ሀገሬን ምን ነካት? (አባይነህ ካሴ (ዲ/ን)) ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

Home Forums Semonegna Stories ሀገሬን ምን ነካት? (አባይነህ ካሴ (ዲ/ን)) ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #11192
    Anonymous
    Inactive

    አብረው ማልቀስ እንጅ አብረው መቆም የማይችሉ ማሽንኮች ተፈልፍለው ሀገሬን ዕረፍት ነሷት። ለቅሶ ቤት ለመድረስ አዛኝ ቅቤ አንጓች ሁላ ከአለባበሱ እስከ አነጋገሩ አሳምሮ ይግተለተል እንደሆነ እንጅ፣ መቃብር ላይ ለመላቀስ ቀብር ለማስፈጸም ይደምቃል እንጅ ቁም ነገር ላይ ነጥፎ በጠመንጃ መፈላለጉን ትውልዱ ጀብድ አድርጎታል። እየሳቁ መግደል ሕገ-መንግሥቱ ሆኗል። የመግለጫ ቃል በማዥጎድጎድ የሸፍጥ ኑሮውን ተክኖታል።

    ሀገሬን ምን ነካት?
    አባይነህ ካሴ (ዲ/ን)

    ከሰቀቀናሟ ዕለተ ቀዳሚት ሰኔ 15 እስከ ዛሬዋ ዕለተ ሰኑይ ሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ሕይወታቸውን በጥይት ላጡት ሁሉ እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በቅዱሳን እቅፍ በገነት ያኑርልን፤ ለሐዘንተኞች በሙሉ ሁሉም ሟቾች የኢትዮጵያ ቤተሰቦች ናቸውና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ አረጋጊው መንፈስ ቅዱስ አጽናኝ መልአክን ይዘዝላችሁ። ሞት ማንም ይሞታል፤ ብርቆች ሲሞቱ ግን ራሱ ሞት ያነጋግራል።

    ከሩቅ ከአድማሱ ሥር የብርሃን ብልጭታ ሲታየን ‘ሊነጋ ነው’ ስንል፣ የሳቀልንን ወገግታ ተከትለን በተስፋ ዓለም ስንፏልል፣ ደረስንብህ ስንለው ብርሃናችን ወዴት ሔደብን? በጥሩር ፀሐይ ሰማይ ሥር የውኃ ሽታ ያዘለ ነጭ ባዘቶ ደመና ሊያዘንብልን ነው ስንለው እንዳንጋጠጥን መና ቀረ። በርኅቀት ሳይሆን በርቀት ተሰወረ። እኛን ቀርቶ ሊቃውንቱን አደናገረ። መጣ ያልነው እጃችን ገባ ያልነው ሁላ እየጣለን በረረ። ማር ያልነው ከምን ጊዜው መረረ፣ ወተት ስንለው የነበረው ከመቼው ጠቆረ፣ ሰላም ምነው ኢትዮጵያችንን አፈረ?

    ‘እኔ፣ እኔ፣ እኔ’ ከሚለው ባሕር ‘እኛ፣ እኛ፣ እኛ’ የሚል የቡድን ውሽንፍር ውስጥ ገባንና ኢትዮጵያን፣ ሀገሬን ረሳናት። እርሷም እነዚህ ከንቱዎች እንኳን ለእኔ ለራሳቸው የማይሆኑ ገልቱዎች ብላ መታዘቡን ቀጥላለች። የደሟን እንባ ወደ ውስጧ ሕቅ ብላ ታነባለች። ከላይ ከላይ ደማቅ ፈገግታ እያሳየች። የጣቷ አንጓዎች እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ሲሉ ሲገዳደሉ ዝም ብላ ታለቅሳለች። የጠጒሮቿ ዘለላዎች በራሷ ላይ ሲሻኮቱ በሐዘኗ በግናለች፤ በክፉ ጦር ልቧን ተወግታለች። ሀገሬን ምን ነካት? ምንስ ነው የሚበጃት?

