Home › Forums › Semonegna Stories › ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
Tagged: አቢሲንያ ባንክ, የኢትዮጵያ አየር መንገድ, የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን, ዳሸን ባንክ, ፀሐይ ባንክ
- This topic has 55 replies, 3 voices, and was last updated 9 months, 1 week ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
December 4, 2022 at 2:09 am #54811SemonegnaKeymaster
“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በሚቀጥሉት አስር ዓመታትም የሚቀጥል ነው – አቶ መላኩ አለበል የኢንዱስትሪ ሚኒስትር
አዲስ አበባ (ኢፕድ) – “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በሚቀጥሉት አስር ዓመታትም ተጠናክሮ የሚቀጥልና ራሱን የቻለ ፕሮጀክት ቢሮ ተቋቁሞለት በጥብቅ ዲስፕሊን እየተመራ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በተለይም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢፕድ) እንደገለፁት፥ “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ እሳቤው በጣም ሰፊ እና በሚቀጥሉት አስር ዓመታትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።
እንደሀገር ለኢትዮጵያ የማምረት ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው፤ ኢትዮጵያ ማምረት አለባት ያሉት ሚኒስትሩ፥ የለመድነውና ደጋግመን የምንለው መሪ ሀሣብ አለን። ይህም “ኢትዮጵያ ለዘላላም ትኑር” እንላለን፡፡ ኢትዮጵያ ዘላለም መኖር የምትችለው ማምረት ስትችል ነው ብለዋል።
‘የምንፈልጋት ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትኖር ለማድረግ ማምረት አለብን፤ ሁሉም ዘርፎችም ማምረት አለባቸው’ ያሉት ሚኒስትሩ፥ “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በሚጀምርበት ወቅት የማምረቻ (manufacturing) ኢንዱስትሪ ላይ ያሉትን ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት በሀገር ምርትና ምርታማነት በማተኮር የመነጨ የአንድ ተቋም ሳይሆን የሀገር ሉዓላዊነት አጀንዳም ጭምር መሆኑን አመልክተዋል።
ለመልፋት፣ ለመድከምና በኢኮኖሚ ጠንካራ ለመሆን መሥራት ያለብንን ባለመሥራታችን ምክንያት ወደ ኋላ ቀርተናል፤ በመሆኑም “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ የሉዓላዊነት፣ የመኖርና የህልውና እሳቤ ነው። “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ጋር የተያያዘ ፖለቲካውንም፣ ኢኮኖሚውንም ማኅበራዊ ጉዳይንም የሚነካ ነው። በመሆኑም ለጠላት ያልተንበረከከ ጉልበት ለስንዴ መንበርከክና እጁን መዘርጋት እንደሌለበት አስገንዝበዋል።
“ያለፉትን 6 ወራት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አፈፃፀም ከፌደራልና ክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ ዛሬ [ኅዳር 9 ቀን፥ 2015 ዓ.ም] ገምግመናል። በተገኙ አበረታች ውጤቶችና ቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይም ተግባብተናል።” የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው
“ኢትዮጵያ ታምርት” የንቅናቄ አጀንዳ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስጀምረውት እስከ ታች ወረዳ ድረስ አምራቾች ማግኘት የሚገባቸውን ድጋፍ ማግኘት አለባቸው በሚል መነሻ የመጣ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ከዚህ አኳያ አንዱ የተሳካው ግብ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ እንደነበር ተናግረዋል።
በተጨማሪም አምራቾች ከእያንዳንዱ የመንግሥት አካልም ማግኘት ያለባቸውን ድጋፍ ማግኘት አለባቸው የሚለው እሳቤ ስኬታማ እየሆነ ነው፤ አጀንዳም ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
“በየትኛውም ሀገር ላይ ኢንዱስትሪዎች ጠንካራ የፖሊሲ ድጋፍ የሚያደርጉ መንግሥታት ውጤት ናቸው” ያሉት አቶ መላኩ አለበል፥ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ኢንዱስትሪዎች የገጠሟቸው ማነቆዎች እንዲፈቱ በማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። በዚህም የቆሙ ኢንዱስትሪዎች ችግራቸው ተፈትቶ ወደ ሥራ ተመልሰዋል፤ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ዘርፉ ገብተዋል፤ ያለአግባቡ የባከኑ መንግሥትና የሕዝብ ሀብቶች እንዲመለሱ ማስቻሉን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ትልቁ ሀብት መሬት ነው። ያለአግባብ መሬት ከያዙት በመቀበል ለአልሚዎች ተላልፏል። ችግሮችን በመለየት እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ችግሮቻቸውን ለመፍታት አቅም ሰጥቷል፤ የአደረጃጀት ችግሮችም ተፈትተዋል። በመሆኑም “ኢትዮጵያ ታምርት” የሚለው ንቅናቄ ትልቅ ውጤት አስገኝቷል። ይህም የአንድ ዓመት ዘመቻ ሳይሆን በዘላቂነት የሚሠራ ነው። የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ፥ ያለውን ፖሊሲ በመተግበርና አማራጮችን በመመልከት የሚስተካከሉ ጉዳዮች መኖራቸውንም አስገንዝበዋል።
ባለፈው ዓመት (የ2014 በጀት ዓመት) የአስር ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ጊዜ፥ በበጀት ዓመቱ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ውጤት ማምጣቱን ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገልጾ ነበር።
ምንጭ፦ ኢፕድ
December 20, 2022 at 2:47 am #55127SemonegnaKeymasterፀሐይ ባንክ አ.ማ. ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊየን ብር ለማሳደግ ወሰነ፤ የቦርድ አስመራጭ ኮሚቴንም አስመረጠ።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – የፀሐይ ባንክ አ.ማ. በባለአክሲዮኖች አንደኛ መደበኛና አንደኛ አስቸኳይ ጉባኤ ታኅሳስ 8 ቀን፥ 2015 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሆቴል ባካሄደው ስብሰባ የባንኩን የተፈረመ ካፒታል ከብር 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወደ አምስት ቢሊዮን እንዲያድግ ተወሰነ።
