Home › Forums › Semonegna Stories › አማራ ባንክ በአንድ ጊዜ ከ70 በላይ ቅርንጫፎችን በመክፈት በይፋ ሥራውን ጀመረ
- This topic is empty.
-
AuthorPosts
-
June 18, 2022 at 3:55 pm #36004SemonegnaKeymaster
“የአማራ ባንክ አርሶ እና አርብቶ አደሮች የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር ባለአክሲዮን እንዲሆኑ አስችሏል” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ (አሚኮ) – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) አማራ ባንክ መከፈቱንና መይፋ ሥራ መጀመሩን አስመልክተው ለባንኩ ባለድርሻ አካላት እና ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
ዶክተር ደሴ ይናገር አማራ ባንክ አጀማመሩ ከሌሎች ባንኮች የተለየ የሚያደርገው ጉዳዮች እንዳሉት አስረድተዋል። የባንኩ አክሲዮን በስፋት በገጠርም በከተማም የተሸጠ መሆኑ፤ በባለ አክሲዮን ብዛት ትልቅ ባንክ መሆኑ ልዩ ባንክ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ዶክተር ይናገር የባንኩ እውን መሆንን ያሳኩ አደራጆች እና የባንኩ የሥራ አመራር ሊመሰገኑ እንደሚገባም ነው የገለጹት። በተለይ የአማራ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ መላኩ ፋንታ በባንክ ምሥረታ ሂደት አሰልቺውን ጉዞ በተለይም ከተቀመጡት መስፈርቶች አንድ እንኳን ቢጎድል መሳካት የማይችለውን ሂደት በማሳካት ያከናወኑት ሥራ ትልቅ በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል ነው ያሉት። አቶ መላኩ ከበርካታ የሕይወት ውጣውረድ እና እስር በኋላ ተቋም መርተው ለሕዝብ የሚጠቅም ባንክ ማቋቋም በመቻላቸው እሳቸው እና የሚመሩት አደራጅ እና የሥራ አመራር ቦርዱ ምሥጋና አቅርበዋል።
በአማራ ባንክ ምሥረታ ላይ ከሀገር ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ እና ባንኩ እውን እንዲሆን ያደረጉት ተሳትፎ የሚመሰገን እንደሆነም ነው ዶክተር ይናገር የገለጹት።
በባንክ ምሥረታ በአንድ ቀን 72 ቅርንጫፍ ለመክፈት ቀን ብቻ ሳይሆን ሌሊትም ተሠርቶ ካልሆነ የማይቻል እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር ይናገር ደሴ፥ ለዚህ ውጤት የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሄኖክ ከበደ እና የሥራ አጋሮቻቸው ያበረከቱት አስተዋጽኦ ትልቅ በመሆኑ ሊመሰገኑ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ ውስጥ የባንክ አቅም ገና ያልተነካ በመሆኑ አሁን የተከፈተውን አማራ ባንክ ጨምሮ አዳዲስ እየተከፈቱ ካሉ ባንኮች በተጨማሪ ከተሳካ የሌሎች ሀገር ባንኮች እንዲገቡ እንደሚደረግ ነው የተናገሩት። ይህም የሀገርን ልማት በማፋጠን የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚቻል ነው ያስገነዘቡት። ባልተነካው የሀገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ እና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት የአማራ ባንክ ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም ዶክተር ይናገር ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
አርሶ እና አርብቶ አደሮች የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር የባንክ ባለአክሲዮን እንዲሆኑ ማስቻል አስፈላጊ በመሆኑ በዚህ ረገድ አማራ ባንክ ሰፊ የአክሲዮን ሽያጭን በገጠር በመሸጥ የሚስተካከለው እንዳልተገኘም ነው የጠቆሙት። ባለአክሲዮኖቹም በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ መሆናቸው ባንኩን ልዩ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል። ይህም ባንኩን የመላው ኢትዮጵያዊያን ባንክ እንደሚያደርገው ዶክተር ይናገር አስረድተዋል።
አማራ ባንክ በአገልግሎት አሰጣጡ እና በፍትሐዊ አሠራሩ ልቆ ከወጣ የውጭ ባንኮች ቢገቡ እንኳን ተወዳዳሪ መሆን ስለሚችል ጠንክሮ መሥራት እንዳለበት ነው ያሳሰቡት። ባንኩ ቁጠባን በማበረታታት ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል፤ ለባንኩ መንግሥት የሚያደርገው እገዛ እንደተጠበቀ ሆኖ ባንኩ ኢትዮጵያዊያንን ሊያገለግል እንዲችል የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎትን በስፋት ገቢራዊ ማድረግ እንዳለበት ነው ዶክተር ይናገር የተናገሩት። አማራ ባንክ ዘመኑ የቴክኖሎጅ በመሆኑ በቴክኖሎጅ ዘርፍ ልቆ እንደሚወጣም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
ምንጭ፦ አሚኮ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.