    አብረው ማልቀስ እንጅ አብረው መቆም የማይችሉ ማሽንኮች ተፈልፍለው ሀገሬን ዕረፍት ነሷት። ለቅሶ ቤት ለመድረስ አዛኝ ቅቤ አንጓች ሁላ ከአለባበሱ እስከ አነጋገሩ አሳምሮ ይግተለተል እንደሆነ እንጅ፣ መቃብር ላይ ለመላቀስ ቀብር ለማስፈጸም ይደምቃል እንጅ ቁም ነገር ላይ ነጥፎ በጠመንጃ መፈላለጉን ትውልዱ ጀብድ አድርጎታል። እየሳቁ መግደል ሕገ-መንግሥቱ ሆኗል። የመግለጫ ቃል በማዥጎድጎድ የሸፍጥ ኑሮውን ተክኖታል።

    በተመቸ ግርድፍ ቃል ወንድምን በመዝለፍ ድንበር በመዝለል ከልክ በላይ በማለፍ አጥንት የሚወጋ የቃል ጦር በማላጋት እና በመወራወር ሀገር መቁሰሏን ማን የወደዳት ተረዳላት? ንክንኩ ድንጋይ ይፈልጣል፤ የመከራ መዓት በአፍላጋቱ ይጓፍጣል፤ አላውቅም የሚል ጠፍቶ ሁሉም ሁሉን ያውቃል። አዎ ሁሉ ዐዋቂ ሲሆን ሁሉም ይታመማል ያን ዕለት ያን ሠዓት መድኃኒት ይጠፋል።

    ለሞቱት አሟሟት የሰማነው ትርክት ልብ አያሳርፍም፤ ገና አበቅ አለበት። እርሱ ሲጠራ የሚታይ ለጊዜው ግን የተሸፈነ እውነት እንዳይኖር ያሰጋል። ከአንድ ወገን ብቻ የሚሰማ በጥፍር የሚያቆም ንግግርም ቢሆን ታማኝነቱ ምን ጊዜም ከአጠራጣሪነት አይዘልልም። ጊዜ እያወጣ የሚያሰጣው እውነት ይኖራል።

    ወታደር ዘር የለውም፤ ‘እኔ የኢትዮጵያ ወታደር ነኝ’ ሲል የነበረውን መልካም ወላዲቷ አምጣ የወለደችውን ጀግና እንደዋዛ ማጣት አለው ብዙ ንዴት፣ አለው ብዙ ቁጭት። ገዳይ የተባሉት ወይ በተኩስ ልውውጥ፣ ወይ ራስን በመግደል እየተባለ ሞታቸው ይነገራል። አይታመንም ባይባልም ተጠግቶ ላየው ምኑም አያሳምንም።

    አንደኛ፡- ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ባሕር ዳር አጠገብ ዘንዘልማ በሚባለው አካባቢ መገደላቸው መነገሩ ጥርጣሬውን ከፍ ያደርገዋል። እኒህ ሰው ተሳዳጅ (fugitive) ሆነው ባለበት ጊዜ አብሯቸው ከነበሩም እንኳ ከጥቂት ተከታዮች በስተቀር ብዙ አጃቢዎች እንደማይኖሯቸው ይታወቃል። ዘንዘልማ ከባሕር ዳር ከተማ ዓባይን ተሻግሮ ያለ አካባቢ እንደመሆኑ በርከት ያለ አጃቢ ይዘው ሊሻገሩ ይችላሉ ብሎ መገመት አይቻልም። በሦስት ምክንያት፥ አንደኛ በከፍተኛ ጥበቃ ሥር ባለችው ከተማ ውስጥ ተሰውረው ቆይተው ነበርና። ሁለተኛ በድልድይ የሚሻገሩ ከሆነ ከፍተኛ ጥበቃ እንደሚደረግበት በመገመት በርከት ብሎ ለማለፍ ቀርቶ ራሳቸው ላለፉበት መንገድ እንኳ ያነጋግራል። ሦስተኛ በድልድይ ካልተሻገሩ ወይ በዋና ወይ በታንኳ ምናልባትም በጨለማ ዓባይን አቋርጠው ሊሆን ይችላል። ይህም በርከት ለማለት የሚመች አይደለም።

