Home › Forums › Semonegna Stories › ባለስልጣኑ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ህገ-ወጥ መድኃኒቶችን አስወገደ
- This topic has 1 reply, 2 voices, and was last updated 5 years, 11 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
February 3, 2019 at 8:03 am #9455SemonegnaKeymaster
አዳማ (ኢዜአ)–የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት እና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን 22 ነጥብ 78 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ህገ-ወጥ መድኃኒቶች እንዲወገዱ ማድረጉን አስታወቀ።
ባለፉት ስድስት ወራት በጤና አገልግሎት ግብአቶች ላይ ቁጥጥርና ፍተሻ ተደርጎ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ መድኃኒትና የህክምና መገልገያ መሣርያዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉም ተመልክቷል።
በባለስልጡኑ የፕሮጀክትና ፕላን ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ዓለም እሸቴ እንዳሉት መስፈርቱን ያላሟሉና ህገ ወጥ የሆኑ መድኃኒቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉና በአግባቡ እንዲወገዱ የተደረገው ባለፉት ስድስት ወራት ነው። መደኃኒቶቹ የተያዙት በመውጫና መግቢያ ኬላዎች ላይ በተደረገ የቤተ-ሙከራ ፍተሻ እንዲሁም በኦዲቲንግ ኢንስፔክሽን ወቅት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከውጭ ሀገር የሚገቡ መድኃኒቶችን ጥራት፣ ደኅንነትና ፈዋሽነታቸውን ለማረጋገጥ ባለስልጣኑ ከዓለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅትና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካለት ጋር በመተባበር የቁጥጥር ሥራ ማከናወኑንም ገልጸዋል። በቶጎ ውጫሌ፣ ሞያሌ፣ ቃሊቲ፣ መተማና ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ባለስልጣኑ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ወ/ሮ ዓለም አንዳሉት በግማሽ በጀት ዓመቱ የምግብ ጥራትና ደህንነት ቁጥጥር ውጤታማነትን ለማሻሻል በተደረገው እንቅስቃሴም 2ሺህ 389 ሜትሪክ ቶን ዱቄት፣ ሩዝ፣ አኩሪ አተርና የምግብ ጥሬ እቃ ተይዟል።
“በተደረገ ፍተሻም ምግብና ጥሬ እቃው የመጠቀሚያ ጊዜው በመቃረቡ፣ አምራች ካምፓኒው ባለመታወቁ፣ በጉዞ ወቅት በደረሰ ጉዳትና በነቀዝ በመባላቱ ምክንያት ወደመጣበት አገር እንዲመለስ ተደርጓል” ብለዋል።
በተጨማሪም ከ200 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው ፓስታ፣ ዱቄት፣ ዘይት፣ ብስኩት፣ ጁስ፣ ሩዝ፣ ወተት፣ ፍራፍሬና የምግብ ጥሬ እቃዎች በተለያየ ምክንያት በመበላሸታቸውና አስፈላጊውን መስፈርት ያላሟሉ ሆነው በመገኘታቸው ከንግድ ተቋማት ውስጥ ተሰብስበው እንዲወገዱ መደረጉን ነው ያስረዱት።
ዘይት፣ ጨው፣ የዱቄት ወተት፣ ጁስና ሌሎች 15 አይነት የምግብ ናሙናዎች ላይ በተካሄደ የቤተሙከራ ምርመራ ሰባቱ መስፈርቱን ሳያማሉ በመቅረታቸው ምርቱ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ መደረጉን አስረድተዋል።
“በመንፈቅ ዓመቱ በጤና አገልግሎት ግብአቶች ላይ ቁጥጥርና ፍተሻ ተደርጎም 4 ነጥብ 23 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው መድኃኒትና የህክምና መገልገያ መሣሪያዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርጋል” ብለዋል። ዋጋቸው ከ457 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የውበትና የንጽህና መጠበቅያ ምርቶችም ቁጥጥርና ፍተሻ ተደርጎላቸው ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን አስረድተዋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ሄራን ገርባ በበኩላቸው ህገ-ወጥ የጤና አገልግሎትና ግብአቶችን ለመቆጣጠር ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በስሩ ስድስት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችንና 17 የመውጫና መግቢያ ኬላዎችን በማደራጀት እየሠራ ይገኛል።
በየደረጃው በሚደረጉ የቁጥጥር ሥራዎች ህዝቡን ተሳታፊ ለማድረግ በተለያዩ የህዝብ ንቅናቄ መድረኮች ላይ ህዝብን የማስገንዘብ ሥራ መሠራቱን ወ/ሪት ሄራን ገልጸዋል። በእዚህም ህገ ወጥ የምግብና የመድኃኒት ንግድን እንዴት መከላከል እንደሚቻልና በዘርፉ ቁጥጥር አለማድረግም በሀገር ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ህብረተሰቡ እንዲገነዘበው የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አመለክተዋል።
ዳይሬክተሯ እንዳሉት በቁጥጥር ሥራው ካጋጠሙ ችግሮች መካከል የምግብ ቤተሙከራ አለመጠናከር፣ የባለሙያዎች አቅም ውስንነት፣ የባለድርሻ አካላትና የህዝብ ክንፉ ተሳትፎ የተደራጀና የተቀናጀ አለመሆን ይጠቀሳሉ። ይህንን ችግር ለማቃለል የባለስልጣኑን አዋጅ የመከለስ ሥራ እየተጠናቀቀ ሲሆን ከምግብና መድኃኒት ጋር የተጣጣመ የአደረጃጀት ትግበራ፣ የሰው ኃይል ድልድልና የህግ ማዕቀፎች ዝግጀት መደረጉንም አመልክተዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
February 28, 2019 at 2:07 am #9958AnonymousInactiveየኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት እና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አገልግሎቱን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዘመኑን ይፋ አደረገ
—–የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት እና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የምግብና መድኃኒት ፈቃድ አሰጣጥ፣ የመድሃኒት ግዢ ፈቃድ፣ የምግብና መድኃኒት የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ አሰጣጥን ቀልጣፋና ግልፅ የሚያደርግ ዘመናዊ አሰራርን መተግበር ጀምሬያለሁ ብሏል፡፡ዛሬ በሒልተን ሆቴል በተካሄደው የአገልግሎቱ ማስታወቂያ መርሃ ግብር ተገኝተን እንደሰማነው እስካሁን በማኑዋል የነበረው የተቋሙ አሰራር በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ታግዞ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
eRIS የተባለው ኤሌክትሮኒክ የቁጥጥርና የመረጃ ስርዓት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የምግብና የመድኃኒት ምርቶችን ደህንነት የማረጋገጥ ስራውን የሚያሻሽል ነው ተብሏል፡፡የምዝገባ ሥርዓቱን ማዘመን የመድሃኒት አቅርቦት እጥረትን ለመቀነስ ያስችላል የሚል ተስፋም ተጥሎበታል ተብሏል፡፡ የካቲት 20 ቀን 2011 ዓም ይፋ የተደረገው ዘመናዊ አሠራር በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር አዋጅ አንድ አካል መሆኑንም ሸገረ ኤፍ ኤም ራድዮ ዘግቧል፡፡
ምንጭ፦ ሸገረ ኤፍ ኤም ራድዮ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.