ፀሐይ ባንክ ካፒታሉን ለማሳደግ በምክንያትነት ያቀረበው በዓለም አቀፍ፣ ሀገራዊ እና በፋይናንስ ዘርፉ የታዩ ዓበይት ለውጦች ምክንያት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሀገር በቀል ባንኮች ሊኖራቸው የሚገባው ዝቅተኛ የካፒታል መጠን ላይ ማሻሻያ በማድረጉ፤ የውጪ ባንኮች በባንክ ዘርፉ እንዲሳተፉ የሚፈቅድ ፖሊሲ በመውጣቱ እና ወደ የባንኩን ዘርፍ በሚቀላቀሉበት ወቅት በሚፈጠረው ውድድር አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት የተሻለ የካፒታል ቁመና ላይ መገኘት አስፈላጊ በመሆኑ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም እጅጉን ተለዋዋጭ በሆነው የፋይናንስ ዘርፍ ምኅዳር ውስጥ አሸናፊ ሆኖ የመሥራች ባለአክሲዮኖች ራዕይ ማሳካት የሚቻለው በቅድሚያ የተፈረመ ካፒታል ቀሪ ክፍያ በአጠረ ጊዜ ውስጥ መሰብሰብ ሲቻል እንደሆነ እና ባንኩ የነደፈውን ስትራቴጂ ለመተግበር እንዲሁም ከግብ ለማድረስ የተፈረመ ካፒታሉን መሰብሰብ አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ በጉባኤው ላይ ተመልክቷል።
በዚሁ መሠረትም ቀደም ተብሎ የተፈረመ ካፒታሉ ላይ ያልተሰበሰበ ገንዘብ የመጀመሪያውን ግማስ 37 ነጥብ 5 በመቶ በፈረንጆች አቆጣጠር እስከ ጥር 2023 (January 2023) መጨረሻ ድረስ፤ እንዲሁም ቀሪውን 37 ነጥብ 5 በመቶ እስከ መጋቢት2023 (March 2023) መጨረሻ፤ በመጨረሻም የማጠናቀቂያውን ክፍያ እስከ ሰኔ 2023 (June 2023) መጨረሻ እንዲከፈል ተወስናል።
የካፒታል ማሳደጉን በተመለከተ አምስት ቢሊዮን ለመሙላት የሚቀረውን 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በፈረንጆች አቆጣጠር በሐምሌ 1 ቀን፥ 2023 (July 1, 2023) ተፈርሞ በዓመቱ ተከፍሎ እንዲጠናቀቅ የተወሰነ ሲሆን፤ የካፒታል እድገት ውስኔው ተግባራዊ የሚደረገው ቀደም ሲል ተፈርመው ያልተከፈሉ የባንኩ አክሰዮኖች ሙሉ በሙሉ ተከፍለው ሲጠናቀቁ መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም የፀሐይ ባንክ አ.ማ. ለቀጣይ ሦስት ዓመታት የሚመሩ የዳይሬክተሮች ቦርድን ለማስመረጥ የሚሠሩ የአስመራጮች ምርጫ የተካሄደ ሲሆን፤ አስር አባላት ተጠቁመው ከፍተኛ ድምጽ ያገኙ አምስት አስመራጮችን ጉባኤው መርጧል።
ፀሐይ ባንክ አ.ማ ሀምሌ 16 ቀን፥ 2014 ዓ.ም “ፀሐይ ለሁሉ” በሚል መሪ ቃል በይፋ ሥራ የጀመረ ሲሆን፤ በመላ ሀገሪቱ በርካታ ቅርንጫፎች ከፍቶ መደበኛ እና “ፈጅር” የተሰኘ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ለሕብረተሰቡ በመስጠት ላይ የሚገኝ ባንክ ነው።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የቅርንጫፍ ቁጥሩን ወደ 100 የሚያደርስ ሲሆን፤ በተጨማሪም 15 የኤቴኤም ማሽን በመትከል አገልግሎት እንደሚሰጥና ከ356 ሺህ በላይ ደንበኞችን የማፍራት እቅድ ይዞ በመሥራት ላይ መሆኑ በጉባኤው ላይ ተገልጿል።
ምንጭ፦ የባንኩ ፈስቡክ ገጽ
December 30, 2022 at 4:43 am #55297SemonegnaKeymasterለኢንቨስትመንት ዘርፍ ተጨማሪ አቅም የሚሆነው ሲዳማ ባንክ
ቀደም ሲል “ሲዳማ ማይክሮፋይናንስ ተቋም” በመባል የሚታወቀው የብድርና ቁጠባ ተቋም “ሲዳማ ባንክ አክሲዮን ማኅበር” ሆኖ በባንክነት ለመደራጀት በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቷል።
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – በአንድ ሀገር የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ውስጥ የጎላ ሚና ካላቸው ባለድርሻ አካላት መካከል የፋይናንስ ተቋማት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ ተቋማት በሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ውስጥ ካላቸው ሚና መካከል አንዱ ለኢንቨስትመንት ተግባራት የፋይናንስ ምንጭ መሆናቸው ነው።
የብድርና ቁጠባ ተቋማትን ጨምሮ ባንኮችና የመድን (insurance) ድርጅቶች በአነስተኛም ሆነ በትልልቅ የኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦች፣ ማኅበራትና ኩባንያዎች የሥራ ማከናወኛ የገንዘብ ምንጮች እና የንብረት ዋስትናዎች ሆነው ይሠራሉ። ውጤታማ የኢንቨስትመንት ተግባራት አስተማማኝ የፋይናንስ አቅርቦት የሚፈልግ በመሆኑ በኢትዮጵያም ሆነ በሌላው ዓለም ያሉ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ከእነዚህ የገንዘብ ተቋማት ተሳትፎ ውጭ የሚታሰቡ አይደሉም።
ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የበርካታ ዜጎችን ሕይወት በበጎ የለወጡት የብድርና ቁጠባ ተቋማት ለአነስተኛና መካከለኛ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ውጤታማነት የነበራቸው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ አይዘነጋም። በኢትዮጵያ የብድር እና ቁጠባ ተቋማት ደንበኞች ቁጥር ከባንክ ደንበኞች ቁጥር በብዙ እጥፍ የላቀ ነው። ይህም ለአብዛኛው ሕዝብ የብድር አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት እነዚህ ተቋማት እንደሆኑ አመላካች ነው። አንጋፋ የሚባሉት የብድርና ቁጠባ ተቋማት የፋይናንስ አቅማቸው ከብዙ አዳዲስ ባንኮች ጭምር የተሻለ ነው። ዛሬ በትልቅ ስምና አቅም የሚታወቁ ብዙ የኢንቨስትመንት ድርጅቶች መነሻቸው እነዚህ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የብድርና ቁጠባ (የማይክሮፋይናንስ) ተቋማት አስተማማኝና ፍትሐዊ በሆነ አሠራር እንዲሠሩና ሕዝባዊ ተዓማኒነት እንዲኖራቸው እንዲሁም ባንክ ሆነው ለመንቀሳቀስ የሚስችላቸው ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው የሚያስችል መመሪያ ከሁለት ዓመታት በፊት ማውጣቱ ይታወሳል። የብድርና ቁጠባ ተቋማቱ ያላቸውን ግዙፍ የደንበኛና የፋይናንስ አቅም ትልልቅ በሆኑና የተሻለ ትርፍ ሊያመጡ በሚችሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲያውሉት የተዘጋጀው ይህ መመሪያ፤ ብዙ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ወደ ባንክ እንዲሸጋገሩና ወደ መደበኛ የባንክ ሥራ እንዲገቡ እያስቻለ ነው።
