የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተቋሙ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ

Home Forums Semonegna Stories የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተቋሙ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #8668
    Semonegna
    Keymaster

    በደቡብ ክልል የሚገኘው ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በአገሪቱ 3ኛ ትውልድ ከሚባሉት 11 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሲሆን፥ ከ1 ሺህ 200 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ሥራውን የጀመረው በ2010 ዓ.ም. ነው።

    ሚዛን (ኢዜአ) – የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተቋሙ የሚስተዋሉ የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የውሃና የምግብ አገልግሎት ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ።

    የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር በበኩሉ ተማሪዎቹ ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች አግባብ መሆናቸውንና ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።

    በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል (ዋና ካምፓሱ ቦንጋ ከተማ ውስጥ) የሚገኘው ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በአገሪቱ 3ኛ ትውልድ ከሚባሉት 11 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሲሆን፥ ከ1 ሺህ 200 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ሥራውን የጀመረው በ2010 ዓ.ም. ነው።

    የተቋሙ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ ከሆኑት መካከል አንዳንዶቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገለጹት ዘንድሮ በዩኒቨርሲቲው መሻሻል ቢኖርም አምና የነበሩባቸው ያልተፈቱ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

    በተለይ ከምግብ አገልግሎትና ከውስጥ ለውስጥ መንገድ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮች ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ እና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል።

    በዩኒቨርሲቲው የሁለተኛ ዓመት የእንስሳት ሳይንስ ተማሪ ብርሌው አገኝ በበኩሉ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ባለመሠራቱ በተለይ በዝናብ ወቅት በጭቃ ምክንያት ለመንቀሳቀስ እየተቸገሩ መሆናቸውን ገልጿል። አካባቢው ዝናባማ መሆኑ ችግሩን እያባባሰው በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ችግሩን ፈጥኖ እንዲፈታላቸው ጠይቋል፤ ከዚህ ባለፈም ዩኒቨርሲቲው ካለበት የውሃ ችግር በተጨማሪ ለተማሪዎች የሚሰጠው የምግብ አገልግሎት ሊስተካከል እንደሚገባ ጠቁሟል። በተለይ በምግብ አቅርቦት በኩል በተለያዩ ቀናት ተመሳሳይ ምግብ ተደጋግሞ የሚቀርብበት ሁኔታ ስላለ እንዲስተካከል ጠይቋል።

    የሁለተኛ ዓመት የአስተዳደር ተማሪ የሆነው ሙላቱ በቀለ በበኩሉ ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ካለፈው ዓመት ብዙም መሻሻል እንዳላየበት ተናግሯል። አምና የመንገድ፣ የውሃ አቅርቦትና የቤተ መጻሕፍት አገልግሎቶች ላይ እጠረቶች እንደነበሩ አስታውሶ እነዚህ ችግሮች ዘንድሮም ባለመሻሻላቸው እየተቸገሩ በመሆናቸው ዩኒቨርሲቲው ትኩረት እንዲሰጠው ተናግሯል።

    የዩኒቨርሲቲው የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መምህር ያሬድ አያሌው በበኩላቸው ችግሮቹን ለመፍታትና ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢ ለመፍጠር ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። የመንገድ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በአሁኑ ወቅት የ5 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ሥራ መጀመሩን ገልጸው፥ መንገዱ የዩኒቨርሲቲውን ዋና ዋና መስመሮች እንደሚያገናኝም አመልክተዋል። አካባባቢው ዓመታዊ የዝናብ ሽፋኑ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው ይህም በተለይ በዝናብ ወቅት በሚፈጠር ጭቃ እንደልብ ለመንቀሳቀስ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

    ለተማሪዎች ከሚሰጠው የምግበ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የጎላ ችግር እንደሌለ የገለጹት ኃላፊው፣ የምግብ አቅርቦት መርሀ ገብሩም ዩኒቨርሲቲው ከተማሪዎች ማኅበራት ጋር ተስማምቶ እንዳወጣውና በእዚያ መሠረት ምግብ እየቀረበ መሆኑን አስረድተዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ዋና ቤተ መጻህፍት ግንባታ ሥራ በአሁኑ ወቅት በመጠናቀቁም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋለው ችግር በቅርቡ ሙሉ በሙሉ እንደሚፈታ አመልክተዋል።

    ከተማሪዎቹ የተነሳው የውሃ ችግር ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን የገለጹት መምህር ያሬድ ችግሩን ለመፍታት ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የራሱን የውሃ ጉድጓድ በመገንባት ላይ መሆኑንና ግንባታው ሲጠናቀቅ ችግሩ ይቀረፋል የሚል እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል።

    የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በሕግ፣ በምህንድስናና በማኅበረሰብ ጥናት አዳዲስ የትምህርት ክፍሎችን የሚጀምር ሲሆን አጠቃላይ የትምህርት ክፍሎቹንም ወደ 26 እንደሚያሳድግ ከዩኒቨሲቲው የተገኘውን መረጃ ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

    ምንጭ፦ ኢዜአ

    ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.