Home › Forums › Semonegna Stories › በኢትዮጵያ በስደት ላይ ለሚገኙ 150 ኤርትራውያን የከፍተኛ ትምህርት እድል ሊሰጥ ነው
Tagged: Eritrea, Scholarship
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years, 1 month ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 2, 2018 at 3:37 am #7830SemonegnaKeymaster
በ2010 ዓ.ም ወደ ከፍትኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ 280 ኤርትራውያን ስደተኞች የመግቢያ ፈተና እንዲወስዱ መደረጉንና በአሁኑ ወቅት ፈተናውን ያለፉ 150 ተማሪዎች መለየታቸውን አስረድተዋል።
አዲስ አበባ (ኢዜአ/UNHCR)፦ በኢትዮጵያ በስደት ላይ ከሚኖሩ ኤርትራውያን መካከል 150 ተማሪዎች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብተው የመማር ዕድል እንደሚያገኙ በኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር አስታወቀ።
በተያዘው ዓመት ሌሎች ቁጥራቸው ከ11ሺህ በላይ የሆኑ ህጻናት (የስደተኛ ኤርትራውያን ልጆች የሆኑ) የቅድመ መደበኛ ትምህርት ዕድል ማግኘታቸውም ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር (Ethiopia Administration for Refugee and Returnee Affairs/ ARRA) የሰሜን ጽህፈት ቤት የትምህርት ኦፊሰር አቶ ኤፍሬም ሀጎስ ለኢዜአ እንደገለጹት ከ180 ሺህ የሚበልጡ ኤርትራውያን ስደተኞች በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ ኤርትራውያን ስደተኞች መካከል 150 ተማሪዎች ዘንድሮ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በነጻ ለመማር እድል እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል።
ወደ ከፍትኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ 280 ስደተኞች የመግቢያ ፈተና እንዲወስዱ መደረጉንና በአሁኑ ወቅት ፈተናውን ያለፉ 150 ተማሪዎች መለየታቸውን አስረድተዋል።
ፈተናውን ያለፉ 150 ስደተኞችም በተለያዩ የኢትዮጵያ መንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉም ነው አቶ ኤፍሬም የገለጹት።
ኤርትራውያን ስደተኛ ተማሪዎች በኢትዮጵያ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መደረጉ በሁለቱ አገራት መካከል አሁን የተጀመረውን ሰላማዊ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረውም ተናግረዋል።
◌ ቪድዮ፦ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር እና የምጽዋ ወደቦችን ለመጠቀም ቅድመ ዝግጅቶችን እያጠናቀቀች ነው
የኢትዮጵያ መንግስት ለኤርትራውያን ስደተኞች የትምህርት ዕድል ሲሰጥ የአሁኑ ለሰባተኛ ጊዜ ሲሆን በየዓመቱ ከ100 ያላነሱ ተማሪዎችም የዕድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል።
በተመሳሳይ በትግራይ ክልል በሚገኙ አራት የኤርትራውያን ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ 11ሺህ 87 ኤርትራውያን በቅድመና በመደባኛ ትምህርት እንዲሁም በሙያ ክህሎት ማበልጸጊያ እንዲማሩ መደረጉን አቶ ኤፍሬም አክለው ተናግረዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ከአገራቸው ተሰደው ወደኢትዮጵያ ቢመጡም ልጆቻው እዚህ የትምህርት ዕድል በማግኘታቸው መደበኛ ትምህርታቸውን መቀጠላቸውን የተናገሩት ደግሞ በማይዓይኒ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙት አቶ ተስፋልደት ይህደጎ የተባሉ ስደተኛ ናቸው።
በአዲ ሓሩሽ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ሌላው ስደተኛዋ ወይዘሮ ለምለም ዘካሪያስ እንደተናገሩት በአካባቢያችን የሚገኙ ትምህርትቤቶች ለኤርትራውያን ተማሪዎች በራቸው ክፍት መሆኑ ትልቅ እድል መሆኑን ገልጸዋል።
“ልጆቻቸው ከኢትዮጵያውያን ወንደሞቻቸው ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲማሩ መደረጉ በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካከል ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት የላቀ አስተዋፅኦ አለው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለኤርትራውያን ስደተኞች እየሰጠ ያለው የከፍተኛ የትምህርት እድል ለሌሎች አገራት በመልካም አርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለማግባት የመግቢያ ፈተና የወሰደው ተማሪ ዓንዶም ፍሳሃየ ነው።
እስከ ግንቦት ወር 2010 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በአጠቃላይ 71,833 ኤርትራውያን ስደተኞች ትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ አራት መጠለያ ጣብያዎችና አፋር ክልል ውስጥ በሚገኙ ሁለት መጠለያ ጣብያዎች ውስጥ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) ዘግቧል።
ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR)
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.