Home › Forums › Semonegna Stories › በዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር አጠቃላይ ማህበረሰቡ ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በጋራ እንዲሠራ ተጠየቀ
Tagged: Assosa University, ሂሩት ወልደማርያም, አምቦ ዩኒቨርሲቲ, አሶሳ ዩኒቨርሲቲ, የመማር ማስተማር, የሰላም ፎረም
- This topic has 1 reply, 2 voices, and was last updated 5 years, 11 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
November 21, 2018 at 9:07 am #8621SemonegnaKeymaster
ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በአማራ እና በኦሮሞ ብሄር ተማሪዎች መካከል በተነሳው ግጭት የሶስት ተማሪዎች ህይወት ማለፉን ገልፀው፥ የተለየ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች በተማሪዎች መካከል የብሄር ግጭት እንዲነሳ በማድረግ የመማር ማስተማር ሂደቱን ከማስተጓጎል በላይ ለስው ህይወት መጥፋት ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል።
አዲስ አበባ (የትምህርት ሚኒስቴር) – በዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር አጠቃላይ ማህበረሰቡ ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በጋራ እንዲሠራ ተጠየቀ።
በአሁኑ ወቅት በመላ ሃገሪቱ እየተካሄደ የሚገኘውን ለውጥ ለመቀልበስ የሚፈልጉ ኃይሎች ፊታቸውን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በማዞር ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን በማወክና ግጭቶች እንዲፈጠሩ በማድረግ ግጭቶቹም የብሄር ግጭት መልክ እንዲይዙ በማድርግ ከፍተኛ ሁከት እና አለመረጋጋት በዩኒቨርሲቲዎች እንዲቀሰቀስ እያደረጉ መሆኑ ተደርሶበታል።
ይህንኑ ሰሞኑን በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የተከሰተውን አለመረጋጋትና ሁከት አስመልክቶ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም ኅዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም በፅህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ “ዩኒቨርሲቲዎች ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የተለያየ አስተሳሰብና ክህሎት ያላቸው ወጣቶች የተሰባሰቡበት ቦታ መሆኑን ገልፀው፥ እነዚህን ወጣቶች ለተለያየ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ ለማድረግና እርስ በእርሳቸው ያለመተማመንና በመካከላቸውም የብሄር ግጭት በማስነሳት የመማር ማስተማር ሥራውን ከማስተጓጎላቸውም በላይ በግጭቱ ውድ የሆነውን የሰው ህይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆነዋል“ ብለዋል።
ዶ/ር ሂሩት አያይዘውም ሰሞኑን በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በአማራ እና በኦሮሞ ብሄር ተማሪዎች መካከል በተነሳው ግጭት የሶስት ተማሪዎች ህይወት ማለፉን ገልፀው፥ በግጭቱ ህይወታቸውን ላጡ ውድ ተማሪዎቻችን የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልፀው ለተማሪ ቤተሰቦችና ለማህበረሰቡ መፅናናትንም ተመኝተዋል።
አሁን የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታትም ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፤ የዩኒቨርሲቲ ቦርድ አባላት፤ የሁለቱም ብሄር ተወካዮችና ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር በመሆን የዕርቅና ሰላም የማስፈን ሥራ ለመሥራት ወደ ዩኒቨርሲቲው እንደሚሄድ ሚኒስትሯ ጨምረው ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች የዕውቀት የክህሎትና የአዳዲስ ሃሳቦች ማፍለቂያ ተቋሞች መሆናቸውን የገለፁት ሚኒስትሯ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ሙሉ ጊዜያቸውን ለትምህርትና ለምርምር በማዋል የመጡበትን ዓላማ ማሳካትና በቆይታቸውም ነገሮችን በደንብ የሚያስቡና አንዳንድ ወደ ጥፋት የሚሄዱ ተማሪዎችንም ወደ በጎነት የሚመልሱ ሊሆኑ እንደሚገባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምቹና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር የአካባቢው ማህበረሰብ የአስተዳደር አካላትና የፀጥታ አካላትም በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ በመግለጫው ተካቷል።
ምንጭ፦ የትምህርት ሚኒስቴር
ተጨማሪ ትምህርት ተኮር ዜናዎች
February 16, 2019 at 5:01 pm #9739AnonymousInactiveአምቦ ዩኒቨርሲቲ በሰላም ጎዳና
—–
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው የሰላም ፎረም ለመማር ማስተማር ሥራ አስተዋጽዖ ማድረጉ ተገለጸ።በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው የማህበረሰብ አቀፍ የሰላም ፎረም የመማር ማስተማር ሥራን በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች በተያዘለት መርሀ ግብር ለማስቀጠል አስተዋጽዖ ማድረጉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ ገለጹ።
የሰላም ፎረሙ በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት አስመልክቶ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የተቀናጀ ጥረት እያደረገ ያለ መሆኑን ዶክተር ታደሰ ገልጸዋል፡፡
በዚህም ውጤታማ ሆነዋል ባሏቸው የወሊሶ፣ የጉደርና የአዋሮ ካምፓሶች የዘመኑ ትምህርት በጥሩ ሁኔታ እንደቀጠለ ተናግረዋል፡፡ ሰላም ከሌላ ትምህርት እንደሚቆምና ይህም ተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸውን ከመጉዳት ባለፈ በሀገርም ላይ ጫና ስለሚፈጥር ሁሉም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት መረባረብ እንዳለበት ዶክተር ታደሰ ጠቁመዋል፡፡
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.