Home › Forums › Semonegna Stories › የልዑል አለማየሁ አፅም ወደ እናት ሀገሩ እንዲመለስ ተጠየቀ
- This topic has 1 reply, 1 voice, and was last updated 5 years, 10 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
March 22, 2019 at 5:17 pm #10375SemonegnaKeymaster
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የአጼ ቴዎድሮስ ልጅ የልዑል አለማየሁ አፅም ከሀገረ እንግሊዝ ወደ እናት ሀገሩ እንዲመለስ ኢትዮጵያ ተጠየቀ። በተጨማሪም ለንደን ከተማ ውስጥ በቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም (Victoria and Albert Museum) የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥያቄ ቀርቧል።
በኢፌዴሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው የተመራው የልዑካን ቡድን መጋቢት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በለንደን ጉብኝት አድርገዋል።
በዚሁ ወቅትም በለንደን የዊንዶዘር ቤተመንግስት (Windsor Castle) የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስን መካነ መቃብር እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አፄ ሃይለስላሴ ይጸልዩበት የነበረውን ወንበር ጎብኝተዋል።
ዶ/ር ሂሩት ካሳው በአጼ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል አለማየሁ መቃብር ላይ የአበባ ጉንጉን ማስቀመጣቸውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን እንደመረጃ ምንጭነት በመጥቀስ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
በጉብኝቱ ወቅትም “የአጼ ቴዎድሮስን ፀጉር ማግኘታችን ደስ ብሎናል፤ ይሁን እንጂ ከትውልድ ቦታው ተለይቶ ህይወቱ ያለፈው ልዑል አለማየሁ አፅም በትውልድ ሀገሩ እንዲያርፍ የኢትዮጵያዊያን ጥያቄ ስለሆነ በክብር ወደ አገሩ እንዲመለስ” ሲሉ ዶክተር ሂሩት ጠይቀዋል።
አፅሙ ወደኢትዮጵያ ተመልሶ ከአባቱ አጼ ቴዎድሮስና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መቀላቀል እንደሚገባውና የዊንዶዘር ቤተመንግስት ለሚመለከተው አካል ጥያቄውን አቅርቦ በአፈጣኝ ምላሽ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል።
በዕለቱ ልዑካን ቡድኑን በመቀበል ከቡድኑ ጋር የተወያዩት የዊንዶዘር ቤተ-መንግስት ሃላፊ ዶ/ር ማርክ ፓወል በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንነጋገርበታለን ብለዋል። ሂደቱን በተመለከተ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመከታተል እልባት እንዲያገኝ አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርግም ሚኒስቴሩ ተገልጿል።
በሌላ በኩል የልዑካን ቡድኑ መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ለንደን የሚገኘውን የቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም ጎብኝቷል። በዶ/ር ሂሩት ካሳው የተመራው የልዑካን ቡድኑና በለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሙዚየሙ ዳይሬክተር ዶ/ር ትሪስታራም ኸንት (Tristram Hunt, PhD) ጋር ተወያይቷል። በውይይቱ ወቅት በቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም የሚገኙ የመቅደላ ስብስብ ቅርሶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥያቄ ቀርቧል።
እ.አ.አ በ2018 የቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም የሚገኙ የመቅደላ ስብስብ ቅርሶች ለኢትዮጵያ መመለስ እንደማይችል፤ ነገር ግን በረጅም ጊዜ ውሰት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚቻል መገለጹ ይታወቃል። የሙዚየሙ ዳይሬክተር ዶ/ር ትሪስታራም ኸንት ጥያቄው ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው ውሰት የሚለው ቃልም ለኢትዮጵያውያን ከባድ መሆኑን እንደተረዱት ተናግረዋል። በመሆኑም “የተቸገሩት ጉዳዩ የሕግ ጉዳይ በመሆኑና ምላሽ ለመስጠት ያለን አማራጭ ይህ ብቻ ስለሆነ ነው ” ብለዋል።
