Home › Forums › Semonegna Stories › የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀንን አከበረ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years, 3 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 12, 2018 at 7:08 am #8041SemonegnaKeymaster
የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል (በተለምዶው አማኑኤል ሆስፒታል) ኢትዮጵያ ውስጥ የአዕምሮ ህክምና የሚሰጥ ትልቁ ሆስፒታል ሲሆን፥ የተቋቋመውም በጣልያኖች እ.ኤ.አ በ1937 ዓ.ም አካባቢ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
አዲስ አበባ – በየዓመቱ እ.ኤ.አ ጥቅምት 10 ቀን የሚከበረውን የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአገራችን ለ26ኛ ጊዜ “ወጣቶች እና የአዕምሮ ጤና በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ” በሚል መሪ ቃል የተለያዩ ምሁራን፣ የህክምና ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም የሆስፒታሉ ሠራተኞች በተገኙበት መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም በአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ በድምቀት ተከበረ።
የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች የተከበረ ሲሆን ቀኑን አስመልክቶ የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዳኦ ፈጆ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ “ወጣቶች ብዙ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት የዓለም መረጃ መረብ ላይ በመጠመድ የሳይበር ወንጀልን በመለማመድ፤ ይህንኑ የመገናኛ መረብ በመጠቀም ህዝብን ወደ አልተፈለገ የእርስ በርስ ግጭቶች ውስጥ በማስገባት እና ከዚህም ሲያልፍ ከማኅበረሰቡ ባህልና ሞራል ውጭ የሆኑ ባዕዳን ቪዲዮዎችን በመመልከት ላይ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።
አያይዘውም ራሳቸውን የሚያጠፉና በአደንዛዥ እፅ ሱስ ስር እየወደቁ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱ እማኝ የሚያሻው ጉዳይ እንዳልሆነ በመጥቀስ በዚህ አዙሪት ውስጥ የሚያልፉት ደግሞ አብዛኛውን ወጣቶች መሆናቸው እጅግ አስደንጋጭ ነው ብለዋል። ዋና ሥራ አስኪያጁ እንደገለፁት አብዛኛው የአዕምሮ ህመሞች በወጣትነት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚከሰቱ መሆናችውና ወጣቶቹ ደግሞ ስለ አዕምሮ ጤና ያላቸው ግንዛቤ እና አስተምህሮ አናሳ መሆኑ ይበልጥ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል ሲሉ አክለዋል።
በመጨረሻም “ይህ ቀን ወጣቶቻችን እንዴት ጠንካራ፣ ችግር ፈች፣ ከሱስ አዙሪት፣ ከእርስ በርስ ግጭቶች፣ ከእፅ ተጠቃሚነት እና ከልክ ያለፈ የኢንተርኔት ተጠቃሚነት (substance abuse and internet overload) ሰብረው መውጣት የሚችሉበትን መፍትሄ የምናፈላልግበትና የምንመክርበት ጊዜው አሁን ነው” በማለት ለታሳታፊዎቹ መልእክታቸውን በአንክሮ አስተላልፈዋል።
በዝግጅቱ ላይ ቀኑን አስመልክቶ የአዕምሮ ጤና ምንነት፤ በአዕምሮ ጤና ላይ የማኅበረሰቡ የግንዛቤ ደረጃ ፤ በአገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የስርጭት ሁኔታ እንዲሁም ወጣቶች እና የአዕምሮ ጤና በአሁኑ ወቅት ምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስፔሻሊስት በሆኑት በዶ/ር ሙሃመድ ንጉሴ እና በዶ/ር ዮናስ ላቀው ለተሳታፊዎቹ ገለፃ ቀርቧል። በመቀጠልም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በእንግድነት የተገኙት ፕሮፌሰር አታላይ ዓለም እንደተናገሩት በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየንተሰራፋ የመጣውን የአዕምሮ ጤና ችግር ለመቀነስና መፍትሄ ለማበጀት መንግስት፤ ባለድርሻ አካላት እና ሚዲያዎች የአንበሳውን ድርሻ ሊወስዱ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በመጨረሻም በተለያየ የአዕምሮ ህመም ተጠቂ ሆነው አማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ ህክምና ተደርጎላቸው በመልካም ጤና ላይ የሚገኙ ሶስት ፈቃደኛ ግለሰቦች ሆስፒታሉን ከማመስገን ባለፈ በአዕምሮ ጤና ላይ የነበራቸውን ግንዛቤ እና ልምድ ለተሳታፊዎች ያካፈሉ ሲሆን በመልእክታቸውም የአዕምሮ ህመም እንደማንኛውም ህመም ውጤታማ ህክምና ያለው መሆኑን በማስተላለፍ በማኅበረሰቡ ዘንድ ስለ አዕምሮ ህመም ያለውን የተዛባ ግንዛቤ ለመቅረፍ መንግስት እና ህዝብ በጋራ ሊሰሩ እንዲሚገባ አስተላልፈዋል።
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስር የሚተዳደረው የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል (በተለምዶው አማኑኤል ሆስፒታል) ኢትዮጵያ ውስጥ የአዕምሮ ህክምና የሚሰጥ ትልቁ ሆስፒታል ሲሆን፥ የተቋቋመውም በጣልያኖች እ.ኤ.አ በ1937 ዓ.ም አካባቢ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሆስፒታሉ ዘርፈ ብዙ ማስፋፋቶችን እያከናወነ ሲሆን፥ በየካቲት ወር 2009 ዓ.ም. በሆስፒታሉ ስር ሆኖ የየካ ኮተቤ ሆስፒታል የአዕምሮ ህክምና መስጠት ጀምሯል።
ምንጭ፦ የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.