Home › Forums › Semonegna Stories › ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት
Tagged: መቱ ዩኒቨርሲቲ, ሠመራ ዩኒቨርሲቲ, ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ, ሰላም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ, አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ, አሶሳ ዩኒቨርሲቲ, አክሱም ዩኒቨርሲቲ, አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ, አድማስ ዩኒቨርሲቲ, ወለጋ ዩኒቨርሲቲ, ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ, የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ, የጎንደር መምህራን ትምህርት ማሰልጠኛ ኮሌጅ, ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ, ዲላ ዩኒቨርሲቲ, ጅማ ዩኒቨርሲቲ, ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ
- This topic has 42 replies, 3 voices, and was last updated 1 year, 10 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
September 5, 2020 at 11:54 pm #15731AnonymousInactive
ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሀግብሮች ያስተማራቸውን ከ900 በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ
ወልቂጤ (ሰሞነኛ) – የሦስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ የሆነው ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሀግብሮች ያስተማራቸውን 929 ተማሪዎች ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ለሰባተኛ ጊዜ ባካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በክብር እንግድነት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ እንዳሉት፥ እውቀትና ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል ለአንድ ሀገር እድገትና ቀጣይነት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። በዚህ ረገድ ጥራትና አግባብነት ያለው ትምህርት በተለይ ደግሞ ከፍተኛ ትምህርት ማስፋፋት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ዶ/ር ሙሉ አክለውም፥ መንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሀገራችንን ሕዝብ ህይወት ቀላልና ዘመናዊ በማድረግ ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ቁልፍ ሚና እንዳላቸው በማመን በየዓመቱ ከፍተኛውን የሀገሪቱን በጀት ለትምህርት መድቦ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥ ሃሳቦችን በማፍለቅና በመተግበር መልካም አርአያ የሚሆኑ ዜጎችን ማፍሪያ፣ የዲሞክራሲያዊ አስተሳሰቦችና ቴክኖሎጂዎች መፍለቂያ፣ የባህላዊ እሴቶቻችን መጎልበቻ፣ የሕዝቦች የመተሳሰብ፣ የመቻቻልና የአብሮነት ባህል የሚቀመርባቸው ማዕከላት እንዲሆኑ ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ብለዋል – ዶ/ር ሙሉ።
ሚኒስትር ዴኤታው ሰላም በምንም ነገር የማይተካ መሆኑን ገልጸው፥ ተመራቂዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉና በህይወት ጎዳናቸው ከጽዩፍ አስተሳሰብና እና ድርጊት ተጠብቀው በተሰማሩበት መስክ የችግሮች መፍትሄ በመሆን ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዶ/ር ሙሉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ተመራቂዎች ሀገራችሁንና ሕዝባችሁን በሚጠቅሙ ሥራዎች ላይ በመሰማራት ታታሪ፣ የሀገራችሁን ሁለንተናዊ እድገት እና ብልጽግና የምታረጋግጡ ሰላም ወዳድ እንድትሆኑ አደራ እላለሁ ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በአዋጅ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት በምርምር፣ በማኅበረሰብ-አቀፍ አገልግሎት (community-based service) እና መማር-ማስተማር መስክ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ኮቪድ-19 ከመጣ በኋላ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች የአንድ ወር ደመወዛቸውን በማዋጣት አቅመ ደካሞችን መርዳታቸውን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው ከ3,000 ሊትር በላይ ሳኒታይዘር፣ 4,000 የፊት ጭንብል (face-mask)፣ 1800 ብሊች (bleach) የማምረት ሥራዎችን ሠርቶ በጉራጌ ዞን ለሚገኙና በሥራ ጸባያቸው ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ ተቋማት ማበርከቱን ጠቁመዋል። ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የለይቶ ማቆያ ማዕከል (quarantine center) ሆኖ በማገልገል ላይም ይገኛል ብለዋል።
በምርምር ረገድም ድርቅን በመቋቋም የሚታወቀውን ቆጮን ጨምሮ በተለያየ መልኩ ለምግብነት የሚውለውን እና የአከባቢው ማኅበረሰብ የኑሮ አለኝታ የሆነውን የእንሰት ተክል እንዳይጠፋ፣ እንዲሁም ዝርያው እንዲጠበቅና እንዲሻሻል የእንሰት ማዕከል በማደራጀት ዝርያዎችን የማሰባሰብ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር ፋሪስ ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂ ተማሪዎች ሥራ ወዳድና ታታሪ፣ በሕግ የበላይነት ላይ የማትደራደሩ፣ የጥላቻን ዘር የማትዘሩ በጥላቻ ሳይሆን የተዘራውን ክፉ አረም በፍቅርና አብሮነት የምትነቅሉ በሥነ-ምግባር የታነጻችሁ ሀገር ተረካቢ ብቻ ሳትሆኑ አሻጋሪ ናችሁ ብለዋል።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የዛሬው ምረቃ ሥነ ሥርዓት የተሳተፉት በክረምትና በማታ መርሀግብሮች በአምስት ኮሌጆች ስር በሚገኙ 15 ትምህርት ክፍሎች ከዓለምአቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) በፊት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወንድ 597፣ ሴት 143፤ በድምሩ 840 የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች እና በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጆች ስር በሚገኙ አራት ትምህርት ክፍሎች ከወረርሽኙ በኋላም በቴክኖሎጂ አማራጮች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ በመደበኛና በማታው የድኅረ ምረቃ መርሀግብሮች ወንድ 81፣ ሴት 8፤ በድምሩ 89 ምሩቃን ናቸው።
በ2004 ዓ.ም በ13 የትምህርት መስኮች 595 መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ጊዜ በስምንት ኮሌጆችና አንድ ትምህርት ቤት በቅድመ ምረቃ 50 መርሀግብሮች እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪ እና 12 ፕሮግራሞች በጠቅላላው ከ14 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛ፣ በማታና በክረምት መርሃ ግብሮች እያስተማረ ይገኛል።
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
September 6, 2020 at 1:06 am #15737SemonegnaKeymasterቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ
ዲላ/አርባ ምንጭ (ኢዜአ/አ.ም.ዩ) – ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መረሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 1,043 ተማሪዎችን ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመረቀ።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫላ ዋታ እንደገለጹት ከተመራቂዎቹ መካከል 283 በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው። ቀሪዎቹ በምስክር ወረቀት የተመረቁ መሆኑን አስረድተዋል።
ተመራቂዎቹ ትምህርታቸውን በበይነ መረብ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ሲከታተሉ እንደቆዩ አመልክተው፥ በተለይ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት የክፍል ትምህርታቸውን ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው በተጓዳኝ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን መከላከልን ጨምሮ በተለያዩ የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ዶ/ር ጫላ ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል አቶ ኡዴሳ ክዮላ በበኩላቸው፥ ተመራቂዎቹ በቀጣይ በሚሰማሩበተ የሥራ መስክ ሀገርና ሕዝብ የሚጠብቅባቸውን ኃላፊነት በታማኝነትና ታታሪነት እንዲወጡ አሳስበዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርቱን የተከታተለው ቅዱስ ይገረሙ በሰጠው አስተያየት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያሳደረውን ተጽዕኖ ተቋቁሞ ትምህርቱን በማጠናቀቅ ለምረቃ በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል። በሰለጠነበት በ“ሶፍትዌር ዲዛይን” ዘርፍ በመሰማራት እራሱንና ሀገሩን ለመጥቀም እንደሚሠራ ተናግሯል።
