የ12ኛ ክፍል ውጤት በድጋሚ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ተጠየቀ

Home Forums Semonegna Stories የ12ኛ ክፍል ውጤት በድጋሚ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ተጠየቀ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #11698
    Semonegna
    Keymaster

    “የዘንድሮ 12ኛ ክፍል ፈተና በገለልተኛ አካል ከሁሉም ክልል ተውጣጥቶ ውጤቱ ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ ሊደረግና የማያዳግም የእርምት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል። አንዳንድ ክልሎች ማኅበር አቋቁመው ፈተናው ሠርተው እንደሰጡ ግልፅ መረጃዎች እየወጡ ነው።” ባይቶና ፓርቲ

    አዲስ አበባ – የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት በድጋሚ ከሁሉም ክልሎች በተውጣጣ ገለልተኛ አካል ተጣርቶ ይፋ እንዲደረግ እና ከፈተናው ውጤት ጋር በተያያዘ ስህተት በፈፀሙ አካላት ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ የታላቋ ትግራይ ብሄራዊ ኮንግረስ (ባይቶና) ፓርቲ የጠየቀ ሲሆን የክልሉ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ፤ በውጤቱ ላይ ያለውን ቅሬታ አቅርቧል፡፡ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮም ቅሬታ ማቅረቡ ታውቋል።

    የዘንድሮ የ12ኛ ከፍል መልቀቂያ ፈተናን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ከ350 ነጥብ በላይ ያመጡት 49 ከመቶ መሆናቸውን ገልጾ ውጤቱን ይፋ ያደረገው በትምህርት ሚኒስቴር አገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ኤጀንሲ (NEAEA)፤ በዋናነት በስኮላስቲክ አፕቲቲዩድ ፈተና እርምትና ውጤት አሰጣጥ ላይ ስህተት መፈጠሩን ተገንዝቦ፣ እርምት ማድረጉን የገለፀ ሲሆን በሌሎች የትምህርት ዓይነት ውጤቶች ላይ ‹‹ስህተት የለም፤ ቅሬታ ያለው በግል ያቅርብ›› ብሏል።

    በርካታ ተማሪዎች የጠበቁትን ውጤት እንዳላገኙ በማመልከት ውጤታቸው በድጋሚ እንዲታይ ቅሬታ ማቅረባቸውንም ምንጮች ለአዲስ አድማስ ሳምንታዊ ጋዜጣ የጠቆሙ ሲሆን፥ ብሔራዊ የምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ በበኩሉ፤ ኮሚቴ አዋቅሮ ቅሬታዎችን መሠረት በማድረግ እያጣራ መሆኑን ገልጿል።

    የውጤት አገላለፁን ተከትሎ ቅሬታውን በይፋ ያቀረበው የትግራይ ትምህርት ቢሮ፥ ፈተናው በተሰጠበት ወቅት በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች፣ የፈተና አሰጣጥ ሥነ ምግባር ጉድለት እንደነበርና ይህንንም በወቅቱ ለሚመለከተው አካል መጠቆሙን አስታውቋል።

    የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ኢንጅነር ገብረመስቀል ካህሳይ፥ ‹‹በክልላችን ፈተናው ሲካሄድ የፈተና አወሳሰድ ሥነ ምግባርን ጠብቆ ነበር፤ ይሁን እንጂ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ሥርዓቱን የጠበቀ አይደለም›› ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

    ይህንን ቅሬታም ለኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር አሳውቀው እንደነበርና ቅሬታው ምላሽ ሳይሰጠው ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተናግረዋል:: ይሄም ኃላፊው፤ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ የትግራይ ትምህርት ቢሮ ጠይቋል።

    ከወራት በፊት መሠረቱን በትግራይ አድርጎ የተቋቋመው ‹‹ብሄራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ›› (ባይቶና) (‹‹የታላቋ ትግራይ ብሄራዊ ኮንግረስ››) የተሰኘው የፖለቲካ ድርጅት ‹‹ዘንድሮ የተለቀቀው የ12ኛ ክፍል ውጤት ከፍተኛ ብልሽት፣ ዝርክርክ አሰራርና የታየበት ስለሆነ ተቀባይነት የለውም፤ ውጤቱ በድጋሚ በገለልተኛ አካላት ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ ይደረግ ኃላፊዎችም በሕግ ይጠየቁ›› ሲል አሳስቧል።

    ባይቶና ከ12ኛ ክፍል የፈተና ውጤት ጋር በተያያዘ የሰጠውን መግለጫ ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ

    ምንጭ፦ አዲስ አድማስ ጋዜጣ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ባይቶና ፓርቲ የ12ኛ ክፍል ውጤት በድጋሚ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠየቀ


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.