Home › Forums › Semonegna Stories › በሕዝብና በዜጎች ላይ የተፈጸመው መጠን የለሽ ግፍና በደል ― የሰው ልጅ በወገኑ ላይ ይህን ይህል መጨከን ይችላል?
Tagged: የሰብዓዊ መብት
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
December 13, 2018 at 7:59 am #8919SemonegnaKeymaster
ታስረው ከነበሩ ሰዎች የተፈጸመውን ግፍ የሰማውና ጠንቅቆ የሚያውቀው ሕዝብ በሌሎችም በርካታ አጋጣሚዎች በዜጎች ላይ የተፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲሰማ የኖረው ሕዝብ የከረረ ተቃውሞ ቢያሰማ አሻፈረኝ ቢል ምንም አይፈረድበትም።
መሐመድ አማን (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–ከሰሞኑ በተለያዩ የቴሌቪዥን ማሰራጫ ጣቢያዎች የቀረበው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዘጋቢ ፊልም በሕዝብና በዜጎች ላይ የተፈጸመው ግፍና በደል መጠን የለሽ እንደነበር ያሳያል። ገራሚው ነገር እኩልነት በተግባር ተረጋግጧል በሚባልበት ሀገር ዜጎች በብሔራቸውና በጎሳቸው መነሻነት ተለይተው እጅግ ዘግናኝና በጭካኔ የተሞላ አረመኔያዊ ድርጊት የተፈጸመባቸው መሆኑ በእጅጉ አሳዝኗል። የት ሀገር ላይ ነበርንም ያሰኛል።
ይህ ዓይነቱ ጸያፍ ድርጊት በዓለም ደረጃ ይፈጸም የነበረው በተለይ በናዚ ጀርመን የማሰቃያና የመግረፊያ በጋዝ መርዝ ሰዎች ይገደሉባቸው በነበሩ ካምፖች ነበር። በተለያዩ የቴሌቪዥን ማሰራጫ ጣቢያዎች የተላለፈው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዘጋቢ ፊልምም ድፍን ሀገርን በእንባ አራጭቷል።
የግፉና የአረመኔያዊ ድርጊቱ ጫፍና ጣሪያ ከሚገመተው በላይ የሆነ በተለይም ዘርና ብሔርን ኢላማ ያደረገ መሆኑ ደግሞ እጅጉን ያማል። ሰው የሆነ ሰው፤ ቤተሰብ ልጅ እህት ወንድም ወገን ያለው ሰብዓዊ የሆነ ፍጡር እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት ይፈጽማል ብሎ ለማመን ይከብዳል፤ ግን ደግሞ ሆነ፤ ተደረገም።
ይህን በዘረኝነት ጥላቻ የተሞላ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ የፈሰሰን እጅግ አረመኔያዊ ድርጊት ለመግለጽ ቃላቶች አቅም ያጥራቸዋል። ሰው በአገሩ እንዲህ ዓይነት በደልና ግፍ በአረመኔነት ተሞልቶ ሲፈጸምበት ሀገሬ አይደለችም አላውቃትም ቢል አይፈረድበትም።
ከሥልጣኔና ከዕውቀት፣ ከመልካም ሥነ-ምግባር የተፋቱ ሰብዓዊነት የሚባል ነገር ያልፈጠረባቸው አረመኔ አውሬዎች ቀጣዩን ትውልድ እንዳይበክሉት መጠንቀቅ ለሕግና ለፍትህ ማቅረብ ግድ ይላል።
