Home › Forums › Semonegna Stories › የትምህርት ተቋማትን ከፖለቲካ ተጽዕኖ ማላቀቅ ይገባል ― ፕሮፈሰር ጣሰው ወልደሃና
Tagged: ሰላም ሚኒስቴር, አልማዝ መኮንን, አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ, ጣሰው ወልደሃና
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
January 12, 2019 at 10:22 pm #9180SemonegnaKeymaster
እንደ ፕሮፈሰር ጣሰው ወልደሃና ገለጻ፥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ስድስት ወራት በተጽዕኖ የሚካሄዱ የፖለቲካ አሠራሮችን በማጽዳትና የፖለቲካ ሃሳቦችን በነጻ የሚያራምዱበት የጋራ መድረክ በማዘጋጀት የተሻለ ሰላም ማምጣት ችሏል።
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ከፖለቲካ ተጽዕኖ በማላቀቅ በሰላም አብሮ የመኖር ባህልን ማሳደግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፈሰር ጣሰው ወልደሃና ተናገሩ።
ዩኒቨርሲቲው ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ”ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሰላም” በሚል ጥር 4 ቀን 2011 ዓ.ም. መክረዋል።
ፕሮፌሰር ጣሰው በዚሁ ወቅት፥ የሰላማዊ አብሮ የመኖር ባህልን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለማሳደግ ተማሪዎችን ከፖለቲካ እንቅስቃሴና ፉክክር ነጻ ማድረግ ይገባል። ባለፉት ዓመታት ሰላም ላይ ትኩረት ተደርጎ ባለመሠራቱ ተማሪዎች በዘር የመከፋፈልና እርስ በእርስ ያለመታማመን ችግሮች አጋጥሟቸዋል። ይህም በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ግጭትና ሁከትን በመቀስቀስ የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ያመጣው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ተማሪዎችና መምህራን በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚያደርጉት ፉክክርና አንዳንድ ድርጅቶችም የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸውን ያለገደብ በተቋማቱ ማራመዳቸው የተማሪዎችን አብሮነት እንደሸረሸረውም ነው ፕሮፌሰሩ ያብራሩት። የዩኒቨርሲቲዎች ዋነኛ ተግባር ማስተማርና መመራመር መሆኑን አጽንዖት ሊሰጡት እንደሚገባም አመልክተዋል።
◌ ትውልድን በመቅረጽ፣ አገርን በመገንባት በኩል መምህራን የበኩላቸውን አስተዋጽዖ መወጣት ይጠበቅባቸዋል ― ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
እንደ ፕሮፈሰሩ ገለጻ፥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ስድስት ወራት በተጽዕኖ የሚካሄዱ የፖለቲካ አሠራሮችን በማጽዳትና የፖለቲካ ሃሳቦችን በነጻ የሚያራምዱበት የጋራ መድረክ በማዘጋጀት የተሻለ ሰላም ማምጣት ችሏል።
ዩኒቨርሲቲው በሰላም ዙሪያ የሚመራመርና ሃሰቦችን የሚያፈልቅ አስር አባላት ያሉት ቡድን አዋቅሮ በተቋሙ ቀጣይነተ ያለው ሰላም ለማምጣት እየሠራ ነውም ብለዋል – ፕሮፌሰር ጣሰው። ለቡድኑም አንድ ሚሊዮን ብር ዩኒቨርሲቲው መመደቡን አስታውቀዋል።
ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ይህንን ተሞክሮ በማስፋት ለአገር ሰላምና ለአብሮነት የሚያደርጉትን ጥረት ማጠናከር እንዳለባቸውም ተመላክቷል።በመድረኩ “ሰላምና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት” በሚል ጽሁፍ ያቀረቡት በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ በበኩላቸው ሰላምን ለማስፈን ተቋማቱን ከፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል።
በተለይ በተቋማቱ የሰላም እጦት መንግስትና ምሁራን በሰላም ላይ ያልተገበሯቸው በርካታ ተግባራት ለመኖራቸው ዋቢ ነው ብለዋል – ፕሮፈሰሩ።
በቀጣይም ኢትዮጵያዊ አብሮነትን ያካተተ መርሃ ግብር በመቅረጽ፤ በጎሳና በዘር የተከፋፈለውን የምደባ ስርዓት በመከለስ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የፌዴራል ተቋማት መሆናቸውን ማጉላትና የተማሪዎች ህብረትን ከፖለቲካ የጸዱ ማድረግ ይገባል ብለዋል። አክለውም ምሁራን የግጭት አራጋቢዎች ከመሆንና የሥራ መርሃ ግብራቸውን በአግባቡ ካለመወጣት ተቆጥበው ትውልድ የመቅረጽ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አልማዝ መኮንን እንዳሉት ምሁራን ለሀገሩ ቀና የሆነ ዜጋንና ስለአገሩ ሰላምና ዲሞክራሲ የሚተጋ ዜጋን የማፍራት ኃላፊነት እንዳለባቸው በመጥቀስ፥ በተለይ ምሁራን አገሪቷ አሁን ከገጠማት የሰላም እጦት ለመውጣት ሙያዊና የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ለአንድ ቀን ብቻ በተደረገው የምከክር መድረኩ ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተወከሉ መምህራን፣ የተማሪዎች መማክርት፣ የሰላም መልዕክተኞችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.