ዘጠነኛው ለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት በሂልተን ሆቴል ተከናወነ፤ ቁራኛዬ ፊልም ሦስት ሽልማቶችን አግኝቷል

Home Forums Semonegna Stories ዘጠነኛው ለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት በሂልተን ሆቴል ተከናወነ፤ ቁራኛዬ ፊልም ሦስት ሽልማቶችን አግኝቷል

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #12341
    Semonegna
    Keymaster

    በኢትዮጵያውያን የኪነ ጥበብ አድናቂዎች ዘንድ ተወዳጅነት እያተረፈ የመጣው ለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በሂልተን ሆቴል፣ አዲስ አበባ፣ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል። ቁራኛዬ ፊልም ሦስት ሽልማቶችን ሲያገኝ፥ ድምጻዊ ቸሊና እና ዘመን ተከታታይ ድራማ ሁለት፣ ሁለት ሽልማቶችን አግኝተዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – በሀገራችን የሙዚቃ ታሪክ እጅግ መቀዛቀዝ፣ የሙዚቃ አልበምም ህትመት መፍዘዝ፣ ፊልም ሠሪዎችም ሥራዎቻችውን ተመልካቾች ፊታቸውን ባዞሩባቸው ወቅት እንደ አንድ የኪነጥበብ አባልና የሚዲያ ባለሙያ አቅማቸው በፈቀደ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ለማበርከት፣ እንዲሁም አድማጭ እና ተመልካቹን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለማነቃቃት በማሰብ ነበር ጋዜጠኛ ብርሀኑ ድጋፌ እና ባልደረቦቹ በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬድዮ ላይ “ለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት” ሥነ ሥርዓትን የየጀመሩት።

    በእርግጥ ኪነ-ጥበብና ኢትዮጵያ ሀገራችን በባህላዊውም ሆነ በዘመናዊው መንገድ እጅግ ብዙ ዓመታትን ያስቆጠረ ቁርኝት ቢኖራቸውም ቅሉ የኪነ ጥበብ ሙያዉን እንደተከበረ ሙያ ባለሙያዉንም የተከበረ ሙያ እንዳለው ቆጥሮ ወቅት ጠብቆ በተገደበ የጊዜ ኡደት ለሙያውና ለባለሙያው ተገቢውን ዕውቅና፣ ብሎም ክብር የሚሰጥ ቋሚ ተቋም ባለመኖሩ ያለመኖሩን በማስገንዘብ የሥነ ስርዓቱ ሀሳብ ጠንሳሾች “ለምን እኛ የቻልነውን አናደርግም?” በሚል ነበር የኪነ ጥበብ ሰዎችን በዓመት አንድ ጊዜ እያሰባሰቡ ለማወያየት፣ በዓመቱ በሙያውና በሙያቸው ጉልህ አስተዋጽዖ ያደረጉትን “በጎ ሥራ ሠርታችኋል! ይበል!” ለማለት ለዛ የኤድማጮች ምርጫ ሽልማትን በ2003 ዓ.ም የጀመሩት።

    በ2003 ዓ.ም በተደረገው የመጀመሪያ ሽልማት ‘የዓመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ’፣ ‘ምርጥ ተዋናይት’፣ ‘የዓመቱ ምርጥ ተዋናይ’፣ ‘የዓመቱ ምርጥ ፊልም’ እና ‘የዓመቱ ምርጥ አልበም’ በሚሉ አምስት ዘርፎች (ዘውጎች) ኢትዮጵያውያን የኪነ ጠበብ ሰዎች ተመርጠው የተሸለሙ ሲሆን ሽልማቱም ያገኙትም ከያኒት ዘሪቱ ከበደ “አርቴፍሻል” በሚለው ነጠላ ሙዚቃዋ፣ ተዋናይት ሰሃር አብዱልከሪም “ያንቺው ሌባ” በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየችው ትወና፣ ጋሽ አበበ ባልቻ “ሄሮሺማ” በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየው ትወና፣ “ሄሮሺማ” ፊቸር ፊልም በምርጥ በፊልምነት፣ እንዲሁም ከያኒ ናትናኤል አያሌው (ናቲ ማን) በመጀመሪያው አልበሙ በአምስቱ የተዘረዘሩት ዘርፎች አሸናፊዎች ሆነው የሥነ ሥርዓቱ የበኩር ተሸላሚዎች ሆኑ።

    በዚህ መልኩ የተጀመረው ለዛ የአድማጮች ምርጫ በየዓመቱ ከጥቅምት ወር ጀምሮ እስከ ሃምሌ ድረስ የሚወጡ የኪነ ጥበብ ሰዎችንና ሥራዎችን በአድማጮች ምርጫ አወዳድሮ ዕውቅና እየሰጠ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተሳታፊዎችን እያበዛ፣ በባለሙያዉም፣ በመራጭነት በሚሳተፈውም ይሁን በየበይ ተመልካችነት በሚከታተለው ኢትዮጵያዊ ዘንድም ተወዳጅነት እያተረፈ ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በሂልተን ሆቴል፣ አዲስ አበባ፣ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል። በዘጠነኛው ለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት በተለያዩ ዘርፎች ሽልማት ያገኙት የሚከተሉት ናቸው።

    • ምርጥ ነጠላ ዜማ፦ “ቢልባ” (ጃንቦ ጆቴ) [ኦሮምኛ ሙዚቃ]፣
    • ምርጥ አዲስ ድምፃዊ፦ ቸሊና የሺወንድም (“ቸሊና” በተባለው የሙዚቃ አልበሟ)፣
    • ምርጥ የሙዚቃ አልበም፦ “ቸሊና” (ቸሊና የሺወንድም)፣
    • ምርጥ የሙዚቃ ክሊፕ፦ ከእሁድ እስከ እሁድ (ጎሳዬ ተስፋዬ)፣
    • ምርጥ ሙዚቃ/ዘፈን፦ “ሰርካለሜ” በድምጻዊ ዚጊ ዛጋ (በኃይሉ ታፈሰ)፣
    • ምርጥ ተዋናይት፦ የምስራች ግርማ ቁራኛዬ በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየችው ትወና፣
    • ምርጥ ተዋናይ፦ ዘሪሁን ሙላት ቁራኛዬ በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየው ትወና፣
    • ምርጥ ፊልም፦ ቁራኛዬ
    • ምርጥ ተዋናይት በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፦ ሀና ዮሐንስ (“ዘመን” ድራማ በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን)፣
    • ምርጥ ተዋናይ በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፦ አበበ ባልቻ (“ዘመን” ድራማ በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን)፣
    • ምርጥ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፦ ደርሶ መልስ በፋና ቴሌቪዥን፣ እና
    • “የ2010 ዓ.ም የኪነ ጥበባ በለውለታ” የክብር ተሸላሚ፦ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ደማቅ አሻራቸውን ያስቀመጡትን የቀድሞዎቹን አይቤክስ ባንድ እና ሮሃ ባንድ ከመሠረቱት አባላት አንዱ የሆኑት ጂዮቫኒ ሪኮ (Giovanni Rico)

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ቁራኛዬ


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.