የግሸን ደብረ ከርቤ በዓል በሰላምና በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው – አስተዳደሩ
ደሴ (ኢዜአ) – የግሸን ደብረ ከርቤ የንግሥ በዓልን በሰላምና በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ካሏት የቱሪዝም መስህቦች መካከል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የሚታደሙበት ባህላዊና ሀይማኖታዊ የንግሥ በዓላት ዋነኞቹ ናቸው።
የመስቀል/ ደመራ በዓል፣ የጥምቀት በዓል፣ እሬቻና ፍቼ ጨምበላላን የመሳሰሉት በዓላት ደግሞ አገሪቷ ለዓለም ቅርስነት በማስመዝገብ የቱርስቶችን ዓይን መማረክ የቻሉ ባህላዊና ሀይማኖታዊ በዓላት ናቸው።
በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ በየዓመቱ መስከረም 21 የሚከበረው ግሸን ደብረ ከርቤ የንግሥ በዓልም ሰላሙን በማረጋገጥ ሀይማኖታዊና ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ በማክበር እስከ ዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ሰፊ ሥራዎች መሠራት ይገባቸዋል።።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን እንደገለጹት፥ በዓሉን በሰላምና በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ናቸው።
በኮሮና ቫይረስ እና አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሚፈለገው መልኩ አለመከበሩን ጠቁመው ዘንድሮ በርካታ ምዕምናን በተገኙበት በልዩ ሁኔታ በድምቀት እንደሚከበር ገልጸዋል።
በዓሉ ያለ ምንም የጸጥታ ችግርና በሰላም እንዲከበር የፀጥታ ኮሚቴ እስከ ታች ድረስ በማዋቀር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው የመሠረተ ልማት ሥራዎችም እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መኮነን በበኩላቸው በዓሉን በድምቀት በማክበር አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ጭምር በማድረግ ለገቢ ምንጭነት እንዲውል እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀንና የመስቀል በዓልን በግሸን ለማክበርም ቅደመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ግማደ መስቀሉ በሚገኝበት ቦታ ሁሉም ሰው ተገኝቶ የበዓሉ ታዳሚ እንዲሆን ጥሪ አስተልፈዋል።
“ሁሉንም በዓላት ታሳቢ ያደረገ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው” ያሉት ኃላፊው በተለይም የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራትና የቴሌ መሠረተ ልማቶችን የማስተካከል ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
በዓሉን ለማክበርም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ምዕመንና ጎብኚዎች በቦታው በመገኘት ይሳተፋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የትራንስፖርት ችግር እንዳይከሰትም ከአጎራባች ዞኖችና ከተሞች ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መምህር አባ ለይኩን ወንድይፈራው በዓሉ ሀይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ በሰላምና በደስታ እንዲከበር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በዓሉ ከመስከረም 16 ጀምሮ እስከ መስከረም 22 በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር ጠቁመው አካባቢው ፍጹም ሰላማዊ በመሆኑ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ሁሉ የበዓሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።፡
ግሸን ደብረ ከርቤ በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ግማደ መስቀሉ ያረፈበት ቦታ በመሆኑ በየዓመቱ መስከረም 21 በድምቀት ይከበራል፡፡
ምንጭ፦ ኢዜአ
