Home › Forums › Semonegna Stories › ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ለነበሩ አርሶ አደሮች ያደረገው ድጋፍ
Tagged: Haramaya University, ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 4 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
June 13, 2019 at 12:18 am #11077SemonegnaKeymaster
ሐረማያ ከተማ (ሰሞነኛ) – ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በባቢሌ ወረዳ ለሚገኙና ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ለነበሩ አርሶ አደሮች ከ750ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ 266 ኩንታል በአጭር ጊዜ የሚደርስ የተሻሻለ የቦቆሎና የማሽላ ዘሮችን በእርዳታ አከፋፈለ።
ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምርጥ ዘሩን ያከፋፈለው ከኢትዮጵያ ሶማሌና ከኦሮሚያ ክልሎች ድንበር አዋሳኝ ዘጠኝ ቀበሌዎች ከ2 እስከ 8 ወር ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የባቢሌ ንዑስ ምርምር ጣቢያና በተለያዩ ቦታዎች ተጠልለው ለነበሩ 964 ወደ ቄያቸው ተመላሽ አርሶ አደሮች ነው።
ዩኒቨርሲቲው ያከፋፈለው የቦቆሎና የማሽላ ምርጥ ዘሮች በሦስት ወር ውስጥ የሚደርሱ በሽታንና ድርቅን የሚቋቋሙ ሲሆን ለገመቹ፣ ኤረር ጐዳ፣ ኢፋዶኒ፣ ቱላ፣ ሼካ አብዲ፣ አውሸሪፍ፣ ኤረር ኢባዳ፣ ራመታ ሠላማ እና አባዳ ገመቹ ለሚኖሩ 964 አባ እና እማወራዎች 241 ኩንታል መልካሣ-2 የተባለ የቦቆሎና 25 ኩንታል መልካም የተባለ የማሽላ ዘር ነው።
የቱላ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነዋሪ የሆነችው ነኢማ ዑመር ቀደም ሲል ከቀዬዋ ተፈናቅላ በባቢሌ ስትኖር እንደ ነበርና አሁን ሠላም ወርዶ ወደ ቀዬዋ ብትመለስም የምትዘራው ዘር አጥታ ስትጨነቅ እንደነበርና አሁን ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ያገኘችው ዘር እንደደረሰላት በመግለፅ ዩኒቨርሲቲውን አመስግናለች።
ሌላው ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ያነጋገራቸው የገመቹ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ አብዱረህማን ሽኩር፥ በኢትዮ ሶማሌና ኦሮሚያ አዋሳኝ በተቀሰቀሰ ግጭት አጠቃላይ የቀበሌው ነዋሪ ከ8 ወራት መፈናቀል በኋላ በሀገር ሽማግሌዎች፣ በመከላከያ እና የፀጥታ ዘርፍ አመራሮች ጥረት በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል እርቅ ተደርጐ ወደ ቄያቸው ቢመለሱም ቀደም ሲል የነበራቸው ንብረት በመዘረፉ እና በመውደሙ የእርሻ ማሳቸውን አዘጋጅተው የመግስትን እርዳታ ሲጣባበቁ እንደነበር ጠቁመዋል። ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ያገኙት ምርጥ ዘር ለ700 አባና እማወራዎች እንደተከፋፈለና ይህም በ355 ሄክታር መሬት ላይ ለመዝራት ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አቶ አብዱረህማን ገልፀው ምንም እንኳን ፍላጎቱ ከአቅርቦቱ ጋር ሲነፃፀር ብዙ ቢቀረንም ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ላዳረገው አስቸኴይ እርዳታ በራሳቸውና በቀበሌው አርሶ አደሮች ስም አመስግነዋል።
በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የባቢሌ ወረዳ ተፈጥሮና ግብርና ልማት ፅህፈት ቤት ተወካይ አቶ ኢዳ አቦንሣ እንደገለጹት ተፈናቃዮችን ወደቄያቸው መልሶ ለማቋቋም በምናደርገው ጥረት ምርት አምርተው ለመኖር እንዲችሉ ለማድረግ የግድ ዘር በማስፈለጉ ይህንኑ ዩኒቨርሲቲው እንዲረዳን በደብዳቤ በጠየቅነው መሰረት ፈጣን ምላሽ በመስጠት ከመጋዘኑ ባይኖረውም ካለው በጀት ላይ 750000 (ሰባት መቶ ሃምሳ ሺህ) ብር የሚያወጣ ዘር በመግዛት በራሱ ትራንስፖርት ወረዳው ድረስ በማምጣት በዘጠኝ ቀበሌ ለሚገኙ 964 አባና እማወራዎች 266 ኩንታል የተለያዩ የተሻሻሉ ዘሮችን አከፋፍሏል። ላሣየው የህዝብ ወገንተኝነት ከፍተኛ ምስጋና ይገባዋል ብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በያዝነው የ2011 ዓ..ም በጀት ዓመት ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተለያዩ የሰብል፡ የአትክልት እና ፍራፍሬ፣ የእንቁላል ጣይ ዶሮ ፤ የቦሎቄ ዘሮችንና የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ለተጠቃሚዎች በነፃ ማከፋፈሉን ከዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ያገኘነው ማስረጃ ያሳያል ሲል ሲሣይ ዋቄ ለዩኒቨርሲቲው ዘግቧል።
ምንጭ፦ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ (ኤፍ ኤም 91.5) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.