    እኒህ ሰው የነገሩ ሁሉ መነሻ እና አቀነባባሪ ተደርገው ስማቸው እየተነሳ ይገኛል። እንደዚህ ያለውን ቀንደኛ በከበባ መያዝ ሲገባ ወደ መግደል የተሔደበት መንገድ ሌላ ጥያቄ ከማስነሳት አያድንም። በዚህ ላይ ሰውዬው ሲታኮሱ ጥይት አልቆባቸው እንደነበር መረጃ ተሰጥቷል። ይህ ከሆነ ደግሞ አስጊነታቸውን በብዙ ደረጃ ቀንሶት ነበርና ለመያዝ የበለጠ ምቹ እንደነበር ያመላክታል። የተባሉት ሁሉ ትክክል ከሆኑ መረጃ ማጥፋት ዓይነተኛ ተልዕኮ ለነበረው ዘመቻ (operation) ብቻ የተፈጸመው ድርጊት ትክክል ይሆናል። ሰውዬው በአካል ቢያዙ የሚያወጡት መረጃ እንደሚኖር በመስጋት በሕይወት ከሚቆዩ ሞታቸውን ማቅረቡ ተመርጦ ሊሆን ይችላል። ራሳቸውን ገደሉ ሳይሆን የተባለው በተኩስ ልውውጥ ተገደሉ ነው። ቀባብቶ ማምጣት ሊኖር ይችላል። እውነትን መልሶ በማቋቋም ‘አይ ሰውየው ራሳቸውን ነው የገደሉት’ የሚል ዜና ከመጣ ደግሞ ነገሩ ዘወርዋራ የሆነበትን ምክንያት ማወቁ ይሻላል።

    ሁለተኛ፡- የአቶ ምግባሩ ከበደ ሞት። ሌላው ተስፋ ሊሰጥ ወደ እውነተኛው መረጃ ሊያደርስ ይችል የነበረው የምግባሩ ከበደ ሞት መረጃ የማጥፋቱን ሥራ አቀላጥፎታል ብሎ ላለማሰብ የሚከለክል ነገር የለበትም። ይህ ሰው በሠዓታት ውስጥ ቅርብ ሀገር እስራኤል ደርሶ ሊታከም ይችል እንደነበር መገመት የማንችልበት ዘመን ላይ አይደለንም። መሞኛኘት እንዳይሆን እንጅ ወዲያው የጸጥታ ቁጥጥር እንደተደረገ ሲነገረን አምሽቷል። በሄሊኮፕተር በታገዘ መንገድ ለተሻለ ሕክምና መወሰድ ነበረባቸው። ይህ ለምን አልሆነም?

    ሦስተኛ፡- የጀኔራል ሰዓረ መኮንን ጠባቂ ሞት*። ‘ተይዘዋል’ እየተባለ በየዜና ማሠራጫው ሲነገር የነበረው ሰው ‘ራሱን ገድሏል’ ወደሚል ዜና የተቀየረበት መንገድ እንድንጠረጥር እንጅ እንድንተማመን የሚያደርገን አይደለም። ራሱን የገደለን ሰው ተይዟል ብሎ ዜና የሚሠራባት ምክንያት ሴራን (conspiracy) ያሻትታል እንጅ ቅቡልነት አያስገኝም። [* የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንንና ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ጄነራል ገዛኢ አበራን ተኩሶ ገደለ የተባለው የጄነራል ሰዓረ ጠባቂ ራሱን ያጠፋው ወዲያው መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ዛሬ በሰጡት መግለጫ መናገራቸው ይታወሳል። ማምሻውን ደግሞ ፌደራል ፖሊስ በብሄራዊው ቴሌቪዥን ኢቢሲ ራሱ የሰጠውን መግለጫ አስተባብሎ ጠባቂው በሕይወት እንደሚገኝ አስታውቋል። – ቢቢሲ ዜና አማርኛ]

