ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄን ሕዝበ ውሳኔ አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

Home Forums Semonegna Stories ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄን ሕዝበ ውሳኔ አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #11418
    Semonegna
    Keymaster

    ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄን ሕዝበ ውሳኔ አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት የሲዳማ ዞን መስተዳደር ምክር ቤት ውሳኔን መሰረት በማድረግ በህዳር 11 ቀን 2011 ዓ.ም. የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን ለመወሰን ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።

    በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን እንደ አዲስ የማደራጀት፣ የምርጫ ቦርድ ስልጣንና ተግባር የሚወስነውን ሕግ የማርቀቅ እና በተወካዮች ምክር ቤት የማጸደቅ፣ የምርጫ ህጎችን የማሻሻል፣ ተቋማዊ ለውጦችን የማከናወን እንቅስቃቄ ሲደረግ ቆይቷል። ከነዚህ ተቋማዊ ለውጦች መካከል የቦርዱን ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት አድርጎ የተከናወነው የምርጫ ቦርድ አባላት መረጣ ዋነኛው ነው።

    በዚህም መሰረት ከዚህ የቦርድ አባለት መረጣ ሰፊ ምክክርና ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጐበት ከተለየ በኋላ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 06 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ተጨማሪ አራት የቦርድ አባላት ሹመት ተከናውኖ ቦርዱ አባላት ተሟልተውለት ሥራውን ጀምሯል።

    ቦርዱ ተሟልቶ ሥራ በጀመረበት ባለፈው አንድ ወር በእንጥልጥል የሚገኙ እና አስቸኳይ ናቸው ያላቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ በመስጠት ላይ ይገኛል።

    በቦርዱ አለመሟላት ምክንያት በእንጥልጥል ከቆዮት ጉዳዮች አንዱ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ለቦርዱ የቀረበው የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን ሕዝበ ውሳኔ ማደራጀት ነው።

    ቦርዱ ሥራ ከጀመረ አንስቶ የሲዳማ ዞን ክልልነትን የሚመለከቱ በተለያዩ ጊዚያት የቀረቡትን ጥያቄዎች ከመመልከቱም በላይ ከክልሉና የዞን መስተዳድር አመራሮች ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት አድርጓል።

    እንደሚታወቀው የሲዳማ ዞን የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ የማደራጀት ጥያቄ ከክልሉ ምክር ቤት ለቦርዱ የደረሰው ህዳር 12/2011 ዓ.ም. ሲሆን በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 47/3/ለ/ ለክልሉ የተሰጠው “ጥያቄው ከደረሰበት ቀን ጀምሮ በአንድ ዓመት” የሚለው የማደራጀት ጊዜ ገደብ ለቦርዱም ተግባራዊ የሚደረግ ነው።

    በመሆኑ በሕግ መንግስቱ የተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ በቀሩት 5 ወራት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔውን ለማከናወን የመጀመሪያ ደረጃ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።

    ሕዝበ ውሳኔ የሚከናወነው የሕዝብን ፍላጐትና ውሳኔ ህጋዊ እና ነፃ በሆነ አግባብ መሰጠቱን ለማረጋገጥ ነው። በመሆኑም ቦርዱ ተገቢና በቂ ዝግጅት አድርጐ ሕዝበ ውሳኔውን ማካሄድ ይችል ዘንድ የሚያደርጋቸው ዝግጅቶች፦

    • የሕዝበ ውሳኔ አካሄድ የሚመራበት የሥነ-ስርዓት መመሪያ ማዘጋጀት
    • የሕዝበ ውሳኔ አጠቃላይ ጊዜ ሰሌዳና በጀት ማዘጋጀት
    • በሕዝበ ውሳኔ ዝግጅትና ድምፅ መስጠት ሂደት ስለሚኖረው የፀጥታ አጠባበቅ ሁኔታ ግብረ ኃይል ማደራጀትና ዕቅድ ማፅደቅ
    • ገለልተኛ የምርጫ አስፈፃሚዎች መመልመል፣ ማሰልጠንና ማሰማራት
    • ከባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ መድረክ ማዘጋጀት፣ የድርጊት መርሃ ግብር ማውጣት
    • በሕዝበ ውሳኔ አፈፃፄም ሂደቱ ላይ የጋራ ምክክር መርሃ ግብሮችን አውጥቶ መተግበር
    • የሰነድና ቁሳቁስ ዝግጅትና ህትመት ሥራዎች ማከናወን
    • ድምፅ መስጫ ወረቀቶችና ፖስተሮች ማዘጋጀት፣ ማሳተም፣ ማሰራጨት
    • ሕዝበ ውሳኔ ድምጽ ማሰጠት
    • ቆጠራና ውጤት ማሳወቅ

    ሲሆኑ በሌላ በኩል ሂደቱ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም የሚጠበቅባቸውን ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

    በዚህም መሰረት፦

    1. የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ከክልሉ መንግስትና ከዞኑ መስተዳደር ጋር በመመካከር በአሁኑ ወቅት የክልሉም የዞኑም አስተዳደር ዋና ከተማ ሆና የምታገለግለው የሀዋሳ ከተማ የሕዝበ ውሳኔው ውጤት የሲዳማን ክልል መሆን የሚያረጋግጥ ቢሆን በከተማዋ ላይ ሁለቱ አካላት የሚኖራቸውን መብትና ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚነሱ የሃብት ክፍፍል ጥያቄዎችን የሚያስተናግዱበትን አሠራር አዘጋጅተው ለቦርዱ እንዲያሳውቁ፤
    2. በአዋጅ 532/1999 አንቀጽ 107 በተጠቀሰው የትብብር ድንጋጌ መሰረት የሕዝበ ውሳኔው ጸጥታና ደኅነትን (electoral security) ማስጠበቅን አስመልክቶ የፌደራል ፓሊስ፣ የክልሉ ፓሊስና የዞኑ ፓሊስ በትብብር የሚሠሩበትን ዝርዝር እቅድ እንዲያወጡና ከቦርድ ጋር ተባብረው እንዲሠሩ፤
    3. የደቡብ ክልል ምክር ቤት በሲዳማ ዞን የሚኖሩ የተለያዩ የሌሎች ብሄር ብሔረሰብ አባላት ከሕዝበ ውሳኔው በኋላ የሚኖራቸውን ህጋዊ የመብቶች ጥበቃ አስመልክቶ ግልጽ አስተዳደራዊና ህጋዊ ማእቀፍ እንዲያዘጋጅና ለቦርዱ እንዲያሳውቅ ምርጫ ቦርድ የወሰነ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የሚመለከታቸው አካላት ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ምላሽ እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. በጽሁፍ እንዲያሳውቁ ወስኗል፤
    4. በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕገ መንግስቱና በምርጫ አዋጁ የተሰጠውን ኃላፊነት ዓለም አቀፍ የምርጫ መሰረታዊ መርሆዎች ጋር በማጣመር ኃላፊነቱን ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ለመግለጽ ይወዳል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
    ሐምሌ 10/2011 ዓ.ም.

    የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄን ሕዝበ ውሳኔ አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.