“ከተሽከርካሪ ፍሰት ነፃ የሆኑ መንገዶች ቀን” – መንገዶችን በወር አንድ ቀን የእግር ጉዞና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጊያ

Home Forums Semonegna Stories “ከተሽከርካሪ ፍሰት ነፃ የሆኑ መንገዶች ቀን” – መንገዶችን በወር አንድ ቀን የእግር ጉዞና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጊያ

Viewing 2 posts - 1 through 2 (of 2 total)
  • Author
    Posts
  • #8877
    Semonegna
    Keymaster

    ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሽከርካሪ ነፃ የሆኑ መንገዶች ቀን በአዲስ አበባ እና በሌሎች የክልል ከተሞች የተመረጡ መንገዶችን ለሰዓታት ለተሽከርካሪዎች ዝግ በማድረግ እና በመንገዶቹም ላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን የማድረግ መርሃ ግብር ተካሄደ።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን (non-communicable diseases/ NCD) በተመለከተ ግንዛቤ ለማስጨበጥና የእግር ጉዞ ልምድን ለማበረታታትና ባህል ለማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶችን ለትራፊክ ዝግ በማድረግ (car free day) የጤናና አካል ብቃት ስፖርቶች ተካሄዱ።

    ህዳር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በመዲናዋ መንገዶችን ለትራፊክ ዝግ በማድረግ በተከናወነው የጤና የአካል ብቃት ስፖርቶች መርሃ ግብር የጤና ሚኒስትሩ አሚር አማን (ዶ/ር) እና የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስን ጨምሮ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የመንግሥት ባለስልጣናት እና ታዋቂ ግለሰቦች ተሳታፊ ሆነዋል።

    መርሃ ግብሩ በየወሩ የሚከናወንና በሌሎች የክልል ከተሞች የሚስፋፋ እንደሆነም ተጠቁሟል። በአዲስ አበባ የተጀመረውን መርሃ ግብር ተከትለው በዚሁ ዕለት ባህር ዳር፣ ጅማ፣ መቐለ፣ ሀዋሳ እና ጅግጅጋ “ከተሽከርካሪ ፍሰት ነፃ የሆኑ መንገዶች ቀን” በሚል ተመሳሳይ ዝግጅቶችን ማዘጋጀታቸውን ዶ/ር አሚር አማን በማኅበራዊ ገጻቸው አስታውቀዋል።

    በመዲናዋ መርሃ ግብሩ ሲከናወን የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አደባባዮችና ጎዳናዎች ዝግ ተደርገው ህብረተሰቡ በእግሩ እንዲጓዝ ተደርጓል።

    መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ሰለሞን ኪዳኔ የአዲስ አበባ መንገዶችን በወር አንድ ጊዜ የእግር ጉዞ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲደረግባቸው ለማስቻል እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል። በሚቀጥለው ዓመት 15 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ለእግረኛ እና ለብስክሌት መንቀሳቀሻ ምቹ መንገዶችን ለመስራት መታሰቡን ጠቁመዋል።

    በየወሩ መጨረሻ እሁድ በመላው አገሪቱ በእግር የመጓዝ ልምድን ለማበረታታትና ባህል ለማድረግ “ከተሽከርካሪ ፍሰት ነፃ የሆኑ መንገዶች ቀን” በሚል መሪ ሀረግ መንገዶችን ለትራፊክ ዝግ እንደሚደረጉ ለማወቅ ተችሏል።

    ህዳር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በተደረገው መርሃ ግብር በርካታ ቁጥር ያላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ የእግር ጉዞና የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል።

    ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችንና አጋላጭ መንስዔዎቻቸውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲቻል ህብረተሰቡ የመመርመር ልምዱን እንዲያሳድግም ጥሪ ቀርቧል። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እ.ኤ.አ የ2016 ዓ.ም. መረጃን/ውሂብን ተገን አድርጎ በ2018 ዓ.ም. ባወጣው የሀገራት ሪፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ ከሚሞተው ሰው 39 በመቶው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት እንደሆነ ያሳያል። ይህ አሀዝ በበሽታዎች ሲከፋፈልም፥ ከልብ ጋር የተያያዙ በሽታዎች (16 በመቶ)፣ የተለያዩ የካንሰር በሽታዎች (7 በመቶ)፣ ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዙ በሽታዎች (2 በመቶ) እና የስኳር በሽታ (2 በመቶ) ሲይዙ የተቀረው 12 በመቶ ደግሞ በሌሎች የተለያዩ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እንደሆነ ሪፖርቱ ያትታል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና የዓለም ጤና ድርጅት (WHO)

    ነፃ የሆኑ መንገዶች

    #9184
    Anonymous
    Inactive

    እሁድ ጥር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ሁለተኛው ዙር ከትራፊክ ፍሰት ነፃ መንገዶች ቀን (car free day) በአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ ሀዋሳ፣ ጅማ፣ መቀሌ፣ ጅጅጋ እና ድሬደዋ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

    የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር

Viewing 2 posts - 1 through 2 (of 2 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.