ግልጽ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ – በአቶ ነአምን ዘለቀ ― አቶ ነአምን ዘለቀ ራሳቸውን ከአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ አገለሉ

Home Forums Semonegna Stories ግልጽ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ – በአቶ ነአምን ዘለቀ ― አቶ ነአምን ዘለቀ ራሳቸውን ከአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ አገለሉ

Viewing 3 posts - 1 through 3 (of 3 total)
  • Author
    Posts
  • #10307
    Semonegna
    Keymaster

    ግልጽ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በአቶ ነአምን ዘለቀ ― አቶ ነአምን ዘለቀ ራሳቸውን ከአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ አገለሉ
    ———

    ለአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ አባላት፣ የሠራዊት አባላት፣ ደጋፊዎችና፣ በልዩ ልዩ መደረኮች ለምታውቁኝ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፦

    በሀገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የአርበኞች ግንቦት 7 የዴሞክራሲና የአንድነት ንቅናቄ (አግ7) አመራር አባላት እ.ኤ.አ. በሀምሌ (July) ወር 2018 በአሜሪካን ሀገር ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በተደረገ ስብሰባ ላይ ከተደረሱት የስምምነት ነጥቦች መካከል አንዱ የአግ7 ንቅናቄ ሠራዊት ከኤርትራ በርሃና ከሀገር ውስጥም የነበሩት የአግ7 ታጣቂዎች ወደ ሀገር ወደ ሰላማዊ ኑሮ መመለስና ማቋቋምን የሚመለከት ነበር። በዚህም መሠረት በኤርትራ የነበሩ የንቅናቄው ሠራዊት አባላት እንዲሁም በየበረሃው የነበሩ የንቅናቄው ታጣቂዎች ወደ ልዩ ልዩ ካምፖች በየጊዜው እንዲገቡ መደረጉ ይታወቃል። በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የንቅናቄው አባላትም ከልዩ ልዩ እስር ቤቶች ቀደም ሲል በተከታታይም እንደተለቀቁ ይታወቃል። በኃላፊነት ስመራ በቆየሁት በውጪው ዘርፍ ስር የማኅበራዊ ፈንድ ኮሚቴ እንዲቋቋም በማድረግ በውጭው ዓለም በሚገኙ በንቅናቄው አባላት፣ በደጋፊዎች፣ እንዲሁም አገር ወዳዶች ትብብር መጠነ ሰፊ ገንዘብ በማሰባሰብ በየእስር ቤቱ የነበሩት ተጋዮች ለሦስት ተከታታይ ወራት እንዲረዱ እንዲሁም ከኤርትራ በረሃ ለመጡትና በካምፕና ከካምፕ ውጭ ለሚገኙትም በልዩ ልዩ መንገዶች እርዳታዎች እንዲያገኙ ለማድረግ ተችሏል።

    ከኤርትራ በረሃ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ የተደረጉትን የአርበኞች ግንቦት 7 የቀድሞ ታጣቂዎች እንዲሁም የሌሎች የፓለቲካ ድርጅቶች ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋሚያ ፕሮጄክት ጽ/ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ስር ከ7 ወራት በፊት የተመሠረተ ሲሆን፥ የውጭ መንግስታትም በተለይም የጀርመን መንግስት ለዚሁ የሚውል ገንዘብ ለመስጠት ከበርካታ ወራት በፊት ተስማምተው ነበር። ሆኖም ከተቋቋመው ጽ/ቤት አቅም ማነስ እንዲሁም ጉዳዩ ተገቢውን ውሳኔዎች ሳያገኝ እየተጓተተ በመቆየቱ ሳቢያ የአርበኞች ግንቦት 7 ሠራዊት አባላት (በተለይም ከካምፕ ውጪ እንዲቆዩ ተደርገው መልሶ የማቋቋሚያ ድጋፍ እንዲጠብቁ የተነገራቸው ጭምር) ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸው ለህሊና እረፍት በሚነሳ ሁኔታ ውስጥ እራሴን አግኝቼ ነበር።

