በአማራ ክልል ከ450 ሺህ ለሚበልጡ ልጃገረዶች የማህፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት ሊሰጥ ነው

Home Forums Semonegna Stories በአማራ ክልል ከ450 ሺህ ለሚበልጡ ልጃገረዶች የማህፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት ሊሰጥ ነው

Viewing 2 posts - 1 through 2 (of 2 total)
  • Author
    Posts
  • #7927
    Semonegna
    Keymaster

    የማህፀን ጫፍ ካንሰር በሽታን በዘላቂነት ለመከላከል የማህፀን ጫፍ ካንሰር ክትባትን ከዘጠኝ እስከ 14 ዓመት የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ልጃገረዶች እንዲሰጥ መንግስት መወሰኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ተወካይ አመልክተዋል።

    ባህር ዳር (ኢዜአ)፦ ከ450 ሺህ ለሚበልጡ ልጃገረዶች የማህፀን ጫፍ ካንሰር (cervical caner) መከላከያ ክትባት በዘመቻ ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።

    በቢሮው የጤና ማበልፀግ ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ መልሰው ጫንያለው ለኢዜአ እንደገለጹት የማህፀን ጫፍ ካንሰር በሽታ እንደሀገርም ሆነ እንደክልል ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ይገኛል።

    ዜጎችን እየጎዳ ያለው ይህንን በሽታ ለመከላከል በክልሉ የተመረጡ 25 ጤና ተቋማት ችግሩን እየለዩ ህክምና እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    ምርመራ ከሚያደርጉ እናቶች መካከልም 30 በመቶ የሚሆኑት የበሽታው ተጠቂዎች ሆነው መገኘታቸውን የምርመራ ውጤቱ አረጋግጧል።

    በሽታውን በዘላቂነት ለመከላከልም የማህፀን ጫፍ ካንሰር ክትባትን ከዘጠኝ እስከ 14 ዓመት የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ልጃገረዶች እንዲሰጥ መንግስት መወሰኑን አመልክተዋል።

    በቀጣዩ ወር በሚጀምረው ዘመቻም በክልሉም ዕድሜያቸው 14 ዓመት የሞላቸው ከ450 ሺህ በላይ ልጃገረዶች የክትባቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ተለይተዋል።

    ክትባቱን የተሳካ ለማድረግ ለጤና ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ቢሮው ስልጠና መስጠት መጀመሩን የስራ ሂደቱ መሪ ጠቁመዋል።

    “አዲስ የሚጀመረው የክትባት ዘመቻም ስለሚያስገኘው ጠቀሜታ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሰጠት ተጀምሯል” ብለዋል።

    በክልሉ በመጪው ጥቅምት ወር በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማትና አማካኝ በሆኑ ቦታዎች ለሚሰጠው የክትባት ዘመቻ ከአንድ ሺህ በላይ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ የጤና ቢሮው የክትባት ፕሮግራም የቴክኒክ አማካሪ አቶ ሙሉጌታ አድማሱ ናቸው።

    RELATED: HEALTH: Breast Cancer Replaces Cervical Cancer as Top Women Illness in Ethiopia

    ክትባቱን በመጀመሪያው ዙር የሚወስዱ ልጃገረዶች ከስድስት ወር በኋላ ክትባቱን ዳግም እንዲወስዱ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

    የማህፀን ጫፍ ካንሰር መንስኤው “ሂውማን ፓፒሎማቫይረስ” (Human papillomavirus) በሚባል ኢንፌክሽን የሚመጣ መሆኑን ጠቁመው እናቶች በበሽታው ሲያዙም ሳያውቁት እስከ 20 ዓመታት ሊቆዩ እንደሚችሉ አስረድተዋል።

    ለበሽታው ከሚያጋልጡት ምክንያቶች ውስጥ ልጃገረዶች በለጋነት እድሜያቸው የግብረ ስጋ ግንኙነት መጀመርና ከተለያዩ ሰዎች ጋር ፆታዊ ግንኙነት ማድረግ ተጠቅሰዋል።

    ወደ ህክምና ተቋማት መጥተው ምርመራ በማድረግ ራሳቸውን ከበሽታው መጠበቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

    በሚሰጠው የክትባት ዘመቻም ከአምስት ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ አካላት እንደሚሳተፉም ታውቋል።

    HPV Information Centre የሚባለው ድርጅት እ.ኤ.አ በሀምሌ ወር በ2017 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ በየ ዓመቱ 7,095 ሴቶች ማህፀን ጫፍ ካንሰር የሚጠቁ ሲሆን፣ በየዓመቱም 4,732 ሴቶች በዚሁ ካንሰር ምክንያት ለሞት እንደሚዳረጉ ዘግቧል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    የማህፀን ጫፍ ካንሰር

    #8050
    Semonegna
    Keymaster

    የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት የሚሰጥበት ጊዜ ተራዘመ

    የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት የሚሰጥበት ቀን መራዘሙን የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ።

    ክትባቱ በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች በጥቅምት ወር እና ከስድስት ወራት በኋላ ደግሞ ለሁለተኛ ዙር ሊሰጥ ታቅዶ ነበር። በቢሮው የክትባት መርሃ ግብር የቴክኒክ አማካሪ አቶ ሙሉጌታ አድማሱ እንደገለፁት ለክትባት የሚሆነው መድሃኒት በመዘግየቱ ምክንያት ክትባት የሚሰጥበት ቀን ወደ ህዳር 5/2011 ዓ.ም ተራዝሟል።

    በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚሰጠው የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ዉጤታማነት በአማራ ክልል በሁሉም ዞኖች እና ወረዳዎች ለጤና ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱንም አቶ ሙሉጌታ ነግረውናል። ከጤና ጥበቃ ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው በክልሉ ከ4 መቶ 50 ሺህ በላይ ልጃገረዶች ክትባቱን ይወስዳሉ። እድሜያቸው 14 ዓመት የሆናቸው ልጃገረዶች ብቻ የክትባቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ለማወቅ ተችሏል።

    የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እድሜያቸው ከ9 እስከ 14 ዓመት የሆናቸው ልጃገረዶችን የግብረ ስጋ ግንኙነት ከመፈጸማቸው በፊት ከበሽታው ለመከላከል ሲባል በዓለማቀፍ ደረጃ ይሰጣል። ይሁን እንጅ በኢትዮጵያ ደረጃ ለሁሉም ልጃገረዶች የሚበቃ መድኃኒት ገዝቶ ማቅረብ ባለመቻሉ ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት ላይ ክትባቱ እንደሚሰጥ ጤና ጥበቃ ቢሮው ገልጿል።

Viewing 2 posts - 1 through 2 (of 2 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.