የትግራይ መልሶ ማቋቋም ተቋም (ትእምት) ለመቀሌ አጠቃላይ ሆስፒታል 11 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
—–
የትግራይ መልሶ ማቋቋም ተቋም የበጎ አድራጎት ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ታረቀ የገንዘብ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት ድጋፉ ሆስፒታሉ የተሻለና ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ለማጠናከር በማሰብ ነው።
የመቀሌ አጠቃላይ ሆስፒታል ለረጅም ዓመታት ከአፋር፣ አማራና ሌሎች አጎራባች ክልሎች ለሚመጡ ህሙማን ጭምር አገልግሎት መስጠቱን አስታውሰው፣ ተቋሙ ከሚሰጠው አገልግሎት እንጻር ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች ሳይሟሉለት መቆየቱን አስታውሰዋል።
በትግራይ ክልል ጤና ቢሮ የህሙማን ህክምናና እንክብካቤ የሥራ ሂደት ተጠባባቂ አስተባባሪ አቶ በሪሁ መስፍን የገንዘብ ድጋፉ ሆስፒታሉ ያለበትን የህክምና መሳሪያዎች ችግር በተወሰነ ደረጃ እንደሚፈታ ተናግረዋል።
የገንዘብ አርዳታው በሆስፒታሉ የሚገኙትን ያረጁ የህክምና መሳሪያዎች፣ የላቦራቶሪ ዕቃዎችና ኬሚካሎችን እጥረት በአጭር ጊዜ ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ይብራህ አለማየሁ ናቸው።
የመቀሌ አጠቃላይ ሆስፒታል በዓመት ከ200 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ህሙማን አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን እስከ 5 ሺህ ነፍሰጡር እናቶችንም እንደሚያዋልድ ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት