Home › Forums › Semonegna Stories › ከዴሞክራሲና ከነጻነት ጋር የተቆራኙ እሴቶች
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 6 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
May 30, 2019 at 6:10 pm #10976SemonegnaKeymaster
ከዴሞክራሲና ከነጻነት ጋር የተቆራኙ እሴቶች
(ነአምን ዘለቀ)ከዴሞክራሲና ከነጻነት መብቶች ጋር ተያያዥነት ያላቸው እሴቶችና ከእነዚህ ጋር የተገናኙ ንድፈ ሃሳቦች ከፍልስፍና አኳያ መነሻቸው አንዱ የሰው ልጅ ክቡርነትና የግለሰብ ሉዓላዊነት መከበር ጋር የተጋመዱና የተያያዙ መሆናቸው ነው። ዴሞክራሲም ሆነ ነጻነት የሰው ልጆችን ክብር፣ የእያንዳንዱን ሰው ሰብዓዊ ክቡርነት (dignity) ከልብ ካልተቀበለ፣ አንዱ ሌላውን ሰው እንደመጠቀሚያ፣ ለአንድ ግብ ማስፈጸሚያ መሣሪያ (means to an end/instrument) የሚመለከት ከሆነ፥ ለምሳሌ በፓለቲካም ሆነ በሌላ “እገሌን ለዚህ ጉዳይ ተጠቀምኩበት” እንደሚባለው ከሆነ ስር የሰደደ የእሳቤው፣ የእሴቶች፣ እንዲሁም የፍልስፍናው ግንዛቤ ላይ ከፍተኛ እጥረት አለ ማለት ነው። ይህንንም በጥልቀት በንድፈ ሃሳብ (theory)፣ እንዲሁም በጽንሰ ሃሳብ (concept) ደረጃ በጥልቀት ማወቅ ቢቻልም፣ ከልባችን ጋር አልተዋሃደም (internalized አልሆነም) ማለት ነው።
ሰዎችን የግብ ማስፈጸሚያ አድርጎ ማየት ብዙ ጊዜ የግራም ሆነ የቀኝ ርዕዮትን ያነገቡ በጣም ጨካኝና ጠቅላይ ከሆኑ (totalitarian) ርዕዮቶች/ፍልስፍናዎች ፣ የነዚህ ውላጅ ከሆኑ የፓለቲካ ስርዓቶችም የሚመነጭ ነው። በምዕራባውያኑ ዘንድ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በሰፊው የተጻፈበትና ልዩ ልዩ አመለካከቶች ያሉ ቢሆንም ከሊበራሊዝም አኳያ በርሊን፣ ከፕራግማቲዝም ሪቻርድ ሮርቲ (Richard Rorty)፣ ከሰብዓዊነት ላይ የተመሠረተ የማርክሳዊ ፍልስፍና አመለካከቶች እንደ ኤሪክ ፍሮም (Erich Fromm) እንዲሁም ሌሎችም ፈላስፎችና ሃያሲዎች የእነዚህ ጠቅላይ ርዮተ ዓለሞች ቅድመ መነሻ/መሠረት ከጥንታዊ ግሪክ ከፕሌቶ ፍልስፍና መሆኑን ተንትነውበታል። ነገር ግን የምዕራባዊ ስልጣኔና አካል ባልሆኑ፣ የእኛንም ማኅበረሰብ ጨምሮ ይህ አመለካከት በቅድመ ዘመናይ (pre-modern) ስርዓተ መንግሥታት የፓለቲካ፣ የባህልና ፣ ማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥም ሰፍኖ የነበረ መሆኑ ግልጽ ነው።
በርካታና እጅግ አንገብጋቢ ሃገራዊ ጉዳዮች ቢኖሩም ቅሉ፣ አንዱ የችግሮቻችን ምንጭ ከአስተሳሰብ ጋር፣ ከአመለካከቶች ጋር የተያያዙ ጎጂ የአስተሳሰቦችና እሴቶች (values) መሆናቸው ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። የሰው ልጅ ውስብስብ ፍላጎቶች ያለን ፍጥረቶች ነንና ወደ ውስጥ መመልከትና የትኛው ፍላጎት ለምን አላማ የሚለውን ራስን መሞገት ወደ ተሻለ በበጎ የሞራል እሴቶች ላይ የተመሠረተ የፓለቲካ ማኅበረሰብ ለማጠናከር የራሱ አስተዋጽኦ ያደርጋል። የፓለቲካ ጉዳይ ከስልጣን ጋር የተያያዘ መሆንና፣ በዴሞክራሲም ሆነ ዴሞክራሲያዊ ባልሆኑ የፓለቲካ ስርዓቶች ውስጥ ስልጣን (power) የሰው ልጆችን ‘ኮራፕት’ [corrupt] (በጥቅም ብቻ ሳይሆን ስልጣን ላይ ያሉትንም ሆነ ወደ ስልጣን የሚመጡትን ሰዎች የሞራል እሴቶን በማዳከም ጭምር) የማድረግ አቅሙ በጣም ከፍተኛ መሆኑ ቢታወቅም፥ ፍትህ፣ ዴሞክራሲና ነጻነት በሀገራችን እንዲመጣ ከልብ ከተፈለገ ደግሞ ከነዚህ ዓይነት አመለካከቶች ለመጽዳት መሞከር አንዱ የቤት ሥራ መሆን አለበት ማለት ነው።
የሰውን ልጅ ክቡርነት (dignity) ከልብ ማመን፣ ይህ እሴት እንዲዋሀደን ማድረግ፣ ለዲሞክራሲያዊ ባህል መስፈን፣ ፍትሃዊና ሰብአዊነት የነገሰበት ስርዓት እውን እንዲሆን ለማድረግ በጣም ወሳኝ ከሆኑ እሴቶች አንዱና ዋነኛው ነው። ቅዱሳን መጻህፍትም የሚሉት ‘በአንተ ላይ ሊደረግ የማትፈልገውን በሌላው ሰው ላይ አታድርግ’ ይመስለኛል። ፓለቲካው በርካታና አስፈላጊ የሞራልና የስነ-ምግባር እሴቶች ያስፈልጉታል የሚለው ዋናው ጭብጥ ነው – በተለይ በፓለቲካ ልሂቃን (political elites)። በቀጣይነት ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ይኖራሉ። በቸር ይግጠመን።
አቶ ነአምን ዘለቀን ፌስቡክ ገጻቸው ላይ ይከተሏቸው (Like ያድርጓቸው)፦ Neamin Zeleke
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.