የሁለተኛው ዙር የኩፍኝ ክትባት በሀገር አቀፍ ደረጃ መሰጠት ተጀመረ
—–
ሁለተኛው ዙር የኩፍኝ ክትባት አስራ ሶስት ወር ለሞላቸው ህፃናት በዛሬው እለት በሀገር አቀፍ ደረጃ መስጠት ተጀምሯል።
የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የጤና ተቋማት እንደሚሰጥ ተገልጿል።
ዛሬ የተጀመረውና ለሁለተኛ ጊዜ የሚሰጠው የኩፍኝ በሽታ የመከላከያ ክትባት ህፃናት በሽታውን የመከላከል አቅማቸው እንዲጨምር ብሎም በሌላ በሽታ እንዳይያዙ እና ጤነኛ እንዲሆኑ የሚያግዝ ነው ተብሏል።
ከዚህ ባለፈም የኩፍኝ በሽታን ሙሉ በሙሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማጥፋት የተያዘውን ዘመቻ ውጤታማ ለማድረግ የክትባት መርሀ ግብሩ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋል።
የኩፍኝ በሽታ ህፃናትን ለሞት የሚዳርግ ብሎም ለከፍተኛ የአካል ጉዳት የሚያደርስ በሽታ መሆኑ ይታወቃል።
በመሆኑም ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ህፃናት እድሜያቸው አንድ ዓመት ከ3 ወር ሲሞላቸው ጀምሮ በአቅራቢያቸው በሚገኝ ጤና ተቋም በመሄድ የኩፍኝ ክትባቱን በማስከተብ ህፃናትን ከበሽታው እንዲታደጓቸው ጥሪ ቀርቧል።
ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