ሕዝብና የሕዝብ ልጆችን ማሰቃየት፣ ብልታቸውን ማኮላሸት፣ ገልብጦ በእንጨት ላይ አንጠልጥሎ መግረፍ፣ ሰቅሎ ማቆየት፣ ዘርን ለይቶ መሳደብ ማንቋሸሽ፣ አፍ ላይ መጸዳዳት፣ ወንድ ላይ የግብረ ሰዶማዊነትን መፈጸም፣ ሴትን ልጅ እርቃኗን እያዩ መሳለቅ፣ ከዚያም አልፎ ወሲብ መፈጸም ሌላ ሀገር ሳይሆን እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸመ ድርጊት ነው። ያውም የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባና ፈጣሪውን የሚፈራ ሩህሩህ ሕዝብ አለበት በሚባል ሀገር።
ይህ ሁሉ ድርጊት በኃይል፤ በጉልበት፤ በጠመንጃ አፈሙዝ አስገብሬና አስፈራርቼ እገዛለሁ በሚል የደንቆሮዎች እምነት መከወኑ ያሳፍራል። ጉዳዮቹ በጥብቅ ምስጢር ተይዘው ሲሠራባቸው የነበሩና የምስጢር ዘበኞቹም ራሳቸው ስለሆኑ ይህን ጉዳይ በአልፎ አገደም ከምንሰማው ውጪ እንዲህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው ሰዎች አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን ለማሰማት የማይችሉባቸው በርካታ ሁኔታዎች ነበሩ። ቀን ሲፈቅድ ሁሉም ይሆናል እንዲሉ ሆነና ቀን በደሉን ግፉን አረመኔነቱንና ጭካኔውን ግፈኝነቱን እንዲህ በአደባባይ አሰጣው።
◌ ግፍ ሠርቶ መደበቅ፣ ዘርፎ መንደላቀቅ አይቻልም ― የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ
ምስጋናው ለሰው ሳይሆን ለቀን ነው የሚሆነው። ለውጡን ላመጣው የሕዝብ ትግልና ለውጡን ከዳር ለማድረስ ሪፎርሙን እየመሩ ላሉት ሰዎች። ይህን ያህል ግፍ በጭካኔና አረመኔያዊነት በዘር ጥላቻ ላይ የተፈጸመ ሰቅጣጭ ድራማ በአገራችን ምድር ላይ ተፈጽሞ እናያለን ብሎ የገመተም የጠበቀም አልነበረም። ያለፈው (የደርግ) ሥርዓት እንዲህ ዓይነት እጅግ ነውረኛና ዘረኛ አረመኔያዊና ፋሽስታዊ ድርጊት በዜጎቹ ላይ ስለመፈጸሙ አልሰማንም።
በፖለቲካ ልዩነት እንጂ በደርግ ዘመን እንኳን በዜጎቹ መካከል ልዩነትን ፈጥሮ ማጥቃት አልተስተዋለም፤ ብሔር እየመረጠ አልረሸነም፤ ብሔር እየመረጠም አልጠቀመም። የደርግ አምባገነናዊ ባህሪይው እንደተጠበቀ ሆኖ በእንዲህ መልኩ አሰቃቂ የግፍ ተግባራት ስለመፈጸማቸውም ያጠራጥራል። ይሁንና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ክቡር ህይወታቸውን ገብረው ለሰብዓዊ መብት መከበር የከፈሉትን መስዋዕትነት ገደል የሚከት ተግባር በእነዚህ ጥቂት አረመኔዎች ተፈጽሟል። የሀገሬ ሰው እንደሚለው “ወንበሬን ማን ነክቶት አይሉም አይሉም፤ ሚስቴንስ ማን ዓይቷት አይሉም አይሉም፤ ቀን የፈቀደ ዕለት ይደረጋል ሁሉም” እንዲሉ ሁሉንም ይፋ ያወጣው ቀን ሆነ። በቀላሉ ይፋ የማይወጡ ሊታወቁ የማይችሉ ምስጢሮች ለአደባባይ በቁ።
መቼም አንዱ ሄዶ ሌላው ሲመጣ አዲስ ለውጥና ሂደት ቢጠበቅም በዚህ ዓይነት ደረጃ መዝቀጥና መውረድ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም ነበር። እነዚህ ሰዎች የፈጸሙትን አረመኔያዊ ድርጊት የጀርመኑ አዶልፍ ሂትለር ስድስት ሚሊዮን አይሁዶች በመፍጀት አሳይቷል። በማቃጠያና መግደያ ካምፖቹ ውስጥ በማስገባት በጋዝ መርዝ ጭስ ተሰቃይተው ከሞቱ በኋላ አስከሬናቸው ተፈጭቶ ወደ ሳሙናነት እስኪለወጥ ድረስ ሠርቷል። ይህን ዓይነቱን አረመኔያዊ ድርጊት በራሱ ዜጎች ላይ ግን አልፈጸመም።
