Home › Forums › Semonegna Stories › “ብሔራዊ የግብር ገቢ ንቅናቄ” በጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት በይፋ ተጀመረ
Tagged: ብሔራዊ የግብር ገቢ ንቅናቄ, አብይ አህመድ, አዳነች አበቤ, ዐቢይ አሕመድ, የገቢዎች ሚኒስቴር
- This topic has 4 replies, 2 voices, and was last updated 5 years, 10 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
December 21, 2018 at 7:21 am #9011SemonegnaKeymaster
የገቢዎች ሚኒስቴር የነደፈው ብሔራዊ የግብር ገቢ ንቅናቄ ዜጎች ግብር መክፈል ሀገራዊ ግዴታቸው መሆኑን በማስገንዘብ እና ከዜጎች የሚሰበሰበውን ግብር በመጨመር ሀገሪቱ እ.ኤ.አ በ2025 የመካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ውስጥ ለመመደብ የምታደርገውን ጥረት ይደግፋል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ጠንካራ የግብር ዘርፍ እንዲኖር ጠንካራ መሠረተ ልማት እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት “ግዴታዬን እወጣለሁ፣ መብቴን እጠይቃለሁ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደውን ብሔራዊ የግብር ገቢ ንቅናቄ (National Tax Revenue Movement) ታህሳስ 12 ቀን 2011 ዓ.ም. በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በይፋ ሲያስጀምሩ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመልዕክታቸው እንዳሉት ቁሳዊ መሠረተ ልማቶችና ቁሳዊ ያልሆኑ እንደ ዴሞክራሲ፣ ፍትህ፣ ጸጥታና የመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች እጅግ በጣም ወሳኝ ናቸው። “ዜጎች በሚከፍሉት ግብር መንግስት መሠረተ ልማቶች በማስፋፋት፣ የግሉ ዘርፉ ጠንካራና ተወዳዳሪ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል” ብለዋል።
ጠንካራና ተወዳዳሪ የሆነ የግል ዘርፍም ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል ከመፍጠር በላይ ትርፋማነቱን የሚያረጋግጥና ለመንግስትም ትልቅ የገቢ ምንጭ በመሆን የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
◌ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያደረጉት የመክፈቻ ንግግር (ቪዲዮ)
በኢትዮጵያ የተጀመረውን ሰፊ የዴሞክራሲ ግንባታ ለማስቀጠል ጠንካራና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባት የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
“ያለበቂ ተሳትፎና ውክልና ግብር የመክፈል ግዴታ ሊኖር አይችልም” ያሉት ዶክተር ዐቢይ “ግለሰባዊ የመብት አያያዝ፣ ማኅበረሰባዊ ደህንነት፣ የዳበረ የፍትህ ስርዓት፣ የላቀ የዕውቀትና ጥበብ አቅም፣ በምግብ ራስን መቻልና መሠረታዊ ጤናን ለሁሉም የማዳረስ ብቃት ሳይቋረጡና ከደረጃቸው ሳይወርዱ ማዳረስ የሚቻለው ያለማቋረጥ ግብር ለመሰብሰብ የሚችል ስርዓትና አቅም ስንፈጥር ብቻ ነው” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያን ለማሳደግና ሰላም እንድትሆን ለዜጎችና ለነዋሪዎች መሠረታዊ ፍላጎቶችን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብና ድህነትን በማሸነፍ ወደብልጽግና ለመገስገስ ከተፈለገ ስለግብር ያለው ደካማ አመለካከት መቀየር እንዳለበት ተናግረዋል።
“ግብር የሚያጭበረብር ሰው እንደ አራዳ መቆጠሩ ቀርቶ አገርና መንግስትን እንደሚጠላ ብቻ ሳይሆን ስለራሱ ልጆች የዛሬና የወደፊት ህልውና ምንም የማይጨነቅ ሞኝ ተደርጎ ሊቆጠር ይገባል” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ዜጎችና ነዋሪዎች ግብር በመክፈል አገሪቱን፣ መንግስትንና ልጆቹን እንደሚወድ በይፋ የሚያሳይ ኩሩ ዜጋ መፍጠር እንደሚያስፈልግም አክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደጠቀሱት ኢትዮጵያ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርቷ (GDP) የግብር ገቢዋ (tax revenue) የሚይዘው 10.7 በመቶ ብቻ ሲሆን፥ ይህም ከአፍሪካ ሀገራት አንጻር እንኳን በጣም ዝቅተኛ ነው።
የገቢዎች ሚኒስቴር የነደፈው ብሔራዊ የግብር ገቢ ንቅናቄ (National Tax Revenue Movement) ኢትዮጵያውያን ለግብር ያላቸውን ዝቅተኛ ብሎም የተሳሳተ አመለካከት በመቀየር፥ ይልቁንም ግብር መክፈል ሀገራዊ ግዴታ እና ማንኛምው ገቢ የሚያገኝ ሰው መክፈል ያለበት ነገ መሆኑን በማስገንዘብ ከዜጎች የሚሰበሰበውን ግብር በመጨመር ሀገሪቱ እ.ኤ.አ በ2025 የመካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ውስጥ ለመመደብ የምታደርገውን ጥረት ይደግፋል ተብሎ ይጠበቃል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
