Home › Forums › Semonegna Stories › የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘላቂ የሆነ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር በአንድነት ለመሥራት ቃል ገቡ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
November 26, 2018 at 1:06 am #8676SemonegnaKeymaster
ድሬ ዳዋ (ሰሞነኛ)– የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘላቂ የሆነ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር በአንድነት ለመሥራት ቃል ገቡ። ከሰሞኑ ግጭት ውስጥ የገቡ ተማሪዎች የሀይማኖት አባቶችና ከፍተኛ የመንግስት አካላት በተገኙበት ዕርቅ አውርደዋል።
ሰሞኑን ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ባልተከሰተና በሀሰት በተሰራጨ መረጃ ምክንያት በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ዳግመኛ እንዳይከሰት ተማሪዎቹ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉና በተማሪዎች መካከል የሚፈጠሩ የግለሰብ ግጭቶችንም ወደ ቡድንና የብሄር ግጭትነት ለመቀየር የሚፈልጉ አካላትን ጥረት እንደሚያወግዙ ተናግረዋል።
ኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ስልጠና ማዕከል ውስጥ በተካሄደው የእርቅ ዝግጅት ላይ የተሳተፉ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት፥ ተማሪዎችን በብሄር እንዲጋጩ ሁኔታዎችን በሚፈጥሩና በሚያነሳሱ ተማሪዎችና አገልግሎት ሰጪ አካላት ላይ ዩኒቨርሲቲው ክትትል አድርጎ አስተማሪ እርምጃዎችን በመውሰድ የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር ጠይቀዋል።
ከየትኛውም ብሄር ጥሩ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ መጥፎዎችም ሊኖሩ እንደሚችሉና እነዚህ ሰዎች በዩኒቨርሲቲያችን ውስጥ የእኩይ ተግባራቸውን ለማስፈፀም ብሄራቸውን ሽፋን በማድረግ ለመጠቀም ስለሚሞክሩ ተማሪዎች ተሳስተው የወንጀለኞች ተባባሪና የእኩይ ተግባራት ማስፈፀሚያ እንዳይሆኑ መረጃዎችንና ሁኔታዎችን ከስሜት በጸዳና በምክንያታዊነት እንዲመለከቱ የመድረኩ ተሳታፊዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።
◌ These two Ethiopian students are working to launch their own rocket – the future Eng. Kitaw Ejigu
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ባለፉት ዓመታት በአንድነት ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ እንደነበርና በመካከላቸውም አለመስማማቶች ሲፈጠሩ በራሳቸው መንገድ ተወያይተው ችግሮችን ሲፈቱ እንደነበር አስታውሰው ዘንድሮም ይህን አንድነታችንን በማስጠበቅ በመካከላችን ልዩነቶችን በመፍጠርና ግጭት እንዲቀሰቀስ በማነሳሳት የድብቅ ሴራቸው ማስፈፀሚያ ሊያደርጉን የሚፈልጉ አካላትን ሴራ እናከሽፋለን ብለዋል። ባለፉት ጥቂት ቀናት መለስተኛ ግጭት በመፈጠሩ ይቅርታ የተጠያየቁት ተማሪዎች አጋጣሚውን ለቀጣይ በመማሪያነት በመውስድ ችግሮችን በጋራ ለመከላከል እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል።
የአማራ ክልልንና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (አዴፓ) ወክለው የተገኙት አቶ ባዘዘው ጫኔ እንደተናገሩት ችግሩ በመፈጠሩ የአማራ ክልልና የክልሉ ገዢ ፓርቲ አዴፓ ማዘኑን ገልፀው ግጭቱ ሳይሰፋና የከፋ ችግር ሳያስከትል በቁጥጥር ስር እንዲውል የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ተማሪዎች እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ አካላት ላደረጉት ጥረት ደግሞ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሰዎች በብዛት ተሰባስበው በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ግጭት ሊከሰት እንደሚችል አቶ ባዘዘው አስታውሰው በግለሰቦች የሚጀመር ግጭትን ወደብሄር ማዞሩ አደገኛና ሊወገዝ የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል። በሐረማያ ዩኒቨርሲቲም ሰሞኑን በተከሰተው ግጭት በርካታ ተማሪዎች ጉዳዩን በማውገዝ ወደ ግጭት ባለመግባታቸው ቶሎ በቁጥጥር ስር እንዲውል እንዳስቻለ የተናገሩት አቶ ባዘዘው ተማሪዎች በአንድነት ተሳስቦ በፍቅር የመኖር ልማዳቸውን በማጎልበት የዩኒቨርሲቲያቸውንና የአካባቢያቸውን ሰላም እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።
የኦሮሚያ ክልልንና የክልሉ ገዢ ፓርቲ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (ኦዲፓ) ወክለው የተገኙት አቶ አብዱላዚዝ መሀመድ ባደረጉት ንግግር ተማሪዎቹ እርቅ ለማውረድ ያሳዩትን ፍላጎት አድንቀዋል። አቶ አብዱላዚዝ አያይዘውም ባለፉት ሰባት ወራት መንግስት ለዓመታት የተከማቹ የሕዝብ ጥያቄዎችን በመፍታት ላይ እንደሚገኝና በዚህም ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ በመሆኑ ይህን ለውጥ የማይፈልጉ አካላት የመንግስትን የለውጥ ጉዞን ለማደናቀፍ በየቦታው ግጭቶች እንዲነሱ በማድረግ መንግስትን ግጭቶችን በመከላከል ላይ እንዲጠመድ በማድረግ የተጀመሩ የለውጥ ጉዞዎችን ለማደናቀፍ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።
ስለዚህ የነገዋ ባለተስፋና የዜጎቿ መኩሪያ የሆነች ኢትዮጵያን ተረካቢ የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ይህን ተረድተው ራሳቸውን ከስሜታዊነት አርቀው፣ መረጃዎችን በጥንቃቄ በመመርመር ምክንያታዊ በመሆን ግጭቶች እንዳይከሰቱ ጥረት እንዲያደርጉና ከግጭቶች በመራቅ የእኩይ ተግባር ማስፈፀሚያ ከመሆን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አቶ አብዱላዚዝ ለተማሪዎች ጥሪ አቅርበዋል።
በሀገራችን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተሻለ አስተሳሰብ ያላቸው ወጣቶች የሚገኙበት እንደሆነ እንደሚታመን የተናገሩት የሳይንስና የከፍተኛ ትምህር ጉዳዮች ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ጌታቸው ነጋሽ በአስተሳሰባችሁ መላቃችሁንና ማኅበረሰባችን የሰጣችሁን ይህን ግምት ትክክለኛነት ለማሳየት ምክንያታዊ በመሆን ለነገሮች መፍትሄ በመስጠት ልታስመሰክሩ እንጂ እንደዘይትና ውሃ የተፈጠራችሁበት ነገር ሳይለያይ በብሄር ልትከፋፈሉና ልትጋጩ አይገባም ብለዋል።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ፕሬዝዳንት ጀማል ዩሱፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው ተማሪዎች በብሄር ከማሰብ ወጥተው አንድነት ላይ በማተኮር የዩኒቨርሲቲውን ሰላም በጋራ በማስጠበቅ በቂ ዕውቀት ጨብጠው በሀገራችን የእድገት ጉዞ ላይ የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉና ራሳቸውን የጥፋት ኃይሎች ድብቅ ዓላማ አስፈፃሚ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዳይኖር እንቅፋት ይፈጥራሉ በማለት በተማሪዎች በቀረቡ ጥቆማዎች ላይም አስፈላጊውን ክትትል ግምገማ በማድረግ የእርምት እርምጃዎችና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራዎች እንደሚከናወኑ ዶ/ር ጀማል አረጋግጠዋል።
በእርቅ መድረኩ ላይ የተሳተፉ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም በተማሪዎች መካከል ሰላም፣ ፍቅርና ይቅር ባይነት እንዲጎለብት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል።
ምንጭ፦ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ (HU FM 91.5 RADIO)
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.