Home › Forums › Semonegna Stories › የወሎ ዩኒቨርሲቲ የደሴ ግቢ ተማሪዎች የአቋም መግለጫ
Tagged: ወሎ ዩኒቨርሲቲ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years ago by Semonegna.
Viewing 1 post (of 1 total)
-
AuthorPosts
-
November 22, 2019 at 1:21 pm #12747SemonegnaKeymaster
የወሎ ዩኒቨርሲቲ የደሴ ግቢ ተማሪዎች የአቋም መግለጫ
ደሴ (ወሎ ዩኒቨርሲቲ) – አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ምድረ ቀደምት ከሚባሉት ጥቂት ሃገራት አንዷ መሆኗ ኣሌ የማይባል ሃቅ ነው። በየዘመናቱ የመጡ ወራሪዎችን መክታና አሳፍራ በመመለሷ ከአፍሪካ በቅኝ ግዛት ካልተገዙ ሁለት ሃገራት አንዷ ነች። የዚህ ዋናው ሚስጢሩ የጥንት አባቶቻችንና እናቶቻችን በዘር፣ በጎጥ፣ በሃይማኖትና ሌሎች ልዩነቶች ሳይከፋፍሉ በአንድነት በመንቀሳቀሳቸው ነው። ነገር ግን ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ጀምሮ ለኢትዮጵያ ሃገራችን እድገትና ብልጽግና ጸር የሆኑ አካላት የውስጥ ጥቅመኞችንና ሆድ-አደሮችን በመያዝ አገራችንን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ ሌት ከቀን መሥራት ከጀመሩ ውለው አድረዋል::
በዚህ መጥፎ ተግባር ሕይወታቸውን እያጡ ላሉ ወገኖቻችን ነብስ ይማር እያልን ይህ መጥፎ ተግባር በአስቸኳይ ይቆም ዘንድ የሚከተለውን ባለ 8 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል።
- ዩኒቨርሲቲዎች የዕውቀት ማዕድ የሚቀርብባቸው የምርምርና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከላት በመሆናቸው የብጥብጥ ቀጠና ለማድረግ የሚደረገውን እንቅስቃሴ አጥብቀን እናወግዛለን፣
- እኛ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዓለም-ዓቀፍ እውቀታችን እንዲጎለብትና እንዲሰፋ በአዕምሮ ልማት ላይ የማይነጥፍ ድጋፍን እንጂ በብሔር፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ ልዩነት እርስ በርስ ሊያፋጁን የሚጥሩትን መንግሥት ከጐናችን ሆኖ እርምጃ እንዲወሰድልን እንጠይቃለን።
- በርካታው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት በተለያየ ምክንያት ወደ ሰሜን፣ ደቡብ ምዕራብ እና ምሥራቅ ሲንቀሳቀስ የቆየ በመሆኑ እንደሰርገኛ ጤፍ ለመለየት በማይቻልበት መልኩ ተዋሕዶና ተጋምዶ የሚገኝ በመሆኑ ሊከፋፍሉን ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቆይቷል። ከተወሰኑ ዓመታት ጀምሮ ከፍተኛ ተቋማት ውስጥ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ማዕከል ተደርጐ እየተሠራ በመሆኑ በየዓመቱ ሕይወታቸው እየተቀጠፈ ያሉ ንፁሃን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየተበራከተ መጥቷል። ይህንን መጥሮ ተግባር እኛ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወዘተ… ሳንከፋፈል በአንድነት ቁመን እንድንጓዝ ጥሪ እናስተላልፋለን።
- የእምነት ተቋማት የአምልኮ ቦታ ብቻ ሳይሆኑ ለረዥም ዘመናት የዕውቀት፣ የምርምር፣ የፈጠራ፣ የፍልስፍና እና የጥበብ ማዕከላት በመሆናቸው የታሪካችንና ማንነታችን አሻራዎች በመሆናቸው ቤተ እምነቶትን ማቃጠል፣ ማፍረስ፣ መዝረፍ እንዲሁም አገልጋዮቻቸውን እጅግ ኢ-ሰብዓዊና ሰይጣናዊ በመሆነ መልኩ መግደል የተለመደ እየሆነ መጥቷል። ይህ ዘግናኝ ተግባር ለእኛ የሃገር ተረካቢዎች የአዕምሮ ጠባሳ በመሆኑ መንግሥት ከእኛ ጋር በመሆን በአስቸኳይ እንዲያስቆምልን ጥሪ እናስተላልፋለን።
- ለፀጥታ አካላት – አለመታደል ሆነና ጠረፍና ዳር ድንበር መጠበቅ የነበረባቸው ቢሆንም እነሆ በዩኒቨርሲቲዎች ተበትነው እየጠበቁን ይገኛሉ። ለዚህ መልካም ተግባራቸው እያመሰገን ለቀጣይ ግን ተቋማት እራሳቸውን ችለው ፀጥታቸውን እንዲያስከብሩ የስልጠናና የሙያ ድግፍ በማድረግ “አሳን ማብላት ሳይሆን አሳን እንዴት ማጥመድና መብላትን” እንድታስተምሩን እንጠይቃለን!
- በወሎ ዩኒቨርሲቲ የኮምቦልቻ ግቢ አጣልቶ- እና አጋጭቶ-አደሮችን አንሰማም በማለት ግቢያችሁን ከአካባቢው ማኅበረሰብ፣ የፀጥታ ኃይል፣ መምህራንና ሰራተኞች ከላይ እስከታች ካለው የውስጥም የውጭም አመራር ጋር በመሆን በተለይም ሁሉም ተማሪና የተማሪ አመራሮች በአንድ በመሥራታችሁ በዚህ መልካም ተግባራችሁ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ በጐነትን፣ መልካምነትንና አርዓያነትን ማድነቅ ስለሚገባን በእናንተ የኮራንና የእናንተን ፈለግ ለመከተል ቃል እንገባለን።
- በተፈጠረው ግጭት ፈርታችሁ ወደ ቤተሰብ የሄዳችሁ ተማሪዎች እንዲሁም ይህን ግጭት ለተራ ፖለቲካዊ ትርፍ ለመጠቀም ባሰቡ አካላት ተቀስቀሳችሁ ከግቢ የወጣችሁ ተማሪዎች እስከ ሰኞ ህዳር ኅዳር 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ወደ ትምህርት ገበታችሁ ትመለሱ ዘንድ ጥሪ እናስተላልፋለን።
- በመጨረሻም ይህንን ችግር ለመፍታት ሌት ከቀን ደከመን ሰለቸን ሳትሉ እልባት እንዲያገኝ ለጣራችሁ የደሴ እናቶች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የጸጥታ አካሎች እንዲሁም ተማሪዎች በጣም እናመሰግናለን። በዚህ አጋጣሚ ለወደፊቱም የዘወትር ድጋፋችሁንና ምክራችሁን አትለዩን እያልን ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ከነአንድነታቸው አጥብቆ ይባርክ እንላለን።
እናመሰግናለን።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ የደሴ ግቢ ተማሪዎች -
AuthorPosts
Viewing 1 post (of 1 total)
- You must be logged in to reply to this topic.