ቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ 79 በመቶ መጠናቀቁ ተገለጸ

Home Forums Semonegna Stories ቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ 79 በመቶ መጠናቀቁ ተገለጸ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #13061
    Semonegna
    Keymaster

    በዲዛይን መዘግየት፣ የግንባታ ግብዓቶች በወቅቱ ባለመቅረባቸው እና በተቋራጮች እቅም ውሱንነት ምክንያት ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ያልተጠናቀቀው ቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ እስከ  የካቲት ወር መጨረሻ (2012 ዓ.ም.) ድረስ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው።

    አዲስ አበባ (ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር) – ቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ (Bure Integrated Agro-industry Park) ግንባታ 79 በመቶ መጠናቀቁን የኢንዱስትሪ ፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳኛቸው አስረስ ገልጸዋል።

    በ1000 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውና በሦስት ምዕራፍ የሚገነባው ይህ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያው ዙር ግንባታ 79 በመቶ መጠናቀቁን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፥ ለማጠናቀቅ ከተያዘለት ጊዜ 20 በመቶ መዘግየቱንም ተናግረዋል።

    በዲዛይን መዘግየት፣ የግንባታ ግብዓቶች በወቅቱ ባለመቅረባቸው እና በተቋራጮች እቅም ውሱንነት ምክንያት ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ሳይጠናቀቅ ቀርቷል ያሉት አቶ ዳኛቸው፥ እስከ የካቲት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

    የውሃ፣ የመንገድና የሌሎች መሠረተ-ልማት ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፥ የመብራት ኃይል አቅርቦት ሥራ ባለመጀመሩ ፓርኩ ተገንብቶ እንደተጠናቀቀ ወደ ማምረት ሥራ ለመግባት እንቅፋት እንደሚሆንባቸውም ጠቅሰዋል።

    በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የቆዳና ጨርቃ-ጨርቅ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረኢየሱስ በበኩላቸው የፓርኩ የመጀመሪያ ዙር ግንባታ ሲጠናቀቅ ሥራ ለመጀመር የሚያስችል ኃይል ጊዜያዊ በሆነ አማራጪ እንደሚቀርብና በዘላቂነት ለኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚያስፈልገውን ንዑስ ጣቢያ (sub-station) ለመገንባት ከቻይና መንግስት ጋር ስምምነት ተደርሷል ብለዋል።

    በ4.3 ቢሊየን ብር እየተገነባ ያለው ይህ ፓርክ ግንባታው ሲጠናቀቅ በሀገሪቱ ያለውን የገበያ ክፍተት ከመሙላቱም በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ የውጪ ምንዛሪ ያስገኛል ያሉት አቶ ዳኛቸው፥ ከፓርኩ ግንባታ ጎን ለጎን 7 የገጠር የሽግግር ማዕከላት ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

    ቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፓርክ ሦስቱም የግንባታ ምዕራፎች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከ3 መቶ ሺህ እስከ 4 መቶ ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል። ዘገባው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው።

    ምንጭ፦ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.