በሁለተኛ ዲግሪ ማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ የተመረቀው ዋቆ ጥላሁን በበኩሉ በትምህርት ቆይታው ያገኘውን እውቀት በመጠቀም ውጤታማ ሥራ ለማከናወን እንደሚጥር ገልጿል።
የሦስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ የሆነው ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መረሃ ግብሮች የሚያስተምራቸው ከ17 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንዳሉት በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ወቅት ተገልጿል።
ከተማሪዎች ምርቃት ጋር በተያያዘ፥ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ለ33ኛ ጊዜ አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው በ2012 ዓ.ም በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር በመደበኛ፣ በክረምት፣ በሳምንት መጨረሻ እና በተከታታይና ርቀት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 2,326 ተማሪዎች ቅዳሜ ነሐሴ 30/2012 ዓ/ም በተመሳሳይ ዕለት አስመርቋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው በስድስት የተለያዩ ካምፓሶች በ76 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በ99 የ2ኛ ዲግሪ እና በ21 የ3ኛ ዲግሪ መርሀግብሮች በአጠቃላይ ከ36 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሀግብሮች በማስተማር ላይ ይገኛል። ተቋሙ ባለፉት 33 ዓመታት በልዩ ልዩ የምህንድስና፣ የሕክምናና የጤና፣ የግብርና፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ የማኅበራዊ እንዲሁም የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ዘርፎች 56,958 ምሩቃንን በማፍራት ለሀገሪቱ የሰው ሀብት ልማት ጉልህ አስተዋፅዖ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አክለውም በ2012 የትምህርት ዘመን በ2ኛው አጋማሽ ላይ በዓለም ላይ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በሁሉም ደረጃዎች በመማሪያ ክፍል ሆኖ የመማር ማስተማር ሂደት የተቋረጠ ቢሆንም፥ ዩኒቨርሲቲዎች ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የጥናትና ምርምር ሥራቸውን ሲሠሩ የቆዩ ተማሪዎች አስፈላጊውን የምረቃ መስፈርት በማጠናቀቅ ለምረቃ መብቃታቸውን ተናግረዋል። በቀጣይ ዓመታት በተከፈቱ የ2ኛ እና የ3ኛ ዲግሪ መርሀግብሮች ላይ የማጠናከር ሥራ የሚሠራ ሲሆን፥ ዩኒቨርሲቲው በ2013 የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ3ኛ ዲግሪ የሚያስመርቅ መሆኑን ባቀረቡት ሪፖርት ጠቁመዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የጋሞ ዞን አስተዳዳሪና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ እንደተናገሩት፥ የመማር ግቡ ከግለሰብ ህይወት እስከ ሀገር ድረስ ያሉ የተለያዩ ችግሮችን በመፍታት ምቹና ተስማሚ አኗኗርን ለመፍጠር የለውጥና የዕድገት ጎዳናን መከተል ነው። በመሆኑም የዕለቱ ተመራቂዎች ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ማማ እንድትደርስ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ሲሉ አሳስበዋል። በተጨማሪም ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል። ሀገሪቱ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እየተሻገረች የምትገኝ እንደመሆኗ መጠን ፈተናዎቹን በብቃት መክተን ወደ መልካም ዕድል መቀየር ይጠበቅብናል ብለዋል።
በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እና የሬጂስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር በለጠ ይልማ የእጩ ምሩቃን መግለጫ በመስጠት አስመርቀዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ በክብር እንግድነት፣ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ (አ.ም.ዩ)
September 9, 2020 at 1:47 pm #15795SemonegnaKeymasterሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት ዘርፎች ያስተማራቸውን 659 ተማሪዎችን አስመረቀ
ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በቅድመ- እና ድኅረ- ምረቃ መርሀግብሮች ያሰለጠናቸውን 659 ተማሪዎችን ጳጉሜን 3 ቀን 2012 ዓ.ም አስመረቀ። ዩኒቨርሲቲው ለ12ኛ ዙር ለምረቃ ካበቃቸው ተማሪዎች መካከል 515 ወንዶች ሲሆኑ 144 ደግሞ ሴቶች ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው በእጽዋት ሳይንስ፣ በእንስሳት ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ፣ በኢኮኖሚክስ፣ በሥራ አመራር (Management)፣ እንዲሁም በጂኦግራፊና አካባቢ-ነክ ጥናቶች (Environmental Studies) በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ አስተምሮ አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አህመድ ሙስጠፋ እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል። እንደ ዶ/ር አህመድ ገለጻ፥ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ከ15 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስመረቅ ለውጤት አብቅቷል።
እንደ ተጠባባቂ ፕሬዝደንቱ ገለጻ፥ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተያዘው ዓመት በ46 የመጀመሪያ ዲግሪና በ23 የሁለተኛኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ከ17ሺ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በጥናትና ምርምር ሥራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ጭብጦች 18 የምርምር ንድፈ ሀሳቦች የቀረቡ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ 15ቱ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል – ዶ/ር አህመድ። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልም ከ3 ሺህ ሊትር በላይ የንጽህና መጠበቂያ ፈሳሽ (ሳኒታይዘር) በማምረት አገልግሎት ላይ እንዲውል ተደርጓልሲሉ አስረድተዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የዩኒቨርሲቲው ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፍቅሬ አማን በክብር እንግድነት ተገኝተው ባስተላለት መልዕክት፥ እንዳሉት የዘንድሮው የምረቃ በዓል ለዓለማችን፣ ብሎም ለሀገራችን ህዝቦች የኮርና ቫይረስ ወረርሽኝ ፈታኝ በሆነበት በዚህ ወቅት ተመራቂዎች የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማጠናቀቅ ለውጤት በመብቃታቸው የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ ገልጸዋል።
ሀገራችን በመደመር ፍልስፍና ከነበረችበት ችግር ወጥታ ወደ ብልጽግና ጎዳና እየተጓዘች ባለችበት በዚህ የይቅርታና የምኅረት ወር በሆነችው በጳጉሜ ወር ተማሪዎች ለምረቃ በመብቃታቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞውን ሚዛን ተፈሪ ግብርና ኮሌጅ መሠረት አድርጎ በደቡብ ክልል ሚዛን ተፈሪ እና ቴፒ ከተሞች በ1999 ዓ.ም የተቋቋመ ዩኒቨርሲቲ ነው።
February 8, 2021 at 1:40 am #18149AnonymousInactiveባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 5117 ተማሪዎች አስመረቀ
