በኦሮሚያ ክልል በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በአፋጣኝ ይቁም!!

Home Forums Semonegna Stories በኦሮሚያ ክልል በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በአፋጣኝ ይቁም!!

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #15035
    Anonymous
    Inactive

    በኦሮሚያ ክልል “ከአንድ ብሔር ተወላጅ ናቸው” በተባሉ ዜጎች ላይ ዘግናኝ ጥቃት መድረሱን ነዋሪዎች ተናገሩ ― የአሜሪካ ድምፅ

    በኢትዮጵያ የአንድ ብሔር ተወላጅ ናቸው በተባሉ ዜጎች ላይ በተነጣጠረ ጥቃት ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቁ ኢትዮጵያውያን በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ (ቪኦኤ) ገልፀዋል።

    በሌላ በኩል ጥቃቱ የተፈፀመው “ከአንድ ብሔር የመጡ ናቸው” የሚሉ ሰዎች ላይ በማነጣጠር ቢሆንም፥ ሕብረተሰቡ የተጋባና የተዋለደ በመሆኑ ተጎጂ ከሆኑት ውስጥ ከተለያየ ብሔር የተወጣጡ ሰዎች መሆናቸውን ነዋሪዎችም፣ የዞኑ አስተዳዳሪም ተናግረዋል።

    ሰኞ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት በአዲስ አበባ ገላን ኮንደሚኒየም አካባቢ ባልታወቁ ሰዎች የተገደለውን ዝነኛውን የኦሮሚኛ ቋንቋ ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች እጅግ አሰቃቂ በሆኑ ሁኔታዎች የተፈጸሙ ግድያዎች፣ አካል ማጉደል፣ ዘረፋና በከፍተኛ ሁኔታ ንብረት ማቃጠል መከሰቱንም ተጎጂዎችና የዓይን እማኝ መሆናቸውን የተናገሩ ለአሜሪካ ድምፅ (ቪኦኤ) ገልፀዋል።

    አንዳንዶቹ ግድያዎች በደቦ የተፈፀሙ ሲሆኑ፥ አንዳንዶቹ ግን በሰለጠኑ እና ተኩሰው በማይስቱ ታጣቂዎች የተፈፀሙ መሆናቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። የአሜሪካ ድምፅ ቤተሰቦቻቸው ፊት ለፊታቸው እደተገደሉባቸው የሚናገሩ፣ ንብረታቸው እንደተቃጠለባቸውና ያለ መጠለያ መቅረታቸውን የሚገልፁ በተለያዩ ከተማ የሚገኙ ወደ 20 የሚጠጉ ሰዎችን ያነጋገረ ሲሆን፥ በዛሬው ዕለት (ሰኔ 29 ቀን) በአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ ዴራ ከተማ እና አካባቢው የሚገኙ ከጥቃት ከተረፉት መካከል የተወሰኑትን አስደምጧል።

    በሌላ በኩል የአርሲ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ጀማል አልዩ በአርሲ ዞን ውስጥ እርሳቸው ከሚያስተዳድሯቸው 25 ወረዳዎችና ሦስት ከተሞች መካከል በስድስቱ ውስጥ በተፈፀሙ አሰቃቂ ግድያዎች የ34 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገፀዋል። ድርጊቱ በአካባቢው ከነበረው ፖሊስ አቅም በላይ እንደነበርና የፀጥታ አባል ጭምር መገደሉን አረጋግጠዋል። የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በተለያዩ ከተሞች ጥቃቶቹ መፈፀማቸውን አምነዋል።

    ድርጊቱ የተፈፀመው በሁለት ብሔሮች መካከል የተካረረ ፀብና ግጭት በመቀስቀስ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዓላማቸው ባደረጉ አካላት ነው ሲሉም ከግጭቱ ጀርባ ሌሎች ቡድኖች እንዳሉ ጥቆማ ሰጥተዋል። መንግሥት ይህንን በአስቸኳይ በመረዳት የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት አባላቱን ከክልል የፀጥታ ጥበቃ አባላት ጋር በማዋቀር የመከላከል ሥራ በመሥራቱ እንጂ ከዚህም የባሰ ጥቃት ይደርስ ነበር ሲል መንግሥት መግለጫ ሰጥቷል።

    የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር ግርማ ገላን እስካሁን የ145 ሰላማዊ ዜጎች እና የ11 የፀጥታ ኃይሎች ሕይወት በድምሩ የ156 ዜጎች ሕይወት ማለፉን አረጋግጠዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ደግሞ በአዲስ አበባ የሁለት የፀጥታ ኃይሎችና የስምንት ሲቪሎች በድምሩ የ10 ሰዎች ሕይወት ማለፉን አረግጋጠዋል። በአጠቃላይ ከመንግሥት የተገኘው መረጃ 166 ሰዎች በቦምብ፣ በጥይት፣ በድንጋይና በመሳሰሉት ሕይወታቸው ማለፉ ይጠቁማል።

    (ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ)

    ምንጭ፦ የአሜሪካ ድምፅ

    ከአንድ ብሔር ተወላጅ ናቸው በተባሉ ዜጎች ላይ ዘግናኝ ጥቃት

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.