በዚሁ መመሪያ መሠረት ቀደም ሲል “ሲዳማ ማይክሮፋይናንስ ተቋም” (Sidama Microfinance Institution) በመባል የሚታወቀው የብድርና ቁጠባ ተቋም “ሲዳማ ባንክ አክሲዮን ማኅበር” (Sidama Bank S.C.) ሆኖ በባንክነት ለመደራጀት በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቷል። ባንኩ 1,988 ባለአክሲዮኖች ያሉት ሲሆን፥ የተፈረመ ካፒታሉ አንድ ቢሊዮን 447 ሚሊዮን ብር ነው። ከዚህ ውስጥ ከ583 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ገንዘብ የተከፈለ ካፒታል ነው።
የሲዳማ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀ መንበር አቶ አብርሃም ማርሻሎ ባንኩ ከብሔራዊ ባንክ የሥራ ፈቃድ ማግኘቱን ተከትሎ በባንክ ዘርፍ ተግባራት ላይ ለመሰማራት የሚያስችሉትን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እንዳከናወነ ይናገራሉ። አቶ አብርሃም በዚህ ረገድ ስለተከናወኑ ተግባራት ሲገልፁ “የባንኩ የውስጥ አሠራር የሚመራባቸውን መመሪያዎችን የማዘጋጀት፤ በብሔራዊ ባንክ መስፈርት መሠረት ውስጣዊ አደረጃጀቶችን የማሟላት፣ ከባንክ ዘርፉ ወቅታዊ እድገት ጋር የሚጣጣምና ባንኩን ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል የኮር ባንኪንግ ሶፍትዌር ግዢ ለመፈፀምና ባንኩ የሚመራበትን የአምስት ዓመታት ስትራቴጂካዊ እቅድ ለማዘጋጀት ቅድመ ዝግጅት ተግባራትን የማጠናቀቅ፣ የሠራተኞችን አቅም በስልጠና የመገንባትና ተቋሙን በብቁ ሰው ኃይል የማጠናከር፣ በመጀመሪያ ዙር የተሟላ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ 10 ቅርንጫፎችን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የማዘጋጀት እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ሂሳብን ጨምሮ የመጠባበቂያና የክፍያ ሂሳቦችን የመክፈት ተግባራት ተከናውነዋል” ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፥ ባንኩ ባለፈው የበጀት ዓመት 142.3 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 177 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ ከእቅድ የበላይ የሆነ አፈፃፀም አስመዝግቧል። ይህም ካለፈው ዓመት የባንኩ አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ58 በመቶ ብልጫ እንዲኖረው አድርጓል። 48 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ አቅዶ 83 ሚሊዮን ብር በማትረፍ በባንኩ ታሪክ የተሻለ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል። በጠቅላላው 165 ሚሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ በመሰብሰብም ከቀዳሚው ዓመት አፈፃፀም የ29 በመቶ እድገት አሳይቷል።
በብድር አቅርቦት ረገድ ደግሞ ባንኩ የሰጠውን ብድር በ86.6 ሚሊዮን ብር (በ29 በመቶ) በማሳደግ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠውን ብድር 462.5 ሚሊዮን ብር ማድረስ ችሏል። “የባንኩ የተበላሽ ብድር ምጣኔ 3.6 በመቶ ሲሆን፣ ይህም ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የአምስት በመቶ ምጣኔ አንፃር ሲታይ የሲዳማ ባንክ የተበላሸ የብድር ምጣኔ ጤናማ እንደሆነ አመላካች ነው” ይላሉ።
የሲዳማ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ሐጢያ ባንኩ ማይክሮፋይናንስ ተቋም በነበረበት ጊዜ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች ሲያገለግል እንደነበር አስታውሰው፤ አገልግሎቱ አዋጭና ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ በብሔራዊ ባንክ ሕጋዊ ማዕቀፍ መሠረት ባንኩ ይህን አገልግሎቱን እንደሚቀጥልም ይናገራሉ። ባንኩ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ የባንክ አገልግሎትን በገጠርና በከተማ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ መሆኑም ይህን አገልግሎቱን የማስቀጠል አካል ነው።
እርሳቸው እንደሚሉት፥ ተቋሙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ አድርጓል። ቀደም ካለው ጊዜ ጀምሮ የባንኩን አገልግሎት የሚጠቀሙ በእርሻ፣ በሆቴልና በሌሎችም የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች አሉ። የተቋሙ በባንክ አሠራር መደራጀት ደግሞ ይህን አገልግሎት ለማስፋትና ለማዘመን ተጨማሪ ዕድልና አቅም ይፈጥራል።
ተቋሙ ወደ ባንክ ሲሸጋገር ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠውን አነስተኛ መነሻ ካፒታል ለማሟላት የአክስዮን ሽያጭ ያከናወነ ሲሆን፣ የተፈረሙ አክሲዮኖች ተከፍለው እንዲጠናቀቁ በማድረግ ከመደበኛ የባንክ ሥራዎች በተጨማሪ ዓለም አቀፍ የባንክ ሥራዎችን ለማከናወን እየሠራ ይገኛል። “ወደ ባንክ ሥራ ስንገባ የጠንካራ የፋይናንስ አቅም ባለቤት መሆን ያስፈልጋል፤ አለበለዚያ አቅም ካላቸው ከሌሎች ባንኮች ጋር ለመወዳዳር አስቸጋሪ ይሆናል። ለትልልቅ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ብድር ማቅረብም ሆነ በፋይናንስ ገበያው ላይ ተፎካካሪ መሆን አይቻልም” ይላሉ። ይህን ለማሳካትም የተፈረሙ አክሲዮኖች እንዲከፈሉና የኮርባንኪንግ (Core Banking) ሥራን ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ አቶ ታደሰ ያስረዳሉ።
የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ መፈቀዱ መልካም ዕድሎችና ፈተናዎች እንደሚኖሩት የሚገልጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፥ መልካም ዕድሎችን መጠቀም ከተቻለ ፈተናዎቹን መቀነስና ተወዳዳሪ መሆን እንደሚቻል ነው የተናገሩት። የባንኮቹ መግባት የሀገር ውስጥ ባንኮች ውድድሩን ለመቋቋም ራሳቸውን እንዲያጠናክሩ፣ በዚህም ተገልጋዩ ሕብረተሰብ ተጠቃሚ እንደሚሆን ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ ባንኮች በካፒታል አቅምም ሆነ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ በሚጠበቅባቸውና ወቅቱ በሚፈልገው ልክ እየተንቀሳቀሱ አለመሆናቸውን ተናግረው፥ እነዚህን ክፍተቶች በማስተካከል ለውድድር መዘጋጀትና ለተገልጋዩ እርካታ መሥራት እንዳለባቸው ይመክራሉ። ከዚህ አንፃር ሲዳማ ባንክ ትልቅ አቅም ያላቸውን ባለሀብቶችን እንዲሁም ዳያስፖራውን ማሳተፍን ጨምሮ ያሉትን መልካም አጋጣሚዎች ሁሉ ተጠቅሞ በባንክ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ማቀዱን አቶ ታደሰ ገልፀዋል።