ባሕር ዳር (ሰሞነኛ)– ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን መመረቅ የነበረባቸው እና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት መቋረጡን ተከትሎ የዘገዩ ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ 4203፣ በሁለተኛ ዲግሪ 759፣ በሦስተኛ ዲግሪ 10፣ በስፔሻሊቲ 40፣ በፒጂዲቲ ቅድመ ምረቃ (post graduate diploma in teaching/PGDT) 105፤ በአጠቃላይ 1623 ሴት፣ 3494 ወንድ ተማሪዎችን፥ በድምሩ 5117 ተማሪዎችን ጥር 29 ቀን 2013 ዓ.ም. የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በክብር እንግድነት በተገኙበት አስመርቋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፥ “የዘንድሮ ተማራቂዎችን እንደተማሪ በርካታ መሰናክሎችን አልፈው ለዛሬው ቀን በመብቃታቸው ‘ከመወርቅ’ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ችግሮች በመከራ ጊዜ እንደ ወርቅ ነጥራችሁ በመውጣታችሁና ለዚህ ታሪካዊ ቀን እንኳን አደረሳችሁ” ብለዋል። ዶ/ር ፍሬው አክለወም፥ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንዲሆንና በሀገራችን ካሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ግምባር ቀደም እንዲሆን ላገዙት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በከተማዋ ውስጥ ላሉ የወጣት አደረጃጀቶችና ለሌሎች አጋር ተቋማትም ምስጋና አቅርበዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ተመራቂዎች ዓለምን እየፈተነ ባለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ ውስብስብ ችግሮችን አልፈው መመረቅ መቻላቸው ታሪካዊ ተመራቂዎች መሆናቸውን አውስተው፤ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገርና ቤተሰብ የጣለባቸውን አደራ በአግባቡ እንዲወጡ፣ በሰለጠኑበት የትምህርት መስክ ጠንክረው በመሥራት ሀገራቸውን በቅንነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው፥ ተመራቂ ተማሪዎች ‘ሀገሬ ምን አደረገችልኝ?’ ሳይሆን ‘ለሀገሬ ምን አደረኩላት?’ ብሎ ራስን መጠየቅ እና በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን ጥልቅ ዕውቀት ተጠቅመው በኮሮናቫይረስ ወረርሽ የቀዘቀዘውን ኢኮኖሚ እንዲሻሻል በማገዝ በሀገር ግንባታ ላይ የበኩላችውን አስተዋፅዖ ማበርከት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለባሕር ዳር ከተማ ብሎም ለክልሉ እንደ ዓይን ብሌን የሚታይ ግዙፍ የዕውቀት ማዕከል መሆኑንም ተናግረዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ በመመረቂያ ፕሮጀክቶች የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የምስክር ወረቀት እና የወርቅ ሜዳሊያ እንዲሁም በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የወርቅ ዋንጫ ተሸልመዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ክብርት ወ/ሮ ወርቅሰሙ ማሞ፣ የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ፣ የባሕር ዳር ዩኒቨረሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ ፣ የአማራ ክልል መልሶ ማቋቋም ድርጅት (አመልድ) ዋና ዳይሬክተር እና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ አባል ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ እና ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ባማረው እና በተዋበው የዩኒቨርሲቲው ስታዲየም በፖሊስ ማርሽ ባንድ በቀረበ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መዝሙር እና በሙሉ ዓለም የባህል የሙዚቃ ባንድ በቀረቡ የተለያዩ ባህላዊ ውዝዋዜዎች እና ዘመናዊ ሙዚቃዎች በመታጀብ ደምቆ ውሏል።
ምንጭ፦ ዩኒቨርሲቲው
August 1, 2021 at 12:34 am #20091AnonymousInactiveጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በድምቀት አስመረቀ፤ ለቴዲ አፍሮ የክብር ዶክትሬት ሰጠ
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ሐምሌ 24 ቀን፥ 2013 ዓ.ም በድምቀት አስመረቀ። በዚህ ደማቅ የምረቃ ሥነ ሥርዓት የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትርና የበዓሉ ልዩ የክብር እንግዳ የተከበሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት አጸደወይን፣ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ሞላ መልካሙ፣ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ብርሀኑ ፈይሳ፣ የቀድሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ፕ/ር መንገሻ አድማሱ፣ የተለያዩ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አባላት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የተመራቂ ወላጆችና ቤተሰቦች እንዲሁም የዕለቱ ተመራቂዎች ተገኝተዋል።
በዓመቱ በዩኒቨርሲቲው በተካሄደው በዚህ በሁለተኛው ዙር የተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት በመደበኛ፣ በተከታታይና በክረምት መርሀግብሮች ወንድ 4153፣ ሴት 2421 በአጠቃላይ 6574 ተማሪዎችን በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ፣ በሦስተኛና በስፔሻሊቲ የትምህርት ደረጃዎች አስመርቋል፤ እንዲሁም ለአንጋፋው የሙዚቃ ሰው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ሰጥቷል።
የነገ የሀገራችን ተስፋ የሆኑ የዕለቱ ተመራቂዎች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ፈታኝ ሁኔታዎችን ሁሉ በጽናትና በታላቅ ጀግንነት ተቋቁመው ለዚህች ልዩ ቀን በመድረሳቸው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት አጸደወይን አስተላልፈዋል። ተመራቂዎቻችን ወረርሽኙ የፈጠረውን አዲስ ሁኔታ በመቋቋም ለዚህ መብቃታቸውም ልጆቻችን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን ተፈትነው ማለፍ እንደሚችሉ ከወዲሁ ያረጋገጠ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ሲሉም አክለዋል።
ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹትም በጎርፍ መጥለቅለቅ ለተጎዱ ዩኒቨርሲቲው የቻለው ድጋፍ አድርጓል፤ የወረታ ግብርና ኮሌጅን የሳተላይት ማዕከል አድርጎ ከፍቷል፤ 6ኛው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲካሄድ ብዙ ሠርቷል፤ እንቦጭን ለማስወገድ በርካታ ጥረት አድርጓል፤ ከተለያዩ የውጭ ሀገራት ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማርና ሀገራዊ ትስስርን የመፍጠር ሥራ ተሠርቷል፤ በማይካድራና ሌሎች አካባቢዎች በተደረጉ ዘር-ተኮር ጥቃቶች ላይ በዩኒቨርሲቲው ምሁራን ጥናቶች እየተካሄዱ ነው፤ የኮቪድ ወረርሽኝን ለመከላከል አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ ይገኛል፤ እንዲሁም በገበታ ለሀገር መርሀ ግብር ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ በዲዛይን ሥራ እና የጎርጎራ ከተማን መሪ ዕቅድ በማዘጋጀት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። በአጠቃላይ 54 የሚሆኑ የማኅበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶች መተግበራቸውን የገለፁት ዶ/ር አሥራት አፀደወይን፥ በዚህ አመርቂ ተግባሩም ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ እውቅናና ሽልማቶች ከተለያዩ አካላት እንደተበረከቱለት በመክፈቻ ንግግራቸው አንስተዋል። “ከአባይ ወንዝ የምንቀዳው ፍቅር እንጅ ጥላቻ እንዳልሆነ ለተመራቂ ልጆቻችን በጓዳም በአደባባይም ነግረን አሳድገናቸዋል” በማለትም አለመግባባቶች በሰላም ይፈቱ ዘንድ በአባይ ተፋሰስ ለሚገኙ ሀገራት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትርና የበዓሉ ልዩ የክብር እንግዳ የተከበሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ እንደአድዋ በአንድ ያቆመን የአባይን ግድብን የውሃ ሙሌት በድል ባከናወንበት ወቅት በመካሄዱ የዛሬውን ምረቃ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል። የራሳችንን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ባለመጠቀማችንና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማፍለቅና መጠቀም ባለመቻላችን በድህነት እንኖራለን፤ ለዚህ ደግሞ በእውቀት የተደራጀ ኃይል ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ፥ ስለሆነም ለትምህርት ትልቅ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል። ተመራቂዎች በትምህርት ህይወታቸው ያገኙትን እውቀት በራስ በመተማመን ስሜት ከሁሉም ጋር በመከባበርና በመሥራት ታላቅ የሆነችውን ሀገር ታላቅነቷን ማስጠበቅ እንደሚችሉ ያላቸውን የጸና እምነት በመግለጽ ለተመራቂዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ አያይዘውም የግድቡ ሥራ ሀገር አቀፍና አለማአቀፍ ትኩረትና ድጋፍ እንዲያገኝና በስኬት እንዲጠናቀቅ ላደረገው ጉልህ ሚና ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ እውቅና ሰጥተዋል። ሁሉም ሰው በተሰማራበት ሥራ መልካም ውጤት በማስመዝገብ ራስንም፣ ሀገርንም የሚያስከብር መሆኑን ከድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ሁሉ ሊማር ይገባል በማለት ለአርቲስት ቴዎድሮስ፣ ለተመራቂዎችና ቤተሰቦቻቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
