Home › Forums › Semonegna Stories › የኢዜማ ከፍተኛ አመራሮች በሎስ አንጀለስ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋራ ተወያዩ
Tagged: ብርሃኑ ነጋ, ናትናኤል ፈለቀ, አንዱዓለም አራጌ, ኢዜማ, የሺዋስ አሰፋ, የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 6 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
June 3, 2019 at 12:18 pm #11026SemonegnaKeymaster
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከፍተኛ አመራሮች አሜሪካ ውስጥ በካሊፎርንያ ግዛት ሎስ አንጀለስ ከተማ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር አዲስ በተቋቋመው ፓርቲ አጠቃላይ ሁኔታና የሀገራችን ኢትዮጵያን (የፖለቲካ) ነባራዊ ሁኔታን በተመለከተ ተወያዩ።
የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የሕዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ናትናኤል ፈለቀ በሰሜን አሜሪካ በሚገኙ ሦስት ከተሞች ከሚያደርጉት ውይይቶች የመጀመሪያው በሆነው የሎስ አንጀለስ ውይይት፣ የፓርቲው አመሠራረት፣ ለመሥራት የታቀዱ ሥራዎች እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በፓርቲው እና በአጠቃላይ ሀገሪቷ ውስጥ እንዲገነባ የሚፈለገው የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንዴት ማገዝ እንደሚችሉ ውይይት ተደርጓል። በቪዛ መዘግየት ምክንያት ለስብሰባው መድረስ ያልቻሉት የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌ የመክፈቻ የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኢዜማ ባደረገው በዚህ ውይይት፥ የሀገራችንን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እና የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችም የውይይቱ አካል ነበሩ። ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣውን ለውጥ “ሁለንተናዊ መሻሻል” ተብሎ የሚፈረጅ (reform) እንጂ አብዮት (revolution) አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክት ያስተላለፉት የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ ለውጡ ያልገባቸው (የሚያስጨንቃቸው) የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚፈጥሩት እንቅፋት፣ በየክልሉ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች እና ብዛት ያለው ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ቁጥር የለውጡ ከፍተኛ ተግዳሮቶች እንደሆኑ እና በየደረጃው መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በኢዜማ እንቅስቃሴዎች ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን የሚችሉበት አደረጃጀት (ቻፕተሮች) በሁሉም የዓለማችን አካባቢዎች የሚዋቀሩ ሲሆን በሀገራችን ዜግነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲፈጠር እና ማኅበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን የሚፈልጉ በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በነዚህ መዋቅሮች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ተላልፏል።
ከፓርቲው ዜና ጋር በተያያዘ፥ የኢዜማ ግብረ-ኃይል በአምስት አቅጣጫ ተንቀሳቅሷል። ከአዲስ አበባ በመነሳት በአምስት አቅጣጫ መዳረሻውን ያደረገ ግብረ-ኃይል ግንቦት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. እንቅስቃሴ ጀምሯል።
መነሻውን ከመስቀል አደባባይ ያደረገው ግብረ-ኃይል የኢዜማ ምክትል የፓርቲ መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌና የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በተገኙበት መሸኛ ተደርጎለታል።
ግንቦት 24 ቀንጉዞውን የጀመረው ግብረ ኃይል፣ በኢዜማ ለተደራጁ ለ216 የምርጫ ወረዳዎች ጊዚያዊ የእውቅና ደብዳቤ፣ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ደረሰኝ፣ የአባላት ፎርም እና የድርጅት ጉዳይ መመሪያዎቹን ተደራሽ ለማድረግ በአምስት አቅጣጫዎች ጉዞ ጀምሯል። በየመጀመሪያው ዙር ጉዞ ተደራሽ የሚደረግባቸው፡-
1. ከአዲስ አበባ – ደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ ወልዲያ መዳረሻውን ሰቆጣ
2. ከአዲስ አበባ – ፍቼ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ባህር ዳር አድርጎ መዳረሻውን ጎንደር
3. ከአዲስ አበባ – ሻሸመኔ፣ ሀዋሳ፣ ጌድኦ፣ አለታ፣ መዳረሻውን አዶላ (ክብረ መንግስት)
4. ከአዲስ አበባ – አምቦ፣ ነቀምት፣ ጊምቢ፣ ጅማ፣ መዳረሻውን ቤንች ማጂ
5. ከአዲስ አበባ – አዳማ፣ አሰላ፣ ወላይታ፣ ሀዲያ፣ ዳውሮ፣ ወልቂጤ፣ መዳረሻውን ጉራጌ በማድረግ ሲሆን በቀጣይም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሌሎች አዳዲስ ቦታዎችንና ከተማዎችን ተደራሽ የሚያደርግ ጉዞ እንደሚኖር ታውቋል።የሀገር መረጋጋትን ቀዳሚ ዓላማ አድርጎ የሚሠራው ኢዜማ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ አባላቱና ደጋፊዎቹ ይህንኑ ዓላማ ተፈፃሚ ለማድረግ እንዲሠሩ በሁሉም አቅጣጫ የሚጓዙት የግብረ ኃይሉ አባላት አፅዕንዎት ሰጥተው የሚያስገነዝቡ ይሆናል። በየአካባቢው የሚገኙ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም የየአካባቢው ሕዝብ ለግብረ -ኃይሉ አባላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉላቸው ጥሪ ተላልፏል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.