ሙሶሎኒ ፋሽስት ስለሆነ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመግዛት ቋምጦ በመጣውና መሪ በነበረው ግራዚያኒ አማካኝነት ኢትዮጵያ ውያንን በአካፋና በዶማ አስጨፍጭፏል። ቤት ውስጥ እንዲገቡ ካደረገ በኋላ እሳት ለኩሶ አንድዷቸዋል። የዘር ማጥፋት ፍጅት ፈጽሟል።
የተላለፈው እጅግ የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የተመለከተው ዘጋቢ ፊልም እነዚህ ሰዎች ከባሕላችን፤ ከእሴቶቻችን፤ ከሀይማኖታዊ እምነታችን በእጅጉ የራቁ፤ በዘረኝነት ጭፍን ጥላቻ የታወሩ፤ የክፍለ ዘመናችን ጥቁር ፋሽስቶች መሆናቸውን ደግሞ ደጋግሞ ያረጋግጣል።
የራሳችን ሰዎች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ምን ያህል ጸያፍ ሥራ ሲፈጽሙ እንደኖሩ፤ አገርንና ሕዝብን እንዳዋረዱ፤ ወደፊትም በዚሁ አሳፋሪ ሥራቸው ቀና ብለው ለመራመድ እንደሚቸገሩ በእርግጠኝነት ለመናገር ይቻላል። ታስረው ከነበሩ ሰዎች የተፈጸመውን ግፍ የሰማውና ጠንቅቆ የሚያውቀው ሕዝብ በሌሎችም በርካታ አጋጣሚዎች በዜጎች ላይ የተፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲሰማ የኖረው ሕዝብ የከረረ ተቃውሞ ቢያሰማ አሻፈረኝ ቢል ምንም አይፈረድበትም።
እንዲህ ዓይነቱ ፋሽስታዊ ድርጊት ከምድራችን ተነቅሎ እንዲጠፋ፤ ሕግና ተጠያቂነት እንዲሰፍን፤ ሁሉም ዜጋ የየበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል። በመዲናዋ አዲስ አበባና በሌሎችም ከተሞች ህቡእ ከመሬት ስር ያሉ እስር ቤቶችን ከፍቶ ዜጎችን ማሰቃየት፣ መግረፍ፣ መግደል፣ የወንጀሎች ሁሉ የከፋው ወንጀል ከመሆኑም በላይ አስቸኳይ የሕግ ውሳኔን ይጠይቃል።
ዋናውና ትልቁ ጥያቄ ይህ ሁሉ ግፍና በደል ሲፈጸም ዜጎች ሲደፈሩ፤ ግብረሰዶም ሲፈጸምባቸው፤ አፋቸው ላይ ሲጸዳዱ፤ ሴቶች እርቃናቸውን ሆነው መጫወቻ ሲሆኑ፤ መንግሥት ተብሎ የሚጠራው መንግሥት ምን ሲሠራ ነበር ብሎ መጠየቅ ይገባል። ሀገሬ የተፈጸመብሽ ግፍ አረመኔነት ጭካኔ ከጣሪያ በላይ ወጣ። የናቁሽ የረገጡሽ ያዋረዱሽ ሁሉ ውርደትን ሽንፈትን ውድቀትን ይከናነቡ ዘንድ ፍርዱ የአምላክም የሕዝብም ይሆናል። ይሁንና ከዚህ ልንማረው የሚገባው ጉዳይ ልክ እንደ ዘራፊዎች ጨካኞችም የትኛውንም ብሔር እንደማይወክሉና የሕዝብ ጠላቶች እንደሆኑ ነው። ሕዝባችንም ለእነዚህ ዓይነት ጨካኞች ምን ዓይነት የመደበቂያ ከለላ ሳይሰጥ የወገኖቼ ጠላቶች ናችሁ ብሎ ሊያወግዛቸው ብሎም ለፍርድ ሊያቀርባቸው ይገባል። ስህተት በሌላ ስህተት አይታረምምና መንግሥትም እነዚህ አካላት ከፈጸሙት ተግባር በተቃራኒው ሄዶ ሰብዓዊነትን የሚማሩበትን የፍርድ ሂደት ማከናወን ጊዜ ሊሰጠው የማይገባው ተግባሩ ሊሆን ይገባል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.