በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በደረሰ ከባድ የመኪና አደጋ የ14 ሰዎች ሕይወት አለፈ

Home Forums Semonegna Stories በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በደረሰ ከባድ የመኪና አደጋ የ14 ሰዎች ሕይወት አለፈ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #8275
    Semonegna
    Keymaster

    በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ፋግታ ለኮማ ወረዳ በደረሰ የመኪና አደጋ የ14 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት (አብመድ) እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የዞኑ ፖሊስ መምሪያን በመጥቀስ ዘግበዋል።

    የመምሪያው የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ባለሙያ ዋና ኢንስፔክተር ወርቅነህ ስዩም በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ይህ የመኪና አደጋ የደረሰው ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ.ም፣ ከጠዋቱ 3፡00 አካባቢ ሲሆን፥ ቦታው ደግሞ በወረዳው “ሉሊስታ” በተባለ ቀበሌ ነው። ከዳንግላ ወደ ኮሶበር እየሔደ የነበረ 16 ሰው የመጫን አቅም ያለው የህዝብ ማመላለሻ መኪና (የሰሌዳ ቁጥሩ፦ 3-20705-አማ) እና ወደ ባህር ዳር አቅጣጫ እየሄደ ከነበረ የመከላከያ ሠራዊት ከባድ የጭነት መኪና (የሰሌዳ ቁጥሩ፦ መከ-01335) ክፉኛ በመጋጨታቸው የ1 ሰዎች ሕይወት የቀጠፈው አደጋ ሊደርስ ችሏል።

    ዋና ኢንስፔክተር ወርቅነህ በገለጻቸው “የህዝብ ማመላለሻ መኪናው ከዳንግላ ወደ ኮሶበር በመጓዝ ላይ ሳለ በተቃራኒ አቅጣጫ ወደ ባህር ዳር ይመጣ ከነበረው ከባድ የጭነት መኪና ጋር በመጋጨታቸው አደጋው ሊከሰት ችሏል” ሲሉ፥ በተከሰተው አደጋ 14 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ ሌሎች 12 ሰዎች በጽኑ ቆስለዋል በማለት አክለው ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ አደጋው በደረሰበት ወቅት 15 ሰው ብቻ መጫን የነበረበት የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪው 25 ሰዎችን ጭኖ እንደነበር ዋና ኢንስፔክተር ወርቅነህ አያይዘው ገልጸዋል።

    በፋግታ ለኮማ ወረዳ የትራፊክ ተቆጣጣሪ ሳጅን መልካሙ ልየው ለአብመድ ሕይወታቸው ስላለፈው ሰዎች ሲያብራሩ፥ በአደጋው ሹፌሩን እና ረዳቱን ጨምሮ የ14 ሰዎች ሕይወት አልፏል ብለዋል።

    የቆሰሉት ሰዎች በዳንግላና እንጅባራ ሆስፒታሎች ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ደግሞ በአዲስ ቅዳም ጤና ጣቢያ ሕክምና ተደርጎላቸው ወደ ቤተሰቦቻቸው ተልከዋል።

    የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የስምንት መንገዶች ግንባታ ሥራ የኮንትራቶችን ከተለያዩ ተቋራጮች ጋር ተፈራረመ

    ከሟቾች መካከል ከሕጻን ልጃቸው ጋር ሕይወታቸው ያለፈው አንዲት እናት እንደሚገኙበት ያስታወቁት ኢንስፔክተሩ፣ የ13ቱ ሟቾች አስክሬን ወደቤተሰቦቻቸው የተላከ ሲሆን ለቀሪው የአንዲት ሴት አስከሬን ቤተሰቦቿን የማፈላለግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ዋና ኢንስፔክተር ወርቅነህ ስዩም ጠቁመዋል።

    ዋና ኢንስፔክተሩ እንዳስታወቁት በአሁኑ ወቅት የአደጋው መንስዔ እየተጣራ መሆኑን አመልክተው፣ የከባድ መኪናው አሽከርካሪ አደጋው ከደረሰ በኋላ በመሰወሩ በቁጥጥር ስር ለማዋል በፖሊስ በኩል ክትትል እየተደረገ ሲሆን፤ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድርስ አልተያዘም። በየቀኑ እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ አሽከርካሪዎች የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ህጉን አክብረው ሊያሽከረክሩ እንደሚገባም ኢንስፔክተሩ አሳስበዋል።

    ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓመት ሀምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም የሀገሪቱ ትራንስፖርት ባለስልጣን ባወጣው በ2010 ዓ.ም የበጀት ዓመት ብቻ 5,118 ሰዎች በተሽከርካሪ አደጋ ሕይወታቸው እንዳለፈ፣ ይህም ከ2009 ዓ.ም የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 13.7 በመቶ እንደጨመረ ያስረዳል። የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ባወጣው በዚሁ መግለጫ ላይ በ2010 ዓ.ም የበጀት ዓመት በተሽከርካሪ አደጋ 7,754 ሰዎች ላይ የከባድ፣ 7,775 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል የመቁሰል አደጋ ደርሷል። በዚሁ የበጀት ዓመት የደረሰው የመኪና አደጋ (የተሽከርካሪ አደጋ) በቁጥር 41,000 ሲሆን ይህም በ2009 ዓ.ም የበጀት ዓመት ከደረሰው የተሽከርካሪ አደጋ ጋር ሲነጻጸር በመቶ እድገት አሳይቷል። ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ ሀገራት በተሽከርካሪ ብዛት ዝቅተኛ ከሚባሉ ሀገራት ብትመደብም በተሽከርካሪ ምክንያት በሰው ላይ በሚደርስ አደጋ ግን አውራ ቦታ ከያዙት ሀገራት ውስጥ ትመደባለች።

    ምንጮች፦ Xinhua፣ አብመድ እና ኢዜአ

    የመኪና አደጋ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.