ኩዊንስ ሱፐርማርኬት ዘመናዊ የሆነውን የኮልፌ ቀራኒዮ ፕላዛ ቅርንጫፍ ሱፐር ማርኬቱን አስመረቀ

Home Forums Semonegna Stories ኩዊንስ ሱፐርማርኬት ዘመናዊ የሆነውን የኮልፌ ቀራኒዮ ፕላዛ ቅርንጫፍ ሱፐር ማርኬቱን አስመረቀ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #11561
    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች አባል ኩዊንስ ሱፐርማርኬት እጅግ ዘመናዊ የሆነውን የቀራኒዮ ፕላዛ ቅርንጫፍ ሱፐርማርኬቱን አስፈላጊዎቹን ሕጋዊ መስፈርቶች አሟልቶ በማደራጀት ማክሰኞ ሐምሌ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ሁሉን በአንድ ባቀፈውና ማራኪ በሆነው በኮልፌ ቀራኒዮ ፕላዛ ቅጥር ጊቢው አስመረቀ።

    በዚሁ የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ባደረጉት ንግግር፤ በዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ደንቦችን መሠረት ባደረገ ዲዛይን የተሠራው፤ ኩዊንስ ሱፐርማርኬት አካሄዱም ለደምበኞች ቀላልና ምቹ የግብይት ሁኔታ ለማስፈን ትኩረት የሠጠ ነው ብለዋል።

    ሱፐርማርኬቱ በሚገኝበት በቀራንዮ ፕላዛ፣ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚ፣ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የነዳጅ ጣቢያ/ማደያና የተሽከርካሪ እጥበትና መለስተኛ ጥገና አገልግሎት መስጫ እና በትንሹ ከ150 በላይ መኪኖች ማቆሚያ፣ የእርሻ ምርቶች መሸጫ፣ ካፌና ሱቅ፣ ባንክ፣ እና ሁለገብ አዳራሽ መኖሩን የገለጹት ዶ/ር አረጋ፥ እነዚህ በአንድ አካባቢ መደራጀታቸው ደንበኞቹን በአንድ የንግድ ማዕከል በርካታ አገልግሎቶች እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑ፣ሱፐርማርኬቱን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

    ለኩዊንስ ኩባንያ መቋቋምና በዚህ ደረጃ መስፋፋት ምክንያት ለሆኑት ለሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀ-መንበርና ባለሀብት ለሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ በቅድሚያ ምስጋና ያቀረቡት ዶ/ር አረጋ፥ በዛሬው ቀን በመካከላችን ለተገኙት ወንድማቸው ለሼህ አብደላ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል።

    እንዲሁም፣ የቀራኒዮ ቅርንጫፍ ፕሮጀክት በዚህ ለገበያ አመቺ በሆነ ቦታ እንዲገነባ ለረዱን የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እና የሚመለከታቸው ሠራተኞች፣ በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች፣ መብራት ኃይል፣ የቴሌፎንና የውሃ ተቋማት፣ የአዲስ አበባ የመንገድ ሥራዎች ተቋም፣ የአካባቢው የፖሊስ እና የፀጥታ ኃላፊዎች እና ሌሎችም ላደረጉልን መተባበር ከፍተኛ ምስጋና አቅርባለሁ ብለዋል።

    ዶ/ር አረጋ በዚሁ ንግግራቸው፥ የኩዊንስ ቀራኒዮ ቅርንጫፍ ፕሮጀክት ለቅድመ መደበኛ አገልግሎት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ፣ ለሥራ ማስኬጃ እና ለሽያጭ የሚያገለግሉ ዕቃዎች (መደርደሪያዎች፣ ማቀዝቀዣዎች፣…) ግዢ፣ የሲስተም ዝርጋታ ወጪን ጨምሮ፣ ለሸቀጣ ሸቀጥ አቅርቦት ጠቅላላ ወጪ 59.3 ሚሊዮን ብር መሆኑን አስረድተው፤ ሕንፃው በ37.7 ሚሊዮን ብር ወጪ መገንባቱንና የኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ ንብረት በመሆኑ፣ ኩዊንስ በኪራይ እንደሚገለገልበት አስታውቀዋል።

