አሶሳ ዩኒቨርሲቲ የ2012 ዓ.ም. ነባርም ሆነ አዲስ ተማሪዎች ላይ በጠቅላላ የመማር-ማስተማር ሂደት ሰላማዊ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎችን በማሳተፍ ውይይት እንደሚካሄድ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት አስታውቀዋል።
አሶሳ (ኢዜአ) – አሶሳ ዩኒቨርሲቲ የ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የመማር-ማስተማር ሒደቱን ሰላማዊ ለማድረግ የሚረዱትን ቅድመ ዝግጅቶች ማጠናቀቁን አስታወቀ።
በአሶሳ ዩኒቨርሲቲው በ2011 ዓ.ም. የትምህር ዘመን በተከሰተ ግጭት የሶስት ተማሪዎች ህይወት ሲያልፍ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙ ይታወሳል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ከማል አብዱራሂም ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገለፁት፥ ከዚህ በፊት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎችን በወቅቱ ምላሽ አለመስጠት ለግጭት መፈጠር ምክንያት ተደርጎ ይጠቀስ ነበር።
በደረሰው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጥፋት የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በእጅጉ ማዘኑን የገለፁት ፕሬዝዳቱ፥ ችግሩ እንዳይደገም በመምህራንና በተማሪዎች ቅንጅት የሚተገበር ጠንካራ ዕቅድ አዘጋጅቷል።
በዕቅዱ መሠረት የዩኒቨርሲቲው የ2012 ዓ.ም. ነባርም ሆነ አዲስ ተማሪዎች ላይ በጠቅላላ የመማር-ማስተማር ሂደት ሰላማዊ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎችን በማሳተፍ ውይይት እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
ተማሪዎች በግጭት ላለመሳተፍ ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀው የጋራ መግባቢያ ሰነድ ላይ እንደሚፈራረሙም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። እርሳቸው እንደሚሉት ባለፈው የትምህርት ዘመን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን (social media) የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት በዩኒቨርሲቲው ግቢ ግጭት እንዲባባስ የሚጥሩ በርካታ መምህራን ነበሩ።
በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ፖለቲካን ከትምህርት የመነጠል ሥራ ጀምረናል ያሉት ዶ/ር ከማል፥ ይህንን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት ከችግሩ የተነካኩ አንዳንድ መምህራን በፈቃዳቸው የዝውውርና የሥራ መልቀቂያ እያቀረቡ ነው ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው ውስጣዊ ችግር ምክንያት ግጭት ዳግም ይከሰታል ብለን አናምንም የሚሉት ዶክተር ከማል፥ የተማሪዎች መማክርት አደረጃጀት፣ ምግብ፣ መኝታ፣ ኢንተርኔትን መሠል የተማሪዎችን ጥያቄዎችን መመለስ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል።
ከሠላማዊ የመማር ማስተማር ተግባር ባሻገር አሶሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት (research and community services) እንዲሁም የትምህርት ጥራትን ማስጠብቅ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው የክረምት ትምህርት እየተከታተሉ ከሚገኙ ተማሪዎች መካከል በኬሚስትሪ የ1ኛ ዓመት የክረምት ተማሪ ለማ ታገሰ በሰጠው አስተያየት የዩኒቨርሲቲ የጸጥታ የተረጋጋ ነው። አልፎ አልፎ የምግብ አቅርቦት ችግር እንዳለበት ጠቅሶ የመጸዳጃ ቤትና ተያየዥ አገልግሎቶች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ጠቁሟል።
ምንጭ፦ ኢዜአ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