    የንቅናቄው ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እንዲሁም ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ በየጊዜው ከጠቅላይ ሚንስትሩና ከሌሎች የመንግስት ኃላፊዎች ጋር የሚያደርጉት ግንኙነትና ክትትል እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በችግር ላይ የነበሩ የሠራዊት አባላት ሁኔታ አየተደራረበ የጭንቀት ድምጾች እየተበራከቱ በመምጣታቸው፣ ይህ ጉዳይ የንቅናቄውን ሊቀመንበርና ዋና ጸሐፊውን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን አባላትና ሠራዊቱ የመረጡን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን በሙሉ በተናጠልም ሆነ በጋራ የሚያስጠይቅ፣ ለሠራዊቱም ሆነ ለአባላት ኃላፊነት አለብን በሚል መንፈስ ይህ ለውጡን ለሚመራው መንግስትም የጸጥታና የፓለቲካ ችግር የሚፈጥር ሁኔታ፣ ከሞራልም ሆነ ከፓለቲካ እኳያ የንቅናቄውንም ውስጣዊ ጤንነት እየተፈታተነ የነበረ ትልቅ ችግር እየሆነ በመምጣቱ፣ ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ እርዳታ ለመስጠት ቃል ከገቡና ለመርዳት ፈቃደኛ ከሁኑ መንግስታት በተለይም ከጀርመን አምባሳደር፣ ከስዊድን መንግስት ኃላፊዎችና የፓርላማ አባላት፣ ከልዩ ልዩ የመንግስት ኃላፊዎችና ከመንግስት መዋቅር ውጭ የሚገኙ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚቀርቡ ግለሰቦች ጋር በመገናኘት ለማስረዳትና መፍትሄ እንዲያገኝ የበኩሌን አስተዋጽዖ ለማድረግ ጥረቶች ሳደርግ ቆይቻለሁ።

    ብዙ ዝርዝሮች ያሉትና ወራት ያስቆጠረ ሂደት ቢሆንም፣ በዚህ አጋጣሚ ለዚህ ችግር መፍትሄ በማፈላለግ ሊያዳምጡን በራቸውን ለከፈቱ የልዩ ልዩ የመንግስት ተቋማት ኃላፊዎች፣ በተለይም የብሄራዊ አደጋና መከላከል ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ፣ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ፣ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ፣ እንዲሁም ከመንግስት መዋቅር ውጭ ያሉና ከለውጡ በኋላ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ሊያገኙን እንደሚፈልጉ በላለቤቴ በኩል መልክት የላኩብኝ የጠቅላይ ሚኒስሩ የአርቅ ኮሚቴ አባል አቶ ብርሃን ተድላ፣ በበርካታ የሕዝብና የሀገር ጉዳዮች ያላሰለሰ አስተዋጽኦ የሚያደርጉትና የረጅም ጊዜ ወዳጄ ለሆኑት ዶ/ር አምባሳደር ካሳ ከበደ፣ በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥተው ለመርዳት ለተንቀሳቀሱት፣ በእርዳታና በመልሶ ማቋቋም ከፍተኛ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ለሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ፣ እንዲሁም ለመለሶ ማቋቋም የተቋቋመው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ኣፍሪድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ይልማ፣ ሌሎችም ለችግሩ መፍሄ ለማግኘት ያገኘኋቸውን ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ሁሉ እስከአሁኑ ቀን ድረስ ለከፍተኛ ችግር ተዳርገው በሚገኙት የሠራዊት አባላት ስም ምስጋና ሳላቀርብ አላልፍም፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ትላንት ከለውጡ በፊት እንኳን እነሱን ደጅ ልንጠና ቀርቶ አጠገባቸው ለመድረስ እንኳን የምንጸየፋቸው፣ የተቀመጡበት የኃላፊነትና የአማካሪነት ቦታ የሀገርና የህዝብ ችግሮች ለመፍታት መሆኑ እምብዛም የሚያስጨንቃቸው የማይመስሉ፣ ራሳቸውን የኮፈሱ አድርባዮች፣ ከንቱና ግብዝ የመንግስት ባለሟሎች በዚህ ሂደት ለመታዘብ ችያለሁ።