“ያለን አማራጭ ይህን ቀዳዳ በመጠቀም ሊስተካከሉ የሚችሉ አባባሎችን ተጠቅመን የሚመለሱበትን ሁኔታ መፍጠር፤ ይህን ካላደረግን ግን በሕጉ ላይ ጸንተን ወደፊት የሚሆነውን ነገር መመልከት ይኖርብናል” ሲሉም ዶ/ር ኸንት አክለዋል።
የባህል ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ቅርሶቹ የኢትዮጵያ በመሆናቸው በረጅም ጊዜ ውሰት ሳይሆን በቋሚነት ቅርሶቹ ለኢትዮጵያ መመለስ የሚችሉበት አማራጭ መፍትሄ ሙዚየሙ ሊያበጅ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በኤምባሲውና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል በአስቸኳይ መግባቢያ ሰነድ በመፈራረም፣ ካለው ሕግ ጋር በማይጋጭና የኢትዮጵያን ጥያቄ ሊመልስ በሚችልበት ሁኔታ በመንቀሳቀስ ጉዳዩ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት እልባት እንደሚያገኝ ዳይሬክተሩ ገልጸፀዋል።
በለንደን ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ባለው ሙሉ አቅምና ጊዜ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በመወጣት ቅርሶቹ ወደ አገራቸው እንዲገቡ እንደሚያደርጉ በብሪታኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍስሃ ሻወል ገብሬ ገልጸዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
March 23, 2019 at 12:25 pm #10387SemonegnaKeymasterበቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም የሚገኙ የመቅደላ ስብስብ ቅርሶች በአጭር ጊዜ ሊመለሱ ይችላሉ
—–ለንደን የሚገኙ ቅርሶች የሚያዙበት ሁኔታና የሚተዳደሩበት ሕግ በጣም ጠንካራ ነው። በየትኛውም አጋጣሚ እጃቸው ላይ የገባ ቅርስ በሕጉ መሠረት ይተዳደራል። ስለሆነም የእኛም ቅርሶች የዚሁ አካል ናቸው ማለት ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ቅርሶች ለኢትዮጵያውያን የማንነትና የእድገት መሠረቶች ናቸውና ሊመለሱልን እንደሚገባ በተደጋጋሚ ሲጠየቁ ቆይተዋል።
እ.ኤ.አ በ2018 ከወደ ቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም ብቅ ያለው መረጃ በረጅም ጊዜ ውሰት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚቻል ገለጸ። የማንን ቅርስ ማን አበዳሪ? ማንስ ተበዳሪ? እንዴት አይነት ድፍረት ነው?ወዘተ… ብለን ተቆጨን። እነሆ የይመለሱልን የሕዝብ ጥያቄው በክብርት ዶ/ር ሂሩት ካሳው (የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር)፣ በልዑካን ቡድኑና በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ቅርሶቹ ተጎበኙ፤ ጥያቄውም ቀረበ ሰፊ ውይይትም ተደረገ። ዳይሬክተሩ ዶ/ር ትሪስትራም ኸንት /Tristram Hunt/ ጥያቄው ተገቢ መሆኑን ‘ውሰት’ የሚለው ቃልም ለኢትዮጵያውያን ከባድ መሆኑን እንደተረዱት በመግለጽ የተቸገሩት የሕግ ጉዳይ በመሆኑና ምላሽ ለመስጠት ያለን አማራጭ ይህ ብቻ ስለሆነ ነው አሉ። አክለውም ያለን አማራጭ ይህን ቀዳዳ በመጠቀም ሊስተካከሉ የሚችሉ አባባሎችን ተጠቅመን የሚመለሱበትን ሁኔታ መፍጠር ይህን ካላደረግን ግን በሕጉ ላይ ጸንተን ወደፊት የሚሆነውን ነገር መመልከት ይኖርብናል ብለዋል። በመቀጠልም ከክብርት ሚንስትሯም የተለያዩ ማሳመኛ ምክንያቶች ከቀረቡ በኋላ በሙዚየሙ፣ በኤምባሲውና በሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል ጊዜ ሳይሰጠው በአስቸኳይ መግባቢያ ሰነዱን ካለው ሕግ ጋር በማይጋጭና የኢትዮጵያን ጥያቄ ሊመልስ በሚችልበት ሁኔታ ሠርተን በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት እልባት እንደሚያገኝ ዳይሬክተሩ ገልጸው ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በፈጣንና ታታሪ አመራሮችና ባለሙያዎች የተደራጀው ኤምባሲም ባለው ሙሉ አቅምና ጊዜ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በመወጣት ቅርሶቹ ወደ አገራቸው እንዲገቡ እንደሚያደርጉ ሃላፊነቱን መቀበላቸውን ክቡር አምባሳደሩ ፍሰሃ ሻወል ገልጸዋል።
ምንጭ፦ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.