ሲዳማ ባንክ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚኖረውን አዎንታዊ አስተዋፅኦ በተመለከተም አቶ ታደሰ ሲናገሩ፥ “ገበያው አዋጭ በመሆኑ ባንኩ ለኢንቨስትመንት ሥራዎች የፋይናንስ ምንጭ የመሆን አቅም አለው። ቀደም ሲልም የባንኩን አገልግሎት የሚጠቀሙ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች አሉ። ወደፊትም ባንኩ ይህን ተግባሩን በስፋት አጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።
ሲዳማ ባንክ በማይክሮፋይናንስ ደረጃ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎችን ሲያገለግልና ለግለሰቦች እንዲሁም በአነስተኛና ጥቃቅን የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ ለተሰማሩ ማኅበራት የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። ብዙ ግለሰቦችና ማኅበራትም በተቋሙ የብድርና ቁጠባ አገልግሎት ሥራቸውን አሳድገው ዛሬ ትልልቅ ኢንቨስተሮች ለመሆን በቅተዋል።
የሲዳማ ክልል የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝደንት አቶ መስፍን ቂጤሳ እንደሚናገሩት፣ ተቋሙ በግል ንግድ ላይ ለተሰማሩ በርካታ ግለሰቦችና ድርጅቶች ባለውለታ ነው። እርሳቸውም ከባንኩ ጋር ያላቸው ደንበኝነት የቆየ መሆኑን አስታውሰው፥ “ከባንኩ የወሰድነው ብድር በጣም ጠቅሞናል፤ ትርፋማ ሆነን እንድንሠራ አግዞናል” በማለት የባንኩ የብድር አገልግሎት ለውጤታማነታቸው አጋዥ እንደሆናቸው አስረድተዋል።
“አካባቢው በቡና ምርት የታወቀ ስለሆነ ባንኩም ለቡናው ዘርፍ ትልቅ ድጋፍ እያደረገ ነው” የሚሉት አቶ መስፍን፤ ለቡና አብቃዮችና ነጋዴዎች እንዲሁም ለተደራጁ ማኅበራትም የፋይናንስ ዕድል እንደሚያመቻች ይገልፃሉ። በቀጣይም ከባንኩ ጋር ያላቸውን ደንበኝነት አጠናክረው፥ በይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተፈጠረውን መልካም ዕድል በመጠቀም ቡናን እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።
“ከዚህ ቀደም የነበረው የባንኮች ተደራሽነት ውስን ስለነበር ብድር ለማግኘት ችግሮች ነበሩ። ሲዳማ ባንክ ለኢንቨስትመንት ሥራዎች ብድር በማቅረብ ጥሩ ዕድል ይፈጥራል፤ ለልማት በተለይ ለኢንቨስትመንት ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ የሚገኝ ባንክ ነው። ጥሩ ተስፋ ያለው ባንክም ነው” በማለት አቶ መስፍን ባንኩ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ስለሚኖረው አስተዋፅዖ ይናገራሉ።
በግል የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ አየለች ዱካሞም የባንኩ ደንበኛ ናቸው። “ቀደም ሲል የሲዳማ ማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ነበርኩ” የሚሉት ወይዘሮ አየለች፥ ተቋሙ ባንክ ከሆነ በኋላ ከባንኩ ብድር መውሰዴ ሥራዬን ሰፋ አድርጌ እንድሠራ አግዞኛል። ብዙ ሰው ከሲዳማ ባንክ ብድር እየወሰደ እየሠራ ነው፤ እየተለወጠም ነው። ከባንክ ጋር መሥራት ጥቅሙ ብዙ ነው” ሲሉ ይገልጻሉ። ሲዳማ ባንክ በጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ሥራዎች ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ትልቅ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር አስታውሰው፤ ከባንኩ ብድር ወስደው ከአነስተኛ የንግድ ሥራ ተነስተው ለትልቅ ደረጃ የበቁ ሰዎችን እንደሚያውቁም ነው የጠቀሱት። ወደፊትም ከባንኩ ጋር ብዙ ሥራዎችን የመሥራት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
January 8, 2023 at 5:12 am #55413SemonegnaKeymasterፀደይ ባንክ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘቡ 24.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገለጸ፤ 1.5 ቢሊዮን ብር ማትረፍ ችሏል
ባሕር ዳር (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – ፀደይ ባንክ የባለ አክሲዮኖች 1ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል። የፀደይ ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘቡ 24.5 ቢሊዮን መድረሱን የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገልጸዋል።
በ2014 ዓ.ም ባንኩ ከተለያዩ መለኪያዎች አንፃር አበረታች ውጤት እንዳስመዘገበም አቶ ገዱ የተናገሩት። አያይዘውም የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ በ12 በመቶ አድጎ 24.5 ቢሊዮን ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ መድረሱንም ገልጸዋል።
ሰኔ 2020/21 በተደረገ ሪፖርት ባንኩ 38.9 ቢሊዮን ብር ካፒታል እንዳስመዘገበና 9.5 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ የተጣራ ካፒታል ማካበቱንም አንስተዋል።
ባንኩ የቁጠባ መጠኑን 28.1 ቢሊዮን ብር ያደረሰ ሲሆን፤ በ2014 የሒሳብ ዓመት 1.5 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ትርፍም አግኝቷል ብለዋል። ካለፈው የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ29 በመቶ እድገት አሳይቷል የተባለ ሲሆን ለበርካታ ዜጎችም የብድር አገልግሎት መስጠት መቻሉም ተነስቷል።
አቶ ገዱ በሪፖርታቸው ካቀረባቸው ነጥቦች ዋና ዋናዎቹ፦
- የፀደይ ባንክ እስከ ፈረንጆቹ ሰኔ 2022 አጠቃላይ ሀብቱ 44 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
- ጠቅላላ ካፒታሉ 11 ቢሊዮን ብር ነው።
- ጠቅላላ የተከፈለ ካፒታል7 ቢሊዮን ብር ነው።
- የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ5 ቢሊዮን ብር ደርሷል። ይህም ከባለፈው ዓመት ከነበረበት በ12 በመቶ እድገት አሳይቷል።
- ባንኩ የእቅዱን 94 በመቶ ማሳካት ችሏል።
- የባንኩ ጠቅላላ የብድር ክምችት6 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
- የብድር መጠኑንም በ29 በመቶ አሳድጓል።
- ባንኩ በበጀት ዓመቱ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች1 ቢሊዮን ብር አበድሯል።
- ፀደይ ባንክ 5 ቢሊዮን ብር ወጭ ማድረጉም በሪፖርቱ ተመላክቷል።
- በ2014 የሒሳብ ዓመት 5 ቢሊዮን ብር ትርፍም አስመዝግቧል፤ የ2015 የሒሳብ ዓመት ትርፉን ወደ 1.66 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ አቅዷል።
- ትርፉ ካለፈው የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነጻጸር 3 በመቶ ማደጉን የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ገዱ ገልጸዋል።
ባንኩ በቀጣይ ከ100 በላይ ቅርንጫፎችን በመክፈት የአገልግሎት አድማሱን እንደሚያሰፋ ነው የተገለጸው። ፀደይ ባንክ ሀገር ችግር ውስጥ በገባችበት ወቅት 100 ሚሊየን ብር ወጭ በማድረግ ለወገን ደራሽነቱን አስመስክሯል። እንደሀገር የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለመቋቋምም አጥብቆ ይሠራል ነው የተባለው።
በአጠቃላይ 471 ቅርንጫፎችን በማቀፍ በብድርና ቁጠባ ተቋምነት (የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም) ሲንቀሳቀስ ቆይቶ በቅርቡ ወደ ባንክ ተቋምነት የተሸጋገረው ፀደይ ባንክ፥ በአሁኑ ሰዓት ከ150 በላይ ቅርንጫፎቹ ውስጥ ከ12,200 በላይ ሠራተኞችን ቀጥሮ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 36 ወለሎች ያሉት ዋና ቅርንጫፍ እያስገነባና፥ ግንባታውም በ2015 የሒሳብ ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተዘግቧል።
January 12, 2023 at 11:41 pm #55494SemonegnaKeymaster“ዱቤ አለ” – ዳሸን ባንክ በቴክኖሎጂ የታገዘ የዱቤ ግብይት አስተዋወቀ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – ዳሸን ባንክ በቴክኖሎጂ የታገዙ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የባንክ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ባንኩ አዳዲስ አገልግሎቶችን የማስተዋወቅ ጥረቱን በመቀጠል አሁንም ከኢግልላየን ሲስተም ቴክኖሎጂ (EagleLion System Technology) ጋር በመተባበር የቆየውን የአብዛኛው ኢትዮጵያውያን የዱቤ ግብይት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና አስተማማኝ የባንክ አሠራር በማገዝ “ዱቤ አለ” የተሰኘና ሸማቾች በዱቤ በፈለጉት ጊዜ ያሻቸውን ገዝተው ቆይተው መክፈል የሚችሉበትን አሠራር እና መተግበሪያ ጥር 02 ቀን 2015 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሆቴል አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ- ሥርዓቱ ላይ የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙን ጨምሮ በርካታ የንግድ ማኅበረሰቡ አባላት ተገኝተዋል።
ይህ “ዱቤ አለ” ተብሎ የተሰየመው አገልግሎት ዳሸን ባንክ ከተለያዩ የንግድ ተቋማት ጋር በመተባበር ሕብረተሰቡ ቋሚና አላቂ ዕቃዎችንና በርካታ አገልግሎቶችን በ3 ወር፣ በ6 ወርና በ12 ወር በሚመለስ ዱቤ በወለድና ያለወለድ መግዛት የሚያስችል አማራጭ ነው። ይህም የማኅበረሰባችንን የኑሮ ጫና ይቀንሳል፤ በገበያው ውስጥ ምርት እንዲገላበጥ፣ አገልግሎቶችም ይበልጥ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እና የንግድ ማኅበረሰቡ ሽያጭ እንዲያድግ ብሎም ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል።
“ዱቤ አለ” የምርትና አገልግሎት አቅራቢዎች ለደንበኞቻቸው እጅግ አመቺ የሆነ የዱቤ አገልግሎት በማቅረብ ተመራጭነታቸውን እንዲያሳድጉም ይረዳል።
ደንበኞች መተግበሪያውን ከጉግል ፕሌይ ስቶር (Google Play Store) ወይም ከአፕ ስቶር (App Store) በማውረድ ለአገልግሎቱ መመዝብ ይችላሉ። ከተመዘገቡ በኋላም ወደ ዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ በማምራት የዱቤ ገደብ ማስፈቀድና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ።
ዳሸን ባንክ ጠንካራ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት መገንባት የቻለ ሲሆን በቅርቡ በግል ባንኮች ታሪክ የመጀመሪያው ትልቅና ዘመናዊ የሆነውን የመረጃ ማዕከል አስመርቋል። በዚህ ጠንካራ መሠረተ ልማት ላይ ተንተርሶም አሞሌ በተሰኘው የዲጂታል ባንክ አገልግሎቱ ሰፊውን የማኅበረሰባችን ክፍል ተጠቃሚ አድርጓል። በቅርቡም አነስተኛ ቁጠባና ብድር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር መጀመሩ ይታወሳል።
ዳሸን ባንክ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት የግል ባንኮች ቀዳሚና አንጋፋው ሲሆን፣ ሀገር ውስጥ በስፋት ከሚንቀሳቀሱት እንዲሁም እጅግ ትርፋማ ከሆኑት የባንክና ፋይናንሻል ተቋማ አንዱ ነው። ባንኩ በመላው ሀገሪቱ ከ675 በላይ ቅርንጫፎች፣ ዘጠኝ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ምንዛሪ አገልግሎት የሚሰጡ ቢሮዎች፣ ከ400 በላይ የገንዘብ ማውጫ ማሽኖች (ATM machines)፣ እና ከ1300 በላይ ፖይንት ኦፍ ሴል ተርሚናሎች (point-of-sale terminals) አሉት።
February 25, 2023 at 3:36 pm #56094SemonegnaKeymasterኢስት አፍሪካን ሆልዲንግ አክስዮን ማኅበር በቢሾፍቱ ከተማ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሊገነባ ነው
አዲስ አበባ – ኢስት አፍሪካን ሆልዲንግ አክስዮን ማኅበር በ108 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በቢሾፍቱ ከተማ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የካቲት 17፥ ቀን 2015 ዓ.ም ስምምነት ተፈራረመ።
በስምምነቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል ተሬሳ፥ ኢትዮጵያ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብት-ተኮር (ኢኮኖሚያዊ) ማሻሻያዎችን እያደረገች እንደምትገኝ ጠቁመው፤ ማሻሻያዎቹ አዳዲስ እና ያሉትንም ኢንቨስትመንቶች አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ ብለዋል።
እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ፥ ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለማጠናከር ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በልዩ ሁኔታ የሚደግፉ ፖሊሲዎች እና ማሻሻያዎች ጸድቀው ወደ ሥራ በመግባት አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገበ ነው። ለአብነትም ባለፉት ስድስት ወራት ከሁለት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (foreign direct investment) መሳብ ተችሏል ብለዋል ።
የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ አክስዮን ማኅበር ሊቀመንበር ዶክተር ብዙአየሁ ታደለ በበኩላቸው እንደገለጹት፥ የፓርኩ ግንባታ ሲጠናቀቅ ስፋቱ ወደ 100 ሄክታር የሚያድግ ሲሆን ለ15 ሺህ የሰው ኃይል የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባሻገር ለቴክኖሎጂ ሽግግር ዕድል የሚፈጥር ነው።
የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ በ108 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚለማ ሲሆን ንድፉ የኢንዱስትሪያል ፓርክ አጠቃቀም ሥርዓትን የተከተለ፣ መሠረተ ልማት የተሟላለት፣ 40 ሜጋ ዋት የኃይል አቅርቦት የሚኖረው እና ታዳሽ ኃይል (renewable energy) ላይ በትኩረት የሚሠራ እንዲሁም ኤክስፖርትን የሚያሳድግ ነው ሲሉ አብራርተዋል። በተጨማሪም የአካባቢውን አርሶ አደሮች በምርት አቅርቦት የሚያስተሳስር እና ለሀገር ውስጥ ግብዓት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ነው ሲሉ አክለዋል።
እንደ ዶክተር ብዙአየሁ ገለጻ፥ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ሙሉ ለሙሉ ወደሥራ ሲገባ ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ከማቅረብ ባሻገር ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ይሆናል።
የኢንዱስትሪ ፓርኩ ከአዲስ አበባ በ40 ኪሎ ሜትር ላይ መገኘቱ እና ከኢትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡር ጣቢያ በቅርብ ርቀት እንደሚገኝ ገልጸው፤ ከአዲስ አበባ – አዳማ ፈጣን መንገድ በሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገነባ መሆኑ እና ከሞጆ ደረቅ ወደብ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ መሆኑ ፓርኩን ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ አክስዮን ማኅበር በውስጡ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን የያዘ የሀገር በቀል ኩባንያ ሲሆን፤ ከዚህም መካከል የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት፣ ሲሚንቶ ምርት፣ አላቂ እቃዎች፣ የሪል ስቴት ልማት፣ ማዕድን ልማት እና ሎጀስቲክ የንግድ ዘርፍ የያዘ እና ከስድስት ሺህ በላይ ቋሚ እና ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ድርጅት ነው።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
April 30, 2023 at 2:04 am #56859SemonegnaKeymasterየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሁሉም መመዘኛዎች ውጤታማ አፈፃፀም ማስመዝገቡን አስታወቀ
የባንኩ ጠቅላላ ሃብት 1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር ደርሷል
የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚዎች ሹመት ጸደቀአዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሁሉም መመዘኛዎች ውጤታማ አፈፃፀም ማስመዝገቡን ፤ እንዲሁም የባንኩ ጠቅላላ ሃብት 1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር መድረሱን አስታውቋል።
በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከሚያዝያ 17-19/ 2015 ዓ.ም በተካሄደው የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ፣ ብድር በመስጠትና በመሰብሰብ፣ የዲጂታል ባንክ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝትና አቅርቦት እንዲሁም በሌሎች ፋይናንስና ፋይናንስ ነክ ባልሆኑ አፈፃፀሞች ውጤታማ ሥራ መሠራቱ ተጠቁሟል።
በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ123 ቢሊየን ብር በላይ ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉ በጉባዔው የተገለፀ ሲሆን፣ የባንኩ ጠቅላላ ሃብትም 1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ያህል ብር መድረሱ ታውቋል።
የዲጂታል ባንክ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ባንኩ ወጤታማ እንደነበር የተብራራ ሲሆን፤ በዘጠኝ ወራት ውስጥ በዲጂታል ባንክ አማራጮች ብቻ 2 ነጥብ 1 ትሪሊዮን ብር ተንቀሳቅሰሷል ብሏል ባንኩ በሥራ አፈፃፀም ግምገማው።
ባንኩ በዘጠኝ ወራት ውስጥ በሁሉም መመዘኛዎች መልካም አፈፃፀም ነበሩት ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በቀጣይ በተለይ ዋና ዋና የትኩረት ዘርፎች በሆኑት በተቀማጭ ሃብት አሰባሰብ፣ በዲጂታል ባንክ አገልግሎት፣ በብድር አሰጣጥና አሰባሰብ፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲሁም የባንኩን የሪፎርም (reform) ሥራዎች በማስቀጠል በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ በበኩላቸው ፋይናንስም ሆነ ፋይናንስ ነክ ባልሆኑ ዘርፎች የታዩትን አፈፃፀሞች፤ መልካሞቹን በማጠናከር ድክመቶችን ደግሞ በማረም በቀጣይ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ሁሉም የባንኩ ማህበረሰብ በአንድ ልብ ሊሠራ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ላይ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትና ከፍተኛ የሥራ አመራሮች፣ የሁሉም ዲስትሪክቶች ዳይሬክተሮች እና የልዩ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች ተሳትፈዋል።
ከባንክ ዜና ሳንወጣ፥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አምስት የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚዎችን ሹመት ማጽደቁን አስታውቋል። በዚህም መሠረት፥ አቶ ሰይፉ አገንዳ ኬርጋ – ቺፍ የከስተመርና ኦፕሬሽንስ ኦፊሰር (Chief Customer and Operations Officer)፣ አቶ ሰለሞን ጎሽሜ በጅጋ – ቺፍ የኮርፖሬት ሰርቪስስ ኦፊሰር (Chief Corporate Services Officer)፣ አቶ መልካሙ ሰለሞን ይመር – ምክትል ፕሬዚዳንት ሂዩማን ካፒታል (Vice President of Human Capital)፣ አቶ አብርሃም ተስፋዬ አበበ – ምክትል ፕሬዚዳንት የስትራቴጂና ማርኬቲንግ (Vice President of Strategy and Marketing) እና አቶ አሚነ ታደሰ ተስፉ – ምክትል ፕሬዚዳንት የኢንተርናሽናል ባንክ ኦፕሬሽን (Vice President of International Bank’s Operation) ሆነው ተሹመዋል።
