የመለብለብ፣ የሚጠበስ ምድራዊ ገሃነም ብቻ ናቸው።
የኦሮሞም የአማራም ከዚያም የደቡባዊና የምሥራቃዊ ኢትዮጵያን፣ እንድሁም የኦሮሞን ታሪክ በአግባቡ አላካተተም ወይንም አይወክልም የሚባለው የግዕዝ ስልጣኔ ታሪክ፣ ሌላም ካለ ሁሉም ወገን የኔ የሚላቸው ትርክቶች፣ ልዩ ልዩ ታሪኮች ወይንም የሚጣጣሙበት ወይንም የሚቀራረቡበት መንገዶችና ዘዴዎች መፈለግ፤ ወይንም ደግሞ ተመሳሳይ የታሪክ አረዳድ ያልነበራቸው አገሮች፣ የሚጋጩ ትርክቶች አገራዊ ትርምስ የፈጠሩባቸው የሌሎች ሀገሮችን ሕዝቦች ልምድ ቀስሞ ከሁሉም የተውጣጣ፣ ይህንኑ የሚያጠና ባለሙያዎች የሚገኙበት ኮሚሽን የሚቋቋምበት ሁኔታ ቢመከር ምናልባት አንዱ የመፍትሄ አካል ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ቀደም ሲል እንደተነሳው የአገራችን ትላልቅ የፓለቲካ ቅራኔዎች አንዱ ከአለፉ ታሪኮቻችን የታሪክ አረዳድና አተረጓጎም ልዩነቶች፣ የሚጋጩ ትርክቶች ላይ የሚመነጩ በመሆናቸው ከፍተኛ ትኩረትና ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል እላለሁ።
ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት፣ ማንም ተሸናፊ የማይሆንበት በሀገሪቱ ዋና ዋና ችግሮች ዙሪያ መፍትሔ ተኮር ውይይቶች በየደረጃው የሚደረጉበት ሁኔታዎች መፈለግ አስፈላጊ ይሆናል። ሁሉም ባለድርሻዎች አገሪቷን እሁን ላይ ከገጠማት የህልውና አደጋ ለመታደግ ከለውጡ መሪዎች ጋር በመነጋገር፣ በለውጡ መሪዎችም በኩል ጉልህ ድምጽ ያላቸውን ባለድርሻዎች፣ የየብሄሩን ልሂቃንና የፓለቲካ ኃይሎች ሁሉ ፍላጎታቸውን በግልጽ ወደ ጠረጴዛው እንዲያቀርቡ፣ ውይይቶች እንዲደረጉ፣ ሰጥቶ የመቀበል፣ ብሎም ሀገራዊና ብሄራዊ መግባባት ላይ መድረስ እንዲቻል መድረኮችን የማመቻቸት ጊዜው አሁን ነው የሚል የሚል ሃሳብ አቀርባለሁ።
የሁሉም ዜጎችና የቋንቋና የባህል ማኅበሰቦች ጥቅምና መብቶች ያልተከበሩባት ኢትዮጵያ የማንም የየትኛውም ብቸኛ ማኅበረሰብ/ወይንም ብሔር መብት፣ ፍትህና ጥቅም ለዘለቄታው ሊከበርባት እይችልም። የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የሌሎችም ማኅበሰቦች ልሂቃንና የፓለቲካ ኃይሎች ቆም ብለው የማንም የማትሆን አገር ሁላችንም ወደ ምድራዊ ሲኦል የሚወስድ መንገድ ከመግፋት እጅግ የተሻለው አመራጭ ለሁሉም ጥቅም፣ ለሁሉም እኩልነት፣ መብቶች፣ ለሁሉም ድምጽና ክብር፣ ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያን እንድትሆን ተነጋግሮ፣ ተግባብቶ፣ ፍኖተ ካርታውን፣ የጨዋታውን ሕግ፣ ሂደቱን፣ የሥነ ምግባር ደንቡን… ወዘተ የሚመለከቱ እንዲሁም ዋና ዋና ፓለቲካዊ ልዪነቶች ላይ ዉይይቶች በማድረግ፣ ወደ መግባባት ላይ ለመድረስ ማሰብ ያለባቸው ጊዜ አሁን ይመስለኛል። ይህ ጥሪ ለኦሮሞ፣ ለአማራ፣ ለሶማሌ፣ ለአፋር፣ ለትግራይ ለሌሎችም ማኅበረሰቦች ልሂቃን፣ የፓለቲካ ኃይሎች፣ እንዲሁም የሕብረ ብሔር የኢትዮጵያዊነት የዜግነት የፓለቲካ ኃይሎች በሙሉ ለህሊናም፣ ለታሪካችሁም እጅግ የተሻለው አማራጭ መሆኑን በአንክሮ ማሰብ ወቅቱ አሁን ይመስለኛል።
በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ ሕብረ ብሔር ኢትዮጵያውያን የዜግነት መብቶችና ጥቅሞች ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዲስተናገድ፣ እንዲከበሩ፣ እንዲረጋገጡ የሚያስችል ሂደት መጀመርም አለበት። የየትኛውም ብሔር የበላይነት (hegemony)፣ በየትኛውም አካባቢ ይህ የኔ ለእኔ ብሔር ብቻ ነው ሌላው ዜጋ መጤ ነው፣ ሰፋሪ ነው… ወዘተ የሚሉ የተዛቡና ብዙ ሚሊዮን ዜጎችን በገዛ አገራቸው ባይተዋር ያደረጉ፣ ስጋትን፣ የነገን ተስፋ አለማየት፣ ከሰሞኑ ደግሞ በንጹሃን ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ሕይወት ያስቀጠፉ አስተሳሰቦችና ሥነ ልቦናዎች የሚለወጡበት ሁኔታ በቅጡ መታሰብ፣ መፍትሔም ማግኘት አለባቸው። በተጨማሪም ይሄ “የኔ ብሔር፣ ይሄ የኔ አካባቢ ብቻ ነው”፣ የሚሉ ኢ-ፍትሃዊ የሆኑ ጸረ-ዴሞክራሲያዊ አመለካከቶች “የኔ” ለተባለውም ብሔር ሕዝብ ጥቅምንም መብቶችንም ለዘላቂው ሊያስከብርና ሊያስቀጥል አይችልም። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሌለበት፣ የሕግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት፣ ተጠያቂነትና ግልጽነት የሌሉዋቸው የፓለቲካ ስርዓቶች በስመ ብሄር፣ ወይንም በሀገራዊ ብሄርተኝነት ስም ወደ ስልጣን የመጡ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነኖች ብሄሬ በሚሉት ሕዝብ ላይ ያደረሱትን መከራ፣ ስቃይና፣ እልቂት በታሪክም አሁን ላይ በዘመናችንም ከበቂ በላይ ሁላችንም የታዘብን፣ ያየን ይመስለኛል።
በአንድ ሀገር ውስጥ ግማሹ የበኩር ልጅና አንደኛ ዜጋ፣ ገሚሱ የሀገሪቱ ሕዝብ ደግሞ የእንጀራ ልጅና ሁለተኛ ዜጋ፣ ከዚያም ወረድ ብሎ በስጋት በፍርሃት፣ ያለዋስትና እየኖረ የሚቀጥልባት ኢትዮጵያ እንደ እንድ የጋራ አገር፣ በጋራ አብሮ ለመኖር ሊያዘልቁ የሚያስችሉ አይሆኑም። ይህን እስከፊና ለ26 ዓመታት የተንሰራፋ፣ ዛሬም ሊደገም፣ ተጠናክሮ ሊቀጠልበት የሚሞከርበት፣ ብዙ ሚሊዮኖች አማርኛ ተናጋሪ ይሁኑ እንጂ ከኦሮሞ፣ ከጉራጌ፣ ከወላይታ፣ ከትግሬ፣ ከከንባታ፣ ጋሞ፣ ከሶማሌ አፋር፣ ከሌሎችም ማኅበረሰቦች ቅይጥና ቅልቅል የሆኑ፣ ወይንም በሥነ ልቦናም፣ በአመለካከትም፣ የትኛውም ብሔር ሳጥን ውስጥ ሊገፉና ሊከተቱ የማይችሉ፣ ነገር ግን ሁሉንም ብሔሮች/ማኅበረሰቦች የሚወዱ፣ አብሮ የኖሩ፣ አፍቅሮ፣ ተጋብቶና ተዋልዶ፣ በልዩ ልዩ ማኅበራዊና ሰዋዊ ገመዶች የተሳሰረ፣ በደም በአጥንት የተለሰነ የልዩ ልዩ ማኅበረሰቦች የተገኙ “ከአስገባሪነት”፣ “ከነፍጠኝነት”፣“ከሰባሪነት” ጋር ምንም ግኙነት የሌላቸው፣ ከኢትዮጵያዊነት ሌላ ቤት የሌላቸው፣ ብዙ ሚሊዮን ዜጎቻችን በአዲስ አበባ አካባቢዎች፣ በሐረር፣ በድሬ ዳዋ፣ በባሌ፣ በአዳማ፣ በአሰላ፣ በአዋሳ፣ በልዩ ልዩ ሌሎች የሀገሪቱ የከተማ፣ ከተማ ቀመስና የገጠር አካባቢዎች ሁሉ ሙሉ መብቶቻቸው፣ ደኅነታቸው፣ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሞ፣ በደቡብ በሌሎችም አካባቢዎች መከበር፣ መረጋገጥ የሚቻልበት ሁኔታዎች፣ ውይይቶች፣ ድርድሮች፣ መግባባቶች መደረስ ይኖርበታል።
በሀገርም ውስጥ በውጭም የምትገኙ የምታውቁኝም የማታውቁኝም ወድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፦