February 4, 2019 at 5:59 am #9470AnonymousInactiveየኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማይናጋ መሰረት ላይ ለመጣል ግብር ከፋዩ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል — ወይዘሮ አዳነች አበቤ
—–የኢትዮጵያን ኢኮኖሚዋ በማይናጋ መሰረት ላይ ለመገንባት ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ የውዴታ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የገቢዎች ሚኒስቴር ወይዘሮ አዳነች አበቤ ገለጹ።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የ2011 በጀት ዓመት የግብር ህግ ተገዥነትን ለማሳደግ የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ አስጀምሯል።
“ግዴታዬን እወጣለሁ፣ መብቴን እጠይቃለሁ” በሚል መሪ ቃል በተጀመረው የንቅናቄ መድረክ ላይ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አበቤ እንደገለጹት በኩሩ ህዝቦቿ ተጋድሎ ማንነቷ ተከብሮ የኖረችው ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ ድሃ ከሚባሉት አገራት ተርታ ትገኛለች።
“ይህን ስሟን ለማስቀየርና ኢኮኖሚዋ በማይናጋ መስረት ላይ እንዲገነባ ለማድረግ ግብር ከፋዩ ሕብረተሰብ በፍላጎትና በአገራዊ ፍቅር ስሜት ከሚያገኘው ገቢ ላይ ለመንግስት ግብርን መክፈል አለበት” ብለዋል።
በአገሪቱ የተከሰተውን ለውጥ ምክንያት በማድረግ ለውጡ ጥቅማቸውን የነካባቸው አካላት ሰላም እንዲደፈርስና የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር ግብረ በአግባቡ እንዳይከፈል እያደረጉ መሆኑንም ሚኒስትሯ ተናግዋል።
” ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ግብር መክፈል ለራሱና ለሚወዳት አገሩ መሆኑን ተገንዝቦ ኃላፊነቱን ከመወጣት ባለፈ እንደ ጥንት አባቶች አንድነቱን አጠናክሮ መንቀሳቀስ ይኖርበታል ” ብለዋል።
የአማራ ክልልም ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የፌዴራል መንግስት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።
February 6, 2019 at 7:50 am #9526AnonymousInactiveጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በፌደራል የመካከለኛ ገቢ ግብር ከፋዮች ቢሮ ጉብኝት አደረጉ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶክተር ) በፌደራል የመካከለኛ ገቢ ግብር ከፋዮች ቢሮ ጉብኝት አድርገዋል።
በጉብኝቱ ወቅትም ሰለ አጠቃላይ እንቅስቃሴው በባለሙያዎች ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
በወቅቱም ከቢሮው ሠራተኞች ጋር እና ከግብር ከፋዮች ጋር ተገናኝተዋል።
ከሳምንት በፊት ከሚኒስትር መስሪያ ቤቶችና ተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር የአፈጻጸም ግምገማ በተካሄደበት ወቅት፥ የመንግስት ተቋማትና ሠራተኞች የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እየተወጡ መሆኑን ለማረጋገጥ ይህን መሰል ድንገተኛ ጉብኝት እንደሚቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጻቸው ይታወሳል።
ምንጭ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ነው
February 7, 2019 at 7:10 am #9549AnonymousInactiveግብርን በመክፈል አገራዊ ለውጡን ማገዝ ይገባል — የደቡብ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን
—–የንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ በመክፈል የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ እንዲያግዝ የደቡብ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ጠየቀ።
ክልል አቀፍ የታክስ ንቅናቄ በወልቂጤ ከተማ ተጀምሯል ።
ባለስልጣኑ ዋና ዲያሬክተር አቶ ንጉሴ አስረስ በወቅቱ እንደገለጹት በግብር አሰባሰቡ ሂደት ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት የክልሉ ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ መሰብሰብ ትኩረት ተሰጥቷል።