ምንጭ፦ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ
August 7, 2021 at 6:01 pm #20145AnonymousInactiveየጅማ እና ዲላ ዩኒቨርሲቲዎች ከ7,390 በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ
ጅማ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ፣ በማታውና በተከታታይ የትምህርት መርሀግብሮች ያሰለጠናቸውን 3,926 ተማሪዎች በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ነሐሴ 1 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. አስመርቋል።
በምርቃ ሥነ-ሥርዓቱ የተገኙት የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዲሪ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ባስተላለፉት መልዕክት፥ ከሀይማኖትና ብሔር ልዩነት ባለፈ ተዋድደንና ተፈቃቅረን እንደኖርነው ሁሉ፣ አሁንም በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘን የሀገራችንን ብልጽግና እናረጋግጣለን ብለዋል።
የኢፌዲሪ የጤና ሚኒስትር ዴኤታና የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው፥ በቀጣይ ዩኒቨርሲቲውን የላቀ የምርምር ማዕከል ለማድረግ የሥራ አመራር ቦርዱ ተግቶ ይሠራል ብለዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ ባደረጉት ንግግር፥ ከከፍተኛ ትምህርት ተልዕኮዎች መካከል የመጀመሪያው ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት በእውቀት፣ በክህሎት እና በሥነ-ምግባር የዳበረና ሀገር ተረካቢ ዜጋ ማፍራት ነው። ግቡም ተመራቂው ባካበተው የቴክኖሎጂ አቅም ራሱን አብቅቶ ሀገርንና ወገንን መቀየር ሲሆን፥ ጅማ ዩኒቨርሲቲም ይህንኑ ዓላማ እውን ለማድረግ ተግቶ በመሥራት ላይ ይገኛል ብለዋል። ለዚህም ምስክሩ በምርምርና ተቋማዊ አመራር የላቀ ውጤት ማስመዝገቡ ነው በማለት አክልዋል።
በዕለቱ ከተመረቁት ተማሪዎች መካከል በቅድመ ምረቃ 2,260 ወንድ ሲሆኑ፣ 1234 ሴቶች ተመራቂዎች ናቸው።
በድኅረ ምረቃ መርሀ ግብር ከተመረቁት 402 ተማሪዎች ውስጥ 318 ወንዶች ሲሆኑ፣ 85 ሴቶች ናቸው፡፡ ከድኅረ ምረቃ መርሀ ግበሩ 18 የሦስተኛ ዲግሪ (ፒ ኤችዲ) ምሩቃን ሲሆኑ፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ ከፍተኛው የሦስተኛ ዲግሪ መርሀግብር ተማሪዎች የተመረቁበት ነው። የሦስተኛ ዲግሪ ተማራቂዎቹ ከሒሳብ፣ ከጤና ግንኙነት (health communication)፣ እና ከኢንፎርሜሽን ሳይንስ ትምህርት ክፍሎች ናቸው።
በተጨማሪም ጅማ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሀግብር በሶፍትዌር ኢንጅነሪንግና በቪዥዋል አርት (ሥነ-ስዕል) የሰለጠኑ ተማሪዎችን ለመጀመሪያ ግዜ አስመርቋል።
ከተማሪዎች ምርቃት ጋር በተያያዘ ዜና፥፥ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በሁለተኛ ዲግር እንዲሁም በተከታታይ መርሀግብር ያሰለጠናቸውን ከ3,450 በላይ ተማሪዎችን እሁድ ነሐሴ 2 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው ያስመረቃቸው ተማሪዎች 2,101 ወንድና 983 ሴት በድምሩ 3,084 ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ፤ 317 ወንድና 72 ሴት በድምሩ 384 ተማሪዎችን በሁለተኛ ዲግሪ፤ በአጠቃላይ 3,468 ተማሪዎችን በዕለቱ አስመርቋል።
የዘንድሮው የዲላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት ለ23ተኛ ጊዜ የተከናወነ ሲሆን፥ ከተመሠረተበት ከ1989 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ71,475 በላይ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ለሀገር ኢኮኖሚ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል። በአሁኑ ወቃትም ከ26ሺህ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን በመደበኛ እና በተከታታይ የትምህርት መርሀግብሮች እያሰለጠነ ይገኛል።
ዩኒቨርሲቲው በዋናው ግቢው ያከናወነው የተማሪዎች ምርቃት ሥነ-ሥርዓት በፋና ቴሌቪዥን በቀጥታ እንደተተላለፈ የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ዘርፍ ዘግቧል።
August 8, 2021 at 11:19 pm #20154AnonymousInactiveለ2013 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ተመራቂዎች
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ያስተላለፉት መልዕክትየኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ምሩቃንና ሥልጠና አጠናቃቂዎች፦
ወቅቱ በሀገራችን የዘመን አቆጣጠር መሠረት የከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ምሩቃንንና ሰልጣኝ አጠናቃቂዎችን መርቀዉ ወደ ቀጣይ የሕይወት ምዕራፍ ሽግግር መልካም ምኞታቸዉን የሚገልጹበት ነዉ።
ከተለያዩ የሀገራችን ከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት የዘመኑ ተመራቂዎችና የስልጠና አጠናቃቂዎች እንዲሁም ወላጆችና ቤተ-ዘመዶች፤ ደማቅ በሆነዉ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ወቅት ላይ ያላችሁ በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ።
በተለይም የመጀመሪያ ዙር ለሆነላችሁ ምሩቃንና ሰልጣኞች፥ ይህ ወቅት የድካማችሁን ፍሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ያያችሁበት ወቅትና የላቀ ደስታ የሚሰማችሁ በመሆኑ፤ በድጋሚ ለዚህ ታላቅ ደስታና የሕይወት ምዕራፍ እንኳን አደረሳችሁ።
በ2013 የትምህርትና ሥልጠና ዘመን በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎችን በመቋቋም ምሩቃንንና ሥልጠና አጠናቃቂዎችን ለወቅቱ ደማቅ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት እያበቃችሁ ያላችሁ የሀገራችን የግልና የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት መምህራንና አሰልጣኞች፣ የትምህርትና ሥልጠና የሥራ መሪዎችና ባለሙያዎች፣ የተማሪዎች የምግብ ቤት፣ የክሊኒክና የግቢ ደህንነት ጥበቃ ሠራተኞች፣ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት አካባቢ ማኅበረሰብ የሰላምና የልማት አማካሪ ምክር ቤት አባላት በሙሉ፥ እናንተ በትብብር፣ በትስስርና በቅንጅት በመሥራት በኢትየዮጵያ ሰብዓዊ ካፒታል ዕድገትና ልማት ጉዞ የምታበረክቱት አስተዋጽኦ ዘመን ተሻጋሪ በመሆኑ ምስጋናችን እጅግ የላቀ መሆኑን ለመግለጽ እፈልጋለሁ።
የሰዉን ልጅ በተለይም ወጣቱን በዕዉቀት፣ በክህሎትና በስብዕና በመቅረጽ ሂደት የምታኖሩት አሻራ የነገዋን ዕዉቀት-መር የኢትዮጵያን ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዳይ ነዉ።
ወድ ምሩቃንና ሰልጣኝ አጠናቃቂዎች፥ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በርካታ ፈተናዎችን እየተሻገረች ትገኛለች።
ኢትዮጵያን ከጀግኖች አባቶቻችን እንዴት እንደተረከብን የታሪክ ምሁራንና አባቶቻችን አስተምረዉናል። በእዉነቱ ለማንም ያልተንበረከከች ሉዓላዊት ሀገር ነበረች፤ አሁንም ነች፤ እንደዚሁም ስለመቀጠሏ የምንወስነዉ እኛዉ የዘመኑ ባለቤቶችና ባለአደራዎች ነን። ዛሬ ላይ፥ ሉዓላዊነቷን ለመንጠቅ ከዉስጥና ከዉጭ በርካታ ኃይሎች እየተፈታተኗት ይገኛሉ፤ ድንበራችንን ከማለፍ ባሻገር እስከ ደጃፋችን ደርሰዉ ሊያጠቁን ይፈልጋሉ።
ኢትዮጵያ በርካታ ተደጋጋሚ ፈተናዎችን የመሻገር ልምድ ያላት ሀገር መሆኗ ይታወቃል። ነገር ግን ፈተናዎቹ በሀገር ሉዓላዊነት ጉዳይ ሲደጋገም ተገቢነት የለዉም፤ ምክንያቱም የሁሉም ዜጋ የህልዉና ጉዳይ አደጋ ላይ በመሆኑና አባቶቻችን ያስረከቡንን ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠችና በጽኑ መሠረት ላይ ያደረገች ሀገር ከትዉልድ ወደ ትዉልድ የማሻሻገር ኃላፊነት በአግባቡ የመወጣት ጉዳይ በመሆኑ ነዉ።
ጀግናዉ መከላከያ ሠራዊታችንና አጠቃላይ መዋቅር ደጀን ከሆነዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመተባበርና በመቀናጀት ሉዓላዊነቷን የሚፈታተነዉን ኃይል አደብ እንዲገዛ ማድረጉ ሩቅ አይሆንም። ሆኖም ግን የኢትዮጵያን ዘላቂ ሉዓላዊነት መገንባት ቀጣይ የቤት ሥራችን በመሆኑ፥ እናንተ ምሩቃንና ስለጠና አጠናቃቂዎች ሚናችሁን ልትወጡ ይገባል።
ምሁራን፣ ምሩቃን፣ እና ሰልጣኞች፡-
