በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ግጭት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ
—–
በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ግጭት አሁንም ተባብሶ ቀጥሏል።
ግጭቱ ትናንት ከቀኑ 9:30 ጀምሮ በአጣዬ በማጀቴና በካራ ቆሬ አካባቢዎች መባባሱም ተሰምቷል።
ስለ ጉዳዩ የጠየቅናቸው የአጣዬ ከተማ ከንቲባ አቶ ጌታቸው በቀለ ግጭቱ በአካባቢው ነዋሪና በታጠቁት ኃይሎች መካከል መፈጠሩን ነግረውናል።
ምክንያቱ በውል እንደማያውቁ የገለፁልን አቶ ጌታቸው የታጠቀው ኃይል ከትናንት ቅዳሜ ጀምሮ በፈፀመው ጥቃት 9 ሰዎች መገደላቸውንና በርካቶች መቁሰላቸውን ገልፀውልናል።
ግጭቱ አሁንም ተባብሶ ቀጥሏል ያሉት ከንቲባው ቤት ለቤት ዘረፋ መጀመሩንና 3 ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸውንም ነግረውናል።
በአካባቢው የነበረው የክልሉ ልዩ ኃይል ጥቃቱ ከአቅሙ በላይ በመሆኑ መከላከያ ኃይል መግባቱንም ከንቲባው አያይዘው ተናግረዋል።
የኤፍራታና ግድም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደምሰው መሸሻ በበኩላቸው ተደራጅቶ ዘመናዊና የቡድን መሳሪያዎችን የታጠቀው ቡድን በከፈተው ጦርነት ብዙዎች ተገድለዋል ብለዋል።
በአካቢው ያሉ የእምነት ተቋማት ጭምር ጥቃት እንደደረሰባቸው ነው አስተዳዳሪው የገለፁት።
ዋና አስተዳዳሪው አክለውም ወደ አካባቢው የገባው የመከላከያ ኃይል ሁኔታውን ማረጋጋት እንዳልቻለ ገልፀዋል።
ምንጭ፦ ኢቢሲ