ታላቁ የአሜሪካን ፕሬዝደንት አብረሃም ሊንከን (Abraham Lincoln) የአሜሪካ ጥቁ ር ሕዝቦችን ከባርነት ለማላቀቅ በተደረገው የደቡብ ባሪያ አሳዳሪ ኮንፌደሬት ሠራዊትና የሰሜኑ የአንድነት ሠራዊቶች ከዛሬ 160 ዓመታት በፊት ባደረጉት የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት እንደተናገረው እርስ በእርሱ ተከፋፈለ ቤት ሊቆም/ሊዘልቅ አይችልም (“A house divided against itself cannot stand”)። አሁን እየታየ ባለው በሕዝብ ውስጥ የሚገኝ ቅሬኔና ትላልቅ ህመሞችና ስንጥቆች ሳቢያ የሁላችንም የጋራ ቤት የሆነችው ሀገረ ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ህልውናዋ መቀጠል አይችልም። ፍትሃዊነትና ልከኝነትን (just and fair) ማዕከል አድርገን አገራዊ የፓለቲካ ችግሮቻችንን ካልፈታን፣ ይህ ብዙ ሚሊዮን ዜጎቻችንን መብት አልባና አንገት አስደፊ ያደረገ፣ እስከፊና አሳፋሪ ሁኔታ እንደ አገር አብሮ ለመኖር አያስችለንም። ይህን አስከፊና ከሀገሪቱ ችግሮች አንዱ የሆነ አስተሳሰብና ሕጎች ለመለወጥ ሂደቶች መጀመር አለባቸው። ተጠያቂነት፣ ግልጽነት፣ ስልጣን የተገደበበት፣ ሕዝብ በርካታ አማራጮች ቀርበውለት በነጻ ርዕቱአዊ ምርጫ ሊወስን የሚችልበት የሕግ የበላይነትና ለአገራችን ውስብስብ ችግሮች መድኅን ሊሆን የሚችል ፌደራላዊም ዴሞክራሲያዊም የሆነ የፓለቲካ ሥርዓት ለዘላቂው ለሁሉም የቋንቋና የባህል ማኅበሰቦች፣ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ዜጎች ሊበጅና ሊጠቅም የሚችለው። በአንድ ጎን በየአካባቢው የሚገኙ የማኅበረሰቦች የስልጣን ምንጭነት፣ የባህል ቋንቋቸው እኩልነት የሚረጋገጥበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሙሉ መብቶች የሚከበሩበት፣ የሚረጋገጡበት መንትዮሽ ግብ ሊያጣጥም፣ ሊያስታርቅ የሚችሉ የመፍትሔ ሃሳቦች፣ ሌሎች መሰል አመራጮችንም ማፈላለግ የአገሪቱ የፓለቲካ ልሂቃንና የተደራጁ ኃይሎች በጥልቀት ሊያስቡበት የሚገባ አንገብጋቢና ከቀዳሚዎቹ የፓለቲካ ችግሮቻችን አንዱ ይመስለኛል።
የ20ኛ ክፍለ ዘመን ታላቁ የሳይንስ ሊቅ አልበርት አንስታይን (Albert Einstein) ከእምሮዋዊ አቅምና እውቀት፣ የወደፊቱን የማለም ምናባዊ ኃይል የበለጠ ነው (“Imagination is more important than knowledge”) እንዳለው ወቅቱ እውቀት አለን የምትሉ ልሂቃን ምናባዊ አቅማችሁን በመጠቀም የሀገራችንን የፓለቲካ ችግሮችና ተግዳሮቶች በውይይት፣ በድርድር፣ ለመፍታት ማሰብን በረጅሙ ማለምን ይጠይቃችሁሃል። ፓለቲካ የዕድሎች ጥበብ (“politics is the art of the possible”) ጭምር ነው ይባላል። ይህ አሻግሮ ማየትን፣ ተግዳሮቶችን ወደ መልካም ዕድሎች፣ አደጋዎችን ወደ ጥሩ አጋጣሚዎች ለመለወጥ ምናባዊ እቅምን መጠቀምንም የሚጠይቅም ጭምር ስለሆነ ይመስለኛል። ዊኒስተን ቸርችል (Winston Churchill) ታላቅ ከመሆን ጋር ታላቅ ኃላፊነትነትም አብሮ ይመጣል፣ ትልቅ ዋጋም ያስከፍላል (“The price of greatness is responsibility”) እንዳለው የብሄርና የሕብረ ብሄር የፓለቲካ ልሂቃን የሀገራችን የፓለቲካ ኃይሎች ለሀገራዊ ሰላም፣ ለሕዝብ መረጋጋት፣ ለፍትሃዊ የፓለቲካ ሥርዓት ምሥረታ፣ እናንተም ትልቅ ለመሆን ለምትችሉበት፣ በርዕቱአዊ ነጻ ምርጫ አማራጭ የፓለቲካ ፕሮግራሞቻችሁን አቅርባችሁ ካሸነፋችሁ 105 ሚልዮን ሕዝብ ለመምራት ለምትችሉበት ዴሞክራሲያዊ የፓለቲካ ሥርዓት በጋራ መሥርቱ። ቆምንለት ለምትሉት ብሄር/ብሄረሰብም ደኅነትና ሰላም፣ ጥቅምና መብቶች፣ እንዲሁ ለመላው ሕዝብ፣ ለሁሉም ኢትዮጵያውን ዜጎች፣ ለሁላችንም የጋራ ሀገር በታላቅ ኃላፊነት መንገድ ለመንቀሳቀስ መወሰን ብልህነትና አስተውሎት ነው። በታሪክ ፊት፣ በሕግም ፊት፣ በህሊናችሁም ተጠያቂ አያደርጋችሁም። በሰማይም እንዲሁ። ሀገር ከሌለ፣ ሀገር ውስጥ ሰላም መረጋጋት ከጠፉ ስልጣንም፣ ጥቅምም፣ ታላቅነትም፣ ማንም ምንም የሚያገኝበት ሁኔታ ሊኖር እንደማይችል፣ ሁሉም ሊጠፋፋ የሚችልበት ሀገራዊ ትርምስ ውስጥ እንደ ዋዛ ፈዛዛ ሊገባ እንደሚቻል በዛሬ ዘመን የተወለዱ የሊቢያን፣ የሶርያን፣ የመንን ሕዝቦች መከራና ስቆቃ እያዩ ያደጉ ታዳጊ ወጣቶች እንኳን የሚገነዘቡት እውነታ ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበት አጠቃላይ ሁኔታ እጅግ እንደሚያሳስበው እንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ፣ ሰሞኑን በተከሰተው የንጹሃን ዜጎቻችን ሕይወት መቀጠፍ፣ መቁሰልና መፈናቀል እንደሚያሳዝነው አንድ ሰብዓዊ ፍጡር፣ ለአማራ ወይንም ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የቋንቋና የባሕል ማኅበረሰቦች፣ ዜጎች በፍትህ፣ በሕግ የበላይነት፣ በማኅበራዊ ፍትህ፣ በዴሞክራሲ ፌደራላዊ የፓለቲካ ሥርዓት የሚኖሩባት ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን የበኩሉን አስተዋጽኦና ትግል እንዳደረገ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብይ አህመድ፣ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ለአቶ ለማ መገርሳ፣ ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ሌሎችም ለውጡን የመሩና በመምራት ላይ የሚገኙ የኢህአዴግ አመራሮች ይህን ጉዳይ በጥብቅ እንዲያስቡበት ከሀገሪቱ ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት፣ የብሔርም/ዘውግም፣ የሕብረ ብሔራዊ የፓለቲካ አመለካከትና ፕሮግራም ያላቸው ልሂቃንና ተጽዕኖ ፈጣሪ ባለድርሻዎች ሁሉ በአግባቡ የሚሳተፉበት ብሔራዊ የውይይት፣ የምክክር መድረኮች ማመቻቸት ሰዓቱ የደረሰ ይመስለኛል። መግባባትና እርቅ የሚደረስበት፣ እንዲሁም ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊያራምዱ የሚችል ፍኖተ ካርታ በሁሉም ባለድርሻዎች ተሳትፎ ወደ ስምምነት የሚያደርሱ መድረኮች የማመቻቸት ሂደት እንዲጀመር የግሌን ሃሳብ እንደ እንድ ኢትዮጵያዊ ለማቅረብ እወዳለሁ።
የሀገራችንን ችግሮችና ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት በማዘጋጀት ላይ ያለሁትን የግሌን ሰፋ ያለ ምልከታ በቀጣይ አቀርባለሁ። ፍትህ፣ ሰላም፣ የሕግ የበላይነት፣ የሕዝብና የሀገርን ጥቅም ማስቀደም በሀገራችን እንዲሰፍን፣ መቻቻልና አብሮ መኖር እንዲለመልም ቸሩ አምላክ ይርዳን!!
ነአምን ዘለቀ
ቨርጂኒያ፡ አሜሪካ -
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.