የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እህተ ማርያም በሌሎች ወንጀሎችም በመጠርጠሯ ምርመራውን እያጠናከረ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ራሷን ንግሥተ ነገሥት (እህተ ማርያም) እያለች በምትጠራው ትዕግሥት ፍትህአወቅ ላይ የአስቸኳይ አዋጁን ከመጣስ በተጨማሪ በሌሎች ወንጀሎችም በመጠርጠሯ ምርመራውን እያጠናከረ መሆኑን ገለጸ።
በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ልዩ ወንጀል ዲቪዥን ምርመራ ኃላፊ ኢንስፔክተር በድሉ ግርማ ትዕግሥት ፍትህአወቅ (እህተ ማርያም) ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነቴንና ቀኖናዬን አቃላለች መገልገያ አልባሳቴን ያለ አግባብ ጥቅም ላይ አውላለች በሚል ያቀረበችው ክስም በምርመራው እየታየ እንደሆነ ገልጸዋል።
ግለሰቧ ሃይማኖትም ሆነ ማኅበር ለመመሥረት ከኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዲሪ) የሰላም ሚኒስቴር ተገቢውን ፈቃድ ሳታገኝ ርትዕት ተዋሕዶ የሚል ሃይማኖት መሥርታ ተከታዮቿን አላግባብ እየሰበሰበች የነበረበት ሂደትም እየተመረመረ ነው ተብሏል።
ተጠርጣሪዋ የትዳር አጋሯ በትራፊክ አደጋ እንደሞተ ብትገልጽም የሟች ቤተሰቦች ይህ ስለመሆኑ ምንም ማስረጃ ባለመኖሩ ተጨማሪ ምርመራ ይደረግልን ማለታቸውም ምርመራው የሚያተኩርበት ሌላ ጭብጥ መሆኑንም ኢንስፔክተሩ ገልጸዋል።
በተጠርጣሪዋ ቤት የተገኘው አስከሬንም ለምርመራ ወደ ሆስፒታል መላኩንም ኢንስፔክተር በድሉ ገልጸዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ሌሎች ዜናዎች፦