    የሆነ ሆነ ይህ ከፍተኛ ችግር መፍትሄ እንዲያገኝና በውጭ የሚገኙትም ሆኑ በካምፕ ውስጥ የሚገኙት የንቅናቄያችን ሠራዊት አባላት ቢያንስ አቅም ባለው፣ ሠራዊቱ የሚገኝበትን ችግር ለማቃለል ብቃትና ተቋማዊ ቁመና ለዓመታት ባካበተ የመንግስት ኮሚሽን በኩል እንዲሆን የሚያስችል እርምጃ እንዲወሰድ በቅርብ ቀን መወሰኑን አዲስ አበባ በነበሩኩባቸው አራት ሳምንታት ከሚመለከታቸው የመንግስት ኃላፊዎች ጋር በተደረገ ውይይት አረጋግጫለሁ። ይህም እርምጃ ለወራት የቆየን ከባድ የህሊና ሸክም ያቃለለ ቢሆንም፣ አሁንም ከካምፕ ውጭ የሚገኙ የሠራዊቱ አባላት የሚገኙበትን ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ ችግሮች አስመልክቶ በየዕለቱ በርካታ መረጃዎች እየደረሰን በመሆኑ ከካምፕ ውጭም ሆነ ከካምፕ ውስጥ የሠራዊቱ አባላት ቃል የተገባላቸው እርዳታ እንዲደርሳቸው፣ የመልሶ ማቋቋሙ ሂደት በቶሎ እንዲጀመር፣ የንቅናቄው የሥራ አፈጻሚ ኮሜቴ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ኃላፊዎች የሚያስፈልገው ያልተቋረጠ ትኩረትና ክትትል እንዲያደርጉ በድጋሚ ለማሳሰብ እወዳለሁ።

    ሀገራችን ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችና ህልውናዋን የሚፈታተኑ ስጋቶች የተጋረጡባት ከመሆኗም በሻገር ከምንጊዜውም በባሰ መልኩ መስቀለኛ መንገድ ላይ የምትገኝ መሆኑን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ሁሉ የሚስማሙ ይመሰለኛል። ይህን አደጋ ለመቋቋም ደግሞ በርካታና ዘርፈ ብዙ ሕዝብ አቀፍ እንቅስቃሴዎች ያስፈልጋሉ። ስለዚህም ውስብስብ በሆኑና ስር በሰደዱ መጠነ ሰፊ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፓለቲካዊ ችግሮች አውድና ከባቢ ውስጥ ተዘፍቀው ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ፣ ፍትህና፣ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን እየተደረገ በሚገኘው የለውጥ ጅማሮ እንዳይቀለበስ የለውጡን አራማጆች፣ ለውጡን ለማስቀጠል በተጨባጭ እርምጃዎች እስከተንቀሳቀሱ ድረስ ማገዝ አማራጭ የሌለው ነው ብዬ አምናለሁ።

    ሀገራችንን ቅርጫ ለማድረግ ሲሉ የ100 ሚሊዮን ህዝብ ዕጣ ፈንታ ላይ ቁማር የሚጫወቱ፣ የሕዝብን የተሻለ ህይወት፣ ለሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች የታገሉለትን፣ የሚመኙትን ፍትህ፣ ነጻነትና የነገን ተስፋ እየረጋገጡ የሚገኙ እጅግ ራስ ወዳድ፣ ስግብግብ ህሊና ቢሶች፣ የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ማኅበረሶቦች አብሮነት አጥፍተው ለራሳቸው ጠባብ ብሄረተኝነት እጀንዳ ጥቅምና ስልጣን ለማምጣትም ሆነ ለማስቀጠል በየአካባቢው ትርምስ የሚፈጥሩ፣ ክቡር የሆነውን ሰብዓዊነት ረግጠው ወደ አራዊትነት በተጠጋ የለየለት ጽንፈኝነትና አክራሪነት የታወሩ ጥቂቶች፣ ከራሳቸው ግላዊ ፍላጎትና ጥቅም ውጭ ለሕዝብና የሀገር ደህንነት፣ ለሰላም፣ ለፍትህና፡ ለሕግ የበላይነት ምንም ቁብ የማይሰጡ የጥፋት ኃይሎች በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች እንደአሸን በፈሉበት ሁኔታ ከኢትዮጵያዊነት ውጪ፣ ከፍትህ፡ ከእኩልነትና፣ ከሕዝብ አብሮነት የተለየ ሌላ አማራጭ እንደሌለ፣ ሌላ ሀገር፣ ሌላ ምድርም አለመኖሩን በሚገባ የተረዱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ሁሉ በየአካባቢያቸው እያፈጠጠ፣ እያገጠጠ ከሚገኘውን የህልውና አደጋ ከእነዚህ አክራሪና ጽንፈኛ የጥፋት ኃይሎች ሊያመጡት ከሚችሉት የሀገራችንን የመኖር አለመኖር ህልውና የሚፈታተን የሲኦል ጎዳና ራሳቸውን፣ ቤተስባቸውንም ለመከላከል፣ ተከላካይ በሆነ መልኩ እርስ በእርስ መደራጀት፣ እንዲሁም ራስን በራስ ማደራጀትና፣ ብሎም ነቅቶ መጠበቅ ሌላው አስፈላጊና ወቅታዊ ተግባር ነው ብዬ አምናለሁ።

    ለአገራችን ሕልውና፣ ለሕዝባችን ሰላም፣ ፍትሕና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሰፈነባት ኢትዮጵያ እንድትኖር የሚያስችል የፓለቲካ ስርዓት እንዲረጋገጥ የሚጨነቁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እልህ አስጨራሽ ሁኔታ ውስጥ ብንገኝም ከዚህም ከዚያም የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ እየጣሉ የሚገኙ አክራሪና ጽንፈኛ ብሄረተኞችና የለውጥ ቅልበሳ ቡድኖች ወጥመድ ሰላባ ላለመሆን በስልት፣ በሰከነ ጥበብና በሃገራዊ ኃላፊነት መንቀሳቀስ የግድ ነው ብዬ አምናለሁ። ለኢትዮጵያዊነት፣ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዜጎች እኩልነትና ሁለንተናዊ መብቶች የቆሙ የፓለቲካ ኃይሎች፣ የሲቪክ ተቋማት፣ እንዲሁም የፕሬስ ድርጅቶችን ማጠናከር እንዲሁ ሌላቅ የወቅቱ ዐቢይ ተግባራት ይመስሉኛል።

    በሀገራችን የተጀመረው ለውጥ ከመጣ ከጥቂት ወራት በኋላ ንቅናቄው የፓለቲካ ፓርቲ እንደሚሆን ስምምነት በተደረሰ ጊዜ የፓለቲካ ፓርቲ አመራርም ሆነ አባል ሆኜ ለመቀጠል ፍላጎት እንደሌለኝ በአመራሩ ላይ ለሚገኙ ሁሉ በተለያዩ ጊዜያት ገልጬ ነበር። እስካሁንም ድረስ የቆየሁት ከመሪዎች አንዱ ሆኜ እንዳገለግል ለመረጡኝ አባላትና የሠራዊት አባላት ባለኝ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ቢያንስ ከኤርትራ በርሃና በኢትዮጵያም ውስጥ ሆነው በጨለማው ዘመን ለኢትዮጵያ አንድነትና ለሕዝብችን ነጻነት ህይወታቸውን ለመገበር ለቆረጡ እነዚህ ዛሬ በካምፕ ውስጥና ከካምፕ ውጭ የሚገኙ የሠራዊት አባላትና ታጋዮች ህይወት ተገቢውን መስመር እስኪይዝ ነበር።

    ቀደም ሲል መልቀቂያ አስገብቸ የነበረ ቢሆንም እንኳን የንቅናቄው ዋና ጸሀፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ የተለያዩ የንቅናቄው አመራሮች በኃላፊነቴ እንድቆይ በነበራቸው ፍላጎት፣ እኔም ከነሱ ጋር ባደረኳቸው ውይይቶች በቦታው መቆየቴ ሠራዊቱን ይጠቅማል ብዬ ስላመንኩ እስካሁን ድረስ በተሰጠኝ የኃላፊነት ቦታ ላይ የምችለውን እያገዝኩ ቆይቻለሁ። ሆኖም ለቆሙለት ዓላማ፣ ለንቅናቄያቸውና ለሀገራቸው ክብር መተኪያ የሌላት ህይወታቸውን ለመክፈል የቆረጡ የትግል ጓዶቸ ላለፉት 7 ወራት በከፍተኛ ችግሮች ውስጥ ወድቀው ማየት ለኔ እንቅልፍ የሚነሳ ጉዳይ መሆኑ አልቀረም።

    ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለዴሞክራሲና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሁለንተናዊ መብቶች መረጋገጥ የበኩሌን አስተዋጽኦ ሳደርግ ቆይቻለሁ። ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በላይ በውጭው ዓለም በተደረገው ትግል ልዩ ልዩ የትግል መድረኮችን በመሥራችነት፣ በአባልነት፣ በአስተባባሪነት፣ እንዲሁም በአመራር ኃላፊነቶች የዜግነት ግዴታዬን ከሚጠበቅብኝ በላይ አስተዋጽኦ በማድረግ ለ26 ዓመታት ያልተቋረጠ የትግል አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ። የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥንን(ኢሳት) በማቋቋም፣ በመገንባት ሂደትና እስከ 2015 ድረስም በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ፣ እሰከአሁኑ ድረስም በቦርድ ሥራ አስፈጽሚ አባልነት የበኩሌን አስተዋጽኦ ተወጥቻለሁ።

    ባለፉት 8 ዓመታት የአርበኞች ግንቦት 7 የአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና ልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊነቶች ላይ በመሰማራት፣ እ.ኤ.አ ከመስከረም (September) ወር 2017 ከተደረገው የንቅናቄው ጉባኤ ላይ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆኜ ከተመረጥኩኝ በኋላም የንቅናቄው የውጪው ዘርፍ ኃላፊ በመሆን እስካሁን ድረስ በቅንነትና በምችለው እቅም ኃላፊነቴን ተወጥቻለሁ። በአሁኑ ወቅት ከአርበኞች ግንቦት 7 የሥራ አስፈጻሚ ኮሜቴ አባልነት፣ እንዲሁም ንቅናቄው የውጭ ዘርፍ ኃላፊነት በገዛ ራሴ ፈቃድ መልቀቄን ለአርበኞች ግንቦት 7 አባላት፣ ደጋፊዎች፣ በልዩ ልዩ የትግል መድረኮች ለምታውቁኝ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለማሳወቅ እወዳለሁ።

    የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ በቅርብ ጊዜ ጉባኤ በማድረግ ይከስማል። አዲስ ሀገራዊና በኢትዮጵያዊነት፣ በዜግነትና በማኅበራዊ ፍትህ ላይ የቆመ የፓለቲካ ፓርቲ የምሥረታ ሂደት ወደ ማገባደጃው በመድረሱ በአዲሱ ፓርቱ ለሚመረጡ አመራሮች እንዲሁም አባላትና ደጋፊዎች ሁሉ ያለኝን ጽኑና መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ። ለወደፊቱ ለኢትዮጵያ ሀገራችን እንዲሁም ለዓዝባችን ፋይዳና ጥቅም በሚያስገኙ ልዩ ልዩ ተግባራት ላይ በመሳተፍ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ድርሻዬን እንደምወጣ ለምታከብሩኝ፡ ለምትወዱኝና ለማከብራችሁና ለምወዳችሁ ወገኖቼ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለማረጋገጥ እወዳለሁ። እዚህ ላይ የንቅናቄው ወዳጆችም ሆናችሁ ሌሎች እንድታውቁት ላሰምርበትም የምፈልገው በንቅናቄው አጠቃላይ የፓለቲካ ራዕይና ተልእኮ፣ በሚመሠረተው የፓለቲካ ፓርቲ ዓላማና ተልዕኮ፣ እንዲሁም ከማንም የንቅናቄው አመራር አባላት ጋር በግል ሆነ በፓለቲካ ምንም ዓይነት ቅራኔ የሌለኝ መሆኑን ለማረጋገጥ እወዳለሁ። ዘለአለማዊ ክብርና ሞገስ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለዓባችን ነጻነትና፣ ለፍትህ ሲሉ አይተኬ የህይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ የኢትዮጵያ ልጆች ሁሉ! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

    ነአምን ዘለቀ ቦጋለ
    ቨርጂኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ
    ማርች 18 ቀን፣ 2019

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ነአምን ዘለቀ


    #10323
    Semonegna
    Keymaster

    “የሠራዊቱ ሁኔታ ከፍተኛ የህሊና መረበሽ ውስጥ ከቶኛል” አቶ ነአምን ዘለቀ
    —–

    ላለፉት 26 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ሲያደርጉ የቆዩት የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ከፍተኛ አመራርና ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ነአምን ዘለቀ ከፓርቲ መልቀቃቸውን ተከትሎ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

    ቢቢሲ፡ የአርበኞች ግንቦት 7 የሠራዊ አባላት አሁን ያሉበት ሁኔታ ትንሽ ያስጨነቀዎት ይመስላል። ግን ደግሞ ለመልቀቅ ከወሰኑ ቆይተዋል፤ እርስዎም በጽሑፍዎ እንደጠቀሱት። እና ዝም ብሎ ከመውጣት፣ መልቀቅዎን ከአንድ ጉዳይ ጋ ሆን ብለው ለማያያዝ የሞከሩ ይመስላል።

    አቶ ነአምን፡ (ዘለግ ካለ ሳቅ በኋላ) ምን እላለሁ እንግዲህ። አንተ የመሰልህን (ማሰብ ትችላለህ). . .። መጀመሪያ (ከጽሑፌ) አንተ ይሄን ብቻ ነጥለህ ለምን እንዳወጣኽው አላወቅኩም። እዚያ ላይ ሠራዊቱን በሚመለከት የተደረገው ጥረት በዝርዝር ተቀምጧል። እስካሁን ድረስ እነኚህ የሠራዊት አባላት በከፍተኛ ችግር ላይ ነው ያሉት፤ ላለፉት ሰባት ወራት።

    መንግሥት የእነርሱን ጉዳይ በተደረገው ስምምነት መሠረት (ማለትም) ቶሎ በሁለትና በሦስት ወር ውስጥ መልሰው ይቋቋማሉ፣ ድጎማ ይሰጣቸዋል አለ፤ የጀርመን መንግሥት ገንዘብ ለመስጠት ቃል ገባ፤ ነገር ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የተቋቋመው ቢሮ ምንም አቅም ስላልነበረው እስካሁን ድረስ ሲጓተት ቆይቶ አሁን ገና ወደ ኮሚሽን ጉዳዩ ተመርቶ ያው ኮሚሽኑ ኃላፊነት ተሰጥቶት በብሔራዊ አደጋ መከላከል ኮሚሽን በኩል የእነርሱ ጉዳይ እንዲካሄድ ነው እየተደረገ ያለው።

    ቢቢሲ፡ ለመሆኑ የሠራዊቱን አባላት በአካል አግኝተዋቸዋል?

    ሙሉውን ቢቢሲ አማርኛ ላይ ያንብቡ

    #11173
    Anonymous
    Inactive

    የፌደራል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የቀድሞ አርበኞች ግንቦት 7 ሠራዊትን ሊያቋቁም ነው
    —–

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የቀድሞ የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ሠራዊት አባላትን የፌደራል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ለማቋቋም ቃል መግባቱን ሠራዊቱን መልሶ የማቋቋም አስተባባሪ ወ/ሮ እማዋይሽ ዘውዱ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ አስታውቀዋል።

    ሠራዊቱን መልሶ የማቋቋም ኮሚቴው በጉዳዩ ላይ ከአደጋ መከላከልና ስጋት አመራር ኮሚሽን ጋር መወያየቱን የገለፁት ወ/ሮ እማዋይሽ፥ መንግስት ተጣርቶ የቀረበለትን የሰው ኃይል መልሶ ለማቋቋም ቃል ገብቷል ብለዋል።

    በአሁን ወቅት በየቦታው ያሉ የሠራዊቱን አባላት ተሳትፎና ማንነት የተመለከቱ መረጃዎችን ኮሚቴው እያጣራ መሆኑን የገለፁት ወ/ሮ እማዋይሽ፥ በአጠቃላይ መደራጀትና መቋቋም የሚያስፈልጋቸው የሠራዊቱ አባላት ከ5ሺህ በላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

    የሠራዊት አባላቱ በአራት ምድብ የሚከፈሉ መሆኑን የገለፁት አስተባባሪዋ፥ በመንግስት ታስረው የነበሩ፣ ከኤርትራ የመጡ፣ በዘመቻ ሲንቀሳቀሱ የነበሩና በዘመቻ ወቅት አባታቸውን ያጡ ልጆች መሆናቸውን አስረድተዋል።

    በአሁኑ ወቅት ባህር ዳር ላይ 1900 (አንድ ሺ ዘጠኝ መቶ ያህል) የሠራዊቱ አባላት ለመቋቋም ተመዝግበው ይገኛሉ ያሉት አስተባባሪዋ፥ በቀጣይ አባላቱ በፈለጉት የሥራ መስክ እንዲሠማሩ መንግስት ሙሉ ኃላፊነቱን ወስዶ ለማቋቋም ቃል መግባቱን አስታውቀዋል።

    ምንጭ፦ አዲስ አድማስ ጋዜጣ

Viewing 3 posts - 1 through 3 (of 3 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.