Home › Forums › Semonegna Stories › ሸገር ዳቦና የዳቦ ዱቄት ፋብሪካ ለ20 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተገለጸ
Tagged: ሆራይዘን ፕላንቴሽን, ሚድሮክ ኢትዮጵያ, ሸገር ዳቦና የዳቦ ዱቄት ፋብሪካ
- This topic has 1 reply, 2 voices, and was last updated 4 years, 5 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
January 29, 2020 at 2:06 pm #13461SemonegnaKeymaster
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – ሸገር ዳቦና የዳቦ ዱቄት ፋብሪካ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ ከዳቦ ማምረት እስከ ማከፋፈል ድረስ ባለው ሰንሰለት ለ20 ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ገለጸ። ከ400 በላይ ያገለገሉ የአንበሳ የከተማ አውቶብሶች ለዳቦ ማከፋፈያነት እንደሚውሉም ተገልጿል።
የጽሕፈት ቤቱ የፕሬስ ሴክሬታሪ ኃላፊ ወ/ት ፌቨን ተሾመ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፥ በሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አባል በሆነው ሆራይዘን ፕላንቴሽን ኩባንያ አማካኝነት እየተገነባ ያለው ሸገር ዳቦና የዳቦ ዱቄት ፋብሪካ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ፥ በመዲናዋ የሚስተዋለውን የዳቦና የዱቄት አቅርቦት ችግር መቅረፍ ከማስቻሉ በላይ ከዳቦ ማምረት እስከ ማከፋፈል ድረስ ባለው ሰንሰለት ለ20 ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ፥ በመዲናዋ የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋትና ማኅበረሰቡ ዳቦ፣ ዘይት፣ ስኳርና ዱቄት የመሳሰሉ ለዕለት ፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን ለመግዛት በረጃጅም ሰልፎች ጊዜውን ከማባከኑም በላይ ብዙ ወጪ ያወጣል፡፡ የከተማ አስተዳደሩም ቢያንስ በዳቦ እና ዱቄት ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረትና ረጃጅም ሰልፎችን ለመቅረፍ የተለያዩ ባለሀብቶችን ወደ ኢንቨስትመንቱ እንዲገቡ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል። በዚህ ድጋፍም ሆራይዘን ፕላንቴሽን ኩባንያ አማካይነት ወደ ግንባታ ገባው የሸገር ዳቦና የዳቦ ዱቄት ፋብሪካ ግንባታ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ፋብሪካው ወደ ሥራ ሲገባ በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ የሚያመርት ሲሆን፣ ምርቱም ዝቅተኛውን የማኅበረሰብ ክፍል ባገናዘበ ዋጋ የሚያከፋፍል ይሆናል። ይህም በከተማው የሚስተዋለውን የዳቦ አቅርቦት ማነስና የዋጋ ንረት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከመቅረፉ በላይ፥ ከዳቦ ማምረት እስከ ማከፋፈል ድረስ ባለው ሰንሰለት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ለረጅም ጊዜ ከሥራ ውጭ የነበሩ 420 ያገለገሉ አንበሳ የከተማ አውቶብሶችም ለሸገር ዳቦ ማከፋፈያነት ለማዋል የተለያዩ የማስዋብና የማስጌጥ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን የሚናገሩት ወ/ት ፌቨን፥ በአደጉ አገሮች ተንቀሳቃሽ ሱቆች የተለመዱ መሆኑን ጠቁመዋል። በአውቶቡሶቹ ላይ ወጣቶች ተደራጅተው ዳቦ በማከፋፈል የሥራ ዕድል የሚፈጠርላቸው ሲሆን፥ በ116 ወረዳዎች የዳቦ ማከፋፋያ ማዕከል ሆነው ስለሚያገለግሉ ማኅበረሰቡ በአቅራቢያው ዳቦን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸመት እንደሚያስችሉ አስገንዝበዋል።
የሆራይዘን ፕላንቴሽን ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው፥ የፋብሪካው የግንባታ ሥራ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ማሽኖች ከጣሊያን አገር ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ሲሆን የተወሰኑት ወደ ፕሮጀክቱ ሄደዋል፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ሞጆ ደረቅ ወደብና ጅቡቲ ወደብ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
የመዲናዋን ማኅበረሰብ የዳቦ ጥያቄ ለመመለስ ሼህ ሙሀመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ የፕሮጀክቱን ሙሉ ወጪ በመሸፈን እንዲገነባ ማድረጋቸውን ዳይሬክተሩ ጠቁመው፥ በሚቀጥለው ወር የማሽን ተከላ ሥራው ተጠናቆ ወደ ምርት ይገባል።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በ40 ሺ ካሬ ሜትር ወይም አራት ሄክታር ላይ ያረፈው ሸገር ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ እስከ አሁን ለግንባታው ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በፕሮጀክቱ ሥራ 450 ሰዎች የሥራ ዕድል እንደተፈጠርላቸው ጠቁመዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
June 25, 2020 at 4:30 am #14957AnonymousInactiveኢትዮጵያ ውስጥ በግዙፍነቱ ቀዳሚ የሆነው ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ
አዲስ አበባ (ፋና) – በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባውና በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ የሚያመርተው ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ። በፋብሪካው ምርቃ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በምረቃው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ፋብሪካው የዳቦ ፋብሪካ ብቻ ሳይሆን በምግብ ራሳችንን የመቻል ፍላጎታችንን፣ ከድህነት የመውጣት ጥማትን እና የብልፅግና ጎዳናን አመላካች ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ በ10 ወራት ፋብሪካ ገንብቶ ማጠናቀቅ የሚታሰብ አልነበረም፤ በተለይም ለሚድሮክ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ ሚድሮክ ከነበረበት ድክመት ተላቆ ፋብሪካውን በዚህ ፍጥነት ማጠናቀቅ መቻሉ ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አክለውም መንግሥት በቀጣይ ሁለት ዓመታት ስንዴን ከውጭ ማስገባት የማቆም ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ፤ ለዚህም የሙከራ ምርቶች መጀመራቸውን አስታውቅዋል። ስንዴ ማምረት ብቻ ሳይሆን ምርቶቹን ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ መቀየር አስፈላጊ መሆኑንም የገለፁ ሲሆን፥ ለዚህም ለግሉ ዘርፍ ጥሪ መቅረቡን አስታውቅዋል።
መንግሥት ላቀረበው ጥሪ ሼክ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ፈጣን ምላሽ መስጠታቸውን በመግለፅ፥ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ እውን እንዲሆን በማድረጋቸውም ምስጋናቸውን ያቀረቡላቸው ሲሆን፥ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሌም ከጎናቸው እንደሆነ አረጋግጠዋል።
መሰል የዳቦ ማምረቻዎችን ከአዲስ አበባ ውጪ በክልል ከተሞችም ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑን እና ለዚህም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሌሎች ከተሞች መሰል መለስተኛ የዳቦ ፋብሪካዎችን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሯን አስታውቀዋል። በተጨማሪም የዱባይ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ዛይድ አልናህያንም ከፍ ያለ ፋብሪካ ቃል መግባታቸውን እና ይህም በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።
እነዚህ አሁን የተገነቡ እና ወደ ፊት የሚገነቡ ፋብሪካዎች በቀን ዳቦ ለማግኘት ለሚያዳግታቸው ሕፃናት ዳቦ እንዲያገኙ የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ።
“አዲስ አበባን፣ ክልሎችን፣ ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን እንለውጣለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ “ኢትዮጵያ የጀመረችውን በሙሉ ታጠናቅቃለች፤ ይህም በየአደባባዩ እየጮኸች ሳይሆን ሪቫን እየቆረጠች ነው” ብለዋል።
ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማም፥ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተገንብቶ እውን እንዲሆን ለተሳተፉ አካላት መስጋና አቅርበዋል። የሸገር ዳቦ ፋብሪካ መገንባት የከተማውን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና ይቀንሳል ያሉት ኢ/ር ታከለ፥ በቀጣይም የከተማዋ ነዋሪዎችን ጥያቄ የሚመልሱ ሥራዎችን በማቀድ ወደ ሥራ መገባቱብንም አስታውቅዋል።
የሚድሮክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብነት ገብረ መስቀል በበኩላቸው፥ ሜድሮክ ኢትዮጵያ ለአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ነዋሪ ሕዝብ በከፍተኛ ጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ አምርቶ ማቅረብ እንዲቻል ሸገር ዳቦ ፋብሪካን ገንብቶ ለፍሬ አብቅቷል ብለዋል።
በ41 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ፋብሪካው፥ የዳቦ እና የዱቄት ፋብሪካ፣ የሻይ ቅጠል ማቀነባበሪያ እና 120 ሺህ ኩንታል ስንዴ ማከማቸት የሚያስችል 4 ጎተራ እንዳለው አስታውቀዋል። በ6 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካው በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ የሚያመርት መሆኑን እና በቀን በሶስት ፈረቃ እስከ 2 ሚሊየን ዳቦ የሚያመርት መሆኑ ገልፀዋል።
ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ግንባታው በአጠቃላይ በ900 ሚሊዮን ብር ወጪ መከናወኑን ያስታወቁት አቶ አብነት፥ አጠቃላይ ወጪውም በሚድሮክ እህት ኩባንያዎች የተሸፈነ መሆኑንም አስታውቅዋል። ፋብሪካው ከምርት እስከ ማከፋፈል ሂደት ቁጥራቸው 3 ሺህ 400 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል።
ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.