Home › Forums › Semonegna Stories › የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ዶክተሮችን ለስድስተኛ ጊዜ አስመረቀ
Tagged: Haramaya University, School of Medicne, ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ, አሚር አማን, ኦርዲን በድሪ, ያደታ ደሴ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
December 22, 2018 at 4:02 pm #9027SemonegnaKeymaster
ሐረር (ሰሞነኛ)–የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የጤና እና የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምና ዶክተሮችን ጨምሮ 220 የጤና ባለሞያዎችን ዛሬ አስመርቋል። በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር አሚር አማን ተመራቂ የጤና ባለሙያዎች ዘርፉ የሚጠይቀውን ሥነ- ምግባር በመላበስ ኅብረተሰቡን በቅንነት እንዲያገለግሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት “ተመራቂ የጤና ባለሙያዎች የሙያውን ሥነ- ምግባር በመላበስ ኅብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት የማገልገል ኃላፊነት ተጥሎባችኋል” ብለዋል።
“ከራስ ጥቅም ይልቅ ለወገን ቅድሚያ መስጠት፣ ብልሹ አሠራሮችን መከላከልና ውጤታማ ሥራን በማከናወን ለሌሎች አርአያ መሆን ይጠበቅባችኋል” ሲሉም አሳስበዋል።
◌ ቪዲዮ፦ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ዶክተሮችና የጤና ባለሙያዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት በአጭሩ
በሽታን አስቀድሞ መከላከል ላይ የተመሠረተውን የአገሪቱን የጤና ፖሊሲ የሚያጠናክሩ አገልግሎቶችን መስጠትና ጥናትና ምርምሮችን ማካሄድ እንዲሁም በእናቶችና ህጻናት ጤና ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደዘገበው የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድ አቶ ኦርዲን በድሪ ዩኒቨርሲቲው በጤናው ዘርፍ የባለሙያዎችን እጥረት ለማቃለል እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። ኮሌጁ በህክምና ሳይንስ ዘርፍ እያከናወነ ባለው የመማር፣ ማስተማርና ምርምር ሥራዎች በክልሉና አጎራባች አካባቢዎች እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ዘርፉን የሚያጠናክሩ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።
ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የተማረ የሰው ኃይል የማፍራት ሥራውን እንዲያጠናክር የክልሉ ህዝብና መንግሥት ድጋፍ እንደማይለየው ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።
የዩኒቨርሲቲው በሐረር ከተማ በሚገኘው ኮሌጁ በመደበኛው የትምህርት መርሐ ግብር ካስመረቃቸው መካከል 173ቱ የህክምና ዶክተሮች መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የኮሌጁ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ያደታ ደሴ ናቸው። ቀሪዎቹ ተመራቂዎች በመጀመሪያ ዲግሪ በነርስነት የሰለጠኑ ናቸው። በተያያዘም ከአጠቃላይ ተመራቂዎች ውስጥ 38ቱ ሴቶች መሆናቸውንም ዶ/ር ያደታ ተናግረዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ኮሌጁ በዚህ ዓመት በሕክምና ሳይንስ የቅድመ ምረቃ መርሐ ግብር በ11 ዘርፎች 2ሺህ 616 ተማሪዎች እያሰለጠነ ነው።
◌ ተመሳሳይ ዜና፦ Addis Ababa University’s School of Medicine graduates 288 medical doctors
በዕለቱ በከፍተኛ የማዕረግ ዕጩ ተመራቂ ዶ/ር ምኅረት ለገሠ “የሙያ ሥነ- ምግባሩን በማክበር ኅብረተሰቡን በቅንነት ለማገልገል ተዘጋጅቻለሁ” ብላለች። የእናቶችንና የህጻናትን ሞት ለመቀነስ፣ የጤና አገልግሎቱን ለማሻሻልና በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል የተየዘውን ጤና ልማት ግብ ለማሳካት የበኩሏን እንደምትወጣ ገልጻለች።
ዕጩ ተመራቂ ዶ/ር ቢሊሱማ ደገፉ በበኩሉ አገሪቱ የነደፈችውን የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስታውቋል።
የሐረማያ ዩኒቨርሲ ከአገሪቱ ቀደምት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ ቢሆንም፤ የህክምና ዶክተሮችን ሲያስመረቅ የአሁኑ ለሰድስተኛ ጊዜ ነው።ምንጭ፦ ኢዜአ | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.