ብሔራዊ ባንክ ሹመቱን ማጽደቁን ባሳወቀበት ደብዳቤ ላይ እንደገለጸው፥ በባንክ ሥራ አዋጅ ቁጥር 592/2000፣ በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1159/2011 እና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ ቁጥር SBB/79/2021 አንጻር የተላኩለትን ሰነዶች እና ሌሎች ማስረጃዎች ላይ ተገቢውን ማጣራት አድርጎ መሆኑን አረጋግጧል።
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በቅርቡ የስትራቴጂክ (መሪ) እቅድ ክለሳ ያደረገ ሲሆን፤ ይኸው የከፍተኛ ኃላፊዎች ሹመትም ከዚሁ ክለሳ ጋር ተያይዞ የተዘጋጀውን አዲስ የባንኩን አደረጃጀት መሠረት ያደረገ ነው።
August 21, 2023 at 3:09 am #58500SemonegnaKeymasterዳሸን ባንክ እና ማስተርካርድ የመጀመሪያውን ቨርቹዋል ዓለም አቀፍ ቅድመ ክፍያ ካርድ አስተዋወቁ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ዳሸን ባንክ ዓለም አቀፍ ቅድመ ክፍያ ካርድ ከማስተርካድ (Mastercard) ጋር በመተባበር ከተለመደው በስም ከሚታተም የፕላስቲክ ካርድ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነ ቨርቹዋል ካርድን (virtual card) በማምጣት ነሐሴ 15 ቀን፥ 2015 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል አስተዋውቀዋል።
የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ዳሸን ባንክ ይህን በዓይነቱ የተለየ ካርድ ማስተዋወቁ ባንኩ ለደንበኞቹ ቀላል፣ ምቹና አስተማማኝ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ይበልጥ ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል። ካርዱ ደንበኞች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ገንዘባቸውን ያለምንም ስጋት መጠቀም የሚችሉበት አማራጭ መሆኑንም አመልክተዋል።
የማስተርካርድ የምሥራቅ አፍሪካ ሥራ አስኪያጅ ሸህርያር አሊ በበኩላቸው፥ ማስተርካርድ ከዳሸን ባንክ ጋር የፈጠረው ጥምረት በኢትዮጵያ እንደ ዓለም አቀፍ ካርድ ያሉ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ማኅበረሰቡ ይበልጥ የዲጂታል አገልገሎቶችን ተጠቃሚ እንዲሆን ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚፈጥር ገልፀዋል።
“ከዳሸን ባንክ ጋር በመጣመር የተለያዩ የዲጂታል አገልግሎቶችን ለማቅረብና ይህን መሰል የክፍያ አማራጭ ለንግዱ ማኅበረሰቡና ሌሎች ደንበኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻላችን ትልቅ ክብር ይሰማናል” ብለዋል።
በዳሸን ቅድመ ክፍያ ማስተርካርድ ደንበኞች ከኤቲኤም (ATM) እና ፖስ (PoS) በተጨማሪ በኢ-ኮሜርስ ክፍያ መክፈል የሚያስችላቸው ሲሆን፤ ደንበኞች ፕላስቲክ ወይም ቨርቹዋል (virtual) ካርድ በመውሰድ መጠቀም ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪ ፕላስቲክ ካርዱ ስም የታተመበትና ስም ያልታተመበት የካርድ ዓይነቶችን የያዘ ነው።
ደንበኞች ዳሸን ማስተርካርድ ላይ የተሞላው የውጪ ምንዛሬ ሲያልቅ እንደገና በመሙላት መጠቀም የሚያስችላቸው ሲሆን ካርዱን ኤቲኤምና ፖስ ማሽን ላይ በማስገባት ወይም ያለ ንክኪ ገንዘብ ማውጣት ወይም ክፍያ መፈፀም ያስችላቸዋል።
ፕላስቲክ ካርዱ በሚስጢር ቁጥር የተጠበቀ ሲሆን ቨርቹዋል ካርዱ ደግሞ በአንድ ጊዜ የይለፍ ቃል ደህንነቱ የተጠበቀ ነው። ደንበኞች ካርዱን ለመጠቀም አቅራቢያቸው በሚገኝ የዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ ፓስፖርት፣ ቪዛ እና የበረራ ቲኬት በመያዝ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ።
ዳሸን ባንክ እና ማስተርካርድ ከካርዱ በተጨማሪ የንግድ ተቋማት ክፍያቸውን በበይነ መረብ ከየትኛውም የዓለም ክፍል መቀበል የሚያስችል የማስተርካርድ የክፍያ መቀበያ ማስተርካርድ ጌትዌይ /MasterCard Payment Gateway System/ አስተዋውቀዋል።
ይህ የማስተርካርድ ጌትዌይ/ MasterCard Payment Gateway System/ ሦስት የካርድ አይነቶችን በመቀበል የተሻለ የአገልግሎት አማራጭ መሆኑ ተመልክቷል። ይህም ለንግድ ተቋማት ክፍያ ለመቀበል እና ሽያጭ ለማከናወን ለምግባረ ሰናይ ድርጅቶች እርዳታ እና የአባልነት ክፍያ ለመሰብሰብ እና ለሌሎች አገልግሎቶች ዘመናዊ የክፍያ መፈጸሚያ መስመር ነው።
ምንጭ፦ ዳሸን ባንክ
December 31, 2023 at 3:39 am #60670SemonegnaKeymasterዳሸን ባንክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ የአየር ትራንስፖርት ክፍያ አገልግሎት ይፋ አደረጉ
December 31, 2023 at 3:39 am #60671SemonegnaKeymasterዳሸን ባንክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ የአየር ትራንስፖርት ክፍያ (የበረራ ክፍያ) አገልግሎት ይፋ አደረጉ
አዲስ አበባ – ዳሸን ባንክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞች የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቅመው ክፍያውን ቆይተው የሚከፍሉበትን አዲስ የክፍያ አማራጭ በጋራ አስተዋወቁ።
አቶ ዮሃንስ ሚሊዮን የዳሽን ባንክ ዲጂታል ባንኪንግ ዋና መኮንን፥ ‘ጉዞዎ ይቀድማል ክፍያው ይደርሳል’ በሚል የተሰየመው ይህ አገልግሎት በደንበኞች ምርጫ መሠረት በ6 ወር ወይም በ12 ወር የብድር ክፍያ የሚሰጥ መሆኑን አመልክተዋል። ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን በዳሸን ባንክ የሂሳብ ቁጥር መክፈት እንደሚገባቸው እና በተጨማሪም በባንኩ ቢያንስ ለሦስት ወራት አገልግሎት ያገኙ መሆን እንደሚኖርባቸውም ጠቁመዋል።
አቶ ዮሃንስ አክለውም አገልግሎቱን ለማግኘት ደንበኞች አቅራቢያቸው ወደሚገኝ የዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ በሚያመሩበት ወቅት አስፈላጊ ሰነዶችን ማሟላት የሚገባቸው ሲሆን፥ ማስያዣም ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸውም ገልፀዋል።
