ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለመቄዶንያ የአረጋውያንና አእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል 15 ዘመናዊ ዊልቸሮችን ለገሱ

Home Forums Semonegna Stories ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለመቄዶንያ የአረጋውያንና አእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል 15 ዘመናዊ ዊልቸሮችን ለገሱ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #8417
    Semonegna
    Keymaster

    ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ከሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የመቄዶንያ የአረጋውያንና አእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከልን ከጎበኙ በኋላ የ15 ዘመናዊ ባለሞተር ዊልቸሮችን ድጋፍ አድርገዋል።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታየቸው ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የአካል ጉዳተኞች መንቀሳቀሻ ወንበር (ዊልቸር/wheelchair) ድጋፍ አደረጉ።

    ቀዳማዊ እመቤቷ የ2011 ዓ.ም አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በማዕከሉ ለሚገኙ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን የምሳ ግብዣ ባደረጉበት ወቅት ባለቤታቸው ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ማዕከሉን እንደሚጎበኙ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።

    በመሆኑም ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ከሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ማዕከሉን ከጎበኙ በኋላ የ15 ዘመናዊ ባለሞተር ዊልቸሮችን ድጋፍ አድርገዋል። ድጋፉ የሚውለውም በማዕከሉ በከፋ የእንቅስቃሴ እክል ውስጥ ለሚገኙ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መሆኑ ተገልጿል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በችግር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ወገን ሲደገፉ ማየት ጥልቅ ሞራልና ተስፋ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። እውነተኛው አክሊል የሚገኘውም እንደዚህ ዓይነቱን ተግባር በመፈጸም ነው ሲሉም አሳስበዋል።

    “መናገር የማይችሉ እራሳቸውን መቆጣጠር የማይችሉ ሰዎችን የሚያየን ያየናል ብለው በንጹህ ልቦና ማገልገል መታደል ነው። እውነተኛው አክሊል የሚገኘው ከእንደዚህ አይነት ስፍራ ነው።እውነተኛውን የሚሹ ሰዎች ዝቅ ብለው መደገፍ የሚገባቸውን ሲደግፉ ሲያግዙ ማየት በኢትዮጵያ እንደዚህም አይነት ስራ የሚሰሩ ግለሰቦችን ማየት ጥልቅ ሞራል ተስፋ የሚሰጥ ነው።” በማለት ተናግረዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

    የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግና ሩህሩህ በመሆኑ ማዕከሉን በቀጣይነት እንደሚደግፍ እምነት እንዳላቸው የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ እርሳቸውም በተቻላቸው አቅም በማዕከሉ ያሉ አረጋውያንንና የአእምሮ ህሙማንን ለመጎብኘት ቃል ገብተዋል።

    “እኔ ልነግራችሁ የምፈልገው ነገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግ ህዝብ ነው። የማየት እድል ካገኘ ይህን የተቀደሰ ዓላማና ተግባር በመደገፍ ከጎናችሁ ሆኖ አልባሌ ቦታ የሚባክን ጉልበትና ሃብት ሰብስቦ እናንተን በማገዝ ከጎናችሁ በመሆን ቤተሰብ መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ሙሉ እምነት አለኝ ፤እኔም አቅሜ በፈቀደ መጠን እናንተን በመጎብኘት ከጎናችሁ እንደምሆን ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ።” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

    የማዕከሉ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ብንያም በለጠ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን በተለይም ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች የጠቅላይ ሚንስትሩን አርአያ በመከተል በማዕከሉ የሚገኙ ወገኖቻቸውን እንድጎበኙ ጥሪ አቅርቧል።

    ለመልካም ሥራ ጊዜ መስጠት እንደሚያስፈልግ በመጠቆም አቶ ብንያም፥ “የዶክተር አብይን አርአያ ተከትለን ዛሬ መጥተው በመጎብኘታቸው ማንም ሰው ከፈለገ ጊዜ እንዳለውና ለእግዚአብሔር ሥራ ጊዜ ሊያንሰው እንደማይገባ ስለአስተማሩን፤ ከእርሳቸው የበለጠ ጊዜ የሌለው ሰው የለም፤ ኢትዮጵያን የሚያህል አገር እየመሩ ጊዜ የለኝም ቢሉ ተቀባይነት አለው። እና ሁላችሁም የመንግስት ሠራተኞችም ብትሆኑ፣ ሚንስትሮችም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችም የእርሳቸውን አርአያ በመከተል ሰዎችን በመርዳት ከእግዚአብሔር ዋጋ እንድናገኝና በዚህ ውሸት በሞላበት ዓለም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለመግለጽ እወዳለሁ።” ብሏል።

    ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታየቸው ያደረጉት ድጋፍም ለማዕከሉ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አቶ ብንያም አክሎ ተናግሯል።

    የመቄዶንያ የአረጋውያንና አእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል አርባ አረጋውያንና አእምሮ ህሙማን በመያዝ የተቋቋመ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን፤ ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ወደ ሁለት ሺህ ለሚጠጉ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታየቸው

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.