    የሪቴል ግሩፕ ፕሪንሰፓል ኦፕሬሽን ኦፊሰር ወ/ሮ ታህሳሥ ወንድምነህ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ኩዊንስ ሱፐርማርኬት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበር ሰኔ 25 ቀን 2002 ዓ.ም. 46 ቋሚ እና 5 ኮንትራት፣ በድምሩ 51 ሠራተኞች በመያዝ የተቋቋመ መሆኑን አስታውሰው፥ ኩባንያው የአግሮ ኢንዱስትሪ ውጤቶችን (የዶሮ፣ የወተት እና የሥጋ ተዋጽዖዎችን)፣ የእርሻ ምርቶችን (ሰብሎች፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ እና አበባዎች)፣ የባሕር ምግቦች (ዓሣ)፣ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች (ሣሙና….) የታሸጉ ምርቶች፣ መጠጦች እና ሌሎች የፋብሪካ ውጤቶችን (የጽሕፈት መሣሪያዎችን፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን እና የቤት ውስጥ የመገልገያ ዕቃዎች) በችርቻሮ እና በጅምላ በመሸጥ እና በማከፋፈል ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

    ወ/ሮ ታህሳሥ በዚሁ ንግግራቸው፤ ኩባንያው በአሁኑ ጊዜ የካፒታል መጠኑ ወደ ብር 23,786,000፣ የሠራተኞቹ ብዛት ወደ 142 (132 ቋሚ እና 10 ኮንትራት) ማደጉን አመልክተው፤ ዓመታዊ ሽያጩም ሥራ ሲጀምር ከነበረው ከብር 12,192,000 ወደ ብር 157,000,000 ማደጉን አሰታውቀዋል።

    አያይዘውም ኩባንያው ቅርንጫፎቹን ወደ ሰባት በማሳደግ ጥራት ያላቸውን ምርቶች በበቂ ሁኔታ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ እና ተጨማሪም አንድ የዳቦ ማምረቻና መሸጫ በመቻሬ ቅርንጫፍ በማቋቋም ለሠራተኞችና ለኀብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን አስረድተው፤ ሱፐርማርኬቱ ለ50 ተጨማሪ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንና ዓመታዊ ሽያጩም ብር 75,000,000 እንደሚሆን፤ የኩባንያውን ዓመታዊ የሽያጭ መጠንንም በግማሽ በማሳደግ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ አሰታውቀዋል።

    ወ/ሮ ታህሳሥ ለኩዊንስ ኩባንያ መቋቋምና በዚህ ደረጃ መስፋፋት ምክንያት ለሆኑት ለሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀመንበርና ባለሀብት ለክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ፣እንዲሁም፣ የቀራኒዮ ቅርንጫፍ ፕሮጀክት በዚህ ለገበያ አመቺ በሆነ ቦታ እንዲገነባ የፕሮጀክት ሀሳብ በማቅረብ፣ አስፈላጊውን በጀት በመመደብ፣ በፕሮጀክቱ ሂደትም ያልተቋረጠ የዕለት ተዕለት ክትትል በማድረግ፣ የቅርብ አመራር በመስጠት እና አቅጣጫ በማስያዝ ፕሮጀክቱ በአጥጋቢ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ላበቁት ለዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር እና ፕሬዚዳንት፤ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

    በዚሁ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለፕሮጅክቱ መሳካት አሰተዋጽኦ ያበረከቱ ድርጅቶችና ግለሰቦች፤ የተዘጋጀላቸውን ሠርቲፊኬት ከዕለቱ የክብር እንግዳ ከሼህ አብደላ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ እጅ ተቀብለዋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ፤ የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ ተወካይና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ አመራሮች፣ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ደንበኞች በተገኙበት ተካሂዷል።

    ምንጭ፦ ሚድሮክ ኢትዮጵያ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    ኩዊንስ ሱፐርማርኬት


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.