ስምምነቱን አስመልክቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና የንግድ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ለማ ያዴቻ የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል፣ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኛ ተኮር አሠራርን እንደመከተሉ የተለያዩ ዘመናዊ እና ለመጠቀም ቀላል የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እያስተዋወቀ ይገኛል። የምናበለጽጋቸው ቴክኖሎጂዎች ለደንበኞቻችን ምቹ መሆናቸው እንደተጠበቁ ሆኖ የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎት ጋርም የተጣጣሙ እንዲሆኑ እናደርጋለን። ዛሬም አጋራችን ከሆነው የዳሽን ባንክ ጋር በመተባበር ለደንበኞቻችን ያቀረብነው አዲስ የክፍያ አማራጭ ተግባራዊ እንዲሆን የሞባይል መተግበሪያችን ከአዲሱ የክፍያ አገልግሎት ጋር የተቀናጀ እንዲሆን አድርገናል። በዚሁም መሠረት ደንበኞች ስለክፍያ ሳይጨነቁ ጉዟቸውን ማቀድ የሚጀምሩበትን ‘Fly Now Pay Later‘ ተብሎ የተሰየመውን የክፍያ አማራጭ ተግባራዊ ማድረጋችንን ስንገልጽ በደስታ ነው። ይህ የድኅረ-ጉዞ ክፍያ አማራጭ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን ከአየር መንገዳችን እና ከዳሽን ባንክ በኩል ለተሳተፉ አካላት ያለኝን ምስጋና በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እፈልጋለሁ።”
አዲሱን የበረራ ክፍያ አገልግሎት ለመጠቀም አንድ ደንበኛ አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎችን ካሟላ በኋላ በቅርንጫፉ የተፈቀደለትን የብድር መጠን የሚወስድ ሲሆን፥ የተፈቀደለትን ገንዘብ ለመጠቀም የሚያስችል የአንድ ጊዜ መለያ ቁጥር መልዕክትም በተንቀሳቃሽ ስልኩ የሚደርሰው ይሆናል። በመቀጠልም ደንበኛው የተሰጠውን መለያ ቁጥር በአየር መንገዱ የሞባይል መተግበሪያ ላይ በማስገባት ትኬት መቁረጥና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ይችላል።
ደንበኞች የተፈቀደላቸው የብድር መጠን ሲያልቅ ማደስ የሚችሉ ሲሆን፥ በአንዴ የወሰዱትን ብድርም ለተለያዩ በረራዎች ከፍለው መጠቀም ይችላሉ።አገልግሎቱ በተለይም በንግድ ሥራ ላይ ለተሰማሩ፣ ጅምላ አስመጪዎች እና ለዕረፍት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ውጭ ለሚሄዱ ደንበኞች አመቺ ነው።
በሁለቱ ተቋማት ስምምነት በቀረበው በዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈቀደው የብድር ገንዘብ መጠን እስከ ስድስት መቶ ሺህ (600,000) ብር የሚደርስ ነው። የሚፈቀደው ብድር ወለድ የሚታሰብበት ሲሆን፥ ይህም ደንበኛው በመረጠውና ብድሩን በወሰደበት የጊዜ ገደብ ከብድሩ ጋር አብሮ የሚከፈል ነው።
አየር መንገዱ እና ዳሽን ባንክ ወደፊትም የደንበኞችን አገልግሎት ለማዘመን አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም በትብብር መሥራታቸውን ይቀጥላሉ።
ምንጭ፦ ዳሸን ባንክ
March 18, 2024 at 12:54 am #62336SemonegnaKeymasterበኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጅታል የባንክ ሥርዓት በጊዜያዊነት መቋረጥን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሰጠ መግለጫ
መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጅታል የባንክ ሥርዓት ላይ ባጋጠመ ችግር ምክንያት የባንኩ መደበኛ አገልግሎቶች ለተወሰኑ ሰዓታት መቋረጣቸዉ ይታወቃል።
እንደሚታወቀው ቀልጣፋና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ባንኮች በሥርዓቶቻቸዉ ላይ በየጊዜዉ የደህንነት ፍተሻ እንዲሁም የማሻሻያ ሥራዎችን ያከናዉናሉ። በሥርዓቶቹ ላይ በሚከናወን ለዉጦችና ፍተሻዎችም የባንኮች አገልግሎት አልፎ አልፎ ሊቋረጥ ይችላል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጋቢት 7 ቀን፤ 2016 ዓ.ም. የተከሰተዉ የአገልግሎት መቋረጥ ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለማረጋገጥ ችሏል። ችግሩ ከተከሰተበት ሰዓት አንስቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የባንኩን እና የደንበኞቹን ደህንነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል። በመሆኑም የባንኩ መደበኛ አገልግሎቶች በአጭር ጊዜ ዉስጥ እንዲጀምሩና ባንኩ ወደተለመደው እንቅስቃሴው እንዲመለስ ማድረግ ተችሏል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተከሰተዉ የአገልግሎት መቋረጥ ባንኩ በመደበኛነት በሥርዓቶቹ ላይ በሚያደርገዉ ማሻሻያና ፍተሻ ምክንያት የተከሰተ እንጂ የባንኩን፣ የደንበኞቹን እንዲሁም አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ክስተት አለመሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለማረጋገጥ ችሏል።በችግሩ ምክንያት የተከሰቱ የደንበኞች መጉላላትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳቶችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስፈላጊዉን ምርመራ በማድረግ ወደፊት ለሕብረተሰቡ የሚያሳዉቅ መሆኑን ያረጋግጣል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት የሚጠቀሟቸዉን ሥርዓቶች ደህንነታቻዉ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ፣ ቀልጣፋና የደንበኞችን ፍላጎት የሚያሟሉ ስለመሆናቸዉ በየጊዜዉ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ በሁሉም የፋይናንስ ተቋማት የሚገኙ የፋይናንስ ሥርዓቶች ደህንነቸዉ የተጠበቀ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ያለምንም ስጋት የፋይናንስ አገልግሎቶችን መጠቀም መቀጠል ይችላል።
የገንዘብ (የፋይናንስ) ተቋማትም የሥርዓቶቻቸዉን ደህንነትና ቀልጣፋነት ይበልጥ ለማሳደግ የቴክኖሎጂ ተለዋዋጭ ባህርይ በማየት በቀጣይነት መሥራት እንደሚኖርባቸዉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጥብቅ ለማሳሰብ ይወዳል።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱ ደህንነት የበለጠ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ እና የተረጋጋ ሆኖ እንዲቀጠል አስፈላጊ እርምጃዎችንና የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያዎችን መዉሰዱን ይቀጥላል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ -
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.