“የክልሉ ህብረተሰብ በተለይም ግብር ከፋዩ የታክስ ስወራና ማጭበርበርን በመከላከል የገቢ አሰባሰቡ ስኬታማ እንዲሆን ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” ብለዋል ።
”የህዝቡ የልማት ጥያቄ ሊመለስ የሚችለው የንግዱ ማህበረሰብ ገቢውን በማሳወቅ የሚጠበቅበትን ግብር መክፈል ሲችል ነው” ያሉት ኃላፊው ግብር ከፋዩ ኃላፊነቱን በመወጣት ለውጡን እንዲያግዝ ጠይቀዋል ።
“ተጠቃሚውም ደረሰኝ በመጠየቅ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል” ብለዋል።
በገቢዎች ሚኒስቴር የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ወልደመሰቀል በበኩላቸው “የታክስ ጉዳይ የግብር ሰብሳቢው ተቋም ብቻ ሳይሆን፤ የሁሉም ዜጎች በመሆኑ ህዝቡ ከሚመለከተው አካል ጋር በጋራ ሊሰራ ይገባል” ብለዋል ።
“ስራ አጥ ወጣቶችን የስራ እድል ባለቤት ማድረግና የመሰረተ ልማት ተቋማትን ማስፋፋት የሚቻለው ተገቢውን ገቢ መሰብሰብበ ሲቻል ነው” ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ኮሚሽን የሐዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ መርዕድ ናቸው ።
ተገቢውን ግብር ለመሰብሰብ እንዳይቻል የሚያደርጉ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ታደሰ ህገወጥ ንግድ፣ የኮንትሮባንድ ታክስ ማጭበርበር ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በገቢና በወጪ ንግዱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያስከተለ ያለውን የኮንትሮባንድ ንግድ ለመከላከል ህዝቡ ከመንግስት ጎን ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጉራጌ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪና የዞኑ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ታጁ ናስር በበኩላቸው በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት ለመሰብሰብ ከታቀደው 918 ሚሊዮን ብር ውስጥ 362 ሚሊዮን ብር ብቻ መሰብሰቡን ተናግረዋል ።
ግብይትን ያለደረሰኝ ማካሄድ፣ የንግድ ፈቃድን በቤተሰብ ከፋፍሎ ማውጣት፣ የታክስ ስወራና ማጭበርበር ዕቅዱን እንዳይሳካ ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል ።
የወልቂጤ ከተማ የሰላም በር ትምህርት ቤት የታክስ ክበብ አባል ተማሪ አያልነሽ አይተንፍሱ “ግብር ያለ ማጭበርበርና በስርዓት መክፈል አገርን ከድህነት እንድታድግ ያስችላል” ብላለች ።
ግብርን አለመክፈል አገራዊ እድገትን እንደሚጎዳም ገልጻለች ።
“ግዴታዬን እወጣለሁ መብቴን እጠይቃለሁ!” በሚል መሪ ቃል የተጀመረው ክልል አቀፉ የታክስ ንቅናቄ እስከ የካቲት 30 ቀን 2011 ድረስ ይቆያል።
February 8, 2019 at 6:13 am #9577AnonymousInactiveሃገራዊውን የግብር ንቅናቄ በደቡብ ክልል ለማስቀጠል በአዲስ አበባ ከተማ የሩጫ ውድድር ሊካሄድ ነው
—–አዲስ አበባን ጨምሮ በአማራና በትግራይ ክልሎች የተጀመረውን የግብር ንቅናቄ በማስቀጠል በአዲስ አበባ ከተማ የሩጫ ውድድር ሊያካሂድ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግላጫ እንዳስታወቁት÷ “ግብር ለሃገሬ “ በሚል መሪ ቃል የካቲት 10 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የሩጫ ውድድር እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሯ የግብር ንቅናቄው በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት፡፡
ሁሉም የሚሳተፍበት የእምዬን ለእምዬ በሚል መርህ የስዕልና የሙዚቃ ድግስ የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድም ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሯ በሀገሪቱ ግብር መክፈል ከነበረባቸው ዜጎች መካከል 60 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሚከፍሉ ገልጸዋል፡፡
ደረሰኝ ከመስጠትና ከመቀበል ጋር በተያያዘም እስካሁን የግንዛቤ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
በሚኒስቴሩ በግብር ማጭበርበርና ስወራዎች ላይ በተደረገ ክትትል ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷልም ነው ያሉት።
ሃገሪቱ ከግብር ስወራና ማጭበርበር ጋር በተያያዘ 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ማጣቷንም አንስተዋል።
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.