Home › Forums › Semonegna Stories › መገናኛ ብዙሃን በሀገሪቱ የሚፈጠሩ ግጭቶችን እያባባሱ ነው – የዘርፉ ባለሙያዎች
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 1 month ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
November 3, 2019 at 10:41 pm #12496SemonegnaKeymaster
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ሥነ-ምግባርን ጠብቀው ከመሥራትና ማህበረሰቡን ከማስተማር ይልቅ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን እያባባሱ መሆኑን ባለሙያዎች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በበኩሉ መገናኛ ብዙሃኑ የሚሠሯቸውን የዘገባ ስህተቶች እና አባባሽ ይዘቶች እንዲያስተካክሉ በቃልና በደብዳቤ እያሳወቅኩ ነው ይላል።
ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚፅፉት አቶ በፍቃዱ ኃይሉ “የክልል መገናኛ ብዙሃን ወገንተኝነት እና ለገዥው ቡድን አጎብዳጅነት” እንደሚታይባቸው አንስተው፤ ብዙ ፖለቲካዊ ዘገባዎችን እና ትርክቶችን በተዛባ መልኩ የሚያቀርቡ እንደሆኑ ነው የገለጹት።
ዘውግ-ተኮር የሆኑ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሙያዊ ስነምግባርን ጠብቀው ያለመዘገብ፣ ሀቅን እንዳለ ያለማቅረብና ሚዛናዊ አለመሆን እንደሚስተዋልባቸው የሚናገሩት አቶ በፍቃዱ ኃይሉ፥ ይህ ደግሞ በሀገሪቱ ግጭት በሚስተዋልበት ወቅት የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ እንዳይዘግቡ አድርጓቸዋል ነው ያሉት።
አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ስህተት የሚፈጽሙት ባለማወቅ መሆኑን ገልጸው፥ ከዚህ ዓይነት ስህተት እንዲወጡ መጀመሪያ በማስተማር የተለየ ሁኔታ ሲያጋጥም በተጨባጭ ማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ይገባልም ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃኑ የሕዝብ ማስተማሪያ አልያም የጦር መሣሪያ የመሆን ዕድል ስላላቸው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ሀሳባቸውን በመስጠት፤ የኢትዮጵያ የብሮድካስት ባለሥልጣልም የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህርና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ አቶ ሃይማኖት ጌታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን አዘጋገብ “ፅንፍ ይዞ እየተጓዘ” መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህም ለግጭት አባባሽ እየሆነ ነው ይላሉ።
በተለይ አንዳንድ “የፅንፍ ፖለቲካ” የሚያራምዱ ግለሰቦች የራሳቸውን መገናኛ ብዙሃን በመክፈት የሚፈልጉትን “ፅንፈኛና የጥላቻ አጀንዳ” እያሰራጩ መሆኑን ተናግረዋል። በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን በኩል ደግሞ “ሕዝብ ሲሞት እና ጉዳት ሲደርስበት ተከታትሎ ከመዘገብና መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ መንግሥትን እየጠበቁ የመዘገብ አዝማሚያ ይታይባቸዋል” ነው ያሉት።
መገናኛ ብዙሃኑ አስቀድመው የስጋት ትንተናዎችን በሚዛናዊነት በማቅረብ ግጭትን የመከላከል ሚና እየተወጡ አይደለም ያሉት አቶ ሃይማኖት፥ ብሮድካስት ባለስልጣንም ለመገናኛ ብዙሃኑ የተሰጣቸው ነጻነት እንዳይታፈን ጥንቃቄ በማድረግ፤ በተሳሳተ መንገድ እየሄዱ ባሉት ላይ የእርምት እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንደወሰን አንዱዓለም “የሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ በተረበሸ ቁጥር መገናኛ ብዙሃኑም አብረው መታመማቸው ከፍተኛ ችግር አስከትሏል” ነው ያሉት።
አብዛኛው መገናኛ ብዙሃን ሕዝብን ከሕዝብ፣ ክልልን ከክልል፣ መንግሥትን ከሕዝብ የሚያራርቁ ዘገባዎችን እየሠሩ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፥ ለሕዝብ የሚጠቅሙ ማኅበራዊ፣ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና ሌሎች የሕይወት መልኮችን ትተው ፖለቲካ ላይ ብቻ የመጠመድ ችግር ይታይባቸዋል ነው ያሉት።
ባለስልጣኑ የመገናኛ ብዙሃኑን ሥራዎች መዝኖ እርምጃ ለመውሰድ ከዚህ ቀደም የነበረውን ፖለቲካዊ መስፈርት በመቀየር ሙያዊ መመዘኛ ማዘጋጀቱን ጠቁመው፥ በመስፈርቱ መሠረት ድክመትና ጥንካሬ ተለይቶ እንዲያስተካክሉት ለተወሰኑ መገናኛ ብዙሃን ደብዳቤ መላክ መጀመሩንም ገልጸዋል።
“ሀገሪቱ ለውጥ ላይ ናት በሚል መገናኛ ብዙሃኑ የነውጥ አራጋቢ ሆነው እንዲቆዩ መፍቀድ አይገባም” ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፥ የፖለቲካ ሁኔታ በተረበሸ ቁጥር ሚዲያው አብሮ መረበሽ እንደለሌበትና በቅርቡ በሚወጣው የመገናኛ ብዘሃን አዋጅ ግልፅ ድንበር እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
የፖለቲካ አመራሮች በቦርድም ሆነ በሚዲያ መሪነት እንዳይሰየሙ በረቂቅ አዋጁ መቀመጡን አንስተው፥ መገናኛ ብዙሃኑ ከባለሥልጣኑ ጋር እንደ ‘አይጥ እና ድመት’ ከሚተያዩ እርስ በራሳቸው የሚተራረሙበት፣ የሚነጋገሩበትና የሚደጋገፉበት የመገናኛ ብዙሃን ካውንስል መቋቋሙንም ነው የገለጹት።
“በልቅነት እየሠሩ ያሉትን ለማረም ሲባል በነጻነት ላይ ያሉት መጎዳት የለባቸውም” ያሉት አቶ ወንደወሰን፥ ችግሩን ለማረምና ሁለቱን ለመለየት ከውይይትና ከአቅም ግንባታ ጀምሮ በቀጣይ በሕግ የተጠና የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተናግረዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.