    አራተኛ፡- በዚያ ጭንቅ ሰዓት ጀኔራል ሰዓረ ቤት መሆናቸውም ሌላው ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው። ከቤቱ ሆኖ “የመንግሥት ግልበጣ” የተባለን ነገር የሚከታታል ጀኔራል አለ ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። ሰውዬውም እንደዚህ ዓይነት ጠባይ የለባቸውም፤ ሀገር ሳታርፍ የሚያርፉ ሰው አልነበሩምና። በቢሯቸው ሆነው ከፍተኛ የአመራር ሥራ ሊሠሩ በሚገባበት ሠዓት ቤታቸው የተኙበት ምክንያት ምንድን ነው? እውን ነገሩን አውቀውት ነበርን?

    አምስተኛ፡- ጉምቱዎቹ ባለሥልጣናት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን በግል ጉዳይ፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ገዱ አንዳርጋቸው ለሥራ ብለው አንዱ አሜሪካ ሌላው ጀርመን እግራቸው በረገጠበት ቀን የመሆኑ ግጥምጥሞሽስ እንዴት በዋዛ ይታለፍ ዘንድ ይችላል?

    እነዚህ ሁሉ ሲጠቀለሉ አቅጣጫቸው ሌላ ያሳያል። ከተነገረን ምህዋር በዘለለ ሁኔታ አንዳች የተቀነባበረ ሴራ ካልነበረ በቀር ወንድም በወንድሙ ላይ እንደዚህ ዓይነት ጭካኔ ያሳያል ብሎ መገመት ይከብዳል። ገና ደብዛዛ መረጃ ላይ ተቀምጠን ጣት ወደ መጠቋቆሙ መሔዱ አያዋጣም። ይሄኛው መንገድ ሌላ ጥፋት ያመጣልና።

    በዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ በምግባሩ ከበደ፣ በእዘዝ ዋሴ፣ በጀኔራል ሰዓረ መኮንን፣ በብርጋዴር ጀኔራል ገዛኢ አበራ፣ በብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ጽጌ ሞት በእጅጉ አዝነናል። ስማቸው ባልተነገረን በሌሎችም ሰዎች ሞት በእጅጉ አዝነናል። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን የምትታየን ኢትዮጵያ ናት። ቁስል የሆንባት እስኪ እንራገፍላት።

    ምንጯ ደፈረሰ እንጅ አልነጠፈም። እስኪጠራ መታገስ ዋጋ ቢያስከፍልም ድፍርሱን ጠጥቶ ከመታመም ታግሶ ጥሩውን መጠጣት ጥምን ይቆርጣል፣ ጤናም ይጠብቃል። በደፈረሰ ውኃ ውስጥ ምን እንዳለ ማወቅ አይቻልም። ሲጠራ ግን ይለያል። የሦስቱን ቀን ሁናቴ በጥሞና እንየው፣ ድፍርሱን ለማጥራት ጊዜ እንስጠው። ለመኮነኑ አንቸኩል። ለመቧደንም አንጣደፍ። እነዚህ ከላይ የተነሡት እና ሌሎችም ጥያቄዎች ሲመለሱ የሚወገዘው ይወገዛል።

    ይህ ጥቁር ደመና መግፈፉ አይቀርም። እስከዚያው ግን ጨለማ መንገሡን ተቀብሎ ለብርሃኑ መትጋት መውጣት እና መውረድ ብቻ ነው አማራጩ። የዘሩን ዘጋተሎ አምዘግዝጎ ወዲያ ጥሎ፣ የሀገርን ሕመም ለመታመም አብሮ ቆስሎ የእናት ልጅ የእናቱን ልጅ ሲደክመው አዝሎ፣ ወድቆ እንዳይቀር ውኃ በልቶት ጉልበቱ ዝሎ፣ እየቆረሰ አጉርሶ እየቀደደ አልብሶ፣ ወደ ብርሃን መውጫው ሥር ካልተጓዘ በማለዳ፣ ተከፍሎ አያልቅም የእናት ሀገር የአደራ ዕዳ።

    አባይነህ ካሴ (ዲ/ን)

    ሀገሬን ምን ነካት?


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.