ዕዉቀት-መር ማኅበረሰብና ፖሊቲካል-ኢኮኖሚ መገንባት ለሀገራችን ኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ግንባታና ዘላቂነት ቀዳሚ መሣሪያ ነዉ ብለን እናምናለን። በዕዉቀት፣ በክህሎትና በጥበብ የበቃ ማኅበረሰብና የበለጸገ ኢኮኖሚ መገንባት ተነጣጥሎ ሊታዩ አይገባም እንላለን። ይህ እዉነት ሊሆን የሚችለዉ ደግሞ ከመማርና ከመሰልጠን ባሻገር፥ ዕዉቀታችንን፤ ክህሎታችንና ጥበባችንን በተገቢዉ ለሀገራችን ዕድገትና ልማት ግብዓት አድርገን በመጠቀም ምጣኔ ይወሰናል።
ጀግናዉ ሠራዊታችን የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በተለያዩ ግንባሮች እየተዋደቀ ይገኛል።
እናንተ የዕዉቀት መሣሪያ የያዛችሁ ደግሞ በሰለጠናችሁበት ሙያ በቅንነትና በታታሪነት ሀገራችንና ሕዝባችንን ያለቅድመ-ሁኔታ በታማኝነት ካገለገላችሁ፤ በኢኮኖሚዉ ግንባር ድጋፋችሁ የጎላ ይሆናል።
ምሩቃን እና ሰልጣኞች፡-
በሀገራችን አዲስ ምሩቅና ሰልጣኝ የመንግሥት ሥራ መያዝ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ መባልን ከስምና ዝና ጋር ያዛመደ ይመስላል። ሆኖም ግን እዉነቱ ከትምህርትና ሥልጠና በኋላ የተፈጠረዉን አቅም፣ ብቃትና ስብዕና እንደአንድ ካፒታል አካል በመቁጠር፥ ከሌሎች ተጓዳኝ የሀብት ምንጮች ጋር በማዳመር የተሻለ ሥራና ገቢ በሚያስገኙ መስኮች ያለብክነት መሰማራትን የሚያካትት መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም።
አዳዲስ ምሩቃንና ሰልጣኞች፥ እስካሁን ያገኛችሁትን የዕዉቀትና የክህሎት አቅምና ብቃት በመጠቀም፥ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ ሀብት ለማመንጨትና ባለጸጋ ለመሆን በርካታ አማራጮችን ኢትዮጵያ እየዘረጋች ነዉ። ይህን ለማየትና ለመገንዘብ የሚቻለዉ ከዚህ በኋላ የሚኖራችሁን የሕይወት ምዕራፍና አማራጭ መንገዶችን የመምረጥና የመወሰን አቅምና ብቃት ጊዜን ያማከለ ማድረግ ያስፈልጋል። ጊዜ እጅግ በጣም ዉድ ሀብት ነዉ፤ ከጊዜ ጋር አብሮ መጓዝ ያስፈልጋል።
የተለመደዉን በ‘ሥራ አላገኘሁም’ እና በ‘ሥራ አልፈጠርኩም’ አባባሎች መካከል ያለዉን ሰፊ ልዩነት የሚሞላዉ ያካበታችሁት ዕዉቀትና ክህሎት ሊሆን ይገባል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ዕዉቀት-መር ኢኮኖሚ እየገሰገሰች ትገኛለች። ይህ ደግሞ የዕዉቀትና የክህሎት ባለቤት የሆኑትን እንደእናንተ ዓይነት ዜጎችን በጽኑ ትፈልጋለች። ኢትዮጵያ መንገዷንም መዳረሻዋንም ለይታለች፤ ጉዞዋንም ጀምራለች። ዕዉቀት-መር ማኅበረሰብ ግንባታ ለፖሊቲካል ኢኮኖሚ ልህቀትና ዘላቂ የሀገር ሉዓላዊነት ወሳኝነቱ ሊረጋገጥ የሚችለዉ፤ ዕዉቀታቸሁና ክህሎታችሁ በተግባር ሲታይ ብቻ ነዉ።
ዕዉቀት-መር ማኅበረሰብ መገንባት ለዕዉቀት-መር ፖሊቲካል ኢኮኖሚ ግንባታ የሚኖረዉን ፋይዳ በአግባቡ ያለመገንዘብ የዋህነት ነዉ። የብዙ ታዳጊ ሀገሮች ዕድገታቸዉና ልማታቸዉ ዘገምተኛ ሆኖ ባለበት የሚሄደዉ፥ ምንም እንኳን ሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች ቢኖሩም፥ በዋናነት ግን ማኅበረሰባቸዉን የማንቃት ኃላፊነትን በአግባቡ ሳይወጡ ለረዥም ዘመናት ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም የረዥምና አጭር ዘመን ዕቅድ ያለበቂና ብቁ ፈጻሚ ዝግጅትና ስምሪት ለማከናወን የሚታትሩ በመሆኑ ነዉ። ሀገራችንም ይህን ዓይነት አዙሪት ባለፉት በርካታ ዓመታት አስተናግዳለች።
ስለሆነም፥ ዕዉቀት-መር ማኅበረሰብና ፖሊቲካል ኢኮኖሚን ነጣጥሎ ማየት፤ የሀገራትን ዕድገትና ልማት እንዲሁም ብልጽግና በእጅጉ እንደጎዳ የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ማስታወሱ በቂ ይመስለኛል።
ሰፊ መሬት፣ የወሃ ሀብት፣ የተመቻቸ የአየር ንብረት ያላት ኢትዮጵያ የዕፅዋትና የእንስሳት ልማት በዕዉቀት፣ በክህሎት፣ እና በጥበብ ያልመራች በመሆኗ፥ ፈጠራና ቴክኖሎጂ የመጠቀም ደረጃዋ ዝቅተኛ በመሆኑ፥ ምርትና ምርታማነትን ከተጨባጭ አቅም አንጻር በበቂ መጠን የማሳደግ ዕድል እስካሁን አጋጥሟት አያዉቅም። ለራሷ ዜጎች እንኳን በበቂ መጠን ምርት ማቅረብ አልቻለችም፤ እንደእኛ ድሃ የነበሩ ሀገራት ዛሬ ላይ የበለጸጉት እርሻቸዉንና ግብርናቸዉን በዕዉቀት፤ በፈጠራ፣ እና በቴክኖሎጂ በማዘመን ዜጎቻቸዉን ከመመገብ አልፈው ለዓለም ገበያ በአቅራቢነት እስከመምራት ደርሰዋል።
የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን ከተመለከትን፥ በደከመና የሰዉን ጉልበት በሚፈጅ ያረጀ ተክኖሎጂ በመጠቀም ወደምርት እንቀይራለን። ለምሳሌ ያህል፥ ደኖቻችንን ተጠቅመን የቤትና የቢሮ ቁሳቁስ እንኳን በጥራት ለማቅረብ ባለመቻል በገቢ ገበያ አቅርቦት ተወስነናል። ጥጥ እና ቆዳ አምራች ሀገር ሆነን ሳለ፥ የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን አብዛኛዉን ግብዓት ከዉጭ የሚያስገቡ በመሆኑ በኋልዮሽ ትስስርና በእሴት ሰንሰለት የሀገራችን ተጠቃሚነት ምጣኔ በሚፈለገዉ ደረጃ ላይ አይደለም። የማዕድናት ሀብት ልማታችን ከፍተኛ ካፒታልና ዕዉቀት የሚፈለገዉን ለጊዜዉ በሌሎች አማራጮች ማየቱ አግባብ ቢሆንም፥ በአነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ደረጃ በበርካታ ወጣት ምሩቃንና ሰልጣኞች ሊለሙ የሚችሉ ማዕድናትን እሴት ከመጨመር ይልቅ በጥሬዉ በማቅረብና መጠነኛ ገቢ በማግኘት ላይ የተወሰነ ሆኖ ዘልቋል። ለዚህም፤ ዋናዉ የመፍትሄ አካል መሆን የሚችለዉ በተለዩ አዋጭ አማራጮች ተግባር-ተኮር የክህሎት ሥልጠና ማበራከትና መጠነኛ መነሻ ካፒታል ማቅረብ ነዉ።
እንደእኛ ባሉ በአብዛኛዉ የሕዝብ ድርሻ በወጣቱ በሚወከልበት ኢኮኖሚ፥ በመረጃ እና ግንኙነት ቴክኖሎጂ (ICT) መስክ ለዜጎች የሚፈጠረዉ የሥራ ዕድል በየዓመቱ በርካታ ቢሆንም፥ የክህሎት ልማታችን በሚፈለገዉ የተግባር ስልጠና ሳይሆን በንድፈ-ሀሳብ የታጨቀ በመሆኑ በሀገር ዉስጥና ከሀገር ዉጭ ባሉ የሥራ ዕድሎች ያለንን ተሳትፎ ዝቅተኛ አድርጓል።
የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ የዘለቀዉና በርካታ መልካም ዕድሎች ያሉት፣ የምርት ኢንዱስትሪ ዘርፍ (manufacturing) ዘርፍ የዉጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና የሀገር ዉስጥ ተዋናዮች እየተበራከቱ ቢመጡም፥ በተሻለ ዋጋ የሠራተኛ ዕዉቀትና ክህሎት ለመጠቀም ባቀዱት ልክ ምርታማ ሆኖ ያለማግኘት፣ ኢንዱስትሪዎችም በተቻለ ፍጥነት እንዳያድጉ እንቅፋት ሆኖ እንደቆየ የሚያመላክቱ መረጃዎች አሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ምርታማና ትርፋማ የሆነ ኢንዱስትሪ እስካልተፈጠረ ድረስ ዕዉቀትና ክህሎት አቅራቢዉ ሠራተኛና ባለሙያ በበቂ መጠን ሊከፈለዉ አይችልም።
በኢንዱስትሪዎቹ መቋቋም ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞች ያሉ ቢሆንም፥ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ከግብዓት እስከ ምርት ድረስ ባለዉ የእሴት ሰንሰለት ሀገራዊ ተሳትፏችን እጅግ አናሳ በመሆኑ፥ ሥራና ሀብት የመፍጠር ዉጤታማነታችን ደካማ ሆኖ እናገኘዋለን። ለዚህም በእያንዳንዱ አምራች ኢንዱስትሪ የእሴት ሰንሰለት በሀገር ዉስጥ አቅም ሊቀርብ የሚገባ ግብዓት፣ ሊፈጠር የሚገባ የሥራ ዕድልና ካፒታል እንዲሁም ሊተካ የሚገባ የገቢ ገበያ አቅርቦት ዕዉቀት-መር ነዉ ማለት አይቻለም። ይህን ጉድለት ማረም እንደእናንተ ላሉ የዕዉቀት፤ የክሎት፣ እና የጥበብ ባለጸጋዎች ሌላ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራልና ጥረታችሁንና ትጋታችሁን ልታክሉበት ይገባል እላለሁ።
የሀገራችን የቱሪዝም ልማት ዘርፈ-ብዙ አማራጮች ያሉት በመሆኑ፥ ብዙ ጀማሪ ምሩቃንና ሰልጣኞች ሊሳተፉበት የሚገባ ምቹ ዘርፍ ነዉ። ለዚህም የቋንቋ ችሎታን የማሻሻል፣ የዲጂታል አሠራር ሥርዓትን የመፍጠር፣ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን መረጃ በማልማትና በማዘመን፣ አለፍ ብሎም በትብብርና በትስስር መጠነኛ ልማት በማከናወን የቱሪዝም ግብይት ተዋናይ መሆን፣ ከብዙ በጥቂቱ እንደዕድሎች ሊታዩት ይገባል።
በመሆኑም፥ ዉድ ምሩቃንና ሰልጣኞች፡-
ወደዕዉቀት-መር ማኅበረሰብና ፖሊቲካል-ኢኮኖሚ እየገሰገሰች ያለች ኢትዮጵያ እንደእናንተ ያሉ የዕዉቀት፤ የክህሎት፣ እና የጥበብ አርበኞችን በእጅጉ ትሻለች። በተለይም የኢትጵያንና የሕዝባችንን አንድነት በማጠናከር፣ ሉዓላዊነታችንን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስፈልገዉን ጠንካራና የማይበገር ፖሊቲካል-ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት ለማፋጠን ሚናችሁ እጅግ የላቀ በመሆኑ፥ በትጋት እንድትሠሩ አደራ እላለሁ።
በመጨረሻም፥ የምሩቃንና የሰልጣኝ ጥራት ባለቤቶች መምህራንና አሰልጣኞች በመሆናቸዉ፥ በ2013 ትምህርትና ሥልጠና ዘመን የላቀ ምርምርና የማስተማር ሥራችሁን በማበርከታችሁ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኛችሁት ምሁራን፥ እናንተም የልፋታችሁን ፍሬ በማግኘታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ እያልኩ፥ በተገኘዉ ተጨማሪ ድልና አቅም ኢትዮጵያን በተሻለ መነሳሳት እንድታገለግሉ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
በዕዉቀት፣ ክህሎት፣ እና ስብዕና የተገነባ ዜጋ በማፍራት፥ ወደዕዉቀት-መር ማኅበረሰብና ወደማይበገር ፖሊቲካል-ኢኮኖሚ በሚደረግ ሽግግር ድርሻችንን የጎላ እናድርግ!
ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትርAugust 9, 2021 at 12:23 am #20158AnonymousInactiveወላይታ ሶዶ ግብርና ኮሌጅ እና ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ከ6 ሺህ 8 መቶ በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ
“የግብርናውን ዘርፍ መዘመን ለምርታማነት መጎልበት የድርሻውን እያበረከተ ነው” – ወላይታ ሶዶ ግብርና ኮሌጅየግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እየተደረገ ያለው ጥረት ለምርታማነቱ መጎልበት የድርሻውን እያበረከተ እንደሚገኝ ወላይታ ሶዶ ግብርና ኮሌጅ አስታወቀ። ኮሌጁ ከ3,200 በላይ ሰልጣኞችን ለ18ኛ ጊዜ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በደረጃ አራት ዲፕሎማ እሁድ ነሐሴ 2 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. አስመርቋል። ምሩቃኑ በሰብል፣ በእንስሳት፣ በመስኖ እና በተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ የሰለጠኑ ናቸው።
በምርቃት መርሀ-ግብሩ ላይ የኮሌጁ ዲን ረዳት ፕሮፈሰር መርኪኔ መሰኔ ወላይታ ሶዶ ግብርና ኮሌጅ ባለፉት 17 ዙሮች ከ19,700 በላይ ሰልጣኞችን ማስመረቁን አውስተው፥ ዘንድሮ ለምረቃ ከበቁት 3,226 ሰልጣኞች መካከል 1,327ቱ ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኮሌጁ የእርሻ ሥራ አመራር በሳይንሳዊ ዘዴ በዘላቂነት እንዲቀጥል የሚያግዝ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ሥራዎችን በ32 ሄክታር ማሳ ላይ እያከናወነ እንደሚገኝ ፕሮፈሰር መርኪኔ ጠቁመዋል። አክለውም ኮሌጁ በ43 ሚሊየን ብር 60 መምህራንን ማስተናገድ የሚችል የመኖሪያ ህንጻ ግንባታ እያካሄደ እንደሚገኝ የተናገሩት ዲኑ፥ ከ30 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ገንዘብ የተለያዩ የካፒታል ፕሮጀክቶች ግንባታ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል። ከ1.3 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ገንዘብ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ችግር የሚፈቱና የሥራ ዕድል ፈጠራን ማዕከል ያደረጉ የምርምር ሥራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል።
የኮሌጁ የአስተዳዳር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዳምጠው ዳንኤል በበኩላቸው፥ በሀገራችን በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ካለው እድገት በስተጀርባ የግብርና ኮሌጅ ምሩቃን ሚና ጉልህ እንደነበር ተናግረው፥ እንቅስቃሴው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
ግብርና ከ80 በመቶ ለሚበልጠው የሀገራችን ሕዝብ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ በተጓዳኝ ለኢንዱስትሪ መስፋፋት መሠረት መሆኑን የተናገሩት አቶ ዳንኤል፥ ኮሌጁ ለዘርፉ መዘመን እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ አርአያነት እንዳለው ጠቁመው፥ በዘርፉ ለላቀ ስኬት የላቀ ጥረት እንዲደረግ አስገንዝበዋል።
ከተመራቂዎች መካከል በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። ከምሩቃኑ መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት በኮሌጁ ቆይታቸው ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት መጨበጣቸውን ተናግረው በቀጣይ ህብረተሰቡን በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀታቸውን መጠቆማቸውን የወላይታ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ዘግቧል።
በተያያዘ ዜና፥ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በዋናዉ ግቢ እና ዱራሜ ካምፓስ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ መረሃ ግብር ያስተማራቸውን ከ3,600 የሚበልጡ ተማሪዎችን ነሐሴ 1 እና 2 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. አስመርቋል።
ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ባስመረቀበት ወቅት በክብር እንግድነት የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ ባደረጉት ንግግር፥ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከድህነትና ኋላ ቀርነት ለመላቀቅ የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት ለማገዝ የጎላ ሚና አላቸው ብለዋል።
ሀገሪቱ የምትገኝበትን ነባሪያዊ ሁኔታ የሚለውጥ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ከማስረጽ ባለፈ የዴሞክራሲ ማጎልበቻ፣ የአብሮነትና የመቻቻል እሴት የሚዳብርበት ተቋማት መሆናቸውን ጠቁመዋል። ሰላም ለሰው ልጆች መሠረታዊና አስፈላጊ መሆኑን ያመለከቱት ዶ/ር ሙሉ፥ ሀገርን ለማፍረስ የሚጥሩ አካላትን በመቆጣጠር ሕግ ለማስከበር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የበኩላቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።
ምሩቃን ወደ ማኅበረሰባቸው በሚቀላቀሉበት ወቅት የሰላም፣ የአንድነት፣ የአብሮነትና የልማት ተምሳሌት በመሆን የቀሰሙትን ዕውቀት ሥራ ላይ አውለው ሕብረተሰቡን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል። እንደ ሀገር ላጋጠሙ ችግሮች የመፍተሄ አካል መሆን እንዳለባቸውም ዶ/ር ሙሉ አመልክተዋል።
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው፥ ተመራቂዎች የመረዳዳትና መተሳሳብ እሴቶችን በማስቀጠል ለሀገር ሰላምና እድገት መረጋገጥ የበኩላቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዩኒቨርሲቲው የአካባቢ ሳይንስ (environmental science) ትምህርት ክፍል ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ተማሪ አበበ ታዘበ በሰጠው አስተያየት፥ ከተቋሙ ያገኘውን ዕውቀትና የአብሮነት እሴት አዳብሮ ለሚያገለግለው ማኅበረሰብ ለማዳረስ እንደሚጥር ተናግሯል።
በተማረችበት የትምህርት መስክ ያገኘችውን ዕውቀትና ክህሎት በመጠቀም ማኅበረሰቡን በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀቷን የገለጸችው ደግሞ ከሜዲካል ላብራቶሪ (medical laboratory) ትምህርት ክፍል በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው ሀውልተ መሐመድ ናት። በተቋሙ ቆይታዋ ያገኘችውን የተለያዩ የባህል እሴቶችን ሌሎች በማካፈል ለሀገራዊ ሰላምና እድገት የበኩሏን አስተዋጽኦ እንደምታደርግ ተናግራለች።
ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ነሐሴ 1 ቀን ያስመረቃቸው ለዘጠነኛ ጊዜ በተለያየ የትምህርት ዘርፎ ያሰለጠናቸው ከ3,200 የሚበልጡ ተማሪዎችን ነው። የዩኒቨርሲቲው ዱራሜ ካምፓስ ደግሞ በተለያዩ መስኮች ያሰለጠናቸውን 434 የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን በነጋታው፥ ማለትም ነሐሴ 2 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. አስመርቋል።
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ዱራሜ ካምፓስ በምክትል ማዕረግ የካምፓሱ አስተባባሪ የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ዳዊት ለገሰ በምርቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በመገኘት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትና የካምፓሱን ዋና ዋና የተልኮ የሥራ አፈፃፀም ለምረቃ ታዳሚዎች በማቅረብ፥ ምሩቃን ወደ ሥራ ዓለም በሚገቡበት ወቅት ፀብና ጥላቻን የሚያባብሱ የሀይማኖት፣ የዘርና የቀለም ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተዉ ለሀገር አንድነትና ፍቅር ጠንክረዉ ዘብ እንዲቆሙና እንዲሠሩ መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል።
ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና ተከታታይ መርሀ-ግብሮች እያስተማረ እንደሚገኝ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ተገልጿል።
July 4, 2022 at 2:31 am #48245SemonegnaKeymasterአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በቅድመና ድኅረ ምረቃ መርሃ ግብሮች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች ለ35ኛ ጊዜ አስመረቀ
