በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደረገ

Home Forums Semonegna Stories በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደረገ

Viewing 3 posts - 1 through 3 (of 3 total)
  • Author
    Posts
  • #11168
    Semonegna
    Keymaster

    የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ዓላማው ክልሉን ለማተራመስና የህዝቡን ህልውና አደጋላይ ለመጣል ያለመ መሆኑን ገልጸው፥ በአሁኑ ወቅት የፌዴራል መንግስት ሁኔታውን የማስተካከልና ክልሉን የማረጋጋት ትዕዛዝ እንደተሰጠው አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገልጸዋል።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መደረጉን በኢፌዴሪ ጠቅላይ የሚኒስቴር ፅህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ። አቶ ንጉሱ ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት ላይ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) በሰጡት መግለጫ በክልሉ መንግስት ላይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደርጓል።

    በተደራጀ ሁኔታ በመንግስት መዋቅር ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የተሞከረው የተደራጀ እንቅስቃሴ ከሽፏል ነው ያሉት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ።

    የአማራ ክልል ወደ መረጋጋት እየመጣ ባለበትና እና ሕዝቡ ቀደም ሲል ያነሳ የነበረውን የህግ የበላይነት ጥያቄ ለመመለስ እየተሠራ ባለበት ወቅት የተሰነዘረው ጥቃት የክልሉ መንግስት ብቻ ሳይሆን የአማራ ሕዝብ ላይ የተሞከረ ነው ብለዋል።

    ሙከራው ክልሉን ለማተራመስና የህዝቡን ህልውና አደጋላይ ለመጣል ያለመ መሆኑን ገልጸው፥ በአሁኑ ወቅት የፌዴራል መንግስት ሁኔታውን የማስተካከልና ክልሉን የማረጋጋት ትዕዛዝ እንደተሰጠው ገልጸዋል።

    የፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ በመግባት ይህን መሰሉን ተግባር የመግታት ሥራ እንደሚሠራና ህብረተሰቡም አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ጸረ-ህገ መንግስትና መፈንቅለ መንግስቶች እንዲሁም በታጠቁ ኃይሎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጸው፥ ክልሉን ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በትብብር እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።

    አቶ ንጉሱ ጥላሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ቴለቭዥን ጋዜጠኛ ጋር ያደረጉትን አጭር ቃል ምልልስ እዚህ ጋር በመጫን ያዳምጡ።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ


    #11171
    Anonymous
    Inactive

    በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ላይ የተደረገውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የፌደራል መንግሥት አወገዘ
    —–

    በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ላይ የተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት የሚፃረር፣ የክልሉ ሕዝብና መንግሥት ለረጅም ጊዜ የታገሉለትን ሰላምና መረጋጋት ለመንጠቅ የተደራጀ በመሆኑ የፌደራል መንግሥት ሙሉ በሙሉ እንደሚያወግዘው የጠቅላይ ሚንስትር ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

    የፌደራል መንግሥት የጸጥታ መዋቅር የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር አውሎ በፈጸሙት አካላት ላይ ተገቢውን ርምጃ እንዲወስድ ትእዛዝ ተቀብሎ ተፈጻሚ በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህ ጥቃት በመንግሥት መዋቅር ላይ ብቻ ሳይሆን በአማራ ሕዝብ ላይ የተቃጣ መሆኑን በመገንዘብ የክልሉ ሕዝብ አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅና ተረጋግቶ ሁኔታዎችን እንዲመለከት ጥሪ ቀርቧል።

    ይህን ሕገ ወጥ ሙከራ ክልሉ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ክልልና መላው ኢትዮጵያዊ ሊያወግዘው የሚገባ ሲሆን የፌደራል መንግሥት የታጠቁ ቡድኖችን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ የመቀልበስ፣ የመግታትና በቁጥጥር ሥር የማዋል ሙሉ ዐቅም ያለው መሆኑን ያረጋግጣል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን

    #11178
    Anonymous
    Inactive

    የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አምባቸው መኮንን መገደላቸው ተረጋገጠ
    —–

    የአማራ ክልል ፕሬዝደንት ዶ/ር አምባቸው መኮንን ትላንት (ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም.) በነበረው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተከትሎ መገደላቸውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አስታውቋል።

    አቶ አምባቸውን ጨምሮ የርዕሰ መስተዳድሩ አደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ የሆኑት አቶ እዘዝ ዋሴም በደረሰው ጥቃት ሕይወታቸውን ማጣታቸው ታውቋል። ጥቃቱ የተፈፀመው ግለሰቦቹ ስብሰባ ላይ ባሉበት ወቅት እንደሆነ ኢቲቪ አስታውቋል።

    አቶ አምባቸው መኮንን የቀድሞውን የክልሉን ፕሬዝደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን በመተካት የተሾሙት የካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ነበር።

    የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ተፈፀመ በተባለው የመንፈቅለ መንግሥት ሙከራ እጃቸው አለበት የተባሉ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉም ተሰምቷል።

    የክልሉ ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ፅጌ መንፈቅለ መንግሥቱን አቀነባብረዋል ተብለው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፓርቲው አስታውቋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ትላንት ከእኩለ ለሊት በኋላ በብሔራዊው ቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት መግለጫ የአማራ ክልል ባለስልጣናት የተገደሉት እና የቆሰሉት በስብሰባ ላይ እያሉ እንደነበር መናገራቸው አይዘነጋም።

Viewing 3 posts - 1 through 3 (of 3 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.