በአገራችን ላይ ሊቃጡ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ በመከላከል እና ቢከሰቱም እንኳን የከፋ ጉዳት ከማድረሳቸዉ በፊት በአፋጣኝና በአጭር ጊዜ ምላሽ በመስጠት ረገድ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ዓይነተኛ ሚናን መጫወት ችሏል።
አዲስ አበባ (ኢመደኤ) – የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ባሳለፍነዉ 2011 በጀት ዓመት በተለያዩ ቁልፍ የሀገሪቱ ተቋማት እና መሠረተ ልማቶች ላይ ሊፈጸሙ የነበሩ 791 የሚደርሱ የሳይበር ጥቃቶችን (cyber-attacks) ማክሸፍ መቻሉን ገለጸ።
በኢመደኤ የኢትዮጵያ ሳይበር የድንገተኛ ዝግጁነት እና ምላሽ ሰጪ ዲቪዥን (Ethiopian Cyber Emergency Readiness & Response Team – ETHIO CERT) ኃላፊ የሆኑት አቶ አብርሃም ገብረጻዲቅ እንደገለጹት፥ በአገራችን ላይ ሊቃጡ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ በመከላከል እና ቢከሰቱም እንኳን የከፋ ጉዳት ከማድረሳቸዉ በፊት በአፋጣኝና በአጭር ጊዜ ምላሽ በመስጠት ረገድ ኢመደኤ ዓይነተኛ ሚናን መጫወት መቻሉን ገልጸዋል። ኃላፊዉ ጨምረዉ እንደገለጹት በ2011 በጀት ዓመት በአገሪቱ ላይ የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ መከላከል በመቻሉ ሊደርስ ከነበረው የደኅንነት እና የገንዘብ ኪሳራ በድምሩ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማዳን መቻሉን የገለጹ ሲሆን፤ ከዚህም በላይ በገንዘብ የማይተመን ሰላምን እና ፍትህ ማስጠበቅ ተችሏል ብለዋል። በቀጣይ 2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት አገራዊ የሳይበር ጥቃትን የመከላከል ሽፋን በማሳደግ እና ዓለም አቀፍ ትስስርንና ቅንጅትን በማጠናከር የአገሪቱን ቁልፍ የሳይበር መሠረት ልማቶችን ደህንነት የማስጠበቅ ሥራ እንደሚሠራም ኃላፊዉ ገልጸዋል።
በኢመደኤ የኢትዮጵያ ሳይበር የድንገተኛ ዝግጁነት እና ምላሽ ሰጪ ዲቪዥን በኢትዮጵያ የሳይበር ሥነ-ምህዳር የሚገኙ የሳይበር መኃረተ ልማቶችን ከጥቃት ከመከላከልና ምላሽ ከመስጠት ባለፈ የሳይበር ደህንነት ክፍተት ትንተና (vulnerabilities) በማከናወን የሳይበር ጥቃት አስቀድሞ የመከላከል፣ የሳይበር ጥቃቶች ከመፈጠራቸው በፊት የማስቀረት፣ የተፈጠሩት ሳይበር ጥቃቶች ከጥቃቱ በፊት ይሠሩበት ወደነበረው ይዞታቸው የመመለስ እና በተመሳሳይ ጥቃት እንዳይጠቁ የደኅንነት ክፍተታቸውን እንዲደፈን የማድረግ፤ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የሳይበር ጥቃት መከላከያ ተቋማት ጋር በቅንጅትና በትስስር ሥራዎችን የሚሠራ ክፍል ነዉ።
ምንጭ፦ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