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በ2ኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች በመደበኛ፣ በማታ፣ በክረምት፣ በሳምንት መጨረሻ እና በተከታታይና ርቀት፣ እንዲሁም በ3ኛ ዲግሪ በመደበኛ መርሃ ግብር ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 2,561 ተማሪዎችን ሰኔ 25 ቀን፥ 2014 ዓ.ም አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 662ቱ ሴቶች ናቸው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የኢትዮጵያን እድገትና ክብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሀገሪቱ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማኅበረሰብና ምሩቃን ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሀገር ሰላምን ለማደፍረስ የሚሰራጩ እኩይ ተልዕኮዎችን ሳያስተናግዱ በስኬት አጠናቀው ለምረቃ በመብቃታቸው አድናቆትና ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ይህን መልካም ሥነ ምግባር በማስቀጠል በሚሄዱበት የሀገራችን አካባቢዎች ሁሉ ለሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ ቅድሚያ ሰጥተው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም አደራ ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ6 ካምፓሶች በ75 የመጀመሪያ፣ በ114 የ2ኛ እና በ26 የ3ኛ ዲግሪ በአጠቃላይ ከ25 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሃ ግብሮች በማስተማር ላይ ሲሆን የዛሬዎቹን ተመራቂዎች ጨምሮ ዩኒቨርሲቲው ከ72 ሺህ በላይ ምሩቃንን ማፍራቱን ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄኔራል፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባልና የእለቱ የክብር እንግዳ አቶ ፈጠነ ተሾመ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ትምህርት ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እድገት ቁልፍ መሣሪያ እንዲሁም የማይከስር ሀብት መሆኑን በመገንዘብ እንዲሁም የሀገራችንን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማረጋገጥ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው በመረዳት ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው በንድፈ ሃሳብና በተግባር ያገኙትን ዕውቀት በሚሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ ለዘላቂ እድገትና ሽግግር እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን /አልሙናይ/ ማኅበር ፕሬዝደንት አቶ ኤርሚያስ ዓለሙ ተመራቂዎች በትምህርት ያገኙትን ዕውቀት በተግባር ውጤታማ ለማድረግ ብዙ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ተናግረው በቀጣይ ራሳቸውን ለማሻሻል እንዲሁም ያስተማራቸውን ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብና ሀገር ለማገልገል በታማኝነትና በትጋት እንዲሠሩ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን አባል በመሆን ለአካባቢው ማኅበረሰብና ለዓለም መልካም አስተዋጽኦዎችን እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል፡፡
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄኔራልና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ አባል፣ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች የተገኙ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እጩ ምሩቃንን ለምረቃ በማቅረብ አስመርቀዋል፡፡
July 21, 2022 at 3:05 am #48766SemonegnaKeymasterኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ 2891 ተማሪዎችን በደማቅ ሥነ-ሥርዓት አስመረቀ
ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በድህረ ምረቃ፣ በቅድመ ምረቃ እና ዲፕሎማ ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን 2891 ተማሪዎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ሐምሌ 10 ቀን፥ 2014 ዓ.ም በደማቅ ሥነ ሥርዓት አስመርቋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና ለዕለቱ ተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ባሰሙበት ንግግራቸው፥ ነባሩ እና አንጋፋው ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ፣ በማታና በተከታታይ የዲፕሎማ፣ የዲግሪ እና የማስትሬት መርሐግብሮች ትምህርታቸውን በሚገባ አጠናቀው፣ አስፈላጊውን የምረቃ መስፈርት አሟልተው በዕለቱ ለምረቃ የበቁት የ2014 ዓ.ም ተመራቂዎች 2891 መሆናቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህም ተመራቂዎች መካከል ወንድ 1409፣ ሴት ደግሞ 1482 ሲሆኑ፣ ይህም የሴት ተመራቂዎች ቁጥር ብልጫ ያለው መሆኑንና ዩኒቨርሲቲውም ለሴቶች ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ ያሳያል ሲሉ ዶክተር ብርሃነመስቀል ተናግረዋል። በመጨረሻም ፕሬዝዳንቱ የዕለቱ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲው አዲሱ ስያሜ፣ ተልዕኮ፣ ሎጎ እና ህብረ ዝማሬ በመመረቃቸው የተቋሙ ታሪክ አካል እንደሚያደርጋቸው አስገንዝበዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር እና የዕለቱ የክብር እንግዳ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአዲስ መልክ እየተዋቀረ ያለው ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሀገሪቱን የትምህርት ችግሮች ለመቅረፍ በከፍተኛ ደረጃ ኃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ፣ ይህንን ልዩ ተልዕኮውን ለመወጣት በሚያደርገው ጥረትም የትምህርት ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግለት ገልጸዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይም በትምህርታቸው ብልጫ ላሳዩ ተመራቂዎች የዋንጫ እና ሌሎች ሽልማቶች ተሰጥቷቸዋል። እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው የሽግግር ወቅት ልዩ ልዩ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላትም የዕውቅና ምስክር ወረቀትና ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡
ከከፍተኛ ትምህርት ዜና ሳንወጣ፥ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጀርመን ስቱትጋርት ከተማ ውስጥከሚገኘው የሆኸንሃየም ዩኒቨርሲቲ (University of Hohenheim) ጋር የአጋርነት ስምምነት ተፈራርሟል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ከዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝደንት እና ከዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ጋር በመሆን በጀርመን ሀገር በግብርናና በሥነ ምግብ ሳይንስ ቀዳሚ ከሆነው ከሆኸንሃየም ዩኒቨርሲቲ (University of Hohenheim) ጋር ላለፉት 8 ዓመታት ሲተገበር በነበረው የCLIFOOD ፕሮጀክት ወርክሾፕ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ ተመራማሪ በዶ/ር ስንታየሁ ይግረም አስተባባሪነት የሚመራው ይህ የCLIFOOD ፕሮጀክት በአየር ንብረት ለውጥና በምግብ ዋስትና ዙሪያ የሚሠራ ሲሆን ለ27 የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሦስትኛ ዲግሪና የድኅረ-ዶክትሬት (postdoctoral) ትምህርት እንዲማሩና፣ የዩኒቨርሲቲው የምርምር ላቦራቶሪዎች አቅም እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ሁለቱ አንጋፋ የትምህርትና ምርምር ተቋማት ግንኙነታቸውን ለማደስና በሌሎች ዘርፎችም አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸውን ውል ተፈራርመዋል፡፡
July 21, 2022 at 3:06 am #48767SemonegnaKeymasterኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ 2891 ተማሪዎችን በደማቅ ሥነ-ሥርዓት አስመረቀ
ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በድህረ ምረቃ፣ በቅድመ ምረቃ እና ዲፕሎማ ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን 2891 ተማሪዎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ሐምሌ 10 ቀን፥ 2014 ዓ.ም በደማቅ ሥነ ሥርዓት አስመርቋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና ለዕለቱ ተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ባሰሙበት ንግግራቸው፥ ነባሩ እና አንጋፋው ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ፣ በማታና በተከታታይ የዲፕሎማ፣ የዲግሪ እና የማስትሬት መርሐግብሮች ትምህርታቸውን በሚገባ አጠናቀው፣ አስፈላጊውን የምረቃ መስፈርት አሟልተው በዕለቱ ለምረቃ የበቁት የ2014 ዓ.ም ተመራቂዎች 2891 መሆናቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህም ተመራቂዎች መካከል ወንድ 1409፣ ሴት ደግሞ 1482 ሲሆኑ፣ ይህም የሴት ተመራቂዎች ቁጥር ብልጫ ያለው መሆኑንና ዩኒቨርሲቲውም ለሴቶች ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ ያሳያል ሲሉ ዶክተር ብርሃነመስቀል ተናግረዋል። በመጨረሻም ፕሬዝዳንቱ የዕለቱ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲው አዲሱ ስያሜ፣ ተልዕኮ፣ ሎጎ እና ህብረ ዝማሬ በመመረቃቸው የተቋሙ ታሪክ አካል እንደሚያደርጋቸው አስገንዝበዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር እና የዕለቱ የክብር እንግዳ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአዲስ መልክ እየተዋቀረ ያለው ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሀገሪቱን የትምህርት ችግሮች ለመቅረፍ በከፍተኛ ደረጃ ኃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ፣ ይህንን ልዩ ተልዕኮውን ለመወጣት በሚያደርገው ጥረትም የትምህርት ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግለት ገልጸዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይም በትምህርታቸው ብልጫ ላሳዩ ተመራቂዎች የዋንጫ እና ሌሎች ሽልማቶች ተሰጥቷቸዋል። እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው የሽግግር ወቅት ልዩ ልዩ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላትም የዕውቅና ምስክር ወረቀትና ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡
ከከፍተኛ ትምህርት ዜና ሳንወጣ፥ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጀርመን ስቱትጋርት ከተማ ውስጥከሚገኘው የሆኸንሃየም ዩኒቨርሲቲ (University of Hohenheim) ጋር የአጋርነት ስምምነት ተፈራርሟል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ከዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝደንት እና ከዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ጋር በመሆን በጀርመን ሀገር በግብርናና በሥነ ምግብ ሳይንስ ቀዳሚ ከሆነው ከሆኸንሃየም ዩኒቨርሲቲ (University of Hohenheim) ጋር ላለፉት 8 ዓመታት ሲተገበር በነበረው የCLIFOOD ፕሮጀክት ወርክሾፕ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ ተመራማሪ በዶ/ር ስንታየሁ ይግረም አስተባባሪነት የሚመራው ይህ የCLIFOOD ፕሮጀክት በአየር ንብረት ለውጥና በምግብ ዋስትና ዙሪያ የሚሠራ ሲሆን ለ27 የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሦስትኛ ዲግሪና የድኅረ-ዶክትሬት (postdoctoral) ትምህርት እንዲማሩና፣ የዩኒቨርሲቲው የምርምር ላቦራቶሪዎች አቅም እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ሁለቱ አንጋፋ የትምህርትና ምርምር ተቋማት ግንኙነታቸውን ለማደስና በሌሎች ዘርፎችም አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸውን ውል ተፈራርመዋል፡፡
September 1, 2022 at 10:29 pm #50333SemonegnaKeymasterሳንቴ የሕክምና ኮሌጅ ለ5ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን የጤና ባለሙያዎች አስመረቀ
አዲስ አበባ (የጤና ሚኒስቴር) – ሳንቴ የሕክምና ኮሌጅ በአጠቃላይ ሕክምና ዶክትሬት ዲግሪ፣ በጥርስ ሕክምና ዶክትሬት ዲግሪ፣ በሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ በBSc እና MPH ዲግሪ፣ በሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ፣ ኒውትሪሽን በMPH ዲግሪ እና በሥነ-ተዋልዶ ጤና በMPH ዲግሪ ያሰለጠናቸውን የጤና ባለሙያዎች አስመረቀ።
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት ተግንኝተዉ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ እንዳሉት፥ ተመራቂዎች በኮሌጁ ቆይታችሁ ፈታኙን የሕክምናና የጤና ሳይንስ ትምህርት እንዲሁም ሌሎች ተግዳሮቶችን አልፉችሁ ነውና የእናንተን የአካልና የመንፈስ ጥንካሬ ያረጋገጣችሁበት ስለሆነ ላደረጋችሁት ጥረት፣ ውጤታማነት ምስጋናና አድናቆት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ዶ/ር አየለ አያይዘውም የተመራቂ ቤተሰቦችንና የኮሌጁ መምህራን እንዲሁም አመራር/አስተዳደር አባላት ተማሪዎች በስኬት መንገድ እንዲጓዙና ውጤታማ እንዲሆኑ ለከፈላችሁት ዋጋ የሚያስመሰግናቸውና የሚያኮራ ተግባር መሆኑን ገልፀው፤ በዛሬው ጊዜ ልጆችን በኃላፊነት አንፆ ለፍሬ ማብቃትና ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዲሆኑ የወላጅ፣ መምህራን እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ጥረት እንደሚያስፈልግ አንስተው፣ ለትውልድ ቅብብሎሹ ላደረጉት መስዋዕትነት ሀገርም እንደምታመሰግናቸው ተናግረው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
የጤና ሚኒስቴር ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በዘርፉ የሚስተዋለውን የጤና ባለሙያዎች እጥረት ለመቅረፍ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከከፍተንኛ ትምህርት ተቋማት፣ እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፥ የጤናና የሕክምና ትምህርት የሚሰጡ በርካታ የመንግሥትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል።
የኮሌጁ ተጠባባቂ ዲን ዶ/ር አህመዲን ኑርሁሴን በበኩላቸው፥ የኮሌጁ ዓላማ ከኮሌጁ ተመርቀው የሚወጡ ባለሙያዎች ሰውን ወዳድ እና አክባሪ፣ አዋቂ፣ በተለያዩ ክህሎቶች የታነፁ፣ ብቁ ለህሙማንና ለማኅበረሰቡ ተቆርቋሪና በጎ አመለካከት ያላቸው ጠቅላላ ሀኪሞች፣ የጥርስ ሀኪሞች፣ ጤና መኮንኖች፣ የሜዲካል ላብራቶሪ ሳይንስ ባለሙያዎች፣ የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ (ፐብሊክ ሔልዝ)፣ ሥነ ምግብ (ኒውትሪሽን) እና የሥነ-ተዋልዶ ጤና ባለሙያዎችን ማፍራት እንደሆነ ገልፀው፥ ተመራቂዎች ለሀገርና ለወገን ጠቃሚ ትውልድ እንዲሆኑ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመው ለ5ኛው ዙር ተመራቂዎችና ቤተሰቦቻቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የኮሌጁ የቦርድ አባል በተጨማሪ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ተመራቂዎች የተማራችሁት የትምህርት ዓይነት ስለ ሰው ነው፤ ሰው ደግሞ ክቡር የሆነ ህይወትን የተላበሰ ልዩ የሆነ የእርሱ ፍጡር እንደሆነ አንስተው፤ ተመራቂዎች በተማራችሁበት ትምህርት ማኅበረሰቡን ለመርዳትና ሀገራችንን በሕክምናው ዘርፍ የላቀ ደረጃ ለማድረስ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ እንድትወጡ በማለት ለተመራቂዎችና ቤተሰቦቻቸው መልካም የምርቃ ጊዜ እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።
ምንጭ፦ የጤና ሚኒስቴር
March 12, 2023 at 10:55 pm #56267SemonegnaKeymasterዲላ ዩኒቨርሲቲ በሥነ-ሕንፃ ምህንድስና፣ በሕክምና እና በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ
ዲላ (ዲላ ዩኒቨርሲቲ) – ዲላ ዩኒቨርሲቲ በቴክኖሎጂና ምህንድስና ኮሌጅ ስር በሥነ-ሕንፃ ምህንድስና (አርክቴክቸር) ትምህርት ክፍል፣ በሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሕክምና (ሜዲሲን) ትምህርት ክፍል እንዲሁም በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች መጋቢት 02 ቀን፥ 2015 ዓ.ም አስመርቋል።
በምርቃቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ማቴዎስ ሀብቴ (ዶ/ር) የዲላ ዩኒቨርስቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ፤ ለተመራቂ ተማሪዎች፣ ለተመራቂ ወላጆች እንዲሁም ለተማሪዎቹ ለምረቃ መብቃት በተለያየ መልኩ ለተጉ ሁሉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዶ/ር ማቴዎስ አክለውም፥ “የዘንድሮ ተመራቂዎች ከትምህርት እና ፈተና ባለፈ በዓለምአቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጫናዎች ተቋቁማችሁ ለዚህ የበቃችሁ በመሆናችሁ በራሳችሁ ልትኮሩ ይገባል” ብለዋል።
ተመራቂዎች ምንም እንኳ ከተቋሙ ተመርቀው ቢወጡም በዩኒቨርሲቲው አሉምናይ (alumni) በኩል ቤተሰባዊ ግንኙነቱ እንደሚቀጥል የገለፁት ዶ/ር ማቴዎስ፥ በቀጣይ ተመራቂዎች በሚሰማሩበት መስክ ሁሉ አምባሳደር ሁነው የዩኒቨርሲቲውን መልካም ስም እንዲያስቀጥሉ የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከተመራቂዎቹ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ችግር በአክሱም ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ይከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች እንደሚገኙበት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በዘገበው ዜና ገልጿል።
የዩኒቨርሲቲው የሬጅስትራርና አሉምናይ ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ይልማ በበኩላቸው፥ በበዕለቱ በድኅረ-ምረቃ መርሃ-ግብር 68 ወንድ እና ዘጠኝ (9) ሴት፤ በድምሩ 77፣ በመደበኛው መርሃ-ግብር በመጀመሪያ ዲግሪ 64 ወንድ እና 24 ሴት በድምሩ 88፣ በተከታታይ የትምህርት መርሃ-ግብር 117 ወንድ እና 30 ሴት፤ በድምሩ 147፣ በአጠቃላይ 249 ወንድ እና 63 ሴት፤ በድምሩ 312 ተመራቂዎች ለምርቃት መብቃታቸውን አብስረዋል።
በዕለቱ የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል ከሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሕክምና ትምህርት ክፍል ምሩቅ የሆነው ዶ/ር ብርሃን አዳነ አጠቃላይ ውጤት 3.86 ነጥብ በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
የማዕረግ ተመራቂው ዶ/ር ብርሃን አዳነ፥ “ከምንም በላይ ፈጣሪዬ ለዚህ ክብር እንድበቃ ስላደረገኝ ክብር ይግባው” ሲል በስኬቱ መደሰቱንና በትምህርቱ ላይ ትኩረት በማድረግ ጠንክሮ በመስራቱ በከፍተኛ ውጤት መመረቁን ጠቅሷል።
ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የድንቅ ኪነ-ሕንፃ ጥበብ ባለቤት መሆኗን የምትናገረው የሥነ-ሕንፃ ምህንድስና ትምህርት ክፍል ተመራቂዋ ተማሪ ሴና ኤቢሳ፥ ይሁንና ዘመናዊ ሕንፃዎች የኢትዮጵያን ባህልና ቀለም በማንጸባረቅ ረገድ ውስንነት እንዳለባቸው ተናግራለች። በቀጣይ በሥራ ሕይወቷ በግል ሆነ በቡድን ሀገር በቀል የሥነ-ሕንፃ ጥበብን ከዘመናዊው ጋር በማዋሃድ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅ የድርሻዬን እወጣለሁ ብላለች ።
የምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ የሕክምና ተመራቂዎች ሙያዊ ቃለ-ምሃላ በመፈፀም የተጠናቀቀ ሲሆን፥ በሥነ-ሥርዓቱ የክብር እንግዶች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር አባላት እና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል። የዲላ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከልም ልዩ ልዩ ጣዕመ ዜማዎችን በማቅረብ ዝግጅቱን አድምቆታል።
ምንጭ፦ የዩኒቨርሲቲው ማኅበራዊ ድረ ገጽ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.